የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) — በመንግሥት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው — የሱሉልታ ወረዳ ፖሊስ ኃላፊን እና ሁለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን በመግደል የወረዳውን የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊን አቁስሏል። በአማራ ክልል ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ እየተካሄደ ባለበት አውድ ውስጥ የፋኖ ታጣቂዎች በብዙ ዞኖች መንገዶች እንደዘጉ አውጅ አውጥተዋል።
በሰላም ስምምነቱ ማግስት የኦነሠ/ኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የሱሉልታ ወረዳ የፖሊስ ኃላፊን ገደሉ
ኀዳር 22 ቀን በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በሰኚ ነጋሳ መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሰኚ ነጋሳ የሚመራው የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ቡድን አባላት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ‘የታሃድሶ ማዕከላት’ መግባታቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ቁጥራቸው በውል ያልተገለፀ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ተዋጊዎች ከምዕራብ ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከላት ገብተዋል። ምንም እንኳን ሰኚ ነጋሳ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ የማዕከላዊ ዞን አዛዥ የነበረ ቢሆንም ምዕራብ ወለጋን ከመሳሰሉ ከማዕከላዊ ዞን ኮማንድ ውጪ ከሆኑ አካባቢዎች የመጡ ተዋጊዎችም ወደ ተሃድሶ ማዕከላት እየገቡ ይገኛሉ።
ተዋጊዎቹ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለመርዳት ወደ ተዘጋጁላቸው ማዕከላት የሚገቡት ተወካዮቻቸው ወይም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ታጣቂዎቹ ለሰላም ጥሪው ፍላጎት እንዳላቸው ለአካባቢ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ካሳወቁ በኋላ ነው። ከዚያም የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር በመሆን ቀድመው በተስማሙበት ቦታ ከተዋጊዎቹ ጋር ይገናኛሉ። የሰላም ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ ብዙ ተዋጊዎች ይህንኑ ሂደት ተጠቅመው ወደ ተዘጋጁላቸው የተሃድሶ ማዕከላት ገብተዋል። ታኅሣሥ 1 ቀን የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ እና የፀጥታ ኃይሎች በሸገር ከተማ ሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ከተማ አጠገብ እሮብ ገበያ በሚባል አካባቢ ከተፈጠረው ክስተት ውጪ ሂደቱ በአጠቃላይ ሰላማዊ ነበር። የሱሉልታ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች እና የብልጽግና አመራሮች የሰላም ስምመነቱን መቀበላቸውን ለገለፁ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ አባላት አቀባባል ለማድረግ ታኅሣሥ 1 ቀን በፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ወደ አካባቢው መጓዛቸው ተነግሯል። ይሁንና በቦታው ሲደርሱ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች ተኩስ የከፈቱባቸው ሲሆን በዚህም የሱሉልታ ወረዳ የፖሊስ ኃላፊ እና ሁለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሲገደሉ የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ ቆስለዋል። አንድ የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ኃላፊ ለግድያው ኃላፊነት የወሰዱ ቢሆንም ክስተቱን ታጣቂዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ አካባቢው ከተንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር የተፈጠረ ውጊያ አድርገው ገልፀውታል።1ሥዩም ጌቱ፣ ማንተጋፍቶት ስለሺ እና ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር፣ ‘ሱሉልታ፦ በኦነግ-ኦነሰ አዲስ ጥቃት ያጠላው ስጋት፣’ ኅዳር 23, 2017
ከዚህ ውጪ ባለፈው ሳምንት በኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል የተደረገ ሌላ ውጊያ አልተመዘገበ ቢሆንም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች የፋኖ ታጣቂዎችን ያሳተፉ ውጊያዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ተመዘግበዋል። እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በምሥራቅ፣ በምዕራብ እና የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ደቡባዊ አቅጣጫ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የሰፈሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች አልፎ አልፎ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሬት እና ሀብት ምክንያት አልፈው አልፈው ይጋጫሉ። እነዚህ ግጭቶች በ2011 የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔ ከመንግሥት ጋር መጋጨት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ተባብሰዋል (ለተጨማሪ መረጃ የኢፒኦን የምዕራብ አሮሚያ ግጭት ገጽን ይመልከቱ)። በሚያዚያ 2015 የኦነሠ/ኦነግ–ሸኔን ያሳተፉ ጥቃቶች አዝማሚያ ወደ ምሥራቅ ኦሮሚያ የዞረ ሲሆን በምዕራብ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚከሰቱ የፖለቲካ ግጭቶች ቁጥር ቀንሷል (ከታኅሣሥ 2016 እስከ ታኅሣሥ 2017 በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ግጭት ይዘት ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአማራ እና ኦሮሚያ ያለው አለመረጋጋት የኢትዮጵያን መረጋጋት ስጋት ላይ ጥሏል በሚል ርዕስ የወጣውን ኢንፎግራፋችንን ይመልከቱ)።
በአማራ ክልል በቀጠለው ውጊያ መሃል የመንገዶች መዘጋት
ኅዳር 30 ቀን የተለያዩ የፋኖ ታጣቂዎች ተወካዮች በምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ2ኢሳያስ ገላው፣ ማንተጋፍቶት ስለሺ እና ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‘የደሴ አላማጣ መንገድ በፋኖ ትእዛዝ ተዘጋ፦ ኗሪዎች በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል አሉ፣’ ታኅሣሥ 2, 2017 ዞኖች መንገዶች እንደሚዘጉ ያስታወቁ ሲሆን ይኽውም የሰላማዊ ሰዎችን ዕለታዊ እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል። በጎጃም የፋኖ ታጣቂዎች ተወካይ የመንገድ መዝጋቱ ተግባራዊ የተደረገው ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር እየተካሄዱ ካሉ ውጊያዎች ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ መሆኑን ገልጿል።3አዜብ ታደሰ እና ሸዋዬ ለገሠ፣ ‘የዓለም ዜና፤ ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ሰኞ፣’ ታኅሣሥ 7, 2017 ባለፈው ሳምንት በአዊ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ወሎ፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውስጥ ውጊያዎች መደረጋቸው ተዘግቧል። በጎጃም ዞኖች የመንገድ መዘጋቱ አዋጁ ታኅሣሥ 8 ቀን ተነስቷል።4አዜብ ታደሰ እና ሸዋዬ ለገሠ፣ ‘የዓለም ዜና፤ ታህሳስ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ሰኞ፣’ ታኅሣሥ 7, 2017 የደቡብ ወሎ ዞን የአስተዳደር ማዕከል የሆነችውን ደሴን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኛት ዋና መንገድ ታኅሣሥ 2 ቀን ተከፍቷል።5ኢሳያስ ገላው፣ ማንተጋፍቶት ስለሺ እና ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‘የደሴ አላማጣ መንገድ በፋኖ ትእዛዝ ተዘጋ፦ ኗሪዎች በኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል አሉ፣’ ታኅሣሥ 2, 2017 የፋኖ ታጣቂዎች ለመጨረሻ ጊዜ የመንገድ መዝጋት ያወጁት መስከረም 23 ቀን መንግሥት በቡድኑ ላይ ሌላ ዙር ዘመቻ መጀመሩን ከገለፀ በኋላ ነው። መንገዶቹ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደገና ተከፍተዋል።
ኢትዮጵያ በጨረፍታ
ኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 4, 2017
ይህ መረጃ/ዳታ ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 4, 2017 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። አክሌድ መረጃን እንዴት እንደሚሰበስብ እና ኩነቶችን እንዴት እንደሚመድብ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን የኮድ መጽሐፍን ይመልከቱ። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በሚቀጥሉት ሳምንታት ዳታ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
የኩነት አይነቶች
ውጊያዎች: 22 ኩነቶች
ፍንዳታዎች/ የርቀት ግጭት: 2 ኩነቶች
ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች: 2 ኩነቶች
የአመፅ ግጭት: 0 ኩነት
ሰልፎች: 2 ኩነቶች
ግጭት ያለበት የተቃውሞ ሰልፍ: 0 ኩነት