ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 በጨረፍታ
አበይት አሃዝ
- አክሌድ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ድረስ 113 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን እና 558 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 387 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የአማራ ክልል በ95 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 66 ኩነቶች ከ274 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ40 ኩነቶች እና 257 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- በአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች ነሐሴ 18 ቀን በመንግስት ኃይሎች እና በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መካከል ሌላ ዙር ውጊያ ተጀምሯል።
- ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መዋጋት ቀጥለዋል።
- በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የቀጠለ ሲሆን በሰላማዊ ሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር በሆሮ ጉዱሩ ዞን በአምሩ ወረዳ ተመዝግቧል።
- ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአፋር ክልል በጋቢ-ዞን 3 በገዳማይቱ፣ በዳንላህላይ እና በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በሚኤሶ ወረዳ በሚገኙ ሌሎች አወዛጋቢ አካባቢዎች በሶማሌ እና በአፋር ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተቀስቅሷል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት፡ የሰብአዊ ፍላጎቶች በሰሜን ኢትዮጵያ
ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከአምስት ወራት አንፃራዊ መረጋጋት በኋላ ነሐሴ 18 ቀን የሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ እንደገና ተቀስቅሷል። በዚህ ምክንያት ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በሰሜን አብዛኛው የውጊያ ኩነቶች የተመዘገቡት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ነው። በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ እና በሶማሌ ክልሎችም የተከሰቱት ጦርነቶች ተመዝግበዋል። ውጊያው የተጀመረው በትግራይ ክልል በደቡብ ትግራይ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ነው። ነሐሴ 18 ቀን የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ፋንቲ ራሱ-ዞን 2 በያሎ ወረዳ በሚገኙ ሶስት ቀበሌዎችን በከባድ መሳሪያ በመደብዳባቸው ሦስት ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል። በወሩ መገባደጃ ላይ በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ውጊያዎች በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን እና በትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ተዛምቷል (በሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ የተከሰተባቸው ቦታዎች ዝርዝር ለማየት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ነሐሴ 7-ጷጉሜ 4, 2014 ይመልከቱ)። ከነሐሴ 18 እስከ 25 ደረስ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች 37 የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ – 25 የጦርነት ኩነቶች – በአማራ ክልል የተመዘገቡ ሲሆን በትግራይ ክልል 11 የጦርነት ኩነቶች ተመዝግበዋል።
በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በድሮን የተደገፈ የአየር ድብደባ በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ ፈፅሟል። እነዚህ የአየር ድብደባዎች የልጆች መጫወቻ ሜዳ እና ሆስፒታል ላይ ያነጣጠሩ ነው ሲባል ቢያንስ አራት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። የፌዴራል መንግስት ለዚህ ክስ ምላሽ አልሰጠም። ነገር ግን ነሐሴ 20 ቀን የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ሰዎች ከትህነግ/ህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ እና ካምፖች አካባቢዎች እንዲርቁ ጠይቋል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 20, 2014)።
ከውጊያዎቹ በተጨማሪ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን አዲስ ዙር ውጊያ ተከትሎ በአማራ ክልል በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች የተፈፀሙ ሁለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ የፋኖ እና የአማራ ታጣቂዎችን ለመፈለግ ቤት ለቤት ባደረጉት ፍተሻ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ወጣቶችን እና አርሶ አደሮችን ተኩሰው ገደለዋል። የፌዴራል መንግስት ኃይሉ ከቆቦ ለቆ የወጣው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከብድ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 21, 2014)። ከዚህም በተጨማሪም ነሐሴ 25 ቀን በዋግ ኽምራ ዞን በሰቆጣ ወረዳ ወለህ ማርያም ቀበሌ በሚገኘው ወለህ የተፈናቃዮች ጣቢያ ሴቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ 25 ተፈናቃዮችን የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ተኩሰው ገድለዋል። በአዲሱ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ለመሰደድ ተገደዋል (በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የሰብአዊ ፍላጎቶች ከዚህ በታች ባለው ክፍል ተብራርቷል)።
ከሰሜን ኢትዮጵያ ውጊያ ውጪ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛው የጦርነት ኩነት ማለት 24 የጦርነት ኩነትቶች የተመዘገቡ ሲሆን ሁሉም የጦርነት ኩነትቶች በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂዎች ማለትም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና በኦሮሚያ ቀበሌ ታጣቂዎች መካከል የተደረጉ ናቸው። እነዚህ ጦርነቶች የተከሰቱት በአርሲ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በጉጂ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በኢሉ አባ ቦራ፣ በቄሌም ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ነው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከእነዚህ ውጊያዎች ውስጥ አብዛኛው ውጊያ – ስምንት ውጊያዎች – በምዕራብ ሸዋ ዞን ተመዘገቡ ናቸው።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተለያዩ አካላት የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። አክሌድ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በፊንፊኔ ልዩ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በቄሌም ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች 35 በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሱ የጥቃት ኩነቶችን መዝግቧል። እነዚህ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል፣ በኦነግ-ሽኔ፣ በፋኖ ታጣቂዎች፣ በአማራ ታጣቂዎች እና ማንነቱ ባልታወቀ የታጠቀ ቡድን ነው። አብዛኛዎቹ እነዚህ ጥቃቶች – 17 ኩነቶች – የተፈጸሙት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሲሆን ሁለተኛውን ከፍተኛውን ጥቃት – 10 ኩነቶች የፈጸመው ኦነግ-ሽኔ ነው። በሰላማዊ ሰዎች ላይ አራት ጥቃቶችን በመፈጸም የፋኖ ታጣቂዎች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ በሆሮ ጉዱሩ ዞን ተመዝግበው ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥቃት የተጎዱ አብዛኛዎቹ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይም የአማፂ ቡድኑን አባላት በመደበቅ ተከሰው ነበር። በወሩ መጀመሪያ ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና ወረዳ ሌሊሴ ቀበሌ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከኦነግ-ሸኔ አማፂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የተጠረጠሩ 35 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል። ነሐሴ 15 ቀን በምዕራብ ሸዋ ዞን የጉደር ከተማ ነዋሪዎች ዋናውን መንገድ በድንጋይና በእንጨት በመዝጋት በከተማዋ ወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለውን የዘፈቀደ እስራት አውግዘዋል። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል ተቃዋሚዎችን ለመበተን እና የተዘጋውን መንገድ ለመክፈት ሲሞክሩ በሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮሳቸው ሁለት ወጣቶች ቆስለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነሐሴ 6 ቀን የዳኖ ወረዳ ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ስዮ ከተማ በመሰባሰብ “በኦነግ-ሸኔ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ፣ ዘረፋ እና የንብረት ውድመት” በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል (ኦቢኤን አፋን ኦሮሞ፣ ነሐሴ 6, 2014)።
በነሐሴ 24 እና 25 ከአምሩ ወረዳ አዲስ አለም ቀበሌ እና ከአማራ ክልል ቡሬ ወረዳ የመጡ የአማራ ታጣቂዎች በአምሩ ወረዳ ከ60 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን ሲገድሉ ከ70 ያላነሱ ደግሞ አቁስለዋል። ጥቃቶቹ የተመዘገቡት በአጋምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶባን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃዋጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ ቀበሌዎች ነው (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጷጉሜ 1, 2014)። ይህ ጥቃት የተፈፀመው ኦነግ-ሸኔ የአምሩ ወረዳ አስተዳደር ማዕከል የሆነችውን አቦራ ከተማን ለመያዝ ሲሞክር በአጋምሳ ቀበሌ ሦስት የአማራ ተወላጆችን ከገደለ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ቡድኑ በቀበሌው የሚገኙ 59 ሰዎችንም ትጥቅ አስፈትቷል። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ነሐሴ 22 ቀን ከአካባቢው ለቆ ወጥቷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 25, 2014)። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከነሐሴ 23 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ኦነግ-ሸኔ በአጋምሳ ከተማ 11 ሰዎችን ገድሎ ሌሎች 11 ሰዎችን አቁስሏል። ቡድኑ በአሙሩ ወረዳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ቅርንጫፎችንም ዘርፏል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 28, 2014)። እነዚህን ጥቃቶች ተከትሎ ከ20,000 በላይ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች ለመሰደድ ተገደዋል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጷጉሜ 1, 2014)።
ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በአፋር ክልልም ተንቀሳቅሰው ነበር። ነሐሴ 18 ቀን ኦነግ-ሸኔ በሃሪ-ዞን 5 በዳዌ ወረዳ በቡርቃ ከተማ ገብተው የቤት ለቤት ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ገድሏል።
በተጨማሪም ባለፈው ወር በሶማሌ እና በአፋር አዋሳኝ ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች ግጭት ተቀስቅሶ ነበር (ሰለእነዚህ አወዛጋቢ አካባቢዎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የአፋር-ሶማሌ የድንበር ግጭት ይመልከቱ)። ነሐሴ 17 አካባቢ የአፋር እና የሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች በጋቢ-ዞን 3 በገዳማይቱ ተዋግተዋል። የሶማሌ ክልል መንግስት በጦርነቱ ሳቢያ ወደ 60,000 የሚጠጉ የሶማሌ ተወላጆች አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን አስታውቋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሐሴ 13, 2014፤ አዲስ ስታንደርድ፣ ነሐሴ 12, 2014)። ከሳምንት በፊት ነሐሴ 5 ቀን በአፋር እና በሶማሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች መካከል በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በሚኤሶ ወረዳ በኡንዱፎ፣ ዳንላህላይ እና ሌሎች አወዛጋቢ አካባቢዎች ውጊያ ተቀስቅሷል። ነሐሴ 12 ቀን በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በቤኪ ከተማ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንታዊ ልዑካን ቡድን በከተማው የሚገኙ ከገዳማይቱ የተፈናቃሉ ሰዎች በሚጎበኙበት ወቅት ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ተቃዋሚዎቹ የክልሉ መንግስት በገዳማይቱ በአፋር እና በሶማሌ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደውን ውጊያ የያዘበት ሁኔታ የተቃወሙ ሲሆን “በውጊያው ወቅት የመንግስትን ዝምታ” አውግዘዋል (ሂይራን ኦንላይን፣ ነሐሴ 12, 2014፣ ቲክቫህ-ኢትዮጵያ፣ 12, 2014)። የክልሉ ልዩ ኃይል እንደሆኑ የተጠረጠሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሰማይ በመተኮስ ተቃዋሚዎቹን በትነዋል።
በተጨማሪም ነሐሴ 23 እና 24 በቆራሄ ዞን ሽላቦ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በሊንታ ቁራኦ ሽሬ መንደር በመሬት ውዝግብ የተነሳ የማረሃን ጎሳ ታጣቂዎች በማቃቡል ጎሳ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ተዋግተዋል። በትንሹ 10 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ የፌዴራል ፖሊስ እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል ከቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ያደረጉ ሲሆን በዚህ ውጊያ 23 የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሲገደሉ አምስት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ 246 ታጣቂዎች ለመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ሰጥተዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ነሐሴ 3, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳል የጋምቤላ ክልል መንግስት በነሐሴ 2 ቀን ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ብሔረሰብ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በአግኛዋክ ዞን ዲማ ወረዳ በዲማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የኡኩጉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። በጥቃቱ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌላ አንድ ሰው መቁሰሉ ተነግሯል። ታጣቂዎቹ ሁለት ልጆችንም አፍነው መውሰዳቸው ተነግሯል።
ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ ውጥረት ተስተውሏል። ሐምሌ 26 ቀን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የጸጥታ ኃላፊዎች “የጉራጌ ዞን የመዋቅር ጥያቄን ሽፋን በማድረግ ህገወጥ እና መደበኛ ያልሆኑ ድርጊቶችን እንደማይታገስ” አስጠንቅቀዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሐምሌ 29, 2014)። ነሐሴ 29 ቀን በጉራጌ ዞን በቡኢ ከተማ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ሲሆን ማንም ሰው አዲስ የታቀደውን የክላስተር ክልል የሚቃወም ምልክት እንዳይዝ ከልክሏል (ትክቫህ- ኢትዮጵያ፣ ሐምሌ 29, 2014)። የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች የጉራጌ ዞንን መልሶ ማዋቀር እና አዲስ የክላስተር ክልል መመስረትን እንደማይቀበሉት የገለፁት “የተለመደ እንቅስቃሴን በማስቀረት” እና በከተማዋ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት “ክላስተር የለም” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ነሐሴ 3, 2014)። በነሐሴ የክልሉ ኮማንድ ፖስት የሰአት እላፊ አዋጅ አውጇል፣ የሞተር ብስክሌቶችን እንቅስቃሴ የገደበ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ እና በጉራጌ ዞን “ምንም አይነት ተቃውሞ እና ህዝባዊ ስብሰባ” እንዳይካሄድ አግዷል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 12, 2014፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አዲስ ስለታቀዱት ክላስተር ክልሎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24, 2014 ይመልከቱ)። ይህንን ክልከላ ተከትሎም የክልሉ ፖሊስ አዲስ የታቀደውን ክላስተር ክልል በመቃወም፣ የራስ አስተዳደር ክልላዊ መንግስት እንዲከበር ጥያቄ በማቅረባቸው እና የቤት ውስጥ መቆየት እና የንግድ ቤቶች እንዲዘጉ በማስተባበር የዞኑ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊን ጨምሮ በርካታ ወጣቶችን እና የዞን አመራሮችን በወልቂጤ ከተማ በቁጥጥር ስር አውሏል። በኋላም የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች በጉራጌ ዞን ውሳኔ ላይ መንግስት የወሰደውን እርምጃ እና መንግስት ለጥያቄያቸው ምላሽ ባለመስጠቱ በቤታቸው በመቆየታቸው እና የስራና የንግድ ማዕከላትን በመዝጋት ተቃውመዋል (አዲስ ማለዳ፣ ነሐሴ 21, 2014)።
በተጨማሪም ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 25, 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በደራሼ ልዩ ወረዳ አታዬ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ኃይል እንደሆኑ የተገመቱ የመንግስት ታጣቂዎች ወደ መኖሪያ ቤቶች ገብተው ስምንት ሰዎችን መግደላቸው ተነግሯል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ግን የጸጥታ ኃይሎች ማንነቱ ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር የተኩስ ልውውጥ በማድረግ አራት ታጣቂዎችን ገድለው ወደ 20 የሚጠጉ ሌሎች ሰዎችንም በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 26, 2014)። ከመጋቢት 2014 ጀምሮ የደራሼ ልዩ ወረዳ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ የፖለቲካ አለመረጋጋት የታየበት ሲሆን የአካባቢ ምክር ቤቱ አባላት በቅርቡ በአዲስ ክልላዊ መንግስት አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ድምጽ ሰጥተዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ከሐምሌ 26, 2014).
በመጨረሻም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በሚገኘው ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎች የኦሮሞ ተማሪዎችን ሐምሌ 26 አካባቢ ደብድበዋል። ከዚህ ጥቃት በስተጀርባ ያለው ምክንያት አይታወቅም። በተመሳሳይ ጊዜ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቂ ቡድን 42 ታጣቂዎች የኃይማኖት አባቶች እና የማህበረሰብ ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥሪ እና የሽምግልና ጥረቶች መሰረት ትጥቃቸውን በሰላማዊ መንገድ በማውረድ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የሰብአዊ ፍላጎቶች በሰሜን ኢትዮጵያ
በግጭቶችም ሆነ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በኢትዮጵያ የሰብአዊ ፍላጎቶች አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት (ዩኤንኦሲኤችኤ) እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ በግጭቶች እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል (ኦሲኤችኤ፣ ነሐሴ 27, 2014)። አፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች በግጭት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ክልሎች ሲሆኑ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በአብዛኛው እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የተጠቁ ናቸው። ኢትዮጵያ አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከ2020 መገባደጃ ጀምሮ አራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ ታይቷል። በድርቁ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ 22 ሚሊዮን ሰዎች ላይ የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠ ይገመታል (ዘ ጋርዲያን፣ ነሐሴ 14, 2014)። በኢትዮጵያ በድርቅ በጣም የተጠቁ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች – ወይም በአፍሪካ ቀንድ ከተጎጂው ህዝብ 45 በመቶው – ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ናቸው (ዲደብሊው፣ ነሐሴ 10, 2014)። በአዎንታዊ ዜና ባለፈው ሳምንት 23,000 ሜትሪክ ቶን የዩክሬን እህል ኢትዮጵያ ገብቷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጳጉሜ 2, 2014፤ ኤፒ ኒውስ፣ ነሐሴ 9, 2014)።
በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ይገመታል። እንደ ዩኤንኦሲኤችኤ ዘገባ ከመጋቢት 23 እስከ ሐምሌ 25 ድረስ 6,105 የሰብአዊ አቅርቦቶችን የጫኑ የጭነት መኪኖች በአፋር ክልል በኩል ወደ መቀሌ የገቡ ሲሆን በተጨማሪ ሐምሌ 27 ቀን 12 የነዳጅ ቦቴዎች በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማከፋፈል መቀሌ ገብተዋል (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ሐምሌ 29, 2014)። ነሐሴ 18 ቀን የሰሜኑ ግጭት እንደገና መቀስቀሱ ግን በምድር እና በአውሮፕላን ወደ ትግራይ የሚገባውን ሰብአዊ እርዳታ አግዶታል (ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ጳጉሜ 2, 2014)። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁሉም ሰብአዊ አቅርቦቶች ለትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ሳይሆን ለተቸገሩ ሰዎች እንደሚውሉ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋስትና እንዲሰጠው ጠይቋል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 19, 2014)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሰብአዊ እርዳታ ተብሎ የታሰበ ምግብ በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች መወሰዱን ተናገሯል (የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ጳጉሜ 1, 2014 ፤ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ነሐሴ 30, 2014፤የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ነሐሴ 27, 2014)። ዩኤስኤአይዲ እነዚህን ውንጀላዎች ለማጣራት ቃል ገብቷል (ትዊተር @ዩኤስኤአይዲኢትዮጵያ፣ጳጉሜ 1, 2014)። ነሐሴ 18 ቀን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ በሚገኘው የአለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) መጋዘን ውስጥ 12 ነዳጅ ጫኝ መኪናዎች ከ570,000 ሊትር ነዳጅ ጋር በትህነግ/ህወሓት እንደተዘረፉ ገልጿል። ትህነግ/ህወሓት ይህንን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ ከዚህ ቀደም ለደብሊውኤፍፒ ያበደረውን ነዳጅ እንደገና እንደወሰደ ገልጿል (ትዊተር@ትግራይኢኤኦ፣ ነሐሴ 19, 2014)።
በሁለቱም አፋር እና በአማራ ክልሎች በፌዴራል መንግስትና በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው አዲስ ውጊያ በመጀመርያ ሳምንት ውጊያ 150,000 የሚጠጉ ከቆቦ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሐሴ 27, 2014)። በአፋር ክልል ጉሊና፣ ያሎ፣ አዋ፣ አውራ እና መጋሌ ወረዳዎች ከ200,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሐሴ 27, 2014)።
ይህ አዲስ ዙር መፈናቀል ቀደም ሲል በ2013 መጨረሻ እና የ2014 የመጀመሪያውን መንፈቀ አመት የተፈጠረውን የጅምላ መፈናቀል ተከትሎ የተከሰተ ነው። በ2014 የመጀመሪያው መንፈቀ አመት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአማራ ክልል ተፈናቅለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሐሴ 27, 2014)። አብዛኞቹ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች የተመለሱ ቢሆንም ከ250,000 በላይ ተፈናቃዮች አሁንም በዋግ ኸመራ፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ ይገኛሉ (ሰሜን ሸዋ ዞን በዋናነት ከ300,000 በላይ ከምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቃዮችን እያስተናገደ ነው፤ ዩኤንኦሲኤችኤ፣ ሰኔ 20, 2014፤ በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ: ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 23, 2014 ይመልከቱ)።
በነሐሴ ወር ያገረሸው ውጊያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጆችን ለመድረስ የሚደረገውን ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገታ ያደረግ ሲሆን በአማራ እና አፋር ተጨማሪ ከ350,000 በላይ እርዳታ ፈላጊ ሰዎችን ጨምሯል። ይህም በመላ ሀገሪቱ በተከሰቱት ሌሎች አደጋዎች እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 10 ሚሊዮን ሰዎች በተጨማሪ ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውጊያዎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየቀጠሉ በሄዱ ቁጥር የሰብአዊ እርዳታ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ይሄዳል።