የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በፈረንጆቹ አዲሱ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የፖለቲካ ግጭት ማስተናገዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች በአንጻራዊነት የተረጋጉ ሆነው ሰንብተዋል። በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የአየር ጥቃቶችን ጨምሮ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (አነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በፀጥታ ኃይሎች እና ማንነቱ በውል ባልተገለጸ ታጣቂ ቡድን መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል ያለው አለመረጋጋት
በኦሮሚያ ክልል በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት የቀጠለ ሲሆን በሁለቱ ኃይሎች መካከል በጉጂ እና በምዕራበ ሸዋ ዞኖች ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተወካዮች ታኅሣሥ 23 ቀን የትራንስፖርት አድማ ማወጃቸው የተነገረ ሲሆን ይኸውም ታኅሣሥ 28 ቀን በተከበረው የኢትዮጵያ የገና በዓል ወቅት መንገዶች እንዲዘጉ እና መጓጓዣ ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።1ዋዜማ ራዲዮ፣ ‘ዋዜማ ዕለታዊ ዜና: ሐሙስ ታኅሣሥ 25፣’ ታኅሣሥ 26, 2016 ታኅሣሥ 29 ቀን የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ አባላት መሆናቸው የተጠረጠሩ ኃይሎች በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ አቅራቢያ ሦስት ሾፌሮችን ተኩሰው በመግደል መኪኖቻቸውን አቃጥለዋል። ተጎጂዎቹ በታጣቂዎቹ የታወጀውን የትራንስፖርት አድማ በመጣስ በጥቃት አድራሽ ታጣቂዎች ተከሰዋል።2ዋዜማ ራዲዮ፣ ‘ዋዜማ ዕለታዊ ዜና: ታኅሣሥ 30፣’ ታኅሣሥ 30, 2016
ውጊያ በአማራ ክልል
በአማራ ክልል ከታኅሣሥ 22 እስከ ጥር 3, 2016 በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል 19 ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በታኅሣሥ ወር መጨረሻ ላይ በደብረ ብርሃን እና ፊኖተ ሰላም ከተሞች ከባድ የከተማ ውስጥ ውጊያ ተደርጓል። በተመሳሳይ ጥር 2 ቀን በጎንደር ከተማ በሞርታር የታገዘ ከባድ ውጊያ መደረጉ ተዘግቧል። ውጊያው እንደቀጠለ ቢሆንም የፋኖ የሸምቅ ውጊያ እየተቀዛቀዘ መሆኑን እና መንግሥት የበላይነት እያገኘ እና በትልልቅ እንዲሁም በትናንሽ ከተሞች እንደገና መረጋጋትን እያረጋገጠ ስለመሆኑ ማሳያዎች አሉ። ከእነዚህ ማሳያዎች መካከል የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ዳግም መከፈታቸው፣ በጎንደር እና በባሕርዳር ከተሞች በባጃጅ የሕዝብ ማመላለሻ (ባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ) ላይ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መነሳቱ እና አጠቃላይ መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተጠቃሽ ናቸው።3አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: ትላልቅ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በመመለሳቸው ምክንያት አማራ ክልል የእፎይታ ትንፋሽ እየተነፈሰ ነው፣’ ጥር 2, 2016 ይህ መረጋጋት የመጣው የክልሉ መንግሥት ለፋኖ ታጣቂዎች ትጥቅ በመፍታት ከሕዝብ ጋር ተመልሰው ለመቀላቀል የስልጠና ማዕከል እንዲገቡ አጠቃላይ ጥሪ ካደረገ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው።4አማራ ሚዲያ ኮፖሬሽን፣ “ከ5 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ሰላምን መርጠው ወደ ማዕከሎች ገብተዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)፣’ ታኅሣሥ 10, 2016
በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር በተያያዘ የተደረገ ውጊያ
የዘይሴ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚኖሩበት የዘይሴ ቀበሌ እንደ ልዩ ወረዳ እውቅና እንዲሰጠው እና ልዩ የአስተዳዳር ደረጃ እንዲያገኝ ከሚል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በኤልጎ እና ወዘቃ ቀበሌዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና ማንነቱ በውል ካልታወቀ የታጣቂ ቡድን መካከል በተደረገ ውጊያ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል።5ሸዋንግዛው ወጋየሁ፣ አዜብ ታደሰ እና ማንተጋፍቶት ስለሺ፣ ‘በግጭት ሥጋት ውስጥ የሚገኙት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ቀበሌያት፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ታኅሣሥ 30, 2016 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታኅሣሥ 23 ቀን ባወጣው መግለጫ በአርባ ምንጭ አካባቢ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከጋሞ ዞን ስር በመውጣት የራሳቸውን ልዩ ወረዳ ለማቋቋም ካላቸው ፍላጎት ጋር በተያያዘ በአካባቢው “ተደጋጋሚ ግጭቶች” መከሰታቸውን አሳውቋ።6የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ‘ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፡ በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ውጥረት እና ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ ይሻል፣’ ታኅሣሥ 23, 2016 ከታኅሣሥ 23, 2015 እስከ ታኅሣሥ 21, 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ አክሌድ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር የተያያዙ አራት የፖለቲካ ግጭት ኩነቶችን መዝግቧል። ከእነዚህ ኩነቶች አብዛኛዎቹ በጋሞ ዞን ውስጥ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰቱ ናቸው።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ታኅሣሥ 22 -ጥር 3, 2016*
ይህ መረጃ/ዳታ ከታኅሣሥ 22 እስከ ጥር 3, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
*አክሌድ የሚያወጣውን ዳታ ከኅዳር ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት እስከ ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ድረስ በእረፍት ምክንያት አቁሞ ስለነበረ ይህ ዘገባ በተለየ መልኩ ሁለት ሳምንታትን ይሸፍናል።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 28 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 1 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 7 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነቶች
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት