በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ህዳር 3, 2014)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,243
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,825
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,820
በቁጥር (ከጥቅምት 27, 2014 እስከ ህዳር 3, 2014)2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 39
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 127
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ውጊያ በክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች በሚደገፈው የኢትዮጵያ መከላከታ ሰራዊት እና የትግራይ ህዝብ ነጻነት (ትህነግ/ህወሀት) መካከል ቀጥሏል። በአፋር ክልል ትህነግ ወደ ምሥራቅ ወደ አዲስ-ጅቡቲ አውራ ጎዳና ለመሸጋገር ያደረገው ሙከራ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአፋር ክልል ልዩ ሃይል እና ታጣቂ አጋሮች ከሽፏል። ጦርነቱ ሳምንቱን ሙሉ በካሳ ጊታ እና ጭፍራ ግንባሮች የቀጠሉ ሲሆን ብዙ እንደዚህ ያሉ ጦርነቶች የከባድ መሳሪያ ድብደባ ያካትታሉ። በአማራ ክልል የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች በተራሮች በኩል ወደ ደቡብ እየተጓዙ ባሉት የትህነግ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ-ሸኔ) ሃይሎች ተገፍተዋል። በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ደቡባዊ ጫፍ በሸዋ ሮቢት ዙሪያ ውጊያዎች እንደነበሩ ተሰምቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የወረ ኢሉ ከተማን ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ ከታጣቂ ሃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰፍረው በሚገኙ የፌደራል ወታደሮች መታሰራቸው ተነግሯል። የካማሺ ዞን የክልሉ ፀረ-ሽምቅ ሃይል ሃላፊም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ህዳር 10 ላይ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይሎች “ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ” ተብሎ በተገለጸ ስፍራ ላይ “ከትህነግ ጋር ግንኙነት ካለው ታጣቂ ቡድን” ጋር ተጋጭተዋል (ኦቢኤን፣ ህዳር 10, 2014)። የፖሊስ ሃይሎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ታጣቂዎችን መግደላቸውን እና ፀረ-ታንክ ፈንጂዎችን ጨምሮ ትጥቅ መያዛቸውን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ከኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ጋር ያለው ውጊያ ቢኖርም እንዲሁም የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ በአጠቃላይ እያሽቆለቆለ ቢመጣም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን በመጥቀስ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 9, 2014)። የሰአት እላፊው የተጣለው ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 4, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዳር 10 ላይ በመቱ ስላሴ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በአማራ ታጣቂዎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ በኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 20 ሰዎች ሞተዋል።3 በዘገባዎች መዘግየት ምክንያት ይህ ኩነት የተካተተው በሚቀጥለው ሳምንት የመረጃ ቋት ውስጥ ነው። የአካባቢው የመንግስት ባለስልጣናት ምርመራ እንዲደረግ ትእዛዝ አስተላልፈዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 13, 2014)።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከሻምቡ ከተማ በስተምስራቅ በሚገኙ አካባቢዎች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ተባባሪ ወታደራዊ ሃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ተከትሎ ሳምንቱን በሙሉ በአካባቢው ግጭት ተዘግቧል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለማን ካሬ ቆራ ቀበሌ እና ኩዩ ወረዳ ተጨማሪ ውጊያዎች ተዘግበዋል። በአርሲ ዞን አርሲ ነገሌ ከተማ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 52 ሰዎች እንዲሁም 152 ሰዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአዳ በርጋ ወረዳ ኢንቺኒ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።
በሶማሌ ክልል የክልሉ ልዩ ፖሊስ ሃይሎች በቀድሞው የክልሉ ፖሊስ አዛዥ የተደረገውን ጥቃት “ማክሸፋቸውን” በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 11, 2014)። ምንም ተጨማሪ ዝርዝሮች አልተሰጡም። ባለፉት ጥቂት አመታት የሶማሌ ክልል በሀገሪቱ የተረጋጋ ሰላም ካላቸው ክልሎች አንዱ ነው።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የትህነግ የመገንጠል ማስፈራሪያ
ባለፈው ሳምንት የትህነግ ተወካይ ቡድኑ በትግራይ ክልል የመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ፍላጎት ሊኖረው እንደሚችል አመላክተዋል (ትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ ህዳር 6, 2014)። ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ “ትግራይን መመስረት ካስፈለገ በህገ መንግስቱ አሰራር መሰረት ትግራይን መመስረት ይችላሉ” ብለዋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 7, 2014)። በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት ድንጋጌዎች የትግራይን መመስረት የሚፈቅዱ ቢመስሉም ይህ ሳምንታዊ ትኩረት መገንጠል በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ያለውን ገደብ ይዳስሳል።
