ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሚያዚያ 28, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,912
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,961
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,225
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከሚያዚያ 15, 2014 እስከ ሚያዚያ 28, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 34
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 154
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –69
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በሚያዚያ ወር ማገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሙስሊሞች የኢድ አል ፈጥር በአልን አከብረዋል። ይሁን እንጂ በዓሉ የተከበረው ለብዙ ቀናት በዘለቀ የእርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ መሃል ነው። ሚያዚያ 18 ላይ በጎንደር ከተማ የአንድ ታዋቂ የአካባቢው ሼክ የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በሙስሊሞች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ ቦምብ ተወርውሮ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ አምስት ሰዎች ቆስለዋል። ግጭቱ ወደ ከተማው ተስፋፍቶ የሁከቱ ፈጣሪዎች ከ20 በላይ የሙስሊም ንግድና መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል ። በተጨማሪም መስጊዶችን አቃጥለው 11 መኖሪያ ቤቶችን ዘርፈዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 21, 2014)። ይህም ለ17 ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን ተጨማሪ 118 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።
በከተማዋ ያለው አለመረጋጋት ለቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ቀጥሏል። በሚያዚያ 18 ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን በሙስሊሞች ላይ በፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች የቀብር ስነ-ስርዓት በሚያዚያ 20 በሚፈፀምበት ጊዜ በጎንደር ከተማ በተፈጠረ አለመረጋጋት ሶስት ሰዎች ሲገደሉ መጠኑ በውል ያልተገለጸ ንብረት ወድሟል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 21, 2014)። በመሆኑም የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከምሽቱ 1 ሰአት እስከ ጠዋት 11 ሰአት ባለው ጊዜ የሰአት እላፊ ያወጣ ሲሆን በከተማው ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ከልክሏል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 21, 2014)። ፖሊስ ንብረት በመዝረፍ እንዲሁም የሀይማኖት ቦታዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን በማውደም የተጠረጠሩ ከ370 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 21, 2014)። ስድስት የፖለቲካ እና የጸጥታ ዘርፍ አመራሮች በሚያዝያ 18ቱ የጎንደር ከተማ አለመረጋጋት ወቅት ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዳቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 25, 2014)።
እነዚህ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተዛምተዋል። ሚያዚያ 20 ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጥቃት በማድረስ ሁለት መስጊዶችን አቃጥለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው እውነታው በቀበሌ 01 የምትገኘው የጎጢት ማርያም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳም ቤተክርስቲያኑ አለመቃጠሉ ሆኖ ሳለ ቤተክርስቲያኒቱ ተቃጥላለች የሚል ጭምጭምታ ከተሰራጨ በኋላ ነበር። እሳቱ የተነሳው በአደጋ ይሁን ሆነ ተብሎ ግልጽ አይደለም (ኢኤምኤስ፣ ሚያዚያ 20, 2014)። የሰሜን ጎንደር ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደገለፁት አንድ የጸጥታ ሃይል አባል ማንነቱ ያልታወቀ ተኳሽ በአካባቢው ከሚገኝ መስጂድ በከፈተው ተኩስ ተገድሏል (የደባርቅ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን፣ ሚያዚያ 21, 2014)። በጎንደር ከተማ በሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም ሙስሊሞች ሚያዚያ 21 ላይ በኦሮሚያ ጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር ሰመራ፣ በሶማሌ ጅጅጋ እና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወራቤ ሰልፎች አድርገዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 21, 2014)። በድሬዳዋ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ሰልፈኞች በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር 22 አባላት ካቆሰሉ በኋላ ወደ ብጥብጥ ተቀይሯል። ሰልፈኞቹ ባንኮች እና የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይም ጉዳት አድርሰዋል። የፖሊስ ሃይሎች በምላሹ ተኩስ ከፍተዋል። አንድ ሕፃን በተባራሪ ጥይት ተገድሏል። በድሬዳዋ ከዚህ ሰልፍ ጋር በተያያዘ 89 ሰዎች ታስረዋል። በወራቤ ሙስሊም ሰልፈኞች ሚያዝያ 20 ላይ ሁለት የኦርቶዶክስ እና ሶስት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት ፈጽመው አቃጥለዋል። በማግስቱ ሌላ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አቃጥለዋል። በተመሳሳይ ሚያዚያ 20 ላይ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ አለም ገበያ በተባለ ቦታ የተወሰኑ ሙስሊም ሰልፈኞች ወደ ሳንኩራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ገብተው መነኮሳት ላይ ጥቃት ፈጽመው ቤተክርስቲያኒቱን አቃጥለዋል። በተጨማሪም የክርስቲያን ሆቴሎችን በማውደም ወደ 15 የሚጠጉ ሰዎችን አቁስለዋል። የስልጤ ዞን አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት እንደገለፀው በወራቤ እና ሳንኩራ ከተደረጉ ሀይል የተቀላቀለባቸው ሰልፎች ጋር በተያያዘ 79 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 1, 2014)።
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በጎንደር ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ ሚያዚያ 19 ላይ በአንዋር መስጊድ ተካሂዷል። ሚያዚያ 24 ላይ በአዲስ አበባ የኢድ አል ፈጥር ሰላት ላይ በመስቀል አደባባይ በፖሊስ ሃይሎች እና በሙስሊም የበአሉ ተሳታፊዎች መካከል ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ እና ተኩስ በመጠቀም ተሳታፊዎችን በትነዋል። ይህ ግጭት የተከስተው አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል “በስህተት” አስለቃሽ ጭስ ከተኮሰ በኋላ ነው። የብሔራዊ ሰላምና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል በአዲስ አበባ የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ በመምራት የተጠረጠሩ 76 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል። ፖሊስ እስረኞቹን “ሃይማኖታዊ ግጭት ለመቀስቀስ” ቢላዎችና የተለያዩ ጽሁፎችን በማዘጋጀት እና ወደ ኢድ አል ፈጥር ሶላት ይዞ በማምጣት ከሷቸዋል (የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሚያዚያ 24, 2014)። በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማነሳሳት በማሴር የተጠረጠሩ 145 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሚያዚያ 26, 2014)። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢድ አል ፈጥር ሶላት ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ በተሳታፊዎችና የጸጥታ ሃይሎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ የፌዴራል ፖሊስ አባል ሚያዚያ 26 ላይ ፍርድ ቤት ቀርቧል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 26, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ለአንድ ሳምንት የዘለቀ ግርግር እና ግጭት ተመዝግቧል። በመሆኑም ሁሉም የመንግስት እና የግል ተቋማት ከአንድ ሳምንት በላይ ተዘግተዋል። ሚያዚያ 18 ላይ በደራሼ ልዩ ወረዳ ታጣቂ ሃይሎች ይደገፋሉ የተባሉት የጉማይዴ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከአርባ ምንጭ ከተማ ወደ ጂንካ ይጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ፣ ሹፌር እና አንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ስምንት ህንዳዊ ዜግነት ያላቸውን ጎብኚዎች እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ኢትዮጵያውያንን በሆልቴ ቀበሌ አግተዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ልዩ ሃይል አባላት ታግተው የተወሰዱትን ጎብኚዎች ለማስለቀቅ ወደ አካባቢው ሲገቡ በሆልቴ ቀበሌ ተገድለዋል። ታጋቾቹ የመንግስት ሃይሎች ወደ ወረዳው ከገቡ በኋላ ተለቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 20, 2014)።
ሚያዚያ 19 ላይ የጉማይዴ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ልዩ ሃይሎች እና የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር በደራሼ ልዩ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ እና ጊዶሌ ከተማ ተዋግተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። እነዚህ ግጭቶች ከሁለቱም ወገኖች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ለሞት ዳርገዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል እንዲሁም ነዋሪዎች ከጋቶ ቀበሌ ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል። ታጣቂዎቹ በጊዶሌ ከተማ የደራሼ ልዩ ወረዳ የመንግስት ባለስልጣናትን ቤቶች አቃጥለዋል። ይህም ባለሥልጣኖቹ ከአካባቢው እንዲሸሹ አስገድዷቸዋል። በጊዶሌ እና ኮንሶ ብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ሚያዚያ 19 እና 21 ላይ በጊዶሌ ከተማ ተመዝግበዋል። ሚያዚያ 22 ላይ የደራሼ እና የኮንሶ ብሄረሰብ ታጣቂዎችም በተመሳሳይ ከተማ ተዋግተዋል። ሚያዚያ 22 ላይ በደራሼ ልዩ ወረዳ ቡስታ ኪላ ቀበሌ አንድ የአካባቢው አስተዳዳሪ በአመጸኞች ተገድለዋል። አመጸኞቹ ግለሰቡ ህብረተሰቡ የራሱን አስተዳደር ለመመስረት ያቀረበውን ጥያቄ ለከፍተኛ ባለስልጣናት አላስተላለፈም በሚል ከሰውታል። አስተዳዳሪው ከሚያዚያ 19 ጀምሮ በደራሼ ልዩ ወረዳ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቡስታ ኪላ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተሸሽገው ነበር። ደራሼ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ የዞን አስተዳደር የመመስረት ጥያቄ ከሚነሳባቸው ወረዳዎች አንዱ ነው። በተጨማሪም በወረዳው ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቀበሌዎች ሌሎች የአስተዳደር ጥያቄዎች አሉ። የደራሼ ልዩ ወረዳ 19 ቀበሌዎችን እና አንድ ከተማን ያቀፈ ነው። የጋቶ ቀበሌ 01 እና 02 ነዋሪዎች ቀበሌያቸው ከተማ ተብሎ እንዲታወቅ ሲፈልጉ የቀበሌ 01 ነዋሪዎች ደግሞ የኮንሶ ዞን አካል መሆን ይፈልጋሉ። ከ2010 በፊት አማሮ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ኮንሶ እና አሌ ወረዳዎች በመጋቢት 19, 2003 በተመሰረተው የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ስር ይተዳደሩ ነበር። ከ2003 በፊት አማሮ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ፣ እና ኮንሶ ‘የልዩ ወረዳ’ ደረጃ የነበራቸው ሲሆን ይህም በከፊል ራሳቸውን የቻሉ እና ተጠሪነታቸው ለዞን ሳይሆን በቀጥታ ለደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ነበር። ህዳር 2010 ላይ የኮንሶ እና አሌ ከሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ተገነጠሉ። ኮንሶ የዞን ደረጃ አገኘ (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ግጭት ገጽ ይመልከቱ)።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር በጉጂ (ጉሚ ኢዳሎ ወረዳ እና ዋደራ ከተማ አካባቢ)፣ ምዕራብ ጉጂ (ሱሮ በርጉዳ እና ገላና ወረዳዎች)፣ ሆሮ ጉዱሩ (አባይ ጮመን፣ አባቦ እና ጉዱሩ ወረዳዎች)፣ ምስራቅ ወለጋ (ኢባንቱ ወረዳ)፣ ምዕራብ ወለጋ (በጊ እና መና ሲቡ ወረዳዎች)፣ ምዕራብ ሸዋ (ኢጀሬ-አዲስ አለም ወረዳ እና ቡስቲሎ ድሄራ)፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ (አመያ ወረዳ) እና ምስራቅ ሸዋ ዞን (ፈንታሌ ወረዳ) ተዋግቷል። ሚያዚያ 19 አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኦነግ-ሸኔ ጋር በጉጂ ዞን ጉሚ ኢዳሎ ወረዳ መልካ ጉባ ውስጥ ተዋግተው አካባቢውን ተቆጣጥሯል። መንግስት 200 የኦነግ-ሸኔ አባላት መገደላቸውን እና የግንባሩን የኦነግ-ሸኔ ምክትል መሪ ጨምሮ 100 አባላት መቁሰላቸውን እንዲሁም ሌሎች 20 ደግሞ እጃቸውን መስጠታቸውን ገልጿል (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 19, 2014)። በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ታጣቂዎች በኦነግ-ሸኔ ላይ የተለያዩ “እርምጃዎች” እየወሰዱ መሆኑን መንግስት አመልክቷል። እንደ መንግስት ከሆነ በእነዚህ እርምጃዎች ወቅት “ብዙ” የቡድኑ አባላት እና አመራሮች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል አልያም ተይዘዋል። ኦነግ-ሸኔን በማሰልጠን ወይም በማዋጋት የተሳተፉ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሚያዚያ 21, 2014)።
በተጨማሪም ሚያዚያ 18 ላይ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ደባቴ ወረዳ ቆርቃ፣ አልባሳ፣ ሶምቦ ስሬ፣ ግሼ፣ ጎንጎ፣ ጨሌ እና ጁላዩ ቀበሌዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኦነግ-ሸኔ ጋር ተዋግቶ እነዚህን አካባቢዎች ተቆጣጥሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቹ በሚል በደባቴ ወረዳ ጋለሳ ቀበሌ እና አካባቢው አንድ የኦሮሞ አባ ገዳ (የኦሮሞ ባህላዊ መሪ) ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ከታሰሩት 300 ሰዎች ውስጥ 180 ከሳምንት በኋላ ተለቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 27, 2014)። ከሚያዚያ 25 ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከድባቴ ወረዳ ጭንጮ፣ ገሼ እና ግሽ ጋራ ገጠር ቀበሌዎች ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 27, 2014)። ከዚህ መፈናቀል ጀርባ ያለው ትክክለኛ ምክንያት አይታወቅም። የመንግስት ሃይሎች በወረዳው ኦነግ-ሸኔን ጨምሮ በተለያዩ ታጣቂ ሃይሎች ላይ ዘመቻ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኦሮሚያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ሚያዚያ 15 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ዳዬ ዊሊንጮ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ በከፈተው ተኩስ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ ጥቃት በስተጀርባ ያለው ምክንያት አይታወቅም። ሚያዚያ 21 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ-አዲስ አለም ወረዳ ገባ ጅማታ ቀበሌ የቤት ለቤት ፍተሻ አድርገው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን ደብቃችኋል በሚል ቢያንስ 21 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው በሚገኙት የክልሉ ልዩ ሃይል መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ 10 የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎችን ገድለው ሌሎች ሶስት ደግሞ ባቆሰሉ ማግስት ነው። የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ተገድለዋል መባሉን አስተባብለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 22, 2014)። በተጨማሪም ሚያዚያ 23 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ዶሮ እርባታ ቀበሌ እየተደረገ በነበረ የሰርግ ስነስርአት ላይ በነበሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ተኩስ ከፍተው አንድ ሰው ሲገድል ሌሎች አራት አቁስሏል። የመንግስት ሃይሎች ሰርጉ ላይ የተገኙ ሌሎች 26 ሰዎችንም በቁጥጥር ስር አውለዋል። የጥቃቱ እና እስራቱ ምክንያት አይታወቅም። ሚያዚያ 25 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ካጃማ ወታደራዊ መጠለያ ውስጥ የኦነግ-ሸኔ አባላት ናችሁ በሚል ቢያንስ 15 ሰዎችን ገድለዋል። ሟቾቹ የተወሰዱት ከአንድ ቀን በፊት ከአዋሬ ጎርጄ ቀበሌ ከሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ነበር። በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ገመኔ ጉደኔ ቀበሌ ከኦነግ-ሸኔ ጋር በመተባበር የቡድኑ ታጣቂዎች የት እንደሚገኙ አልጠቁምም ብለዋል በማለት ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። በመጨረሻም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በቄለም ወለጋ ዞን ጅማ ሆሮ ወረዳ ሲቻዎ መንደር ውስጥ በኦነግ-ሸኔ የሙዚቃ ክሊፕ ላይ ፎቶውን ያገኙትን አንድ ታዳጊ የቡድኑ አባል ነው በማለት በጥይት ተኩሰው ገድለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰባት ሰላማዊ ሰልፎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ሰባት ሰልፎች ውስጥ አምስቱ በምዕራብ ሸዋ ዞን የተካሄዱ ናቸው። በዚህ ዞን ሰልፎች በአቡነ ግንደ በረት ወረዳ አዋራ እና ባቄ ቀላቴ ከተሞች፣ በዳኖ ወረዳ ስዮ፣ በአዳ በርጋ ወረዳ ኢንቺኒ እና በአምቦ ከተማ ተመዝግበዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ዋረ ጃርሶ ወረዳ ጎሃፅዮን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ተመሳሳይ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በሐረሪ ክልል ሚያዚያ 16 ላይ በሐረር ከተማ ሸንኮር ወረዳ ነፍጠኛ ሰፈር ዮድ ሆቴል ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች የእጅ ቦምብ ወርውረዋል። በዚህ ጥቃት ስምንት ሰዎች ቆስለዋል።
በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ የአል ሸባብ አባል ናቸው እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ጥቃት ለማድረስ አስበዋል ተብለው የተጠረጠሩ 34 ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግስት አስታውቋል።
