የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት(ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — ኃይሎችን ኢላማ ያደረጉ የመንግሥት ዘመቻዎች ሪፖርት የተደረጉ ግድያዎችን አስከትለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአንጻራዊነት ሰላማዊ ሆነው ሰንብተዋል።
በአማራ ክልል ያለው ውጊያ
በአማራ ክልል ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ውጊያዎች ተደርገዋል። በመንግሥት ምንጮች መሠረት ጥር 28 ቀን በሰሜን ሸዋ ዞን አለም ከተማ አቅራቢያ በተደረገ ውጊያ የዞኑ የፋኖ ታጣቂዎች የፖለቲካ እና የፖሮፖጋንዳ ኃላፊ ተገድሏል።1ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መከላከያ ሠራዊት፣ ‘የሰሜን ሸዋ ዞን የጽንፈኛ ቡደኑ የፖለቲካ እና የፕሮፖጋንዳ ሃላፊ ላይ እርምጃ ተወሰደ፣’ ጥር 27, 2016
የፋኖ ታጣቂዎች አደረጃጀት ያልተማከለ ሲሆን በአንድ የውጊያ ማዕከል ስር በመሆን አንድ ለመሆን ጠንካራ መሰናክሎች እየገጠሙት ይገኛሉ። ከታኅሣሥ 23, 2014 እስከ ከታኅሣሥ 22, 2015 እንዲሁም ከታኅሣሥ 23 እስከ መጋቢት 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች የፋኖ ታጣቂዎች አመራሮችን እና አባላትን ኢላማ በማድረግ እሰር የፈጸሙ ቢሆንም የፋኖን የአመጽ እንቅስቃሴ ከመስፋፋት በአግባቡ ማስቀረት አልቻለም። በነሐሴ 2015 ውጊያዎች ከደረሱበት ከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ያሳዩ ቢሆንም በአማራ ክልል መደበኛ ውጊያዎች መዘገባቸው የቀጠሉ ሲሆን ይህ ደግሞ የደህንነት ስጋቶች የቀጠሉ መሆኑን ያሳያል። ቀደም ሲል ነሐሴ 2015 ውስጥ በዋነኝነት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥር 24 ቀን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማራዘም ድምጽ የሰጠ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞታል።
በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ላይ ያአደረገው ዘመቻ
ከሁለት ሳምንታት በፊት በኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ የተጣለ የትራንስፖርት አድማ ከፌዴራል መንግሥት ኃይሎች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ያደረገ ሲሆን ይኸውም አማጺ ቡድኑን እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ስር የሚገኘው የሪፐብሊካን ጋርድ ኃይሎችን — በ2010 መጀመሪያ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን እና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ የተቋቋመው— ያሳተፉ ብዙ ውጊያዎችን አስከትሏል።2ዳንኤል ሙምበሬ፣ ‘ፎቶ፡ ‘ሪፐብሊካን ጋርድ’ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጠበቅ ዝግጁነቱን አሳየ፣’ አፍሪካ ኒውስ፣ ታኅሣሥ 14, 2011 እነዚህ ውጊያዎች ባለፈው ሳምንትም የቀጠሉ ሲሆን ጥር 29 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጃዊ ወረዳ ከኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች ጋር ተዋግቷል። የመንግሥት ኃይሎች ሁለት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 70 የአማጺ ቡድኑ ታጣቂዎችን መግደላቸውን ገልፀዋል።3የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ‘የዕዙ ማዕከል ኮር በሸኔ ላይ በወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ አመራርና አባላት ተመትተዋል፣’ የካቲት 02, 2016 በተመሳሳይ ሁለቱ ቡድኖች በምስራቅ ወለጋ ዞን ቦነያ ቦሼ ወረዳ ውስጥ ተዋግተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተገናኘ
በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም እና ውዝግብ የተነሳባቸው አካባቢዎችን ላይ ለመምከር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር የካቲት 1 ቀን በአዲስ አበባ ተገናኝተዋል። ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የፌዴራል መንግሥት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።4ናርዶስ ዮሴፍ፣ ‘ኢትዮጵያ፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ ሕዝበ ውሳኔን በሚመለከት የቀረቡ ሐሳቦች በፌዴራል እና በትግራይ አስተዳደር መካከል ውጥረት ቀሰቀሰ፣’ ኦልአፍሪካ፣ የካቲት 2, 2016 ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሁለቱም ወገኖች ስምምነቱን በሚመለከት መግለጫ ያወጡ ሲሆን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥቱን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አለመፍቀዱን በመጥቀስ ወቅሷል።5የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ‘በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፣’ ጥር 27, 2016
የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ባወጣው ባለ ስምንት ገጽ መግለጫ ስምምነቱን አክብሮ እየሠራ መሆኑን በመዘርዘር ምላሸ የሰጠ ሲሆን—ይኸውም ትህነግ/ህወሓት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መፍቀዱን፣ የሕዝብ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ማድረጉን፣ ለመልሶ ግንባታ የሚረዳ ገንዘብ መመደቡን ይጨምራል። በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥቱ ለትጥቅ ማስፈታት እና ለቀድሞ ተዋጊዎች መልሶ ማቋቋም የበጀት ድጋፍ ማቅረቡን አስቀምጧል።6 የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ‘የፕሪቶሪያ ስምምነት ተጨባጭ ምላሽ ይሻል፣’ ጥር 24, 2016 በእነዚህ የቀድሞ ተዋጊ ቡድኖች መካከል ያለው አለመስማማት ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ ውዝግብ የተነሳባቸው በደቡባዊ ትግራይ ዞን የሚገኘው የራያ እና በምዕራብ ትግራይ ዞን በሚገኙ የወልቃይት፣ ፀገዴ እና ሁመራ አካባቢዎች ጉዳይ ሲሆን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጀመረበት ጥቅምት 2013 ጀምሮ በአማራ ክልል ስር በመተዳደር ላይ ይገኛሉ።
ስምምነቱ ከተፈረመ ከዓመት በኋላ በጥቅምት 2016 የፌዴራል መንግሥት “ውዝግብ ከተነሳባቸው” የትግራይ ክልል አካባቢዎች የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚመለሱ መሆኑን እና የአካባቢዎቹ እጣ ፋንታ ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ የሚወሰን መሆኑን አስታወቋል።7የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት፣ ‘‘ለዘላቂ ሰላም ግጭትን በቋሚነት ለማቆም’’ ስምምነት የተፈረመበት አንደኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ፣’ ጥቅምት 26, 2016 የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ማንኛውንም ሕዝበ ውሳኔ የሚቃወም መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞውን አሰምቷል።8አዲስ ስታንዳርድ፣ ‘ዜና: የዲሞግራፊ ለውጥ እየተደረገ ባለበት፣ ማፈናቀል በቀጠለበት በምዕራብ ትግራይ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የማይቻል ነው: የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣’ የካቲት 5, 2016 ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በቀድሞ የትህነግ/ህወሓት ኃይሎች — የትግራይ መከላከያ ሠራዊት ተብለው የሚታወቁ — በትግራይ ክልል የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስን ጨምሮ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ለመፈፀም የተሻለ እንዲሠራ ጫና ፈጥሮበታል (እነዚህን የተቃውሞ ሰልፎች በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ (ጥር 21, 2016) እና የኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ (ጥር 28, 2016) ይመልከቱ)።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ጥር 2 እስከ የካቲት 1, 2016
ይህ መረጃ/ዳታ ከጥር 25 እስከ የካቲት 1, 2016 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 10 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 1 ኩነት
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 3 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነቶች
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት