ነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 በጨረፍታ
አበይት አሃዝ
- አክሌድ ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ድረስ 127 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን እና 626 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾችን መዝግቧል።
- በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ከፍተኛው ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 379 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ተመዝግበዋል። የትግራይ ክልል በ133 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
- ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተደጋግሞ የተከሰተው የኩነት አይነት ጦርነት ሲሆን 80 ኩነቶች ከ335 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር ተመዝግበዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች በ29 ኩነቶች እና 206 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር በሁለተኝነት ይከተላል።
አበይት ክንውኖች
- ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመንግስት ኃይሎች እና በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ቀጥለዋል።
- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የሰው አልባ አውሮፕላን የአየር ጥቃቶችን አድርሷል።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በኦሮሚያ ክልል መዋጋት ቀጥለዋል።
- በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችም ቀጥለዋል።
በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱ
- ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሀዊ ትኩረት፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ሊካሄድ የሚችለው የሰላም ድርድር ውሎች
ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቦታዎች ጦርነቶች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። አብዛኞቹ የጦርነት ኩነቶች – 66 – በሰሜን ኢትዮጵያ ማለትም በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተመዘገቡ ናቸው (በእነዚህ ክስተቶች ላይ የበለጠ ዝርዝር ለማግኘት የወርሃዊ ትኩረት ክፍሉን ይመልከቱ)። የሚቀጥለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦርነት በኦሮሚያ ክልል የተመዘገበ ሲሆን 13 ኩነቶች እና 208 ሪፖርት የተደረጉ ሟቾች ቁጥር የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከሌሎች ክልሎች ከተመዘገበው ሟቾች ቁጥር ከፍተኛው ነው።
የኦሮሚያ ክልል ከሰሜን ኢትዮጵያ ቀጥሎ ሁለተኛው ያልተረጋጋ አካባቢ ነው። ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ኃይሎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መዋጋት ቀጥለዋል። ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአርሲ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በጉጂ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች በእነዚህ ሁለት ኃይሎች መካከል የተደረጉ ውጊያዎች ተመዝግበዋል። መስከረም አጋማሽ አካባቢ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳን የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተነግሯል። በዚህ አካባቢ በኦነግ-ሸኔ እና በአማራ እና በፋኖ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስ ቆይቷል። ከመስከረም 12 ጀምሮ በጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶች እና በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ውጊያዎች መከሰታቸው ተዘግቧል (በእነዚህ ኩነቶች ላይ የበለጠ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 14-20, 2015 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 7-13, 2015 ይመልከቱ)።
በኦሮሚያ ክልል ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ አክሌድ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የደረሰውን ጥቃት ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ 18 ጥቃቶችን ከ171 ሪፖርት የተደረጉ የሟቾች ቁጥር ጋር መዝግቧል። እነዚህን ጥቃቶች የፈጸሙት ኦነግ-ሸኔ፣ የመንግስት ኃይሎች ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የቀበሌ ታጣቂዎች እና የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ኦነግ-ሸኔ ከ75 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደሞቱ በተዘገቡበት ስድስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ተሳትፏል። ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የቡድኑ አብዛኛው ጥቃቶች የተመዘገቡት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነው። አብዛኛው በአማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሱት ጥቃቶችም በዚሁ ዞን ተመዝግቧል። ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች ከ75 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደሞቱ የተዘገቡበት አምስት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የተፈፀሙ ሲሆኑ የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ በምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈፀሙ ነበሩ (በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: መስከረም 14-20, 2015 ይመልከቱ )። የመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀሙ ሰባት ጥቃቶች የተሳተፉ ሲሆን በአጠቃላይ 21 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፤ አብዛኞቹ ጥቃቶች የተከሰቱት በምዕራብ ሸዋ ዞን ነው።
የኦነግ-ሸኔ ኃይሎች በአማራ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በተከሰቱ ኩነቶችም ተሳትፈዋል። መስከረም 8 ቀን የኦነግ-ሸኔ አባላት በቡርጂ ልዩ ወረዳ አውራጄ ቀበሌ ከብቶቻቸውን በሚጠብቁ አርሶ አደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው ሁለት አርሶ አደሮችን ገድለው ሌላ አንድ አርሶ አደርን አቁስለዋል። ቡድኑ ወደ 30 የሚጠጉ የቀንድ ከብቶችንም ገድሏል። ከሶስት ቀናት በኋላ፣ መስከረም 11 ቀን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የመጣ ኦነግ-ሸኔ ነው ተብሎ የሚጠረጠር ማንነቱ ያልታወቀ የታጣቀ ቡድን ዘጠኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ሲጠባበቁ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ ከፍቷል።። እነዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአማሮ ልዩ ወረዳ በዶርባሌ ቀበሌ መልካ ኦዳ መንደር በቆሬ ብሄረሰብ አባላት ላይ የሚፈፀሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲያጣሩ የተመደቡ ናቸው (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 12, 2015)። በዚህ ጥቃት አምስት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ አራት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በአማራ ክልል ኦነግ-ሸኔ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ደዋ ሀረዋ ወረዳ ቡርቃ፣ ዋርሳመት እና ካራ ዳካ አካባቢዎች ላይ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ከአማራ ክልል ፖሊስ እና ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል።
በመጨረሻም መስከረም 11 ከደቡብ ሱዳን ድንበር ማሉዋል ጋኦት በተባለው አካባቢ ከደቡብ ሱዳን የመጣ ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ባሮ ወንዝ ላይ ከጃካዎ ድልድይ ወደ መተሃር ከተማ ሲጓዝ በነበረ ሞተር ጀልባ ላይ ተኩስ ከፍቷል። የታጠቀው ቡድን ከታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ተኩስ መክፈቱ ተነግሯል። በዚህ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት ሰባት ሰዎች ቆስለዋል።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ሊካሄድ የሚችለው የሰላም ድርድር ውሎች
በሰሜን ኢትዮጵያ በትህነግ/ህወሓት እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ያለው ውጊያ ዳግም ካገረሸ አንድ ወር አልፎታል። ውጊያው የተከሰተው በመጋቢት 15 ቀን የሰብአዊ ተኩስ አቁም መታወጁን ተከትሎ ከአምስት ወራት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ ነው። ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች አንዱ ሌላውን አዲሱን ውጊያ አነሳስቷል በሚል ክስ ሰንዝረዋል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ነሐሴ 18, 2014፤ ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ ነሐሴ 18, 2014)።
በሁለቱ ወገኖች ጦርነቱ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን፣ በትግራይ ክልል ደቡብ ትግራይ ዞን እና በአፋር ክልል ፋንቲ ረሱ-ዞን 4 የተጀመረ ሲሆን በፍጥነት በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ እና ሰሜን እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ትግራይ፣ መቀሌ እና ምስራቅ ትግራይ ዞኖች ጨምሮ ሌሎች የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ስፍራዎች ተዛምቷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከነሐሴ 26, 2014 እስከ መስከረም 20, 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በኢትዮጵያና በሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች በመንግስት ኃይሎች እና በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች እና እንደ ሳምሪ የወጣት ታጣቂዎች አይነት ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግንኙነት ካላቸው ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እንደነበረ ተዘግቧል። ምንም እንኳን ብዙም መረጃ ባይገኝም የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በሰሜን ትግራይ ክልል ከፍተኛ የሆነ ውጊያ ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል።
ለድርድር ቅድመ ሁኔታዎች
በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ መስከረም 1 ቀን ትህነግ/ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚደረገውን የሰላም ድርድር ተቀብሏል (ትዊተር @ትግራይኢኤኦ፣ መስከረም 1, 2015)። ከዚህ ቀደም ትህነግ/ህወሓት በድርድር ጠረጴዛ ላይ ከመቀመጡ በፊት በፌዴራል መንግስት ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር አስቀምጦ ነበር (በትህነግ/ህወሓት ሰለተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 ይመልከቱ)። በተጨማሪም ቀደም ሲል ትህነግ/ህወሓት መንግሥት ያቀረበውን በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የሚመራውን የሰላም ድርድር ውድቅ አድርጓ ነበር (ዘ አፍሪካ ሪፖርት ነሐሴ 16, 2014፤ ትግራይ ቲቪ፣ ነሐሴ 12, 2014)።
አዲሱ ዙር ጦርነት ለመቀስቀስ ሳምንታት ሲቀረው በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት መመለስን በተመለከተ በሁለቱም በትህነግ/ህወሓት እና በፌዴራል መንግሥት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ተሰጥተዋል። ትህነግ/ህወሓት የምዕራብ ትግራይን ጉዳይ፣ የኮሙዩኒኬሽን እና የመብራት እና የባንክ አገልግሎት የመሳሰሉ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት መመለስን ለድርድሩ እንደ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል። ትህነግ/ህወሓት እነዚህን አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት ለመመለስ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች በኩል ለፌዴራል መንግስት “አገልግሎቶቹን ወደ ነበረበት ለመመለስ ለሚሰሩ ሰዎች የደህንነት ዋስትና ይሰጣል” የሚል ደብዳቤ በመላክ ጠይቋል (በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ሐምሌ 26, 2014)። የፌዴራል መንግስት በትግራይ እነዚህን አገልግሎቶች ወደ ነበረበት ለመመለስ “ማእከላዊ የሆነ ማጥፊያ እና የማብሪያ ቁልፍ የለም” በማለት ምላሽ የሰጠ ሲሆን የተበላሹ መሳሪያዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የሚያስፈልግ ሂደትን በማብራራት እንደ ኢትዮቴሌኮም ያሉ የተለያዩ ተቋማት በአካል ተገኝተው በክልሉ ውስጥ ቢሮዎቻቸውን መክፈት እንደሚያስፈልጋቸው ዘርዝሯል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት – ኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 12, 2014)። በተጨማሪም መንግስት በትግራይ የሚገኙ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሲሞክሩ በትህነግ/ህወሓት ተገድለዋል የተባሉ የመንግስት ሰራተኞችን እና ሌሎች ሰራተኞችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል (ኢትዮጵያ ከረንት ኢሹ ፋክት ቼክ፣ ጳጉሜ 3, 2014)።
አገልግሎቶቹን ወደ ነበረበት መመለስ ለድርድር ቅድመ ሁኔታ እና ውጊያው እንደ አዲስ ለመቀስቀስ እንደ ምክንያት ሆኗል። ትህነግ/ህወሓት በትግራይ ክልል ላይ ያለውን ከበባ ለመስበር እና የክልሉን የመገናኛና የመሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ከሆነ የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በሐምሌ 26 ቀን ትግራይን በጎበኙበት ወቅት የትህነግ/ህወሓት መሪዎች የኮሙዩኒኬሽን እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በፌዴራል መንግሥት ካልተመለሱ ሠራዊታቸው ጦርነት ለመክፈት ዝግጁ መሆኑን እንዳሳወቁዋቸው ገልፀው ነበር (አፍሪካ ሪጅናል ሚዲያ ሃብ፣ መስከረም 10, 2015)።
በሰኔ 2014 የፌዴራል መንግስት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የሰላም ኮሚቴ በመሰየም በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ድርድር አፅድቋል። መንግሥት የሰላም ድርድሩ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት አጥብቆ ይናገራል። ከመስከረም 1 በፊት ግን ትህነግ/ህወሓት በአፍሪካ ህብረት የማይመራ የሰላም ድርድር እንዲደረግ ግፊት አድርጓል።
ሊካሄድ በሚችለው የሰላም ንግግር ውሎች
የጦርነቱ ተፋላሚ አካላት በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም በምዕራብ ትግራይ ዞን፣ የባንክና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች፣1ትህነግ/ህወሓት እነዚህን ጉዳዮች በቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር ውስጥ ሲያስቀምጥ (የመጀመሪያውን የትህነግ/ህወሓት ቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር ለመመልከት ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013ን ይመልከቱ ) መንግሥት በግልጽ እነዚህ ጉዳዮች በድርድር ጠረጴዛ ላይ መወያየት እንዳለባቸው ገልጿል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት – ኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 12, 2014)። የትግራይ መገንጠል፣ የትግራይ ያልሆኑ ኃይሎች መውጣት እና የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች እና የትህነግ/ህወሓት ሊኖራቸው ሰለሚችለው ሚና ላይ ሊወያዩ ይችላሉ። የካቲት 2014 የትህነግ/ህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለድርድር የማይቀርቡትን የትህነግ/ህወሓትን ጉዳዮች ዘርዝረዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 11, 2014፤ ቢቢሲ፣ ጥር 27, 2014፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ የካቲት 12, 2014)። እነዚህ ጉዳዮች ከትግራይ ያልሆኑ ኃይሎች ማለትም የአማራ ክልል እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት፣ ትግራይን ለመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ማድረግ፣ እና የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ባሉበት መቀጠልን ያካትታሉ (በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 እና ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 ይመልከቱ).
የምዕራብ ትግራይ ዞን – ወልቃይት፣ ሁመራ እና ጸገዴ አካባቢዎች – በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል መንግስት እየተዳደረ ይገኛል። ሱዳንን የሚያዋስን በመሆኑ፣ እነዚህን አካባቢዎች መቆጣጠር ለትህነግ/ህወሓትም ሆነ ለፌዴራል መንግስት ወሳኝ ነገር ነው፤ መንግስት ድንበሮቹን በሙሉ ቁጥጥር ማድረግ ሲኖርበት፣ በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ ባለው ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ አደረጃጀት መሰረት፣ የዞኑ ብሄረሰቦች የአማራ እና የትግራይ ተወላጆች እውቅና እንዲሰጣቸው እና የክልል አስተዳደሮችን ለየብሄረሰቦቻቸው መጠየቅ ይችላሉ። የትግራይ ግጭት በጀመረበት ወቅት የአማራ ክልል ጦር እነዚህን አካባቢዎች በመቆጣጠር ለአማራ ክልል መንግስት ታማኝ የሆነ አስተዳደር መስርቷል። የምዕራብ ትግራይ ዞን ላለፉት 30 ዓመታት ውዝግብ ውስጥ ቆይቷል። ከ1984 እስከ 2011 በትህነግ/ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ገዥው ፓርቲ የብሔር ተኮር ፌደራሊዝምን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ አካባቢው የትግራይ ክልል አካል ሆኗል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በዚያን ጊዜ ከአማራ ክልል ጋር መቀላቀል ፈልገው ነበር (ፎሪን ፖሊሲ፣ ሚያዚያ 20, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሃምሌ 1, 2013)። ትህነግ/ህወሓት ግን ምዕራብ ትግራይ የትግራይ ክልል አካል ሆኖ እንዲቀጥል አድርጏል። ለአማራ ክልል ነዋሪዎች ምዕራብ ትግራይ የማንነት መገለጫ ሆኗል፤ መንግስት አካባቢውን ለትህነግ/ህወሓት ቢመልስ በአማራ በትጥቅ ትግል ያለውን ተቃውሞ ሊያሳይ ይችላል የሚለው አነጋገር የተለመደ ነው (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሰኔ 26, 2013 እስከ ሐምሌ 2, 2013 እና ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥር 24, 2014 እስከ የካቲት 21, 2014 ይመልከቱ)።
በድርድሩ ላይ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ታጣቂ ኃይሎችን – የትግራይ መከላከያ ሠራዊትን (ቲዲኤፍ) – ትጥቅ የማስፈታት ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል። ትህነግ/ህወሓት ግን የሠራዊቱ ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ገልጿል። አሁን ያሉ ዘገባዎች እንደ ሚያመለክቱት የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት የፌዴራል መንግስቱን በመደገፍ በውጊያው ውስጥ እንደሚሳተፍ፣ ኤርትራ በሰሜን ኢትዮጵያ ለመዋጋት ከ60 አመት በታች ያሉ “ተጠባባቂ” ታጣቂ ኃይሎቿን ጠርታለች (ሮይተርስ፣ መስከረም 7, 2015)። የራሱ ትጥቅ ያለው የትግራይ ክልል ለኤርትራ እና ለአማራ እና አፋር ክልሎች ስጋትን ስለሚወክል የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ባሉበት ደረጃ እንዲቀጥሉ መንግስት ይቀበላል ተብሎ አይታሰብም።
በተጨማሪም ትህነግ/ህወሓት በምን አይነት ሚና መቀጠል እንዳለበት በድርድር ጠረጴዛ ላይ ሊነሳ የሚችል ሌላ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። የፌዴራል መንግስት የትህነግ/ህወሓት መሪዎች እጃቸውን ሰጥተው ለፍርድ እንዲቀርቡ ሊጠይቅ ይችላል። ይህ ልክ እንደ ቀደሙት ጉዳዮች በትህነግ/ህወሓት ዘንድ ለድርድር የማይቀርብ ነው ተብሎ ይታሰባል። አንዳንዶች እንደሚጠቁሙት ከሁሉ የተሻለው አማራጭ የትህነግ/ህወሓት መሪዎች ሀገሪቱ ለቀው እንዲወጡ ማደረግ ነው ሲሉ ይደመጣሉ (ቦርከና፣ ጥር 3, 2014)። ቡድኑ እንደገና በመደራጀት ከጎረቤት ሀገራት ሆኖ ኢትዮጵያን ማጥቃቱን እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የታጠቁ ቡድኖችን መደገፉን በመፍራት ይህ አማርጭ በፌዴራል መንግስት እንደ ችግር ሊቆጠር ይችላል። የፌዴራሉ መንግስት ትህነግ/ህወሓትን ኦነግ-ሼኔን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖችን በመደገፍ ተጠያቂ ያደርጋል።
ለትግራይ መገንጠል ህዝበ ውሳኔ ማድረግ ፖለቲካዊ እና ህጋዊ ተግዳሮቶች አሉት። የፌዴራል ህገ መንግስት የትኛውም ክልል፣ ቡድን ወይም ግዛት በማንኛውም ጊዜ መገንጠልን እንዲጠይቅ ይፈቅዳል። ለምሳሌ በደቡብ ትግራይ ዞን የራያ አንዳንድ ነዋሪዎች፣ በምዕራብ ትግራይ ዞን ወልቃይት፣ ሁመራ፣ ፀገዴ አካባቢዎች እና በምስራቅ ትግራይ ዞን አንዳንድ ቀበሌዎች ለሁለት አስርት አመታት ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለመቀላቀል ሲጠይቁ ቆይተዋል። የመገንጠል ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ውዝግብ ባለባቸው አካባቢ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች ተጨማሪ ግጭቶችን ለማስወገድ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችን መፍታት አለባቸው። በተጨማሪም በፌዴራል መንግስት መሰረት ትግራይ ክልል በህጋዊ መንገድ የተመረጠ ምክር ቤት የለውም። ትህነግ/ህወሓት እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2020 ክልላዊ ምርጫ ቢያደርግም የሀገሪቱን የምርጫ ህግ የተከተለ አልነበረም (የትግራይ መገንጠል አስመልክቶ ለበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከህዳር 4, 2014 እስከ ህዳር 10, 2014 ይመልከቱ)። ይህ ያለው የሕግ ክፍተት የመገንጠል ህዝበ ውሳኔን መጀመሪያ ውድቅ የሚያደርገው ቢሆንም ጉዳዩ ግን እልባት ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል የለውም።
ተጨማሪ ተግዳሮቶች
በቅርቡ በተከሰትው ውጊያ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች የሰላም ድርድር ለማካሄደ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ውጊያውን ማስነሳቱ ማንን ይጠቅማል ከሚል ጋር የተገናኙ ናቸው። በነሐሴ ወር አዲስ የተቀሰቀሰው ውጊያ ከመጀመሩ በፊት ያሉት ጊዜያት የፌዴራል መንግስት እና ከአማራ ክልል ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደ ፋኖ ታጣቂዎች እና የአማራ ብሄርተኞች ጋር ያለው ግንኙነት ሻክሯል በሚል የፌዴራሉ መንግስቱን ድክመት አመላክተው ነበር። ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2014 በትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ላይ በተደረገው ዘመቻ በክልላቸው ከፍተኛ መከላከል ቢያደርጉም በኃላ ላይ ከአማራ ጋር የተገናኙ ታጣቂዎች ከመንግስ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል። ግንቦት 2014 የፌዴራል መንግስት እና የአማራ ክልል መንግስት “በፋኖ ስም” በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ላይ “ህግ የማስከበር ዘመቻ” አድርገዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 11, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 15, 2014 )።
በዚህ የህግ ማስከበር ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በፋኖ ስር በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ውጊያ ተፈጥሯል (ስለእነዚህ እስራቶች እና ውጊያዎች የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 6 እስከ 12, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014 ይመልከቱ)። ይህ በአማራ ክልል በአማራ ብሔርተኞች፣ ጋዜጠኞች እና ግለሰቦች ላይ የተወሰደው እርምጃ በአማራ ብሔርተኞች እና በአማራ ክልል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት አዲስ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክቷል። ይህ ዘመቻ የፋኖ ታጣቂዎችን ለመበተን የመንግስት ሙከራ ነው ተብሎ ስለሚታመን ሌላ ዙር ግጭት ቢነሳ የፋኖ ታጣቂዎች እና የአማራ ብሄርተኞች ከፌዴራል መንግስት ጋር ዳግም ላይተባበሩ እንደሚችሉ ብዙዎች ገምተው ነበር። ከዚህ ግምት በተቃራኒ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ፋኖ እና አማራ ታጣቂዎች በጥምረት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ከትህነግ/ህወሓት ኃይሎች ጋር እየተዋጉ ይገኛሉ።
በድንበር ላይ ያለው ውጥረት ሌላ የፌዴራል መንግስቱ ያለበትን ተጋላጭነት አመላክቷል። በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በትህነግ/ህወሓት እና ከትህነግ/ህወሓት ጋር አጋርነት ካለው ታጣቂ ቡድን መካከል ውጊያዎች በኢትዮጵያ እና በሱዳን አዋሳኝ ድንበር ላይ መከሰታቸው ተነግሯል (የእነዚህን ውጊያዎች ዝርዝር በኢፒኦ ሳምንታዊ: ነሐሴ 7-ጷጉሜ 4, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ: ጷጉሜ 5, 2014- መስከረም 6, 2015 ይመልከቱ)። አንድ ዘገባ እንዳመላከተው የሱዳን ኃይሎችም ትህነግ/ህወሓትን እየረዱ ሲሆን የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች በሱዳን ከቱመታ ሜዶካ አካባቢ እየተዋጉ ነበር (ኢኤምኤስ፣ መስከረም 4, 2015)። በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ላይ በተካሄደው ውጊያ ውስጥ የተሳተፉት በርካታ የትህነግ/ህወሓት ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል አጨቃጫቂ የድንበር አካባቢ የሆነችው በአቢዬ ካገለገሉ በኋላ በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው የነበሩ መሆናቸውን ሌላ ዘገባ አመልክቷል (ብሉምበርግ፣ ነሐሴ 27, 2014)። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) በቅርቡ እንዳስታወቀው በጥቅምት 2012 በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰወን ግጭት ተከተሎ የትግራይ ተወላጆች ተጠልለው በሚገኙበት በሰሜን በምስራቅ ሱዳን በሚገኙ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ እንደነበረ ገልጿል (ሱዳን ትሪቡን፣ ጷጉሜ 2, 2014)።
የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ትህነግ/ህወሓት እና የፌዴራል መንግስት ሶስት ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል – አንድ ጊዜ በሲሸልስ እና ሁለት ጊዜ በጅቡቲ (ኢዩኤስአር ሚሽን ቱ ኢትዮጵያ፣ መስከረም 6, 2015)። የእነዚህ ስብሰባዎች ይዘት ለህዝብ ይፋዊ ባይሆንም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደገለፁት በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን አለመኖሩ ንግግሮችን እያደናቀፈ ነው (አፍሪካ ሪጅናል ሚዲያ ሃብ፣ መስከረም 10, 2015)። በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን ለመፍጠር የአፍሪካ ህብረት እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ እየሰሩ ነው ተብሎ ይታሰባል። እስከዚያው ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጊያ የመቀጠሉ እድሉ ከፍተኛ ነው።