በመጨረሻም ሚያዝያ 17 ላይ ትህነግ/ህወሃት ሃይሎቹ ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን አስታውቋል (ሮይተርስ፣ ሚያዚያ 17, 2014)። ነገር ግን የአፋር ክልል መንግስት እና ፌዴራል መንግስቱ ይህንን ውድቅ በማድረግ የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች አሁንም በአፋር ክልል አባላ ወረዳ እና ሌሎች ወረዳዎች እንዲሁም አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ይዘው እንደሚገኙ አስታውቀዋል (የአፋር ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 19, 2014፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሚያዚያ 21, 2014፤ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሚያዚያ 21, 2014)። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ትህነግ/ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ኃይሉን በማሰባሰብ ላይ መሆኑን አመልክተዋል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሚያዚያ 21, 2014)። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ80 በላይ የሚሆኑ የሰብአዊ አቅርቦቶችን የጫኑ መኪኖች መቀሌ ከተማ ደርሰዋል (አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ሚያዚያ 22, 2014፤ ደብሊውኤፍፒ ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 17, 2014፤ ደብሊውኤፍፒ ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 23, 2014)። ሆኖም ግን አሁንም የተላኩት የሰብአዊ አቅርቦቶች በመሬት ላይ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ አይደሉም። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ 145 መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል ቢገቡም የተመለሱት ከ40 በታች መሆናቸውን ገልጿል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ሚያዚያ 21, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች አዝማሚያ
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የነበሩ የፖለቲካ ግጭቶች በመላው ሃገሪቷ ያሉ ግጭቶች የመቀነስ አዝማሚያ መቀጠሉን የሚያሳይ ሲሆን ይህም በዋናነት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ያለው ግጭት የመቀነሱ ነጸብራቅ ነው። ጥቅምት 2013 የጀመረው የሰሜኑ ጦርነት በጣም ከባድ ግጭት ሲሆን ከዚህ ጋር የተያያዙ ኩነቶች እና ሟቾች በቀሪው የሃገሪቱ ክፍሎች ያሉትን ሸፍነዋል። ነገር ግን ካለፉት ሁለት ሳምንታት ማየት እንደሚቻለው በአገሪቱ ያሉ አነስተኛ እና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ ግጭቶች እየጨመሩ ነው። እነዚህ ትንንሽ ግጭቶች የጸጥታ ሃይሎችን እያጨናነቁ እና በሰሜናዊው ካለው ግጭት ጋር በሚስተካከል መልኩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ህይወት ላይ ተጽእኖ እያሳረፉ ነው።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ግጭት በአንጻራዊነት የማይፈጠር ሲሆን በዚህ ሳምንታዊ ዘገባ የሁኔታዎች አጭር ዘገባ ውስጥ የተዘረዘሩ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች ማህበረሰቡ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለው አቅም የመዳከም አዝማሚያ ያሳያል። ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ እስከ ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በፍጥነት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መስፋፋቱ አነስተኛ ግጭቶች በግጭቱ አቅራቢያ ከሚገኙት በተጨማሪ ወደ ሌሎች ማህበረሰቦች እንዴት በፍጥነት እንደሚዛመቱ ያሳያል። ይህ በተወሰነ መልኩ ከትህነግ/ህወሃት እና ኦነግ-ሸኔ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ነገር ግን እንደ ሃይማኖት እና ማህበረሰብ በመሳሰሉ ሌሎች ግጭቶች ውስጥም ከተሳተፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በቀጥታ ይገናኛል። በተጨማሪም ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች እየተዳከሙ መሆናቸውን ሊጠቁም ይችላል። በኦሮሚያ ክልል በተለምዶ የአካባቢ ግጭቶችን የሚፈቱ አባ ገዳዎች በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶችን እንዲሁም ትልቅ የሆነውን በኦነግ-ሸኔ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት መካከል የተፈጠረውን ግጭት መፍታት አልቻሉም። በተመሳሳይ የሀይማኖት አባቶች በጎንደር ከተማ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ሁከት ማስቆም አልቻሉም።