ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 በጨረፍታ
አበይት አሃዝ
- አክሌድ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ (እ.ኤ.አ በአፕሪል ወር) 92 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና ሪፖርት የተደረጉ 377 ሟቾችን መዝግቧል፤ አክሌድ ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ (እ.ኤ.አ በሜይ ወር) 67 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና ሪፖርት የተደረጉ 450 ሟቾችን መዝግቧል።
- ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር የተዘገበው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን በክልሉ 309 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። የአማራ ክልል በ37 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ በተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 287 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። የትግራይ ክልል በ121 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 61 ኩነቶች ከ251 ሟቾች ጋር ተመዝግቧል። በተመሳሳይ፣ ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 34 ኩነቶች ከ368 ሟቾች ጋር ተመዝግቧል።
አበይት ክንውኖች
- ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እና ኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መዋጋት ቀጥሏል።
- ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በኤርትራ መከላከያ ሰራዊት መካከል ውጊያዎች እንዲሁም በኤርትራ መከላከያ ሠራዊት የተፈፀመ የከባድ መሳሪያ ድብደባ በትግራይ ክልል ተመዝግበዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ግን ከትህነግ/ህወሓት ጋር የተያያዘ ምንም አይነት ኩነት አልተዘገበም።
- በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ውጊያዎች ተቀስቅሰዋል በሰላማዊ ሰዎችም ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
- ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ የሀይማኖት ቡድኖችን ያካተተ የፖለቲካ አለመረጋጋት ጨምሯል። በዚያው ወር አክሌድ ከግንቦት/ሰኔ 2012 በኃላ ከፍተኛ የሆነውን የረብሻ ኩነቶችን መዝግቧል።
- ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ መንግስት ባደረገው “የህግ ማስከበር” ዘመቻ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የጅምላ እስራቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከፍተኛው የታሳሪዎች ቁጥር የተዘገበው በአማራ ክልል ነው።
ይህ ሪፖርት ያካተተው
- ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 የሁኔታዎች ማጠቃለያ
- ወርሃዊ ትኩረት: የኃይማኖት ጥቃት በኢትዮጵያ
ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 የሁኔታዎች ማጠቃለያ
ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 (እ.ኤ.አ በአፕሪል እና ሜይ ወራቶች) የውጊያ ኩነት አይነት ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ማለትም ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ (እ.ኤ.አ በአፕሪል ወር) ከ61 ኩነቶች 37ቱ ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ (እ.ኤ.አ በሜይ ወር) ደግሞ ከ34 ኩነቶች 25ቱ በኦሮሚያ ክልል ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። አብዛኛው ውጊያ የተካሄደው በኦነግ–ሸኔ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል መካከል ነው። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ አክሌድ በኦነግ–ሸኔ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል 35 የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ደግሞ በኦነግ–ሸኔ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል 25 የውጊያ ኩነቶች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ተመዝግበዋል። በሁለቱም ወራት ውስጥ ውጊያዎች በምስራቅ ሸዋ፣ ጉጂ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ጉጂ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተመዝግበዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ውጊያዎች የተመዘገቡት በቦረና በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ብቻ ሲሆን በምስራቅ ሀረርጌ፣ ፊንፊኔ ልዩ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች ውጊያ የተመዘገቡት ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም በነበሩት ቀናት ውስጥ ብቻ ነበር።
ኦነግ–ሸኔ የተሳተፈባቸው ውጊያዎች ከኦሮሚያ ክልል ውጪም ተመዝግበዋል። ሚያዚያ 18 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ኦነግ–ሸኔ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በዲባጤ ወረዳ በቆርቃ፣ አልባሳ፣ ሰንቦስሬ፣ ገሼ፣ ጎንጎ፣ ጨሌ እና ጁላዩ ቀበሌዎች ተዋግተው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ተቆጣጥሮታል። በሚያዚያ 9 እና 10 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች የፋኖ እና የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ከኦነግ–ሸኔ እና ከኦሮሞ ብሔር ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ ዘንቦ፣ አዲስአለም እና ነጌሶ ቀበሌዎች እና በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ቀወት ውጊያዎች ተመዝግበዋል። በኦሮሚያ ልዩ ዞን በጅልዬ ጥሙጋ ወረዳ ወሴን ኩርኩር፣ ሙቴ ፋጫ እና ትኩሬ ዋዳዎ ውስጥ ጦርነት ተከስቷል። በእነዚህ ወረዳዎች በተፈጠረ ጦርነት በትንሹ 20 ሰዎች ሲሞቱ 48 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፤ ሚያዚያ 13, 2014)። ውጊያውን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና የፌዴራል ፖሊስ በቦታው ተንቀሳቅሰዋል። ውጊያውን ለመቆጣጠር በተወሰደው እርምጃ ቢያንስ ሁለት የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በአንዱ ተፋላሚ ወገን ተገድለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፤ ሚያዝያ 13, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀር ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 በነበሩት ጊዜያት ከፍ ያለ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም አክሌድ በኢትዮጵያ 27 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን የመዘገበ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 17ቱ የተመዘገቡት በኦሮሚያ ክልል ነው። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ 28 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 17ቱ በኦሮሚያ ክልል ተመዝግበው ይገኛሉ። በኦሮሚያ ክልል በተከሰቱት እነዚህ ኩነቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል፣ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች፣ የፋኖ ታጣቂዎች እና ኦነግ–ሸኔ እጃቸው እንዳለበት ተነግሯል። የአክሌድ መረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 በነበሩት ግዚያት በመንግስት ሃይሎች የተፈፀሙ ከህግ አግባብ ውጭ የሚደረጉ ግድያዎች መጨመሩን ያሳያል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከተመዘገቡት 17 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ውስጥ አስሩ እንዲሁም ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም በሉት ግዚያት ከተመዘገቡት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ውስጥ ደግሞ አስራ አንዱ የተፈፀሙት የመንግስት ሃይሎች ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል እንደፈፀሙት ተመላክቷል። ይህም አክሌድ ቀደም ባለው ወር ማለትም ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 ድረስ (እ.ኤ.አ በማርች ወር) በምዕራብ ሸዋ ዞን በመንግስት ሃይሎች የተፈፀሙ ሶስት ከህግ አግባብ ውጭ የተደረጉ ግድያዎች ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ አሳይቷል። የዚህ ጥቃት ተጎጂዎች የኦነግ–ሸኔ አባላት ናቸው አልያም ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም የቡድኑን አባላት ደብቀዋል በሚል ይወነጀላሉ። ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 በነበሩት ጊዜያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር በምዕራብ ሸዋ ዞን ተመዝግቧል። በተጨማሪም ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉደቱ ኮንዶሌ ወረዳ ቦጂ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ከኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ከ300 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በኦሮሚያ ክልል ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 በነበሩት ጊዜያት በኦነግ–ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ቀደም ካለው ወር ማለትም ከየካቲት 22, 2014 እስከ መጋቢት 22, 2014 (እ.ኤ.አ ከማርች ወር) ጋር ሲነጻጸር ቀንሷል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ እንደዚህ ያለ ክስተት ሲመዘገብ ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ሁለት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ኦነግ–ሸኔ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በመኔዮ እና ድሬ ቀበሌዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስምንት ሰዎችን ገድሏል፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናትን አፍኗል፣ ቤቶችን አቃጥሏል እንዲሁም ዘርፏል። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አማሮ ወረዳ እና በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ባቲ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ሁለት ጥቃቶች ኦነግ–ሸኔ ተሳትፏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም አክሌድ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ውስጥ እነዚህ ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው ስድስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ኩነቶችን መዝግቧል። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የፋኖ ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው አራት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ኩነቶች ተመዝግበዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ አክሌድ በኢትዮጵያ ውስጥ 23 የሰልፍ ኩነቶችን መዝግቧል – ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም 16 የሰልፍ ኩነቶችን እና ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ስምንት የሰልፍ ኩነቶችን መዝግቧል። አብዛኛዎቹ እነዚህ የሰልፍ ኩነቶች – ማለትም ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ድረስ ዘጠኙ እና ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ስድስቱ – በኦሮሚያ ክልል ተካሂደዋል። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ከነበሩት ዘጠኙ የሰልፍ ኩነቶች ሰባቱ እና ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ድረስ የተካሄዱት ሁሉም ሰልፎች በሙሉ ኦነግ–ሸኔን በመቃወም የተደረጉ ሠላማዊ ሰልፎች ነበሩ። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም የተደረጉት ሁለት ተጨማሪ ሰልፎች በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ሰልፎች ነበሩ። አብዛኛው ኦነግ–ሸኔን በመቃወም የተደረጉት ሰልፎች የተካሄዱት በምዕራብ ሸዋ ዞን ነው። በዚህ ዞን በአቡና ጊንደ በረት ወረዳ በአዋራ እና ባኬ ከላቴ ከተሞች፣ በዳኖ ወረዳ ስዮ፣ በአዳ በርጋ ወረዳ ኢንቺኒ፣ በጀልዱ ወረዳ ሽኩቴ ከተማ እና አምቦ ከተማ እነዚህ ሰለፎች ተመዝግበዋል። ተመሳሳይ ሰልፎች በሰሜን ሸዋ ዞን ጎሃጽዮን፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ገብረ ጉራቻ እና ዋቤ ከተሞች እንዲሁም በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ተካሂዷል። መጋቢት 27 ቀን በምስራቅ ባሌ ዞን በለጌ ሂዳ ወረዳ የበልቱ ከተማ ነዋሪዎች በከተማቸው የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥን በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ሰልፉን ለመበተን ተኩስ በመክፈቱ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ተቃዋሚዎችን አቁስሏል። የተቃውሞ ሰልፉን አስተባብረዋል የተባሉ ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ታስረዋል። ሚያዚያ 21 ቀን በጅማ ከተማ ሙስሊሞች በጎንደር ከተማ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል። ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ጥቃቶቹን ተከትሎ የተፈጠረው አለመረጋጋት በወርሃዊ የትኩረት ክፍል በዝርዝር ተብራርቷል።
በሲዳማ ክልል ጪሪ ወረዳ ሀሌላ እና ሱጫ ቀበሌዎች እና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ሻምበል እና ውሮ ቀበሌዎች መጋቢት 25 ቀን በኦሮሞ እና በሲዳማ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ቆስለዋል። ግጭቱ የተከሰተው በሲዳማ ክልል በጪሪ ወረዳ በሀሌላ ቀበሌ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን አንድ የአካባቢውን የሲዳማ ሽማግሌ ከገደለ በኋላ ነው (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት, 27 2014)። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት በቤንሳ ወረዳ ሃሜሾ ቦረና ቀበሌ እና በቡራ ወረዳ በሳንጎታ ቀበሌ የኦሮሞ ብሔር ታጣቂዎች እና የሲዳማ ብሔር ታጣቂዎች መዋጋታቸውን ተከትሎ የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 17 ሰዎች ቆስለዋል።
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከአስተዳደራዊ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ሁከቶች እና ውጊያዋች ተመዝግበዋል። መጋቢት 28 ቀን በደቡብ ኦሞ ዞን አሪ ወረዳ እና ጂንካ ከተማ ውስጥ ለአሪ ብሔር የራሱ የሆነ የዞን አስተዳደር እንዲቋቋም የጠየቁ የአሪ ብሔር አባላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተወሰኑ ቤቶችን አቃጥለዋል። በተፈጠረው አለመረጋጋት ቢያንስ አንድ ሰው ሲሞት 25 ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃቱ የተቀሰቀሰው የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ጥቃቱ ከመሰንዘሩ አንድ ሳምንት በፊት ባደረገው ስብሰባ ላይ የአሪ ብሔረሰብ ጥያቄዎችን ለውይይት አጀንዳነት ባለማቅረቡ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ነዋሪዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል። የዞኑ አስተዳደር ኃላፊዎች ለዚህ ስህተት ይቅርታ በመጠየቅ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ሁኔታውን ለማረጋጋት ሞክረው ነበር (ቲክቫህ–ቤተሰብ፣ ሚያዝያ 2, 2014)። ነገር ግን ከሚያዝያ 1 እስከ 3 ድረስ የአሪ ወጣቶች በጂንካ ከተማ በጋዘር፣ ቶልታ እና ማፀር አካባቢዎች የመንግስት ህንፃዎችን፣ የመኖሪያ ቤቶችን እና ሱቆችን ማጥቃት እና ማቃጠል ቀጥለዋል። በዚህም ምክንያት ሚያዝያ 2 ቀን የሰዓት እላፊ የታወጀ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ሁከቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥሪ ተደርጎላቸዋል (ብስራት ራዲዮ፣ ሚያዝያ 3, 2014)። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም አራት የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 842 ሰዎች በሁከቱ ተሳትፈዋል በሚል ታስረዋል። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላም አልጎ ወረዳ ማንነታቸው ያልታወቁ የብሔር ቡድኖች መካከል ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ውጊያ ተደርጓል። በዚህ ውጊያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል::
በሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ ረብሻ እና ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ውጊያው በግንቦት ወርም ቀጥሏል። በመሆኑም ሁሉም የመንግስት እና የግል ተቋማት ከአንድ ሳምንት በላይ ተዘግተው ነበር። ሚያዚያ 18 ቀን በደራሼ ልዩ ወረዳ ካሉ ታጣቂ ሃይሎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል የተባሉት የጉማይዴ ታጣቂዎች ስምንት የህንድ ቱሪስቶችን እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ኢትዮጵያውያንን ከአርባ ምንጭ ከተማ ወደ ጂንካ ይጓዙ የነበሩበትን ተሽከርካሪ፤ ሹፌር እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ላይ በሆልቴ ቀበሌ ጥቃት በማድረስ አግተዋቸዋል። ታግተው የተወሰዱትን ቱሪስቶች ለማዳን ወደ ሆልቴ ቀበሌ የገቡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ተገድለዋል። የመንግስት ሃይል ወደ ወረዳው ሲገባ የታገቱት ሰዎች ተለቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 20, 2014)። በማግስቱ በደራሼ ልዩ ወረዳ በጋቶ ቀበሌ እና በጊዶሌ ከተማ የጉማይዴ ታጣቂዎች ከደቡብ ክልል ልዩ ሃይል እና የቀበሌ ሚሊሻዎች ጋር ተዋግተዋል። በዚህ ውጊያ ከሁለቱም ወገኖች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል፣ ነዋሪዎችም የጋቶ ቀበሌን ለቀው ለመሸሽ ተገደዋል። ታጣቂዎቹ በጊዶሌ ከተማ የደራሼ ልዩ ወረዳ የመንግስት ኃላፊዎችን መኖሪያ ቤትም አቃጥለዋል። ይህም ባለሥልጣኖቹ ከስፍራው እንዲሸሹ አስገድዷቸዋል። ሚያዚያ 19 እና 21 በጊዶሌ ከተማ በጊዶሌ እና በኮንሶ ብሔር ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተመዝግቧል። በተጨማሪም ሚያዝያ 22 ቀን በደራሼ ልዩ ወረዳ የደራሼ እና የኮንሶ ብሔር ታጣቂዎች ተዋግተዋል። በእለቱም በወረዳው ቡስታ ቂላ ቀበሌ አንድ የአካባቢው አስተዳዳሪ በሁከት ፈጣሪዎች ተገድለዋል። ረብሻ ፈጣሪዎች አስተዳዳሪውን ህዝቡ የራሳቸውን አስተዳደር ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ ለከፍተኛ ባለስልጣናት አላስተላለፉም ብለው ከሰዋቸዋል። አስተዳዳሪው በደራሼ ልዩ ወረዳ በተፈጠረው አለመረጋጋት ከሚያዝያ 19 ጀምሮ ቡስታ ቂላ ቀበሌ አካባቢ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ተደብቀው ነበር።
ግንቦት 1 ቀን በጊዶሌ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት በሐታያ እና ሰለሌ ገጠር መንደሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ የፌዴራል ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ከደራሼ ብሔር ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ተከትሎ የትጥቅ ትግሉ በግንቦት ወርም ቀጥሏል። በደራሼ ልዩ ወረዳ በተፈጠረው አለመረጋጋት እና በውጊያ እጃቸው አለበት የተባሉ 316 ሰዎች ባለፈው ወር በቁጥጥር ስር ውለዋል። ደራሼ በደቡብ ክልል የዞን አስተዳደር የመመስረት ጥያቄ ከሚነሳባቸው ወረዳዎች አንዱ ነው (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ የግጭት ማብራሪያ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
በኮንሶ ዞን በሰገን ዙሪያ ወረዳ ጉማይዴ በበቾ ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ግንቦት 3 እና 4 በንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት በማድረስ ቢያንስ አንድ ሰላማዊ ሰው ገድለዋል። ቡድኑ ቤቶችን እና ቤተ ክርስቲያንን አቃጥሏል። በእነዚህ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር ማዕከል በሆነው በሲዳማ ክልል በሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ሶስት ሰልፎች ተመዝግበዋል። ከጉራጌ ዞን የመጡ የማረቆ ብሔር አባላት የማረቆ ወረዳ ከጉራጌ ዞን ተነጥሎ ልዩ ወረዳ ተብሎ እንዲሰየም በመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ከጉራጌ ዞን የመጡት የሰባት ቤት ዶቢ ክስታኔ ብሔር አባላትም ለብሔራቸው የተለየ ወረዳ እንዲቋቋምላቸው በመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። በተመሳሳይ ወቅት የኮሬ ብሔር አባላት በሃዋሳ ከተማ ከደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት በመሰባሰብ “የኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች በአማሮ ወረዳ በኮሬ ገበሬዎች ላይ እየደረሱት ያለውን ግፍ” መንግስት እንዲያስቆምላቸው በሰላማዊ መንገድ ጠይቀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሚያዚያ 5, 2014)።
በአማራ ክልል ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ያለውን ጊዜ ሁለት አበይት ክንውኖች ተቆጣጥረውት ነበር። ከዚህ በታች ባለው በወርሃዊ ትኩረት ክፍል ላይ በዝርዝር እንደተብራራው፣ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ከሃይማኖት ቡድኖች ጋር የተያያዘ የፖለቲካ አለመረጋጋት ተባብሶ ነበር። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23 , 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የክልሉ መንግስት በክልሉ ውስጥ “የህግ ማስከበር” ዘመቻ ጀምሯል። በዚህም ምክንያት በፋኖ ታጣቂዎች፣ አማራ ብሔርተኞች እና በመንግስት መካከል ያለው ውጥረት ወሩን ሙሉ ጨምሯል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 6 እስከ 12, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014 ይመልከቱ)። በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች፣ ተኩስ እና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ላይ ጣልቃ ገብነት በመጨመሩ “የህግ የማስከበር ዘመቻው” አስፈላጊ መሆኑን የክልሉ መንግስት ገልጿል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 10, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13, 2014)። በዚህ ዘመቻ ጋዜጠኞችን እና የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል መሪ የነበሩትን ጨምሮ ከ4,500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 15, 2014)።
ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ከ“ህግ ማስከበር” ዘመቻው በፊት የፋኖ ታጣቂዎች፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል የተሳተፉባቸው ሶስት ውጊያዎች በክልሉ ተመዝግበዋል። ሚያዝያ 2 ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የፋኖ ታጣቂዎች አመራር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በከተማዋ ዙሪያ ካሉ አካባቢ የመጡ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ሊገቡ ሲሉ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተኩስ ተለዋውጠዋል። በግጭቱ አንድ ታጣቂ እና አንድ ቄስ ተገድለዋል። በተመሳሳይ ቀን በሰሜን ወሎ ዞን ጎብዬ እና ሮቢት ሁለቱ ቡድኖች ተዋግተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የተመዘገበ ጉዳት የለም።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ሁሉም የጦር መሳሪያዎች መመዝገብ አለባቸው የሚል አዋጅ ካወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በክልሉ ውስጥ ሶስት ውጊያዎች ተመዝግበዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 8, 2014)። በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ በመንግስት ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተመዝግቧል። በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ እና በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቡ ወረዳ በቢስቲማ ከተማ በመንግስት ሃይሎች እና ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች መካከል ሌሎች ሁለት ውጊያዎች ተመዝግቧል። በቢስቲማ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በከተማዋ የሃይማኖት አመፅ ለመቀስቀስ ተንቀሳቅሷል በሚል በቁጥጥር ስር የዋለን ሰው በኃይል ለማስፈታት ሲሞክሩ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል። በዚህ ውጊያ አራት ሰዎች ሲሞቱ 11 ሰዎች ቆስለዋል።
በሌላ በኩል በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ እና በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶች እንዲፈቱ የሚጠይቁ ሰልፎች ተካሂደዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል በሰልፈኞቹ ላይ ጥይት በመተኮሳቸው ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን ገድለዋል አቁስለዋል። በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ ባንቧ ወሃ ክፍለ ከተማ በኬላ አካባቢ በፖሊስ የፋኖ ታጣቂ ነን የሚሉ ናቸው የተባሉ የታጠቀ ቡድን አባላት በፖሊስ አባላት ላይ የእጅ ቦምብ ወርውረዋል። በዚህም ሶስት ፖሊሶች ቆስለዋል ተብሏል። የአይን እማኞች ግን ይህንን ክስ ውድቅ በማድረግ በእስር ላይ የሚገኙ የፋኖ አባላት እንዲፈቱ የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢው በተሰባሰቡት ወቅት አንድ ፖሊስ ጠመንጃው ባርቆበት ራሱን እና ሌላ ፖሊስ ተኩሶ ማቁሰሉን አስረድተዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከመጋቢት 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ጸጥታ ሃይሎች የተሳተፉበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ከሚያዚያ 2 እስከ 4 በቡለን ወረዳ በጎዶራሬ መንደር ፣በዳንጉራ ወረዳ ድልሳምቤ እና መንደር 3፣ በመዲራ ወረዳ ኦሺጊ እና የኪታ መንደር የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የጉሙዝ ተወላጆችን መግደላቸው ተዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመተከል ዞን የዳንጉር ወረዳ ኮማንድ ፖስት እንዳስታወቀው እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ 247 የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) አባላት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሰጥተዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 7, 2014) ። በግንቦት ወር በድባጤ ወረዳ ጊፎ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁለት ሰዎችን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ከተገደሉት መካከል አንዱ የኦነግ–ሸኔ አባል ነው ተብሎ የተጠረጠረ ሲሆን ሁለተኛው ሟች በምን ምክንያት እንደተገደለ ግን አይታወቅም። በሚያዚያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል ከኦነግ–ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል በድባጤ በጋሌሳ ቀበሌ እና አካባቢው አንድ የኦሮሞ አባ ገዳን (የኦሮሞ ባህላዊ መሪን) ጨምሮ ከ300 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ከታሰሩት 300 ሰዎች ውስጥ 180ዎቹ ከሳምንት በኋላ ተለቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 5, 2014)።
