የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከሽምቅ ውጊያ ጋር የተያያዙ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስራቶች ተዘግበዋል። በአማራ ክልል ውጊያዎችን እና የአየር ጥቃቶችን ያካተተ በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረግ ጦርነት ቀጥሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግስት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (አነግ)-ሸኔ ተብሎ በሚጠራው — እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የተወሰኑ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግበዋል። እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በቀበሌ ታጣቂዎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መከሰቱ ተዘግቧል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የባለፈው ሳምንት ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር የግጭት መጠን ጨምሯል።
ውጊያ እና የአየር ጥቃቶች በአማራ ክልል
በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት የቀጠለ ሲሆን በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል በአዊ፣ በሰሜን ወሎ፣ በምዕራብ ጎጃም እና በማዕከላዊ ጎጃም ዞኖች ውጊያዎች ተዘግበዋል። በሁለቱ ቡድኖች መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን አዴት ከተማ ለአራት ተከታታይ ቀናት የዘለቀ ጠንካራ ውጊያ መደረጉ ሪፖርት ተደርጓል። በውጊያው ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቢያንስ ሁለት የአየር ጥቃቶች የተደረጉ ሲሆን በዚህም ሪፖርት የተደረጉ 32 ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም በአዊ ዞን ፈንዲቃ ከተማ በተከሰተው ውጊያ የብዙ ሰዎችን ህይወት ማለፉን የተነገረ ሲሆን ይህ ግን በገለልተኛ ወገን አልተጣራም። ጥር 3 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን አለም ከተማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፋኖ ታጣቂዎች የሚጠቀሙበት የመዝናኛ ማዕከል ላይ የድሮን ጥቃት የፈፀመ ሲሆን በዚህም ሁለት ሰዎችን መገደላቸው እና አንዳንድ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።1ቢቢሲ አማርኛ፣ ‘በመርሐቤቴ ወረዳ ከትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገደሉ፣’ ጥር 6, 2016
በኦሮሚያ ክልል ያሉ የተለያዩ ግጭቶች
በኦሮሚያ ክልል በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረግ ውጊያ ቀጥሏል። ይሁን አንጂ ከህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች ቀንሰዋል። ጥር 3 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በጉድሩ ወረዳ የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ካምፕን ኢላማ በማድረግ በፈፀመው የድሮን ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ይህንኑ የድሮን ጥቃት ተከትሎ በጉደሩ ወረዳ በሹንኬ እና አቤይ ሮቢ ቀበሌዎች ከጥር 4 እስከ 6 ቀን ለሶሰት ቀናት የዘለቀ ውጊያ መደረጉን ዘገባዎች ያሳያሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥር 7 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎች — የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ወሰን አካባቢ — ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ከአካባቢው የቀበሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በዚህ ውጊያ ምክንያት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን አንዳንድ ቤቶችም ተቃጥለዋል። ባለፈው ዓመት በሰሜን ሸዋ ዞን ያለው የፖለቲካ ግጭት በ60% አካባቢ የጨመረ ሲሆን ከእነዚህ ግጭቶች አብዛኛዎቹ በደራ ወረዳ የተከሰቱ ናቸው። በደራ ወረዳ ከተከሰቱ የፖለቲካ ግጭቶች ከ80% በላይ የሚሆኑት በነሐሴ 2015 እስከ ታኀሣሥ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል የፋኖ ታጣቂዎችን የተሳተፉባቸው ውጊያዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ቢሆንም የታጣቂዎቹን ማንነት በሚመለከት ብዙ ጊዜ ስምምነት የለም። በኢትዮጵያ ያለው ያልተማከለ የፋኖ ታጣቂዎች ስምሪት እና ታጣቂዎቹ የአማራን ማህበረሰብ ከመከላከል አንፃር የያዙት የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ሲታዩ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የአማራ ብሔር ተወላጅ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ፀረ-መንግስት ከሆነው የፋኖ አማጺ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም አንደሚችል ያሳያል። የአማራ እና የኦሮሞ ማህበረሰቦች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ይጋጫሉ። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የአማራ ብሔር ታጣቂዎች በመጋቢት 2014 ላይ 28 የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል አባል የሆኑ — የቀበሌ ታጣቂዎች እና የክልሉ የፖሊስ አባላትን — በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ ላይ በሚገኘው እና በሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት አካባቢ ላይ ተኩሰው በገደሉበት ወቅት ነበር። ይህ ክስተት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አመራሮች መካከል ውጥረት እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን ኩነቱን በሚመለከት ሁለቱም ወገኖች የሚቃረኑ መግለጫዎችን ሰተዋል። በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለድርጊቱ የአማራ ብሔር ታጣቂዎችን የከሰሰ ሲሆን በአማራ ክልል ስር የሚገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በበኩሉ ክስተቱ የኦሮሞ ብሔር ታጣቂዎች አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባልን ተኩሰው መግደላቸውን ተከትሎ የተፈጠረ መሆኑን አስረድቷል2አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: የኦሮሚያ ክልል መንግስት “በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ”፣ ክልሉን ሾልኮ በመግባት “አስቀያሚ ድርጊቶችን” የሚፈጽሙ ‘’አክራሪ ሀይሎችን’’ አስጠነቀቀ፣’ መጋቢት 26, 2014; አማራ ኮሙኒኬሺን፣ ‘በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራ ቤት አውራ ጎዳና ንዑስ ቀበሌ ላይ ጉዳት ያደረሱ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የምሥራቅ ሽዋ ዞን እየሠሩ እንደኾነ ተገለጸ፣’ መጋቢት 22, 2014 (በኦሮሚያ ክልል ስላለው የግጭት ውስብስብነት እና በክልሉ ስላሉ የፋኖ ታጣቂዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ፡ ኀዳር 22 አስከ ታኀሣሥ 22 2015ን ይመልከቱ)።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተፈፀሙ አስራቶች
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሐዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የፀጥታ ኃላፊዎች ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና ግጭት በመቀስቀስ የከሰሱዋቸውን የአንድ ሚዲያ ባለቤትን ጨምሮ 29 ግለሰቦችን ማሰራቸውን ገልፀዋል።3ዮናታን ዘብዴዎስ፣ ‘በማዕከላዊ ኢትዮጵያ 29 ሰዎች በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ተጠርጥረው ታሰሩ፣’ ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 10, 2016 የሐዲያ ዞን በተከታታይ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ ከመክፈል ጋር በተያያዘ ችግሮች የገጠመው ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የጅምላ እስር እና የተቃውሞ ሰልፎች ከሐምሌ 16, 2015 እስከ ታኀሣሥ 21, 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በተከታታይ ተዘግበዋል። በዞኑ በገንዘብ እጦት ምክንያት ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት መደበኛ ስራቸውን ማከናወን አልቻሉም።4የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ‘አዳዲስ አስተዳደር እና መዋቅር በሚዘረጉባቸው አካባቢዎች ከበጀት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እና የሰብአዊ መብቶች እንድምታ፣’ ታኅሣሥ 13, 2016; ሸዋንግዛው ወጋየሁ፣ ማንተጋፍቶት ስለሺ እና ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‘ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን የጅምላ እስር ቀጥሏል ፣’ ዲደብሊው አማርኛ፣ ኅዳር 16, 2016; አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: በሐዲያ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ካልተከፈላቸው ደሞዝ ጋር በተያያዘ የስራ አድማ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፣ በዚሁ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ቆሟል፣’ ጥቅምት 7, 2016 በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ስር በሚገኙ አካባቢዎች ብዙን ጊዜ ግጭት የሚያስከትሉ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እንዲነሱ የሚያደርጉ ከመልካም አስተዳደር እጦት እና ከደሞዝ አለመከፈል ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች የተለመዱ ናቸው።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
4-10 ጥር 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከታኅሣሥ 22 እስከ ጥር 3, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 19 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 2 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 4 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 0 ኩነት
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት