ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 በጨረፍታ
አበይት አሃዝ
- አክሌድ ከግንቦት 24, እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ 98 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 976 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 722 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልል በ162 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 64 ኩነቶች ከ481 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ29 ኩነቶች እና 494 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከቀበሌ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ማድረጉን ቀጥሏል።
- በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ ከፍተኛው የሰላማዊ ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።
- ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ጦርነት ተመዝግቧል። ይህ ጦርነት ከመጋቢት 2014 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተመዘገበ የጦርነት ኩነቶች ናቸው።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 የሁኔታዎች ማጠቃለያ
- ወርሃዊ ትኩረት፡ በኦሮሚያ ክልል የቶሌ ግድያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች
ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 የሁኔታዎች ማጠቃለያ
ባለፈው ወር በአማራ፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና በትግራይ ክልሎች የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛው የጦርነት ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን 54 የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከአንድ የጦርነት ኩነት በስተቀር፣ የተቀሩት የጦርነት ኩነቶች ኦነግ-ሸኔን እና የመንግስት ኃይሎችን – ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የቀበሌ ታጣቂዎችን ያሳተፉ ነበር። ከእነዚህ ጦርነቶች ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር ያለው የጦርነት ኩነቶች የተመዘገቡት በጉጂ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ነው። በአርሲ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በፊንፊኔ ልዩ፣ በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖችም ውጊያዎች ተመዝግበዋል።
ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ውጪ በተከሰቱ ውጊያዎች ውስጥም ተሳትፏል። ሰኔ 7 ቀን በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና የኦነግ-ሸኔ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ተዋግተዋል። በውጊያው 11 የመንግስት የፀጥታ ኃይሎችን እና ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ በትንሹ 40 ሰዎች መሞታቸው የተገለፀ ሲሆን ከ36 በላይ የጸፀጥታ ኃይሎች እና ሶስት ሰላማዊ ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል። የመንግስት ኃይሎች ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይል እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ኃይሎች በከተማዋ ከ10 ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል። ግድያው የተፈፀመው የመንግስት ኃይሎች በከተማው ውስጥ ተደብቀዋል የሚባሉትን የጋነግ እና የኦነግ-ሸኔ አባላትን ለማፈላለግ የቤት ለቤት ፍተሻ ባደረጉበት ወቅት ነበር። ከተገደሉት ውስጥ አብዛኛዎቹ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 4 እስከ 10, 2014 ይመልከቱ)። ሰኔ 20 ቀን የኦነግ-ሽኔ እና ጋነግ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ መራ ቀበሌ የአማራ ባለሃብቶች ንብረት የሆኑ ሁለት የእርሻ ካምፖችን በመውረር 80 የቀን ሰራተኞችን አፍነው ወስደዋል። የኦነግ–ሸኔ ዋና አዛዥ ጃል መሮ በሚያዝያ ወር የተካሄደውን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ መንግስት ኦነግ–ሸኔ ተደምሰሷል ሲል ያለውን ለማስተባበል በነዚህ ቦታዎች ላይ ኦነግ–ሸኔ ጥቃት መፈፀሙን አመላክቷል (ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ ሰኔ 17, 2014)።
ከዚህ በተጨማሪም በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በድባጤ ወረዳ በቦንፎ ቀበሌ እና በቡለን ወረዳ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተዋግቷል። በቦንፎ ቀበሌ አማፂ ቡድኑ ይጠቀምበት የነበረውን ማሰልጠኛ በማውደም 43 የቡድኑን አባላት መግደሉን እና በድባጤ እና ቡለን ወረዳዎች አራት መንደሮችን መቆጣጠሩን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ እነዚህን አካባቢዎች ከሦስት ዓመት በላይ ተቆጣጥሯቸው ነበር።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ አክሌድ በክልሉ ውስጥ 20 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶችን መዝግቧል። ከእነዚህ ኩነቶች ውስጥ አስሩ በመንግስት ኃይሎች፣ ስባቱ በኦነግ-ሸኔ እና ሦስቱ በፋኖ ታጣቂዎች የተፈፀሙ ናቸው። የአክሌድ የመረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከሚያዚያ 2014 ጀምሮ በመንግስት ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀሙ ግድያዎች መጨመሩን ያሳያል። ካለፉት ሁለት ወራት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዚህ አይነት ኩነቶች በምዕራብ ሸዋ ዞን የተመዘገቡ ሲሆን አራት ኩነቶች ተመዝግበው ይገኛሉ። በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ እና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖችም ከህግ አግባብ ውጪ የተፈፀሙ ግድያዎች ተመዝግበዋል። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ወይም የአማፂ ቡድኑን አባላት በመደበቅ ተጠርጥረው ነበር። ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ አብዛኛው በኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ተመዝግቧል። ነገር ግን በአማፂ ቡድኑ የብዙ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘረ የጥቃት ኩነት የተመዘገበው በምዕራብ ወለጋ ዞን ነው። ይህ ኩነት ከሰር በሚገኘው በወርሃዊ ትኩረት ክፍል ውስጥ በዝርዝር ተብራርቷል። በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች የፋኖ ታጣቂዎችን ያሳተፈ ውጊያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶችም ተመዝግበዋል (ለበለጠ መረጃ የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3, 2014 ይመልከቱ)።
ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የትህነግ/ህወሓት እና የመንግስት ኃይሎችን ያሳተፈ አዲስ የጦርነት ኩነቶች ተዘግበዋል። እነዚህ የጦርነት ኩነቶች ከመጋቢት 2014 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተዘገቡ የውጊያ ኩነቶች ናቸው። በአማራ ክልል እነዚህ ውጊያዎች በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ፣ጊዳን እና ቆቦ ወረዳዎች የተከሰቱ ሲሆን በትግራይ ክልል ሁሉም ውጊያዎች የተመዘገቡት በደቡብ ትግራይ ዞን ራያ አላማጣ ወረዳ በዋጃ አካባቢ ነው (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ባለፈው ወር የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ቆቦ ወረዳ የጄሮታ ቀበሌን እና በአካባቢው የሚገኙትን አረንገቦ፣ አገዳ እና አዲሱን መንደሮች እንዲሁም በቆቦ ወረዳ የሚገኙትን ሰሚዛ ጊዮርጊስ፣ መቀነት ጋሪያ እና ጃን አሞራ ቀበሌዎችን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ እና ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከተዋጉ በኃላ ተቆጣጥረውታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በደቡብ ትግራይ ዞን በራያ አላማጣ ወረዳ ጥሙጋ እና አየር ማረፋያ ቀበሌዎችን ከትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ጋር ከተዋጉ በኃላ ተቆጣጥረዋል።
በአማራ ክልል እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሁለት ግለሰቦች ግድያን ተከትሎ ረብሻ ተቀስቅሶ ነበር። ከግንቦት 25 እስከ 27 የአፋር ብሔረሰብ ታጣቂዎች በአማራ ክልል በአርጎባ ልዩ ወረዳ ወርቁ አዲስ በተባለው አካባቢ ንፁሃን ሰዎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ የአፋር ብሔረሰብ ታጣቂዎች እና የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች የተዋጉ ሲሆን ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ እና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል። ይህ ግጭት የተነሳው ግንቦት 23 ቀን የአፋር ተወላጅ የሆነ ሰላማዊ ሰው ከአርጎባ ልዩ ወረዳ መዲና ገበያ ሲመለስ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ከተገደለ በኋላ ነው። በተመሳሳይ ግንቦት 27 ቀን በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ በሶያማ ከተማ ገበያ የቡርጂ ብሔር ተወላጆች ከጉጂ ዞን የመጡ 10 የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ደብድበው የገደሉ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል። ተጎጂዎቹ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሱሮ ባርጉዳህ ወረዳ ወደ አካባቢው እቃዎችን ለመግዛት እና ለመሸጥ የመጡ ናቸው። ይህ ጥቃት የተፈፀመው አንድ የቡርጂ ተወላጅ ማንነቱ ባልታወቀ ቀበሌ ከጉጂ ዞን በመጡ የኦሮሞ ተወላጆች ተገድሏል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ነው። እንደ አካባቢው ባለሥልጣናት ከሆነ ግን ይህ ግለሰብ የተገደለው በኦነግ-ሸኔ ነው (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 29, 2014)። ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 29 ቀን የቡርጂ ብሔር አባላት በሶያማ ከተማ በመሰባሰብ በሰላማዊ ኦሮሞዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ አውግዘዋል። በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ተቃውሞ በኦሮሞ ተማሪዎች ተካሂዷል። በግድያው ተሳትፈዋል የተባሉ 70 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቡርጂ ልዩ ወረዳ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ግንቦት 24 ቀን የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) አባላት ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር በካማሺ ዞን ምዥጋ ወረዳ ሶጌ ከተማ ውስጥ ባደረጉት ውጊያ 16 የጉህዴን አባላትን፣ የምዥጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን እንዲሁም አንድ የአካባቢውን ባለሀብት እና ልጁን ጨምሮ 19 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። በማግስቱም የጉህዴን ታጣቂዎች በክልሉ ልዩ ሃይል ላይ በካማሺ ከተማ ከበባ አድርገው ነበር። ውጊያው የተከሰተው አንዳንድ የጉህዴን አባላት በዞኑ በተካሄደው ባህላዊ የሰላምና የዕርቅ ሥነ-ሥርዓት ላይ በገቡት ስምምነት መሰረት ትጥቅ አልፈታም ማለታቸውን ተከትሎ ነው። እነዚህን ክስተቶች ተከትሎ፣ የጉህዴን ሊቀመንበር በካማሺ ዞን ሁከት ለመፍጠር አሲሯል በሚል ታሰሯል (በዚህ ኩነት ዙሪያ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 ይመልከቱ)። ሐምሌ 15 ቀን ሊቀመንበሩ ከእስር ተለቋል። ሊቀመንበሩ ከእስር የተፈታሁት በእርሳቸው ላይ ማስረጃ ማግኘት ሰላልተቻለ መሆኑ ሲገልጹ የክልሉ መንግስት ደግሞ በዞኑ እየተሰራ ያለውን የሰላም እና እርቅ ስራ ለማሳለጥ ማሆኑን ገለጿል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 19, 2014)።
በመጨረሻም ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰባት የሱዳን ጦር ኃይል አባላትን እና አንድ ሰላማዊ ሰው ገድሏል በሚል በመክሰሱ ምክንያት በሱዳን እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ውጥረት ተባብሶ ነበር። ሰኔ 15 ቀን በአወዛጋቢው አል ፋሽጋ ክልል ውስጥ በአል ኩሬይሻ አካባቢ በሚገኘው ከአል አሲራ በስተምስራቅ በሚገኝ አካባቢ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት አባላት ማንነቱ ካልታወቀ የኢትዮጵያ ኃይል ጋር ከተዋጉ በኋላ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት አባላት መጥፋታቸው ተነግሮ ነበር።ከሰኔ 20 እስከ 22 በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሌሎች ባልተጠቀሱ ቦታዎች ላይ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ከባድ ጦር መሳሪያ ተኩሷል። በእነዚህ የከባድ ጦር መሳሪያ ጥቃት ምክንያት በሰዎች ህይወት ላይ የደረስ ጉዳት የለም (ሰለ እነዚህ ኩነቶች ተጨማሪ ዝርዝሮችን ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 18 እስከ 24, 2014 ይመልከቱ)።
ወርሃዊ ትኩረት፡ በኦሮሚያ ክልል የቶሌ ግድያ እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች
አክሌድ መረጃ ቋት ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን ያሳያል፣ ከእነዚህም የሟቾች ቁጥር ውስጥ 40% ያህሉ የሞቱት በአማራ ተወላጆች ላይ ባነጣጠሩ ሁለት ከባድ ጥቃቶች ነው። ሰኔ 11 ቀን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ በጉቱ፣ ጨርቆሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካው ሰፈር እና ሀያው አካባቢዎች የኦነግ-ሸኔ አባላት በትንሹ 338 ባብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሆኑ ሰዎችን ገድለዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014 ይመልከቱ)። ጥቃቱ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በካማሺ ዞን ቦሎ ጅንጋፎይ (ምዥጋ) ወረዳ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ሰኔ ቀበሌ ተዛምቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። አንዳንድ ዘገባዎች የሟቾች ቁጥር ከ500 በላይ ሊሆን እንደሚችል እና ከተጎጂዎች መካከል ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት ያመላክታሉ። ኦነግ–ሸኔ የቡድኑ ኃይሎች በእነዚ ጥቃቶች ተሳትፈዋል የሚለውን ክስ ውድቅ በማድረግ “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ጠይቋል (ኦኤልኤ የህዝብ ግንኙነት፣ ሰኔ 13, 2014)። በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ በቶሌ ቀበሌ የተፈፀመው ግድያ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአማራ ተወላጆች ላይ ከተፈፀሙ ጥቃቶች አስከፊው ጥቃት ሲሆን በሀገሪቱ ከተፈጸሙት ግድያዎች ደግሞ ሁለተኛው ነው።
በአማራ ክልል በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በሸዋ ሮቢት እና በባህር ዳር ከተሞች እና በመዲናይቱ አዲስ አበባ የቶሌ ግድያን የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሂደዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 11 እስከ 17, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሰኔ 18 እስከ 24, 2014 ይመልከቱ)። የአዲስ አበባ እና የባህርዳር ሰልፈኞች በኃይል እንዲበተኑ ተደርጏ። በሰኔ 21 በሸዋ ሮቢት የተካሄደው ሰልፍ በሰላም ቢጠናቀቅም የፀጥታ ኃይሎች ሰልፉን አስተባብረዋል የተባሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል። ከአንድ ቀን በኋላ የሸዋ ሮቢት አስተዳደር እስረኞችን ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆኑ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። በእዚህ ግጭት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሰላማዊ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እና የውጭ ታዛቢዎች በክልሉ ሁከትና ብጥብጥ እየተለመደ መምጣቱ አሳስቧቸዋል። በዚህ ትንታኔ ውስጥ የተከሰቱትን ኩነቶች ብዛት እና ያስከተሉትን ሞት፣ ጥቃቶቹ የተከሰቱበትን የፖለቲካ ምህዳር እና ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እቅድ ቢኖርም ለምን እንደዚህ ያሉ ኩነቶች እንደማይቀንሱ እንመለከታለን።
በአክሌድ ትርጏሜ መሠረት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ማለት የተደራጀ የታጠቀ ቡድን ሆን ብሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ወይም ከስራ ሰዓት ውጭ በሆኑ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ፍንጂዎችን ወይም የርቀት የጥቃት ስልቶችን ሳይጠቀም የሚፈፅመው ጥቃቶች ማለት ነው። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ጥቃት ፈፃሚው ብቻኛ ጥቃት አድራሽ እንደሆነ ስለሚታሰብ ያልተመጣጠነ ነው ተብሎ ይታሰባል (ለበለጠ ዝርዝር የአክሌድን የኮድ መፅሀፍ ይመልከቱ)። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሶስት ንዑስ የኩነት ዓይነቶችን ማለትም ፆታዊ ጥቃት፣ ጥቃት እና ጠለፋ/አስገድዶ መሰውርን ያቀፈ ነው።
ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ አክሌድ በኢትዮጵያ 1,022 በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ከ6,843 ሪፖርት ከተደረጉ ሟቾች ጋር መዝግቧል። እነዚህ ኩነቶች የተመዘገቡት በአሰራ አንዱም የሀገሪቱ ክልሎች እና በሁለቱ ከተሞች – አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ – ነው። ከፍተኛው የኩነት ቁጥር የተመዘገበው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን 499 ኩነቶች እና 2,075 ሪፖርት ከተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በምዕራብ ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና በምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች ነው። ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት 381 ሪፖርት ከተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ 381 የተዘገቡ ሟቾች ውሰጥ 338ቱ የሞቱት በምዕራብ ወለጋ ዞን በቶሌ በደረሰው ግድያ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ምክንያት ከተዘገቡት የሟቾች ቁጥር 67 በመቶውን ይይዛል።
በክልል ደረጃ ሊታዩ የሚችሉ የተለዩ አዝማሚያዎች አሉ። አንደኛ፣ አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊትም አልፎ አልፎ የተፈፀሙ ግድያዎች ተከስተዋል። ከታህሳስ 2008 እስከ ታህሳስ 2009 ባሉት ጊዚያት ውስጥ አብዛኛዎቹ እነዚህ ግድያዎች በኦሮሞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በመንግስት ኃይሎች የተፈፀሙ ናቸው። ከታህሳስ 2009 እስከ ታህሳስ 2011 ባሉት ጊዚያት ውስጥ በምስራቅ እና በደቡብ ኦሮሚያ በኦሮሞ እና በሶማሌ ታጣቂዎች መካከል በተነሳ ከባድ ግጭት በሁለቱም ማህበረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ግድያ የተለመደ ነበር። ከታህሳስ 2012 እስከ ከታህሳስ 2013 ባሉት ጊዚያት ውስጥ የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ኃይሎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈጽመው 32 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ከታህሳስ 2013 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። እነዚህ ክስተቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሞቶችን አስከትለዋል።
ሁለተኛ፣ ከታህሳስ 2013 ጀምሮ በኦሮሚያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በኩነቶቹ ብዛትም ሆነ ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጨምረዋል። በእነዚህ ኩነቶች ላይ የተሳተፉት ኦነግ-ሸኔ፣ የመንግስት ኃይሎች – ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ልዩ ኃይሎች እና የክልሉ ፖሊስ – የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ፣ የፋኖ ታጣቂዎች እና ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች ናቸው። ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ከታህሳስ 2013 ጀምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ወርሃዊ ጥቃት በአንጻራዊ ሁኔታ ትንሽ ለውጥ ቢኖረውም ከታህሳስ 2014 ጀምሮ በክልሉ በየወሩ የሚዘገቡ የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል ይህም ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተዘገበው 381 የሟቾች ቁጥር እስከአሁን ከተመዘገቡት ወርሃዊ የሟቾች ቁጥር ከፍተኛው ነው (ከዚህ በታች ያለውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ)።
ማንነታቸው ያልታወቀ ታጠቂ ቡድኖች በዋነኛነት የሚሳተፉት በመንግስት ባለስልጣናት እና ባልታጠቁ የፀጥታ ሃይሎች ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ነው። ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም አክሌድ በኦሮሚያ 21 የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠሩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች ከ51 ሪፖርት ከተደረጉ ሟቾች ጋር መዝግቧል። አብዛኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ባለፈው ዓመት ነው። በእነዚህ ጥቃቶች ሁለቱም ኦነግ-ሸኔ እና ማንነታቸው ያልታወቀ ታጠቂ ቡድኖች ተሳትፈዋል። ኦነግ-ሸኔ በዋናነት የመንግስት ባለስልጣናትን የጫኑትን ተሸከርካሪዎች አድፍጦ ያጠቃ ሲሆን የማንነታቸው ያልታወቀ ታጠቂ ቡድኖች ጥቃት ደግሞ ባለስልጣናቱን በቤታቸው ወይም በቤታቸው በአቅራቢያቸው ላይ ባሉበት ወቅት የሚያነጣጥር ነበር። በርካታ ከንቲባዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል አስተዳዳሪዎች እና በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት ሃላፊዎች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገድለዋል፣ ምናልባትም እነዚህ ታጣቂዎች አባ ቶርቤ ከሚባለው የኦነግ-ሸኔ የከተማ ክንፍ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል (ቦርከና፣ ታህሳስ 15, 2011)።
ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ከተመዘገቡት 391 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተሰነዘሩ የጥቃት ኩነቶች መካከል ኦነግ-ሸኔ ከ1000 በላይ ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን ባስከተሉት በ112 ኩነቶች ውስጥ ተሳትፏል። ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ አንድ ሶስተኛው በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ወደ 750 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን አስከትለዋል- 70 በመቶ የሚሆነው የሟቾች ቁጥር ከኦነግ-ሸኔ ጋር በተገናኘ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩት ጥቃቶች ምክንያት የተመዘግቡ ናቸው። ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር በምዕራብ ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች እንደ ቅደም ተከተላቸው ተመዝግቧል። እነዚህ ሶስት ዞኖች በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ወቅት ከአማራ ክልል ወሎ አካባቢ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሰፈሩ የአማራ ብሔር የሆኑ ብዛት ያላቸውን ማህበረሰቦችን ያስተናግዳሉ (ካሳ በላይ፣ እ.ኤ.አ. 2004፤ ደስአለኝ ራህማቶ፣ እ.ኤ.አ.2003)። ከታህሳስ 2010 ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተደጋጋሚ ጥቃቶች ምክንያት ከእነዚህ ዞኖች ተፈናቅለዋል። በእነዚህ ዞኖች ውስጥ በተፈጠረው ግጭት መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት በርካቶች አሁንም በስፈራው ለመቆያት ተገደዋል። ከምዕራብ ኦሮሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል እየተጠለሉ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ከምዕራብ ኦሮሚያ ከ29,000 በላይ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው እንደሚገኙ ተነግሯል (ብስራት ራዲዮ፣ መጋቢት 20, 2014)።
ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የሱማሌ፣ የጋሞ፣ የጉራጌ እና የቆሬ ብሔረሰብ አባላትን ጨምሮ በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ሰለባዎች ነበሩ። በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚከሰት ሲሆን በሶማሌ ተወላጆች ላይ የሚደርስው ጥቃት ደግሞ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ – በቦረና እና በምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች – በኦሮሞ እና ሶማሌ ብሔረሰቦች መካከል በሚፈጠር የአካባቢ ግጭት ምክንያት የሚከሰት ነው። በተመሳሳይ የቆሬ ብሔረሰብ አባላት ላይ የሚደርሰው ጥቃትም በኦሮሚያ ክልል እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አዋሳኝ በሚገኝው የጉጂ ዞን ድንበር አዋሳኝ በሚኖሩ የብሔሩ ተዋላጆች ላይ ነው። በፊንፊኔ ልዩ ዞን የጋሞ እና የጉራጌ ብሔረሰብ አባላት ጥቃት ደርሶባቸው።
በተጨማሪም ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ ውስጥ ከሚከሰቱት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች 580 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን ያስከተለው ወደ 50% የሚጠጋው በመንግስት ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ በሚፈፀሙ ግድያዎች ነው። አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች የኦነግ-ሸኔ አባላት ናችሁ፣ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት አላችሁ ወይም የቡድኑን አባላት ድብቃችኃል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል። ከእነዚህ ኩነቶች ጋር በተያያዘ አብዛኛው ሞት የተመዘገቡት እንደ ቅደም ተከተላቸው በምስራቅ ሀራጌ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ነው። በምስራቅ ሀረርጌ አብዛኛው የዚህ አይነት ኩነት ማለትም 50 ኩነት ከ141 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ጋር የተመዘገበው ከታህሳስ 23, 2010 እስከ ታህሳስ 22, 2011 ቄሮ በዞኑ ንቁ እንቅስቃሴ በሚያደርግበት ወቅት እና በኦሮሞ እና በሶማሌ ብሔር ተወላጆች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች በተፈጠሩበት ወቅት ነው (የቄሮ እንቅስቃሴን በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የቡድኖች መግለጫ ገጽን ይመልከቱ)። ነገር ግን ከመጋቢት 2014 ጀምሮ በመንግስት ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጪ በሚፈፀሙ ግድያዎች በአብዛኛው በምዕራብ ሸዋ ዞን የተከሰቱ ናቸው። ይህ በዞኑ በመንግስት ኃይሎች እና በኦነግ-ሸኔ መካከል ከተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ውጊያ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
ከመጋቢት 23, 2010 እስከ ሰኔ 23, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎችም ተሳትፈዋል። ከታህሳስ 2013 ጀምሮ የአማራ ብሔረሰብ ታጣቂዎች በዋነኛነት በክልሉ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል – 39 ኩነቶች ከ238 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ጋር ተመዝግበዋል። የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ በክልሉ በዚህ አመት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ናቸው።
ባለፈው አንድ ወር በሃገሪቱ ያለው ውጥረት በቅርቡ በቶሌ ቀበሌ ከተፈፀመው ግድያ በኋላ እንደገና ተባብሷል። የፌዴራል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2014 በኦነግ-ሸኔ ላይ በጋራ በወሰዱት ወታደራዊ ዘመቻ ከ153 በላይ የአማፂ ቡድኑን አባላት ገድለው ከ900 በላይ መማረካቸውን አስታውቋል (የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሐምሌ 16, 2014)። በርካቶች በተለይም የአማራ ክልል ነዋሪዎች በኦነግ-ሸኔ ላይ ቁጣቸውን ሲገልጹ እና መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ አለመቻሉን ገልጸዋል። ባለፈው ወር ግድያውን በመቃወም በተደረጉ ሰልፎች ላይ መንግስት የፀጥታ ስጋትን በመጥቀስ ከፍተኛ እርምጃ ወስዷል። በአማራ ክልል በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በባህር ዳር፣ በሸዋ ሮቢት ከተሞች እና በአዲስ አበባ በአብዛኛው በአጭሩ እንዲቆሙ የተደረጉ ሰልፎች ተካሂደዋል። ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በቄለም ወለጋ ዞን በሃዋ ጋላን ወረዳ ለምለም ቀበሌ በመንደር 20 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸው እና በትንሹ 150 በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሁኑ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። አማፂ ቡድኑ በዚህ ጥቃት እጁ እንደሌለበት በመግለፅ የአካባቢውን የመንግስት ታጣቂዎች ጥቃቱን ፈጽመዋል ሲል ከሷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 28, 2014)።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚደርሱ ጥቃቶች የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ያለመቻላቸውን ወይም አለመፈለጋቸውን የሚያሳዩ አሳሳቢ አዝማሚያዎች ናቸው። ልክ እንደ ኦሮሚያ ክልል በተከሰቱት በአብዛኛዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በቀዳሚነት የሚፈፅሙት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ እያንዳንዱን ሰላማዊ ዜጋ መጠበቅ አለመቻሉ እንደ አንድ ነጥብ የተነሳ ነበር (ኢቢሲ፣ ሰኔ 30, 2014)። በኦሮሚያ ክልል ልክ የአማራ ተወላጆች እንደሰፈሩባቸ ቦታዎች ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ መንግስት የጋራ ታጣቂዎችን (የቀበሌ ሚሊሻዎችን) ሊያደራጅ እና ሊያስታጥቅ እንደሚችል ምልክቶች አሉ። ይህ ከስር የሚገኙ የመንግስት አካላት አዲስ የሚቋቋሙትን እነዚህን ያጋራ ታጣቂ ቡድኖችን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ እና በማህበረሰብ መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለመቆጣጠር ባላቸው ችሎታ መስረት እነዚህ አዲስ ሊቋቋሙ ይታሰቡት የጋራ ታጣቂ ቡድኖች ሁኔታውን ሊያሻሽሉ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ።
በኢትዮጵያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየጨመሩ ሲሆን ከታህሳስ 2010 ጀምሮ ከፍተኛ ሞት ያስከተሉ ኩነቶች እየተለመዱ መጥተዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዜናዎች በሀገር ውስጥ እና በአለምአቀፍ ተዋናዮች እየተለመደ በመምጣቱ የሁኔታውን አስከፊነት በመዘንጋት እንደዚህ ያሉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ቅድሚ ያለመስጠት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አለ። በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት በመላ አገሪቱ በመንግስት እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል እየተባባሰ ያለው ውጥረት በኢትዮጵያ አዲስ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳይከፈት ያሰጋል። የፀጥታ ኃይሎች በሀገሪቱ እየተጋፈጡ ካሉት የፀጥታ ችግሮች ብዛት አንጻር አዳዲስ ግጭቶች የሰላማዊ ሰዎች ህይወትን የበለጠ ስጋት ላይ ይጥላሉ። አገሪቷ ለድርድርና ለአገራዊ ምክክር እየተንቀሳቀሰች ባለችበት በዚህ ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ እና ባለፉት አራት ዓመታት የተፈጸሙ በደሎች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። ትኩረት ካልተሰጠው ግን ጥቃቶች ከፍ ባለ ደረጃ ሊቀጥሉ ይችላሉ።