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (1) መሠረት “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡” (አንቀጽ 39 (1))። ይህ መብት ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው በ1983 የአዲስ አበባ ቻርተር ሲሆን ግንቦት 15 ቀን 1985 ላይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ህጋዊ መሰረት ሰጥቷል (የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ቻርተር፣ 1983፣ አንቀጽ 2፤ በተጨማሪም ከአንቀጽ 6 እስከ 13 ይመልከቱ)። ይህ ቻርተር በትህነግ መራሹ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት እንደ ጊዜያዊ ሕገ መንግሥት ተቆጥሯል። በመርህ ደረጃ የ1983ቱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት የሶቪየትን የብሄር ፌደራሊዝም ሞዴል ተከትሏል። የሽግግር መንግስቱ የተወካዮች ምክር ቤት 87 አባላት የነበሩት ሲሆን 32ቱ በትህነግ ከሚመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ናቸው። 12 ተወካዮች ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተወጣጡ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ትንንሽ በብሄር የተመሰረቱ ነፃ አውጭ ግንባር ተወካዮች እና ታዋቂ ሰዎች ነበሩ።
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት መሠረት የመገንጠል መብት ለማግኘት ሦስት ዋና ዋና ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። መጀመሪያ ጠያቂው ቡድን “በኢትዮጵያ የሚገኝ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ እና ሕዝብ” መሆን ይጠበቅበታል። በሕገ መንግሥቱ መሰረት ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ማለት “….. ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው” (አንቀጽ 39 (5))፡፡ ሁለተኛ የመገንጠል ጥያቄ በሚመለከተው የብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ መጽደቅ አለበት። ሦስተኛ የሕግ አውጪው ምክር ቤት መገንጠል ካፀደቀ ሕዝበ ውሳኔ መካሄድ አለበት። የፌደራል መንግስት ይህ ከፀደቀ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያዘጋጅ ይጠበቅበታል (አንቀጽ 39 (4) ይመልከቱ)።
በዚህ የህግ ማዕቀፍ መሰረት የትግራይን የመገንጠል ጉዳይ ከወዲሁ በከፍተኛ ውስብስቦች የታጀበ ነው። አንደኛ የትግራይ ክልል (አሁን ባለው ወሰን ውስጥ እንዳለ) በህገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት “በአንድነት ወይም በተዛመደ ማንነት” የሚያምኑ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች አያካትትም። በደቡብ ትግራይ ዞን የሚገኙት የራያ ነዋሪዎች እና በምዕራብ ትግራይ ዞን ወልቃይት አካባቢ የሚገኙ ወደ አማራ ክልል ለመግባት በመሞከር ሁለት አስርት አመታትን አሳልፈዋል። በምስራቅ ትግራይ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎችም እንዲሁ በአፋር ክልል እንዲተዳደሩ ጠይቀዋል። ጉዳዩን የበለጠ የሚያወሳስበው የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች ግጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ምዕራብ ትግራይ ዞን እና አንዳንድ የደቡብ ትግራይ ዞንን ተቆጣጥረዋል። የምእራብ ትግራይ ዞን – ወልቃይት – በአሁኑ ሰአት በአማራ ክልል መንግስት እየተዳደረ ይገኛል። በተመሳሳይ የአፋር ክልል መንግስት የአፋር ክልል አካል ናቸው ያላቸውን ቀበሌዎች ተቆጣጥሮ ያስተዳድራል። በህገ መንግስቱ መሰረት እነዚህ የአፋር እና የአማራ ክልል መንግስታት በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ለማስተዳደር ህጋዊ ከለላ የላቸውም። የመገንጠል ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎች ፖለቲከኞች በክልሉ ውስጥ ተጨማሪ ግጭቶችን ለማስወገድ እነዚህን ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎች መፍታት አለባቸው።
ሁለተኛ እንደፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልል በህጋዊ መንገድ የተመረጠ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የለውም። የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ከፌደራል መንግስት እውቅና ውጪ በጷጉሜ 2012 ክልላዊ ምርጫ አካሂደዋል። በሕገመንግሥቱና ሌሎች የምርጫ ሕጎች መሠረት የፌዴራልና የክልል ምርጫዎችን የማካሄድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 102 (1)፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ አዋጅ 1133/2011፣ አንቀጽ 7(1)፤ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1162/2011)። ምርጫ ቦርድ በትግራይ ምርጫ እንዲያካሂድ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ያቀረቡት ጥያቄ የፌደራል መንግስት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲዘገይ በመወሰኑ ውድቅ ተደርጓል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 17, 2012)።
በህጉ መሰረት የፌደራል መንግስት በህገመንግስቱ መሰረት መገንጠልን መፍቀድ የሚገባው ቢሆንም በታሪክ ግን የኢትዮጵያን አንድነት ለማደፍረስ የሚደረገውን ጥረት ለማክሸፍ ሃይል ተጠቅሟል። ባለፉት አመታት ከማዕከላዊ መንግስት ለመላቀቅ የተደረጉ በርካታ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ቆመዋል። ለምሳሌ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ የመገንጠል ዛቻ በፍጥነት እንዲቆም የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌደራል ወታደሮችን ወደ ጅጅጋ ልከው ኢሌን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ነው (ሃግማን፣ መስከረም 1, 2013)። ኦብነግ በ1986 የሶማሌ ክልል መገንጠልን ከጠየቀ በኋላ ለአስርት አመታት የዘለቀው ጦርነት አስነስቷል (ሮይተርስ፣ ነሃሴ 6, 2013)።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 39 በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። ለአንዳንዶች አንቀጹ የማንኛውም ብሄረሰብ የበላይነት የመሰብሰብ ጥበቃን ይወክላል እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ያስቀምጣል። በተግባር ግን አተገባበሩ የተወሳሰበ ስለሆነ ማለቂያ የሌለው የብጥብጥ ሂደት ሊፈጥር ይችላል።