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በተለያዩ መስመሮች የተከፋፈለ ሲሆን አሁን ያለው ሁኔታ በብዙ መልኩ ከ2006-2010 ከነበሩት ሰልፎች አንጻር አደገኛ ነው። በኦሮሚያ ክልል በኦነግ-ሸኔ ላይ ለአንድ ወር የተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ አንዳንድ ለውጦችን ያመጣ ቢመስልም በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ ነው (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 3, 2014)። የኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች ከኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በብዙ አካባቢዎች መዋጋት ቀጥለዋል እንዲሁም የጸጥታ ሀይሎችን የመንገዶችን ደህንነት ከወንጀለኞች መጠበቅ ከመሳሰሉት መደበኛ ስራቸው አውጥቷቸዋል። በግንደ በረት አካባቢ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን የአየር ድብደባ ጨምሮ የመንግስት ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚፈጽሟቸው ግድያዎች ጨምረዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 25, 2014)። በማህበረሰብ መካከል ያሉ ግጭቶች፣ የአናሳ ብሔረሰቦች ኢላማ መደረግ እና በግዛት ምክንያት የሚነሱ ውዝቦች በኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶችን መጠን ሊጨምሩ ይችላሉ።
በአማራ ክልል የመንግስት ሃይል ያልሆኑ ታጣቂዎች ለመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ትልቅ ፈተና ፈጥረዋል። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ እነዚህን ቡድኖች የተሳተፉባቸው ግጭቶች ነበሩ። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም እነዚህ ግጭቶች ከዚህ ዓመት በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለአማራ ክልል አዲስ የጸጥታ ፈተናን ፈጥረዋል። በጎንደር ከተማ እንደታየው የሀይማኖት ግጭት ሁሉ እንደ ፋኖ ያሉ ታጣቂዎች የግጭቱ ቀስቃሾች ናቸው የሚል ውንጀላ ቀርቧል። እነዚህ ሃይሎች ከአማራ ክልል መንግስት መዋቅር ውጭ መሆናቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ በክልሉ ግጭት የመባባስ እድሉ ከፍተኛ ነው።
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የአካባቢ ባለስልጣናት በኮንሶ/ሰገን ህዝቦች አካባቢ የተፈጠረውን ሁከት ለመቆጣጠር እየታገሉ ነው። በዚህ ዘገባ አጭር ሁኔታ መግለጫው ላይ በዝርዝር እንደተገለፀው አስተዳደራዊ ለውጦች እንዲደረጉ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እንዲሁም የአካባቢው መንግስት ለእነዚህ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እና ሁከትን መቆጣጠር ባለመቻሉ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። እነዚህ ግጭቶች በሰሜናዊው ክፍል ካለው ጦርነት ጋር ሲነፃፀሩ አነስተኛ ቢሆኑም የአካባቢው የጸጥታ ሃይሎችን አጨናንቋል። በደራሼ ልዩ ወረዳ ለሳምንት ያህል በዘለቀው ግጭት ምክንያት የአካባቢው መስተዳድር አካባቢውን ማስተዳደር ባለመቻሉ በወረዳው ካሉ ቀበሌዎች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ቀበሌያቸውን የማስተዳደር እና የማረጋጋት ኃላፊነት ተረክበዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 25, 2014፤ ኢኤምኤስ፣ ሚያዚያ 22, 2014)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአካባቢውን የጸጥታ ሀላፊነት የወሰደው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በማሰብ ነበር። በደራሼ ልዩ ወረዳ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከሰቱት ግጭቶች ህዳርእና ጥር 2013 ላይ የተከሰቱት ግጭቶችን ቀጣይነት የሚያሳይ ነው።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተዘገቡት ጥቂት ኩነቶች ላለፉት ሁለት ዓመታት እየተባባሱ የነበሩ ትንንሽ ግጭቶች ጋብ ያሉ መሆናቸውን ያሳያል ። ነገር ግን ግጭቶቹ በመተከል ዞን ያሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ህይወት ያናጉ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት በቅርቡ ባወጡት ግምት በዞኑ ካለው መታረስ የሚችል መሬት በዚህ አመት የለማው 35% ብቻ ነው (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 22, 2014)።
ትህነግ/ህወሃት እና የኢትዮጵያ መንግስት በአፋር ክልል ሁኔታ ላይ እርስ በእርስ እየተካሰሱ ባሉበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እየቀነሰ የመጣ ይመስላል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሚያዚያ 25, 2014)። ነገር ግን ሁሉን አቀፍ የሰላም እቅድ ባለመኖሩ በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ግጭት በድጋሚ የመቀስቀስ እድሉ ከፍተኛ ነው። በመላ አገሪቱ ለሚፈጠሩ ትንንሽ ግጭቶች በብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን የታቀደው ብሔራዊ ውይይት የተስፋ ጭላንጭል ይፈጥራል። ይሁን እንጂ በብሔራዊ ውይይቱ ፅንሰ-ሀሳቡ፣ ተሳትፎ እና ረጅም የአጀማመር ሂደት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች ግጭቶች ቀስ በቀስ በፈረንጆች ባለፈው ዓመት ወደ ነበረበት ነገር ግን ከበፊቱ በሰፋ አካባቢ ላይ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ማሳያ ነው።