በሌላ በኩል በሐረሪ ክልል ሚያዚያ 16 ቀን ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን በሐረር ከተማ በሸንኮር ወረዳ በነፍጠኛ ሰፈር በሚገኘው ዮድ ሆቴል ላይ ቦምብ በመወርወሩ ስምንት ሰዎች ቆስለዋል። በጋምቤላ ክልል ግንቦት 13 ቀን በአኝዋክ ዞን ዲማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በኡኩጎ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን ተኩስ ከፍቶ ጥቃት በማድረስ አራት ሰዎችን ገድሏል። በእለቱ ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቂ ቡድን በመርከስ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሁለት ሰዎችን ተኩሶ ገድሏል። እነዚህ አጥቂዎች ተመሳሳይ ታጣቂ ቡድን ስለመሆናቸው ግን ግልጽ አይደለም።
ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ከጎረቤት ሀገራት በመጡ ታጠቂዎች የተፈፀሙ ሁለት ጥቃቶች ተዘግበዋል። ሚያዚያ 5 አካባቢ ከኬንያ የመጡ የቱርካና ብሔር ታጣቂዎች የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣንን ተኩሰው እንደገደሉ ተዘግቧል (ዘ ስታንደርድ፣ ሚያዚያ 5, 2014)። የዚህ ክስተት ትክክለኛ ቦታ በውል ባይታወቅም በኬንያ ድንበር ውስጥ መከሰቱ ግን ተዘግቧል። ሚያዚያ 6 ቀን ከጎረቤት ሃገር ሶማሊያ የመጡ የማሬሃን ጎሳ ታጣቂዎች በሶማሌ ክልል ኮራሄ ዞን አሊን ከተማ አቅራቢያ ከማቃቡል–ሙሴ ጉምአድሌ ክፍለ–ጎሳ የሆኑ ሰላማዊ አርብቶ አደሮች ላይ ጥቃት ሰንዝረው አምስት ሰዎችን ገድለዋል። የጥቃቱ ምክንያት ባይታወቅም የካቲት 23 ቀን ሁለቱ ቡድኖች በመሬት ውዝግብ ምክንያት ተዋግተው ነበር።
በአፋር ክልል ኪልባቲ ረሱ–ዞን 2 በትህነግ/ህወሓት ሃይሎች፣ በአፋር ክልል ልዩ ሃይል እና በአፋር ታጣቂዎች መካከል ለወራት የዘለቀ ውጊያ በኃላ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ከትህነግ/ህወሓት ጋር የተያያዘ ምንም አይነት ውጊያ አልተዘገበም። ከሚያዚያ 23 እስከ ግንቦት 23, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ግን በትህነግ/ህወሓት እና በኤርትራ መከላከያ ሠራዊት መካከል ሁለት ውጊያዎች በማዕከላዊ ትግራይ ዞን ራማ እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን አዲ አዋላ ምዕራባዊ ክፍል ተዘግበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በግንቦት 20 እና 21 የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ሸራሮ ከተማ በትህነግ/ህወሓት ቁጥጥር ሰር የሚገኙ ቦታዎች ተደጋጋሚ መድፍ በመተኮስ ተፈናቃዮች ያረፉበትን ትምህርት ቤት መቷል፣ ቤቶችንም አወድሟል (ሮይተርስ፣ ግንቦት 23, 2014)። በጥቃቱ የ14 ዓመት ሴት ልጅ ስትገደል 18 ሰዎች ድግሞ ቆስለዋል።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የኃይማኖት ጥቃት በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ረጅም እና የበለጸገ ሃይማኖታዊ ታሪክ ያላት እና ብዙ ጊዜ በኃይማኖቶች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። ለጥንት ክርስትናም ሆነ እስልምና አስፈላጊ ቦታ እንደመሆኗ መጠን፣ አገሪቱ ለተለያዩ እምነቶች ቅዱሱ ተብለው የሚታሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስፍራዎች መገኛ ነች። ይህም ሆኖ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በመላ ኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶች ኢትዮጵያውያን የተቀደሱ የሚሏቸው ሥፍራዎች እና የሀገሪቱን ኃይማኖታዊ ማህበረሰብ በሚያስተሳስራቸው ጉዳዮች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ግጭቶች አልፎ አልፎ ቢከሰቱም፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው ከፍተኛ የፖለቲካ ፉክክር በኃይማኖት ላይ የሚፈጥሯቸው ጫናዎች በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኃይማኖት ማህበረሰብ አዲስ ፈተናዎች ሆነዋል። ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ የኃይማኖት ግጭቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
ይህ ወርሃዊ ትኩረት የተፃፈው ታዋቂው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ኤክስፐርት Terje Østebø ለፃፈው ፅሁፍ ምላሽ እንዲሁም ለፅሁፍ እንደ ቀጣይነት ያለው ፅሁፍ ነው። በጥቅምት 2012 ረብሻ ከተፈጠረ በኋላ በአዲስ ስታንዳርድ ባወጣው ትንታኔ ፕሮፌሰር Østebø ከ2010 ፖለቲካዊ ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ኃይማኖታዊ ጥቃቶች “አዲስ ሁኔታ” እንደሆኑ እና “ኃይማኖት እንደ አዲስ ግልጽ የሆነ የግጭት ምክንያት እየሆነ ነው?” ወይስ አይደለም የሚለውን ለመመለስ ይመራመራሉ (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 27, 2012)።
በዚህ ጽሑፍ የአክሌድን የፖለቲካ አለመረጋጋት መረጃ ቋት በመጠቀም በቅርቡ የተከሰተውን ኃይማኖታዊ ጥቃት እንተነትናለን። በኢትዮጵያ ከኃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግጭቶች በኃይማኖት እና ብሔር መካከል ባለው መተሳሰር ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው እንጂ የኃይማኖት አክራሪነት እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት የተፈጠሩ ግጭቶች አይደለም ሲሉ ፕሮፌሰር Østebø በሰጡት መደምደሚያ እኛም እንስማማለን።
አክሌድ ኃይማኖተኞችን የሚያካትቱ ሁከቶች በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሰፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከሰት ይገነዘባል፤ ስለዚህ የትኛውም ኩነት ሙሉ ለሙሉ ኃይማኖታዊ ይዘት ያለው ብቻ አይደለም። በዚህ ጽሑፍ፣ ኃይማኖታዊ የግጭት ኩነቶች ማለት በኃይማኖተኞች የተሳተፉበት፣ የአንድ ኃይማኖት ቡድን አባል በሆኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን ጨምሮ ግልጽ የሆነ ኃይማኖታዊ ይዞታ ያላቸውን ክስተቶች ነው።
በድህረ-2010 ኢትዮጵያ ውስጥ ኃይማኖታዊ ጥቃት
ከ2010 በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ የኃይማኖት ግጭቶች እየተለመደና ገዳይም እየሆነ መጥቷል። የአክሌድ የመረጃ ቋት ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በአፕሪል ወር) የኃይማኖት ወገኖች የተሳተፉበት ስድስት የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን፣ ሶስት አመጽ የተቀላቀለባቸው ሰልፎችን እና አምስት ሰላማዊ ሰልፎችን ጨምሮ 14 የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን ከ26 ሪፖርት ከተደረጉ የሰዎች ሞት ጋር መዝግቧል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኃይማኖት ግጭት ከሌሎች ግዛቶች ወይም ብሔር ተኮር ግጭቶች ጋር ሲነፃፀር ምንም እንኳን የማይካድ ግንኙነት ቢኖራቸውም በጣም የተለየ መገለጫ አለው። በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመደው የግጭት አይነት ከሆነው በታጠቁ ቡድኖች መካከል ከሚደረገው ጦርነት በተቃራኒ በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ግጭቶች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚሰነዘር ጥቃት ወይም በሁከት ወቅት ነው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያሉ የኃይማኖት ቡድኖች በተደጋጋሚ በሰልፎች ላይ ይሳተፋሉ – በአዲስ አበባ ሙስሊም ተማሪዎች “መንግስት በኃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እየገባ ነው” ያሉትን በመቃወም በአዲስ አበባ ያካሄዱትን ሰልፍ እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 30, 2014)።
የፖለቲካ ተጽእኖ እና ኃይማኖትን እንደ “ሥነ–መለኮት የተደገፈ የፖለቲካ መሣሪያ” መጠቀም በኢትዮጵያ የኃይማኖት ወገኖች መካከል ላለው ከፍተኛ መካረር አስተዋፅዖ አድርጓል (በርክሌይ ሴንተር፣ ሐምሌ 12, 2013)። እንደየአካባቢው የሚለያዩት አናሳ የኃይማኖት ቡድኖች ከአንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም ብሔር ጋር ባላቸው ግኑኝነት ምክንያት ብዙ ጊዜ እነሱን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ይህንን ሃሳብ በመደገፍ በኢትዮጵያዊ ላይ ብዙ እውቀት ያላቸው ጃን አቢንክ እንዲህ ብለዋል፡– “የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ኃይማኖትን እንደ ፖለቲካዊ መሳሪያነት መጠቀም ሲጀመር ብቻ የተወሰነ ግጭት ይቀሰቅሳል” (ዲደብሊው፣ ሚያዚያ 28, 2014)። በግልፅ እንደሚታየው በኢትዮጵያ ውስጥ በኃይማኖት ግጭት እና በፖለቲካ ግጭት መካከል ግልፅ የሆነ ግንኙነት አለ። ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም የተፈጠሩት በሁከት መልክ የተገለጡት የፖለቲካ አለመረጋጋት ኩነቶች በዚህ አመት ያልተጠበቀ ኃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን አሳይተዋል።
ፖለቲካዊ የስህተት–መስመሮች እምነትን ይከፋፈላሉ፡ የብልጽግና ወንጌል
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ክርስትና እና እስልምና ኃይማኖት ተከታዮች እጅግ ብዙ ቢሆኑም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጴንጤቆስጤ (ፕሮቴስታንት) እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2010 ላይ ስልጣን በያዙበት ወቅት በጥቂቶች ዘንድ አከራካሪ ነበር ተብሎ ይታሰባል።ይህ የሆነው ምናልባት ከሳቸው በፊት የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝም ፕሮቴስታንት ስለነበሩ ይሆናል (ዮርግ ሃውስተይን፣ ህዳር/ታህሳስ 2013)። አብይ በተሾመበት ውቅት ደጋፊዎቹ በብዛት በምዕራብ እና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች በሚበዙበት በምስራቅ ኦሮሚያ ውስጥም ነበር።
ነገር ግን አብይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢህአዴግ) ፈርሶ የብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተ ወዲህ ግን አብይ ኃይማኖቱን ወደ ሀገሪቱ ፖለቲካ በማምጣት የሀገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን ለቤተክርስቲያኑ አባላት ሰጥቷል በሚል በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ትችት ይደርስበታል (ዘ ኢኮኖሚስት፣ ህዳር 15, 2011)። እንደ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ያሉ የአብይ የቅርብ የፖለቲካ አጋሮች ከተመሳሳይ ኃይማኖት የመጡ ናቸው። አንዳንድ ጥቂት ግጭቶች በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚነሱት የህዝብ ቦታዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሱ ናቸው። ለምሳሌ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን አቃቂ ኮራ አካባቢ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በድምፅ ብክለት የከሰሷቸው የጴንጤቆስጤ (ፕሮቴስታንት) እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። በግጭቱ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል። በየካቲት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን በነቀምት ከተማ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዛፎችን እንዳይቆርጡና እንዳይጠቀሙ ለማድረግ በሞከሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ጥቃት በማድረስ ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል (ኢሳት፣ የካቲት 3, 2014)። በአቃቂ ወረዳ ገላን ከተማ በጨፈቱማ ቀበሌ ኃይማኖታዊ ቅርስ አግኝተናል ያሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቅርሱ የተገኘበትን መሬት ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ የአካባቢው ባለስልጣናት መሬቱ ለመንግስት ፕሮጅክት የተያዘ በመሆኑ ሰዎቹን “መሬት ያላግባብ በመውረር” በሚል ክሷቸዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 30, 2014)። በአዲስ አበባ፣ ሙስሊም ተማሪዎች መጋቢት 30 ቀን “መንግስት በኃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባቱን” በመቃወም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ጸሎት እና ሌሎች ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳያደርጉ በመከልከላቸው ተቃውሞ አደረገዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 30, 2022)። በሚያዚያ 4 ቀን ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ቅጥር ውጭ የቀትር ሰላት እንዲሰግዱ መፈቀዱን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ተለቀዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 4, 2022)።
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎች የኦርቶዶክስ ቤተ–ክርስቲያን – እንዲሁም ቤተ–ክርስቲያኒቷ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት – የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥራለች ሲሉ ይወቅሳሉ። አሁን ያለውን የፖለቲካ አስተዳደርን የሚቃወሙ ተቃዋሚዎች አብይ አህመድን በተመሳሳይ ሁኔታ ይከሱታል። ሆኖም፣ የኢትዮጵያን ኃይማኖታዊ ጥቃቶች በሙሉ በፓለቲካ ሊሂቃኖቿ (መሪዎቿ) ኃይማኖታዊ ትስስር ላይ ብቻ ለማያያዝ መሞከር ኃይማኖት አነስተኛ ሚና የሚጫወትበትን ውስብስብ የግጭት ምክንያቶችን በእጅጉ ያቃለለ ያደርገዋል። የኃይማኖት ግጭት መንስኤ ምን እንደሆነ ለመመርመር በጣም አስፈላጊው ፖለቲካ እና ብሔር ያላቸውን ትስስር በጥልቀት መመርመር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኝነት እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር የብዙ ቡድኖች ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ያላቸው ኃይማኖታዊ ትስስር ይበልጥ ጽንፈኛ እየሆነ መጥቷል። ይህንንም በምሳሌ ለማስረዳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የተከስቱ ግጭቶች ዋና የኃይማኖት ድርጅቶችን በማዳከም ከገቡበት የፖለቲካ ግጭት ራሳቸውን ከማዳን ይልቅ ለሁለት እንዲከፈሉ ምክንያት ሆነዋል። በሌላ አነጋገር በአሁኗ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግጭት የሚገፋፉ ሁኔታዎች ሃገሪቷ ካላት የጋራ እምነት ትስስር የበለጠ ጠንካራ ሆነው ይታያሉ። ይህ ከጥቅምት 2013 ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ የሚቀጣጠለውን ግጭት የኃይማኖት መሪዎች ለምን ለማስቆም ወይም ለማቀዛቀዝ ያልቻሉበትን ምክንያት ሊያብራራ ይችላል (የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ጥቅምት 25, 2013)።
በግንቦት 2013 የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በትግራይ ያለውን ግጭት በመቃወም ግጭቱን በትግራይ ተወላጆች ላይ የተቃጣ “የዘር ማጥፋት” ነው በማለት ገልፀውታል (ቪኦኤ፣ ግንቦት 1, 2013)። በጥቅምት/ህዳር 2013 የታየው የኃይማኖት ወገኖችን የሚያካትቱ ኩነቶች ላይ የሞት መጨመር የተፈጠረው (ከዚህ በታች ያለውን ምስል ይመልከቱ) በትግራይ ክልል የሃይማኖት ወገኖች እና ምእመናን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በመንግስት እና በትህነግ/ህወሓት መካከል ባለው የሰሜኑ ግጭት አካል በመሆኑ ነው (ኢሰመኮ፣ መጋቢት 14, 2014)። ፓትርያርኩ ግን በሌሎች ብሔሮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንደ በምዕራብ ትግራይ ዞን ማይ ካድራ እና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት ሳይናገሩ ቀርተዋል። በርካቶች ፓትርያርኩን እንደ አንድ የሃይማኖት መሪ በአገሪቱ ውስጥ በአጠቃላይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል ከማውገዝ ይልቅ ወገንተኝነት በማሳየታቸው ተችተዋቸዋል።
በትግራይም ሆነ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የኃይማኖት አባቶች ግጭቱ ሲጀመር ቢያወግዙም ውሎ አድሮ ግን በየራሳቸው ወገን ያሉትን ተፋላሚ ወገኖች የፖለቲካ ልዩነት ማሸነፍ አልቻሉም። በትግራይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በፌዴራል ደረጃ ካሉት የየራሳቸው ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል (አፍሪካ ኢንተለጀንስ፣ የካቲት 16, 2014)። በ2012 ዓ.ም የኦሮሞ ብሔርተኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ ከአገልግሎት ቋንቋ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት በአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃላፊዎች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመለያየት መንቀሳቀሳቸውን ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ የፖለቲካ ልሂቃን መደገፋቸውን ተከትሎ ለመለየት አስፈራርተው ነበር (ዲደብሊው፣ ነሃሴ 29, 2011)።
የኃይማኖት ብጥብጥ እንደ የፖለቲካ ግጭት ማራዘሚያ
ባለፉት ጥቂት አመታት በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አናሳ ኃይማኖቶች ላይ የሚደርሱ የኃይል ጥቃቶች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። በአብዛኛው አናሳ ኃይማኖቶች አላቸው ተበሎ በሚገመተው የፖለቲካ ማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ኢላማ ይሆናሉ።
በሚያዚያ 18, 2014 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የአንድ ታዋቂ ሼኽ የቀብር ሥነ–ሥርዓት ላይ ግጭት መፈጠሩን ተከትሎ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በሙስሊሞች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በቀብር ሥነ–ሥርዓቱ ላይ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ ቦምብ ተወርውሮ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ አምስት ሰዎች ቆስለዋል። ግጭቱ ወደ ከተማዋ ዘልቆ በመግባት ሁከት ፈጣሪዎች ከ20 በላይ የሙስሊም የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል። በተጨማሪም ሁከት ፈጣሪዎች መስጊዶችን አቃጥለዋል 11 መኖሪያ ቤቶችንም ዘርፈዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 21, 2014)። ይህም ለ17 ሰዎች ህይወት ማለፍ እና 118 ሰዎች መቁሰል ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል። በከተማዋ ያለው አለመረጋጋት ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ቀጥሏል። ሚያዚያ 20 ቀን በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18 ቀን በተፈጠረው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች የቀብር ሥነ–ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ መጠኑ በውል ያልተገለጸ ንብረት ወድሟል። ንብረት በመዝረፍ እና የኃይማኖት ቦታዎችን እና ሌሎች ንብረቶችን በማውደም የተጠረጠሩ ከ370 በላይ ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዝያ 20, 2014)። በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18 ቀን በተፈጠረ ግጭት ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዳቸው ስድስት የፖለቲካ እና የጸጥታ ዘርፍ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዝያ 25, 2014)።
በጎንደር ባለፈው ወር እና በኦሮሚያ በ2010 የተከሰቱት ኩነቶች ብዙ ተመሳሳይነት አላቸው። በጥቅምት 2010 በኦሮሚያ ክልል ምስራቃዊ አካባቢዎች ሁከት ፈጣሪዎች ኦሮሞዎች ከተጨቆኑበት ከአሮጌው የኢትዮጵያ አገዛዝ ጋር በሚያይዙት በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ጥቃት ፈጽመው በጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ ሰዎችን ገድለዋል። እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ገጠራማ አካባቢዎች በአካባቢው ታጣቂዎች እና ኦነግ–ሸኔ ባደረሱት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ተገድለዋል ።
በ2010 እና በ2014 የተከሰቱት ክስተቶች ብሔርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ወገኖች የተሳተፉበት በተወጠረ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸው አናሳ ኃይማኖቶች ያካተቱ ናቸው። ሁለቱም ጥቃቶች የተከሰቱት ለማህበረሰቡ ማንነት አስጊ ነው ተብሎ በታሰበ የለውጥ ‘አውድ’ ውስጥ ነው። በምስራቅ ኦሮሚያ በተለምዶ ሙስሊም ኦሮሞዎች በብዛት የሚገኙበት ስፍራ ከሌላ ስፍራ በመጡ የአማራ ተወላጅ ሰራተኞች፣ የሱቅ ባለቤቶች እና ኩባንያዎች ምክንያት ምስራቅ ኦሮሚያ በሚገኙ ከተሞች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቁጥር በፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል። በተመሳሳይም በጎንደርም በተለምዶ በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሚገኙበት ሥፍራ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊም ነዋሪዎችን እያስተናገደ ነው። በሁለቱም ስፍራዎች፣ አናሳዎቹ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመጠቀም በመቻላቸው በአንፃራዊነት ሀብታም እንደሆኑ ይታወቃል። በሁለቱም ግጭቶች፣ ሌሎች የፖለቲካ ግጭቶች ከጀመሩ በኋላ ግጭቶችን በማነሳሳት ሕንፃዎችን በማውደም እና አናሳዎችን በማጥቃት አጥቂዎች ነባራዊ ሁኔታቸውን ለማስጠበቅ ሞክረዋል (ኢሮፓውያን ኢንስቲትውት ኦፍ ፒስ፣ ታህሳስ/ጥር 2013)።
እንዲሁም በሁለቱም ሁኔታዎች ሁከቱ በፍጥነት በመስፋፋት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከተሞችን አዳርሷል። ከጥቃቱ ሁለት ቀናት በኋላ ሚያዝያ 20 ቀን በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቡድን ሁለት መስጊዶችን አቃጥለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው በቀበሌ 01 የሚገኘው የጎጥ ማርያም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ነው፣ እውነታው ግን በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳም ቤተክርስቲያኑ አልተቃጠለም። ይህ እሳት ሆን ተብሎ የተለኮሰ ይሁን ወይም ድንገተኛ አደጋ ይሁን ግልጽ አይደለም (ኢኤምኤ፣ ሚያዝያ 20, 2014)። የሰሜን ጎንደር ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንደገለፁት አንድ የጸጥታ ሃይል አባል በአካባቢው ከሚገኝ መስጊድ ማን እንደተኦሰው ባልታወቀ ጥይት ተገድሏል (የደባርቅ ከተማ ኮሙዩኒኬሽ፣ ሚያዚያ 20, 2014)። በጎንደር ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም በሚያዝያ 19 ቀን በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ሰላማዊ ተቃውሞ ተካሄዷል። ከሁለት ቀናት በኋላ በጎንደር ከተማ በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመቃወም በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር ክልል ሰመራ፣ በሶማሌ ጅግጅጋ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ወራቤ ህዝበ ሙስሊሙ ሰልፍ መጥቷል። በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደው ተቃውሞ ሰልፍ ሰልፈኞች በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወራቸው እና 22 ፖሊሶችን በማቁሰላቸው ወደ ሁከት ተቀይሯል ። ሰልፈኞቹ ባንኮች እና የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይም ጉዳት አድርሰዋል። በምላሹ የፖሊስ ሃይሎች ተኩስ ከፍተዋል። አንድ ሕፃን በተተኮሰ ጥይት ተገድሏል። በድሬዳዋ ከዚህ ሁከት ጋር በተያያዘ 89 ሰዎች ታስረዋል። በሚያዝያ 20 ቀን በወራቤ ሙስሊም ተቃዋሚዎች ሁለት የኦርቶዶክስ እና ሶስት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥለዋል። በማግስቱ ሌላ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን አቃጥለዋል። በተመሳሳይም ሚያዚያ 20 ቀን በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ አለም ገበያ ሚገኘውን የሳንኩራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን የሙስሊም ቡድን ሁከት ፈጣሪዎች መነኮሳቱ ላይ ጥቃት በመፈፀም ቤተክርስቲያኑን አቃጥለዋል። ሁከት ፈጣሪዎቹ የክርስቲያን ሆቴሎችን በማውደም ወደ 15 የሚጠጉ ሰዎችን አቁስለዋል። የስልጤ ዞን አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት እንደዘገበው በወራቤ እና ሳንኩራ በተቀሰቀሰው ሁከት የተጠረጠሩ 79 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 1, 2014)።
የብሔር እና የሃይማኖት አንድነት ጥያቄ
ብሔር እና ሀይማኖት ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያዊያን ማንነት ጋር የተሳሰሩ ቢሆንም፣ የብሔር ማንነት ግን ባህላዊ የሀይማኖት ድንበሮችን በመሻገር የፖለቲካ መሰረታቸውን በለውጥ ጊዜ ለመለየት አስቸጋሪ የሆኑ አናሳ ማንነቶችን ሊፈጥር ይችላል። እነዚህ አናሳ ማህበረሰቦች ለፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያሳዩ ሲሆኑ ለብሔርተኞች ደግሞ ያላቸውን ጥላቻ ያሳያሉ። ለምሳሌ በምስራቅ አማራ ክልል በተለምዶ ሙስሊም በሚበዛበት አካባቢ የብልጽግና ፓርቲን በቅርቡ በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በከፍተኛ ሁኔታ ደግፈዋል፣ነገር ግን ወደ ክርስትና እምነት እና ወደ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ለሚያደላው የአማራ ብሔርተኝነት ብዙ ጊዜ ያላቸውን አለመመቸት ይገልፃሉ። (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 7, 2013)። በተመሳሳይ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ኦሮሞዎች ወይም በአጠቃላይ በምስራቅ ኦሮሚያ የሚገኙ ክርስቲያን ኦሮሞዎች ባላቸው አነስተኛ የኃይማኖት ደረጃ ምክንያት በአካባቢያቸው ያለው የኦሮሞ ብሔርተኞች አጀንዳዎች እነሱን እንደማይጨምር በማሰብ የፌዴራል መንግስቱን ሊደግፉ ይችላሉ።
እንደ መጨረሻ ነጥብ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የኃይማኖት ቦታዎችን እና ኃይማኖተኞችን ያሳተፈ እጅግ አሳሳቢው፣ ገዳይ እና ጎጂ ግጭት የተከሰተው በሰሜን ባለው ግጭት ውስጥ ነው። በግጭቱ ምክንያት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ የኃይማኖት ማኅበረሰቦች ሊጠገን የማይችል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ የሰው ሕይወት ጠፍቷል ታሪካዊ ቅርሶችም ወድመዋል። በህዳር 2013 ላይ፣ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው እና በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን የሙስሊም ስደተኞች መቃብር የያዘው ጥንታዊው የአል ነጃሺ መስጊድ – በመድፍ ተመትቶ ወድሟል (ኤኤፍፒ፣ ሚያዚያ 21, 2013)። በግጭቱ ወቅት በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች የሃይማኖት ቦታዎች ሆን ተብሎ ወድመዋል (ዘ ጀሩሳሌም ፖስት፣ መጋቢት 21, 2014)።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ የኃይማኖት ግጭቶች ዛሬ ኢትዮጵያን እየናጣት ካለው የፖለቲካ ውዥንብር ጋር በእጅጉ የተያያዙ ናቸው። ግጭቶችን በመቅረፍ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች በመላ ሀገሪቱ የሚነሱትን የተለያዩ ግጭቶች ግን ማስቆም አልቻሉም። ነገር ግን፣ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደመሆናቸው መጠን፣ ግጭትን ለመቀነስ ወደፊት የሚያበረክቱት አስተዋጾ ቸል ሊባል አይገባም።