ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
-
- አክሌድ ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 ድረስ 92 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 342 ሟቾችን መዝግቧል።
- ኦሮሚያ ክልል በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር 187 ሟቾች የተመዘገበበት ክልል ነው። ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በ101 የተዘገቡ ሟቾች ቁጥር ይከተላል።
- ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 50 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 217 ሟቾች ተዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እንዲሁም በአፋር ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እንዲሁም ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው።
- በአዲስ አበባ በተደረገው የአድዋ ድል ክብረ በአል ላይ ውጥረቶች ነግሰው ነበር።
- በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሰገን ህዝቦች አካባቢ ዞን፣ ኮንሶ ዞን እና አሌ ልዩ ወረዳ የትጥቅ ግጭቶችና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንደገና ተቀስቅሰዋል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ እና ህዝቡ የሚጠብቃቸው ነገሮች
ባለፈው ወር የካቲት 23 ላይ ኢትዮጵያውያን በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የጣሊያን ሰራዊት ኢጣሊያ በየካቲት 1888 ድል የተቀዳጀበት 126ኛውን የአድዋ ድል በአል አክብረዋል። በአዲስ አበባ በዓሉ የሚከበርበት ቦታ ላይ የተደረገው ለውጥ በህዝቡ እና የመንግስት ባለስልጣናት, መካከል ውጥረት መፍጠሩን ተከትሎ በሚከበርበት ወቅት ፀረ-መንግስት መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡ በማግስቱ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፖሊሶች በሃዲያ ዞን ሆሳዕና በሚገኘው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በመግባት የዳግማዊ ምኒልክን ፎቶ የሚያሳይ ቲሸርት የለበሱ በርካታ ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። የጸጥታ ሃይሎቹ ተማሪዎቹን ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችሁል በማለት የከሰሱ ሲሆን የዳግማዊ ምኒልክ ምስል የታተመበትን ቲሸርት እና ኮከብ የሌለው የቀድሞ ብሄራዊ ባንዲራ – አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ በመያዝ ምክንያት የተነሳ የተማሪዎች የእርስ በእርስ ግጭት ለማስቆም ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተናል ብለዋል። ከሁለት ቀናት በኋላ የካቲት 26 ላይ በአዲስ አበባ የካራማራ የድል በዓል ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ የነበሩ 35 የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላትን ሁከትና ብጥብጥ ቀስቅሰዋል በሚል ክስ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል። በተመሳሳይ እለት ኦሮሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎ ካምፓስ በመሰባሰብ በግቢው ውስጥ የተበተኑ በኦሮሞ ብሄር ላይ የተቃጡ የጥላቻ እና አዋራጅ ቃላትን የያዙ በራሪ ወረቀቶች ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ከሳምንት በኋላ መጋቢት 4 ላይ በግቢው በተበተኑት በራሪ ፅሑፎች ላይ ያለ ቅሬታ ተከትሎ በተነሳው ግጭት በርካታ ተማሪዎች ቆስለዋል።
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 በአፋር ክልል በትህነግ/ህወሃት እና አፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት ቀጥሏል። እነዚህ ግጭቶች በአብዛኛው በቂልበቲ ረሱ-ዞን 2 በአባላ፣ በርሃሌ፣ ዳሎል፣ ኤረብቲ፣ ኮኔባ እና መጋሌ ወረዳዎች ላይ የተከሰቱ ነበሩ። መጋቢት 8 ላይ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰመራ ከተማ በአዋሲ ረሱ ዞን 1 ትህነግ/ህወሃት አፋር ክልልን መውረሩን እና የፌደራል መንግስት ምላሽ አለመስጠቱን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ከአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና የከተማው ፖሊሶች የተወጣጡ የጸጥታ ሃይሎች ሰልፈኞችን በኃይል የበተኑ ሲሆን በዚህም 20 ሰዎች ሲያቆስሉ 5 ተማሪዎችን አስረዋል።
በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ፣ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ እና በሰሜን ጎንደር ዞን ዛሪማ ወረዳ የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ ከፋኖ ታጣቂዎች እና ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። ባለው ውስን ዘገባ ምክንያት በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የደረሰው ጉዳት አይታወቅም። የካቲት 25 ላይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ባህር ነጋሽ ሪዞርት እና ሽሬ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ባሉ ያልተገለጹ ኢላማዎች ላይ በሰው አልባ አይሮፕላኖች ሁለት ጥቃቶችን አድርሷል። በጥቃቶቹ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። በደቡብ ትግራይ ዞን የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች 160 ወጣቶችን ከአላማጣ አግተዋል። እነዚህ ወጣቶች የራያ ብሔር ተወላጆች እንደሆኑ ይታመናል። እንደ እማኞች ገለጻ ትህነግ/ህወሃት ያገታቸው ለቡድኑ እንዲዋጉ ለማስገደድ ነው (ኢሳት የካቲት 24፣ 2014)።
ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በአንፃራዊነት ሰላም ወደአለባቸው አካባቢዎች መድረሳቸውን እንደቀጠሉ ነው። ከየካቲት ወር ማገባደጃ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታ ፍለጋ ከማዕከላዊ ትግራይ በአማራ ክልል ወደሚገኘው ቆቦ ከተማ መድረስ ጀመሩ። ወሩን በሙሉ በክልሉ በሚገኙት ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች መድረሳቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ሁለት ዞኖች በትህነግ/ህወሃት ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችን እያስተናገዱ ነው (ቪኦኤ አማርኛ፣ መጋቢት 1, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 6, 2014)። በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች በተለይም የሴቶችና ህጻናት ሁኔታ አስከፊ ነው (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 20, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 21, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ, መጋቢት 29, 2014)። በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች በየእለቱ መፈናቀል እንዳለ የሚያሳዩ ዘገባዎች አሉ (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 22, 2014)።
መጋቢት 15, 2014 ላይ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርቅ አውጇል። በትህነግ/ህወሃት አባላት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት ብዙም ሳይቆይ “ጦርነቱ እንዲቆም” ተስማምቷል (የትግራይ ውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 15, 2014)። ይህ እርቅ የታወጀው መንግስት ሰብአዊ አርዳታ ይዘው ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ በነበሩ መኪኖች ላይ ትህነግ/ህወሃት “አባላና መቀሌ ኮሪደር” ላይ ተኩስ ከፍቷል ብሎ ከከሰሰ ከአንድ ቀን በኋላ ነው (ኢሳት፣ መጋቢት 14, 2014)። ስምምነቱን ተከትሎ በርካታ ሰብዓዊ አርዳታዎችን የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል በሰመራ-አባላ- መቀሌ መስመር ደርሰዋል (አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ መጋቢት 24, 2014፤ ትዊተር @reda_getachew, መጋቢት 23, 2014)። ይህ ከታህሳስ 6, 2014 ወዲህ በመኪና የደረሰ የመጀመሪያው የሰብአዊ አርዳታ ነው (የተኩስ ማቆም አተገባበሩን ላይ ስላለው ችግር የበለጠ መረጃን ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 10, 2014 እስከ መጋቢት 16, 2014 ይመልከቱ)።
መንግስት የፋኖ ታጣቂዎችን ማሰልጠን አንዲያቆሙ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ያልተቀበሉ የፋኖ አመራሮችን ማሰሩን ተከትሎ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ፣ የጁቤ፣ ቢወግን እና ግንደወይን ፋኖ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። በሞጣ ከተማ በተኩስ ልውውጡ አራት የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ሲገደሉ ስድስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተዘግቧል። መጋቢት 1, 2014 ላይ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ደዋ ሀረዋ ወረዳ ሃሮ ቀበሌ ውስጥ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ኦነግ-ሸኔን ይደግፋሉ በሚል የጠረጠሯቸውን በርካታ ሰዎችን ደብድበው ከ40 በላይ ቤቶችን አቃጥለዋል።
በመጋቢት አጋማሽ ላይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል መንግስታት መካከል ያለው ውጥረት በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራቤት ቀበሌ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን እና ኦሮሚያ ክልልን በሚያከራክረው የቆርኬ/አውራ ጎዳና አካባቢ የተፈፀመን ጥቃት ተከልሎ ተካሯል። መጋቢት 20 ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራቤት ቀበሌ ከኦሮሚያ ክልል በመጡ ታጣቂዎች እና በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ቆስለዋል። በተመሳሳይ ዕለት በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት “አክራሪ የአማራ ታጣቂ ቡድን” በሚል የተገለጸ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በአወራ ጎዳና/ቆርኬ አካባቢ ሲጓዙ በነበሩ ከ130 የሚበልጡ የአካባቢ ታጣቂዎች እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ሃይሎች ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈጽሞ 26 ሰዎችን ሲገድል ሌሎች 15 ደግሞ አቁስሏል። የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባለስልጣናት እያንዳንዳቸው ስለኩነቱ ያቀረቡትን ትረካ ውድቅ አድርገዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ (አማራ) ኩነቶቹ የተከሰቱት የኦሮሞ ታጣቂዎች አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ነው ሲሉ (የአማራ ኮሙኒኬሽን፣ መጋቢት 22, 2014፤ ኢሳት፣ መጋቢት 22, 2014) የምስራቅ ሸዋ ዞን (ኦሮሚያ) አስተዳዳሪ ይህንን ክስ ውድቅ አድርገዋል (ኢሳት፣ መጋቢት 22, 2014)። ጥቃቱን የተፈጸመው ከሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በመጣ “አክራሪ ታጣቂ ቡድን” ሆኖ የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይሎች ከኦሮሚያ ክልል ቦሴት ወረዳ ወለንጪቲ አካባቢ እርምጃ ወስደው በአውራ ጎዳና/ቆርኬ በኩል ሲመለሱ እንደነበር ገልጸዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላትም ጣልቃ በመግባት ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲሞክሩ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል በኦነግ–ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች እና በኦሮሚያ ታጣቂዎች መካከል የትጥቅ ግጭቶች ቀጥለዋል። ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 በነበረው ወቅት አክሌድ በምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች 19 የትጥቅ ግጭቶችን የመዘገበ ሲሆን ከፍተኛው 11 ኩነቶች በምዕራብ ሸዋ ዞን ተከስተዋል (ከዚህ በታች የሚገኘውን ካርታ ይመልከቱ)። ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ የሚፈጠሩ ግጭቶች በምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂ እና ጉጂ ዞኖች የሚከሰቱ ነበሩ። ሆኖም ከመስከረም 21 እስከ መጋቢት 22 ድረስ አክሌድ በሰሜን ሸዋ ዞን በኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት የጽጥታ ሃይሎች መካከል የተፈጠሩ 34 የውጊያ ኩነቶችን የመዘገበ ሲሆን ከ ታህሳስ 23 2010 እስከ መስከረም 20 2014 ድረስ የዚህ አይነት ሁለት ክስተቶች ተመዝግበው ነበር።
በተጨማሪም መጋቢት 10 ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቡልቡላ ከተማ ስታዲየም እየተካሄደ በነበረ የአካባቢው ታጣቂዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ የሶስት የአካባቢ ታጣቂዎች አባላት እና አንድ የ12 አመት ህጻን ተገድለዋል። 35 ሰዎች በጥቃቱ ቆስለዋል። ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካላይት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ቀጥሏል። ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ አምስት ጥቃቶችን ፈጽመዋል። ከየካቲት 26 እስከ 28 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆራን ጎጆ እና ቆርቆራ ሙሊ መንደሮች ውስጥ የአማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የከራዩ አርብቶ አደሮች ገድለዋል፡፡ በየካቲት ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ ዲቾ አባገርማማ ቀበሌ የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች የበርካታ አርሶ አደሮችን ቤቶች እና የህዝብና የግል ንብረቶችን አቃጥለዋል እንዲሁም አራት ሰዎችን ገድለዋል። በሲቡ ሲሬ ወረዳ ሀገሎ ቱለማ ቀበሌ ተመሳሳይ ኩነት ተከስቶ 27 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ወቅት አክሌድ ጥቃቶች እና እገታዎችን ጨምሮ ኦነግ-ሸኔ የፈጸማቸው ዘጠኝ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን መዝግቧል። የካቲት 23 ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ ዋሊ ጋሌ መንደር የኦነግ-ሸኔ አባላት ቢያንስ ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። የካቲት 29 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ ኦቤራ ቄራሮ ቀበሌ ኦነግ-ሸኔ በፈጸመው ጥቃት አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ሰባት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድሏል። ጥቃቱ በማግስቱ በአቅራቢያው በሚገኘው የኢጃጂ ከተማ እና አካባቢው ቀጥሏል። የካቲት 29 ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ መንደር-ስድስት የገጠር መንደር ውስጥ ከኦነግ-ሸኔ፣ ቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ እና ትህነግ/ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች 24 ቤቶችን አቃጥለው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ሃብቶች ዘርፈዋል። ታጣቂዎቹ አንድ ነዋሪን በጥይት ተኩሰው ገድለው ሁለት ደግሞ አግተዋል። በቀጥዩ ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር ተባብረዋል በሚል አራት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ከሊሙ ወረዳ ገሊላ ከተማ አግተዋል። መጋቢት 8 ላይ ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ እንዶዴ ቀበሌ አንድ ቄስን ጨምሮ ስምንት አማራዎችን ገድሏል። በወሩ መጨረሻ መጋቢት 15 ላይ በተጎጂው ኦነግ-ሸኔ ነው ተብሎ የሚታመን ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ በሚገኘው የጉጂ አባ ገዳዎች (የባህል ሽማግሌዎች) ማኅበር ሊቀመንበር እና አባ ገዳ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ሰንዝሮ እቃዎችን ዘርፏል። ኦነግ-ሸኔ ከጥቃቱ ጀርባ አለ የሚባለውን አስተባብሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 17 ቀን 2014)። መጋቢት 22 ላይ ቡድኑ በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ አቅራቢያ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የካማሺ ዞን ማረሚያ ቤት ሶስት (በቀቅቱ ስራ ላይ አልነበሩም የተባሉ) ፖሊሶችን አግቷል።
በተጨማሪም መጋቢት 8 ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ አልጌ ቀበሌ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ 10 ሰዎች ሲገድሉ ከ20 በላይ አቁስለዋል። አንዳንድ እማኞች ጥቃቱ የተፈጸመው በኦነግ-ሸኔ ሆኖ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል (ኢሳት፣ መጋቢት 9, 2014)። የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ ብሄርን መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት አጥብቀው ተናግረዋል ((ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 9, 2010)። መጋቢት 1 ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን ቀኚ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያለው ግለሰብ ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተመትቶ ተገድሏል። በተመሳሳይ እለት በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜቲ አንድ የምዕራብ ሸዋ ፖሊስ እና ሹፌሩ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተመተው ተገድለዋል። ከዚህ ቀደም ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት ያለው አባ ቶርቤ ቡድን በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ባለስልጣናትን በመግደል ተሳትፏል። ሆኖም እነዚህ ግድያዎች የተፈፀሙት በዚህ ቡድን ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም።
በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ታጣቂዎች ከህግ ውጪ የሚፈጽሟቸው ግድያዎችም ቀጥለዋል። ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 የተፈጸሙ እንደዚህ ዓይነት ግድያዎች የተመዘገቡት በምዕራብ ሸዋ ዞን ነበር። ይህ ምናልባት በመንግስት ሃይሎች እና በኦነግ-ሸኔ መካከል ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ውጊያዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። የካቲት 25 ላይ የኦሮሚያ ክልል ሃይሎች እና የአካባቢው ታጣቂዎች በሜታ ወልቂጤ ወረዳ በጎዳ ሊባሲ መንደር በኤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ታስረው የነበሩት ሶስት ወጣቶችን ተኩሰው ገድለዋል። ከግድያው በስተጀርባ ያለው ምክንያት አልታወቀም። የካቲት 30 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ቃላቴ አንድ አባትና ልጅ ተኩሰው ገድለዋል። ሟቾቹ የኦነግ-ሸኔ አባል ነው የተባለውን የቤተሰባቸው አባል በመደበቅ ተጠርጥረው ታስረው ነበር። መጋቢት 14 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ባልታወቀ ምክንያት አምስት ተማሪዎችን በኮቢ ወረዳ ማክሳ ለኩ ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ቤታቸው ውስጥ በጥይት ገድለዋል።
በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚሰነዘረው ጥቃት ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ወቅት ትንሽ ቀንሷል። ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ባለው ወቅት አክሌድ ይህ ቡድን የተሳተፈባቸው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶችን እና አንድ ውጊያ የመዘገበ ሲሆን ባለፈው ወር ሁለት ውጊያዎች እና ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በአጠቃላይ አምስት ኩነቶች መዝግቧል (በጋምቤላ ውስጥ ስላለው ግጭት መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)። የካቲት 22 ላይ በኑዌር ዞን ማኩዬ ወረዳ ላንግጆክ ቀበሌ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በመግባት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር አንድ ሰው ገድለው ሌላ አንድ ሰው አቁስለዋል። በዛው እለት በአኙዋክ ዞን የሙርሌ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው ገድለዋል። ከሁለት ሳምንት በኋላ መጋቢት 6 ላይ የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች በኢታንግ ልዩ ወረዳ አሊያ ቀበሌ ከሙርሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። የክልሉ መንግስት ታጣቂዎቹ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ሊያደርሱ የነበረውን ጥቃት የክልሉ ሃይሎች መመከታቸውን አሳውቋል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክርተሪያት ጽ/ቤት፣ መጋቢት 6, 2014)።
በተጨማሪም የካቲት 29 ላይ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ-በተቃዋሚ አባላት ከደቡብ ሱዳን ጦር ጋር በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በኑዌር ዞን በጅካዎ ተዋግተዋል። በማግስቱ የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ-በተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈት በኑዌር ዞን ላሬ ወረዳ አንድ ሰው ሲገድሉ ስድስት አቁስለዋል። እነዚህ ኩነቶች በዞኑ አራት ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ9,500 በላይ ግለሰቦች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት፣ መጋቢት 4, 2014)። በተጨማሪም መጋቢት 18 ላይ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች ባልታወቀ ምክንያት የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። አንድ ሰው ሲገደል አንድ ሰው ደግሞ ቆስሏል።
ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውጊያዎች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። የካቲት 23 ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በመተከል ዞን ዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች መካከል በሚገኘው የአፍሪካ ግብርና ልማት አካባቢ ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝዎችን ሲያጓጉዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈጽመው አንድ ከፍተኛ አዛዥ እና ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ጨምሮ 20 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትን ገድለዋል። በማግስቱ የፌደራል ወታደሮች ከአማራ እና ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተወጣጡ የክልሉ ሃይሎች ለጥቃቱ ምላሽ ሰጥተው ቢያንስ 30 የጥቃቱ ፈጻሚዎች ናቸው የተባሉ ሰዎችን ገድለዋል። በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ በተባለው አካባቢ ስለደህንነት እንቅስቃሴዎች መረጃ በመስጠት የተጠረጠሩ አካባቢው ላይ የነበሩ የጉሙዝ ተወላጆች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ 11 ሌሎች ሰዎች ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ተይዘው በጸጥታ ሃይሎች ተገድለዋል። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በህይወት እያለ መቃጠሉ የተመዘገበ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተግባር ላይ ቅሬታ አስነስቷል (ኢሰመኮ፣ መጋቢት 4, 2014)። በተጨማሪም የመጋቢት 7 ሳምንት ላይ በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ የጉሙዝ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በግጭቱ 30 የቡድኑ አባላት እንደተገደሉ የተዘገበ ሲሆን ሌሎች 15 በውጊያው ቆስለዋል። 27 የቡድኑ አባላትና በርካታ የጦር መሳሪያዎችም ተማርከዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የፋኖ ታጣቂዎች እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱት ጥቃት ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ ባለው ወቅት ጨምሯል። በዚህ ወቅት አክሌድ ስድስት ይህን የመሰሉ ኩነቶችን የመዘገበ ሲሆን ከአንዱ በስተቀር ሁሉም በመተከል ዞን ድባቴ ወረዳ ተከስተዋል። ይህ ወረዳ ከአማራ ክልል ጋር ይዋሰናል። ሌላው ከላይ የተጠቀሰው ኩነት በጉባ ወረዳ የተፈጠረ ነው። መጋቢት 6 ላይ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይሎች እና የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በድባቴ ወረዳ አንዲት እርጉዝ ሴትን ገድለዋል። በቀጣዩ ቀን የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በድባቴ ወረዳ ቢሻን አዲ አካባቢ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በማስቆም 18 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ የኦሮሞ ተወላጆችን አግተዋል። ይህንን ተከትሎ መጋቢት 8 ላይ የወረዳው ነዋሪዎች በመተከል ዞን ባርባራ ተሰባስበው “እየጨመረ የመጣ በአማራ ሃይሎች እየደረሰ ያለ ግፍና በደል” በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውመዋል። ሰልፈኞቹ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ከክልሉ እንዲወጡ ጠይቀዋል (ኦኤምኤን፣ መጋቢት 8, 2014)። መጋቢት 10 ላይ ሁለቱ ታጋቾች በድባቴ ወረዳ በአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች በጥይት ተመተው ተገድለዋል። መጋቢት 13 ላይ የፋኖ ታጣቂዎች በድባቴ ወረዳ ቱስኪ ጋምቤላ ቀበሌ የፋኖ ታጣቂዎች አንድን ወጣት ተኩሰው ገድለዋል እንዲሁም ብዙ ከብቶችን ከማህበረሰብ ዘርፈዋል። በማግስቱ የፋኖ ታጣቂዎች በዲባቴ ወረዳ ዳማዳስ ቀበሌ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ገድለው ከ50 በላይ ቤቶችን አቃጥለው በርካታ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል።
የካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 ድረስ ባለው ወቅት በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን፣ በኮንሶ ዞን እና በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የአሌ ልዩ ወረዳ ሁከት መቀስቀሱ ይታወሳል። መጋቢት 10 ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን እና የክልሉ ልዩ ሃይሎች እንዲሁም የኮንሶ ብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል በአሌ ልዩ ወረዳ ባራሃዋ በተፈጠረ ግጭት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የሰው ህይወት እና ንብረት ጠፍቷል። እነዚህ ቡድኖች በድጋሚ መጋቢት 17 ላይ የእርሻ መሬት ምክንያት በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ዲማያ በተባለ ቦታ ተጋጭተዋል። ግጭቱን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። ዲማያ በአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን አዋሳኝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁለቱም መስተዳድሮች የይገባኛል ጥያቄ ያቀርቡበታል። በተመሳሳይ ቀን የሰገን አካባቢ ወረዳ ገቢዎች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ከጓደኞቻቸው ጋር በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ እራት ሲበሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተኩስ ተገድለዋል። ከአንድ ቀን በኋላ ማንነታቸው ያልታወቁ የአሌ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች በኮንሶ ዞን ዲሚያ፣ ሰገን እና ቆልሜ ክላስተር አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረው ዘጠኝ ሰዎች ሲገድሉ 13 አቁስለዋል። በርካታ ቤቶችንም አቃጥለዋል። መጋቢት 22 ላይ ከደራሼ ልዩ ወረዳ የመጡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አንድ የቀበሌ አስተዳዳሪን፣ የአካባቢ ታጣቂ እና ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚስተዋለው ሁከትና ብጥብጥ ከድንበር ውዝግብ እና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር የተያያዘ ነው። እንደ ዞን፣ ልዩ ወረዳ ወይም ወረዳ መታወቅ አመታዊ በጀት እና አካባቢው በሚተዳደርበት እርከን ላይ ለውጥ ያመጣል። በዚህ አካባቢ ያለው ግጭት የተቀሰቀሰው በ2010 የኮንሶ ወረዳ ዞን እና አሌ ወረዳ ልዩ ወረዳ ከሆኑ በኋላ ነው። ከዚህ ቀደም እነዚህ አካባቢዎች በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ስር ይተዳደሩ የነበረ ሲሆን መጋቢት 19 ላይ የተመሰረተው አማሮ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ኮንሶ እና አሌ ወረዳዎችን ያቀፈ ነበር (የግጭትን አዝማሚያ በተመለከተ ኢፒኦ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የግጭት ገጽ ይመልከቱ)። ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በቀጥታ የሚተዳደሩት በክልል መንግስታት ሲሆን ወረዳዎች በየዞናቸው ይተዳደራሉ።
የሀገሪቱ አዲሱ ክልል በሆነችው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ የመጋቢት 21 ሳምንት ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በጉራፈርዳ እና ደቡብ ቤንች ወረዳዎች ሶስት ሰዎችን ገድለው ቢያንስ 20 የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል።
በመጨረሻም የካቲት 23 ላይ ከሶማሊያ የመጡ የመርሃን ታጣቂዎች ከመቃቡል-እስማኤል ጉምካድሌ ክፍለ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር በሶማሌ ክልል በሌሄሎው ዩቁብ መንደር አካባቢ የተፈጠረ የመሬት ውዝግብን ተከትሎ ተዋግተዋል። ግጭቱ በአካባቢው ነዋሪዎች የተመከተ የማረሃን ጎሳ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረ ነው። በእነዚህ ኩነቶች በአጠቃላይ ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። በተጨማሪም በፋፋን ዞን ጉርሱም ወረዳ በቦምባስ ከተማ በአንድ የአካባቢውን የጎሳ መሪ በአለ ሲመት ስነስርአት ላይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች ከሶማሌ ክልል ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። ግጭቱ የተፈጠረው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች ስነስርአቱን ለማስቆም መሞከራቸውን ተከትሎ ነው። ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ከ20 በላይ ቆስለዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ እና ህዝቡ የሚጠብቃቸው ነገሮች
አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ አራት አመታት ተቆጥረዋል። ምንም እንኳን አብይ መጀመሪያ የተሾሙት በሕዝብ ድምፅ ሳይሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሆንም በፍጥነት በመላው አገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ብዙዎች በአንድነት፣ በይቅርታ እና በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ላይ ለተመሰረተው እንቅስቃሴ ደጋፊ ነበሩ። በኢትዮጵያውያን እና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ኢትዮጵያን ከእርስ በርስ ጦርነት በመታደግ ትልቅ እውቅና አግኝተው ነበር (ሲኤንኤን፣ ነሃሴ 23, 2010)። ተቀባይነታቸው የፖለቲካ ክፍፍልን ያለፈ እና ከኢትዮጵያ ድንበር የተሻገረ ሲሆን ይህንንም የሀገሪቱን ያልተሟላ በጀት ፍላጎቶች በዳያስፖራ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመሰብሰብ አረጋግጠዋል (ኢቢሲ፣ ሰኔ 29, 2010፣ በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኤምባሲ፣ በተጨማሪም ኢዲቲኤፍን ይመልከቱ)።
አብይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተቀባይነት ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዲግ) እንዲፈርስ እና ብልፅግና ፓርቲ እንዲመሰረት መወሰናቸው እንዲሁም የፓርቲው ያለፈው አንድ አመት ተኩል ተግባራት አወዛጋቢ ሆነዋል። ብልጽግና ለመጀመሪያው የፓርቲው ጉባኤ በተሰበሰበበት ወቅት የፓርቲው ስኬቶች እና ድክመቶች የታዩ ሲሆን ይህም ፓርቲው ወደፊት እንዴት ሊቀረጽ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የተቋቋመው ህዳር 21, 2012 ላይ ሲሆን ከትህነግ/ህወሓት በስተቀር ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው። በወቅቱ የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ የነበረው ትህነግ/ህወሓት አባል ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፓርቲው እና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረው ግጭት ከጊዜ በኋላ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተለወጠ። በመጀመሪያ የአራት ብሄርን መሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ጥምረት ሆኖ የተመሰረተው ኢህአዴግ ትህነግ/ህወሃትን፣ የአማራ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን፤ በ2010 የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተብሎ የተሰየመ)፣ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ፤ በ2010 ስሙን ወደ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀየረ)፣ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) (ለበለጠ ዝርዝር በኢፒኦ የቡድኖች ዝርዝር ውስጥ Ethiopian People’s Revolutionary Democratic Front (EPRDF)- የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ይመልከቱ)። እነዚህ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሄርን መሰረት ያደረገ የፌደራል ስርአት አወቃቀር በቅደም ተከተል ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ እና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችን ያስተዳድሩ ነበር። የቀሩትን ክልሎች የሚመሩት ፓርቲዎች “አጋር ፓርቲዎች” ሲሆኑ የኢህአዲግ አባል አልነበሩም እንዲሆም በምንም አይነት የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ አይሳተፉም ነበር። አዲስ የተቋቋመው የብልጽግና ፓርቲ እነዚህን አጋር ፓርቲዎች ወደ ፓርቲ መዋቅሩ በማዋሃድ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ሰጣቸው። ሆኖም የፓርቲው ክልላዊ ክንፎች አሁንም የኦሮምያ ብልጽግና፣ የአማራ ብልጽግና እና በመሳሰሉት ተለይተው ይታወቃሉ (ለዝርዝር መረጃ በኢፒኦ የቡድኖች ዝርዝር ውስጥ Prosperity Party (PP)- ብልጽግና ፓርቲ ይመልከቱ)።
በዚህ መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በዛውም ብልጽግና ፓርቲ በቀድሞዎቹ “አጋር ፓርቲዎች” ዘንድ ፖለቲካዊ ተቀባይነት አግኝተዋል። አብይ አሁንም ከቀድሞ የኦሮሚያና አማራ ክልል የኢህአዴግ አባላት ድጋፍ ያላቸው ቢሆንም ለመወጣት አስቸጋሪ ሊሆኑ የሚችሉ ጠንካራ ተቃውሞዎች እየተፈጠሩ ነው።
በተወለዱበት ክልል ኦሮሚያ ታዋቂ የሆኑት የማህበረሰብ አንቂ ጃዋር መሀመድ መታሰር እና የኦነግ አመራር (ዳውድ ኢብሳ) ወደ ጎን መገፋት አብይ ከኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች የሚነሳውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደማይታገሱ እንዲያምኑ አድርጓል (አልጀዚራ፣ መስከረም 9, 2013)። በአዲስ አበባ እና አማራ ክልል ትህነግ/ህወሃት እና ኦነግ-ሸኔ የያዙበት መንገድ እንዲሁም በቅርቡ የተደረገው የተያዙ የትህነግ/ህወሃት መሪዎች መለቀቅ በሀገሪቱ የሚታየውን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ በቂ አቅም እንደሌላቸው ጥርጣሬን ጭሯል። በተጨማሪም በእርሳቸው አመራር ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ያሉ ቤቶች አለመረጋጋት እና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ንረት አጋጥሟቸዋል (ሮይተርስ፣ የካቲት 1, 2014)። ውጤቱም አብይ በአንድ ወቅት ይደግፏቸው በነበሩ ሰዎች ዘንድ እንዳሰቡት ባለራዕይ እንደ ደካማ፣ ስትራቴጂ የሌላቸው እና ምላሽ ሰጪ አድርገው እንዲያዯቸው ሆኗል።
አብዛኛው የአብይ ተቀባይነት የፖለቲካ ምህዳሩን በመክፈታቸው የተገኘ ሲሆን በዚህም በቀድሞው መንግስት በስደት ላይ የነበሩት ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አስችለዋል (ቢቢሲ፣ ታህሳስ 25, 2014)። በ2013 አጠቃላይ ምርጫ ወቅት ብዙ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች በአወዛጋቢ ሁኔታ ከታሰሩ በኋላ የአብይ ብልጽግና ፓርቲ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ውስጥ 448 መቀመጫዎችን አሸንፏል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ይመልከቱ)። ይህም አብይ መስከረም 24 ላይ አዲስ በተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በህጋዊ መልኩ በድጋሚ እንዲመረጡ አስችሏል።
ከመጋቢት 2 እስከ 4 የተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ በዋናነት አብይ እና ገዥው ፓርቲ ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ዳሷል። “ከፈተና ወደ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ጉባኤ 1,600 የሚደርሱ የፓርቲው አባላት እና ሌሎች 400 እንግዶች ተገኝተዋል (ኢቢሲ፣ የካቲት 21, 2014)።
አብዛኛው የአብይ ተቀባይነት የተገኘው የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በቀድሞው መንግስት ስደት ላይ የነበሩ ዳያስፖራዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በማስቻላቸው ነበር (ቢቢሲ፣ ታህሳስ 25, 2011)። በ2013 አጠቃላይ ምርጫ መዳረሻ ወቅት ብዙ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከታሰሩ በኋላ የአብይ ብልጽግና ፓርቱ ከ547 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 448 አሸንፏል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ይመልከቱ)። ይህ አብይ መስከረም 24, 2014 ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በድጋሚ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾሙ ህጋዊ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
ከመጋቢት 2 እስከ 4 ድረስ በተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ ዋናዎቹ ነጥቦች አብይ እና ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ላይ የተጋረጡ ችግሮች ነበሩ። “ከፈታና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ 1,600 የሚደርሱ የፓርቲው አባላት እና ሌሎች 400 እንግዶች ተሳትፈውበታል (ኢቢሲ፣ የካቲት 21, 2014)።
ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ተመርጠዋል (ብልጽግና ፓርቲ፣ መጋቢት 3, 2014)። በተጨማሪም ጉባኤው 225 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እና 45 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል (ኢቢሲ፣ መጋቢት 4, 2014፤ ብልጽግና ፓርቲ፣ መጋቢት 4, 2014)። ጉባኤው የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ የሚገልጽ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል (ብልጽግና ፓርቲ፣ መጋቢት 4, 2014)። የውሳኔ ሃሳቡ ሀገራዊ ለውጡን ማጠናከር፣ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ደህንነትን ለማምጣት ጠንካራ ቁርጠኝነት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ የምጣኔ ሃብት መሻሻል፣ የብሄራዊ ሉዓላዊነትን መጠበቅ እና ሀገራዊ አንድነትን እውን ማድረግን ያካትታል።
በቀጣይም ፓርቲው በእያንዳንዱ የአስተዳደር እርከን 108,258 የስራ ኃላፊዎች ግምገማ እንዳደረገ ተጠቁሟል። ፓርቲው ከግምገማው በኋላ ከሥነ–ምግባር፣ ለማገልገል ባላቸው ፍላጎት፣ በውጤት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በ10,658 የስራ ኃላፊዎች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ወስዷል። ከእነዚህ ባለስልጣናት መካከል 2,574 ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው የተባረሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ ወይም ወደ ሌላ ቦታ እንዲቀየሩ ተደርገዋል (ብልጽግና ፓርቲ፣ መጋቢት 6, 2014)። ከጉባኤው በመቀጠል ከህዝብ ጋር ምክክር ተደርጓል። እነዚህ ምክክሮች በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን በቀጣይ የሚደረጉ ተግባራትን በጽሁፍ በማስቀመጥ ተጠናቋል። ምክክሩ በትግራይ ክልል አልተካሄደም። በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ እንዴት እንደተመረጡ ግልጽ አይደለም።
በኢትዮጵያ ያሉ በርካቶች እነዚህ ውሳኔዎች ወደ ተግባር መቀየራቸውን ይጠራጠራሉ። መሬት የወረደ እውነተኛ ለውችን ለማየት ተስፋ ያደርጋሉ። ገዥው ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላለፉት አራት አመታት በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ተቋማዊ ለውጥ ለማድረግ ቃል ገብተው የነበረ ሲሆን ይህም ወደ ተጨባጭ ተቋማዊ ለውጥ መቀየር ይኖርበታል። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በከብዙ ችግሮች ጋር እየታገለ ነው። በመዲናዋ አዲስ አበባ ድህነት እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ህይወትን አስቸጋሪ አድርጎታል። ከከተማዋ ውጪ መንግስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ከተለያዩ የፖለቲካ ጥቃቶች መጠበቅ ባለመቻሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የደህንነት ስጋት ውስጥ ይገኛል። እንደ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ባሉ አንዳንድ ክልሎች ብሔርን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ኢትዮጵያውያን ብሔር ሳይለዩ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመሥራት መብታቸው ተጥሷል። በሁለቱ የውስጥ ግጭቶች እንዲሁም በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት የመሠረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ ጨምሯል (የዩክሪን እና ሩሲያ ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከየካቲት 19, 2014 እስከ የካቲት 25, 2014 ይመልከቱ)። ለምሳሌ ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 22 በነበረው ወር አምስት ሊትር ዘይት እስከ 1,200 ብር (23 ዶላር አካባቢ) ይሸጥ ነበር። መንግስት የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል የሚሉ ጭምጭምታዎች ያሉ ሲሆን ይህም በሌሎች እቃዎች ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱት ሌሎች የፖለቲካ ግጭቶች በተጨማሪ በብልጽግና የመጀመሪያ ኮንግረስ ላይ የነበረው ስሜት ኢትዮጵያ ወደበለጠ ወደ ፖለቲካዊ ቀውስ ልትገባ እንደምትችል አመላካች ነው። በመላ ሀገሪቱ ያሉ ህዝቦች የጸጥታ እና የምጣኔ ሃብት ፈተናዎችን ለማሸነፍ የራሳቸውን የመቋቋሚያ ዘዴዎች እየተጠቀሙ ነው። መንግስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ከጥቃት መከላከል ካልቻለ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ማህበረሰባቸውን ለመከላከል ራሳቸውን ሊያስታጥቁ ይህም ወደ ተጨማሪ ብጥብጥ እና ህገ-ወጥነት ሊስፋፋ ይችላል። በመሆኑም ገዥው ፓርቲ የህዝብ ብሶት ተባብሶ እንደ ሰላማዊ ሰልፍ እና ህዝባዊ አመፅ በመሳሰሉ መንገዶች ከመገለጹ በፊት ቃል የገባውን ለውጥ ወደ ህብረተሰቡ ለማምጣት ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል።