በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 23, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,409
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 6,249
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 3,657
ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ የሚገኙ ግጭቶች መቀጠላቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ላይ የሚያርፈው ጫና እየጨመረ መጥቷል። ምንም እንኳ የተለያዩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ክፍሎች የተጠናከረ እርምጃ ቢወስዱም በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ እና የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልሎች የሚገኙ ተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ የሚታዩ የታጣቂዎች እንቅስቃሴዎች፣ ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ እና ግለሰቦች ህይወታቸውን የሚያጡባቸው ክስተቶች አሁንም ድረስ እንደቀጠሉ ነው። በአብዛኞቹ ግጭቶች አማራዎች በተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች በተለይም የኦሮሞ ታጣቂዎች እና የደህንነት ቡድኖች የጥቃት ኢላማ ይደረጋሉ። ይህም በብሄራዊ ደረጃ ያለውን የፖለቲካ ፍጭት እና በአካባቢ ደረጃ የድንበር እና የህዝብ አቀማመጥን ለመቀየር የሚደረጉ የሀይል እንቅስቃሴዎችን የሚያንፀባርቅ ነው። በግንቦት የሚካሄደው ምርጫ እየተቃረበ ባለበት ሁኔታ ባለፈው ሳምንት የተከሰቱትን የመሳሰሉ ብዙ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበባቸው ክስተቶች መንግስት በግዛቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖችን የመቆጣጠር ችሎታ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋሉ።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ላይ የምትገኘው የትግራይ ክልል አሁንም አልተረጋጋችም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስታቸው ለትግራይ ህዝቦች ነፃነት ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ.) ታማኝ ሆነው የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ ጋር ´´አስቸጋሪ አና አድካሚ´´ የሆነ ግጭት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል (The Guardian, 4 April 2021)። በመጋቢት 2013 ማገባደጃ ላይ እንኳ በአሰገደ ፂምብላ፤ በዛና፣ ሳምሬ፣ ሀውዜን፣ ተከዜ ወንዝ ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎች፤ ከብርኩታ እስከ ጎሎንኮ፤ ማይክነታል፤ ቆላ ተምቤን፤ ማይጨው፤ እና ግጀት አካባቢዎች ውጊያ እንደቀጠለ ነው። የትግራይን ተደራሽነት ተከትሎ የወጡ የዜና ዘገባዎች የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወታደሮች በያዟቸው የተለያዩ የክልሉ ክፍሎች የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ እና የተለያዩ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አመልክተዋል (Reuters, 25 January 2021, CNN, 2 April 2021)። ለምሳሌ ሲ.ኤንኤን ማህበረ ደጎ በተባለ አካባቢ የኢትዮጵያ ወታደሮች 11 ያልታጠቁ ግለሰቦችን በጅምላ መግደላቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለቋል (CNN, 2 April 2021)። እነዚህ ዘገባዎች እየጨመሩ የመጡ በክልሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ እንደደረሱ የሚዘገቡ የጅምላ ግድያዎች ላይ የሚካተት ነው። በቅርቡም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው የቅድመግኝት የምርመራ ውጤት ከህዳር 9 እስከ 20, 2013 ብቻ ከ100 በላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ህይወት ማለፉን አስታውቋል (Ethiopian Human Rights Commission (EHRC), 24 March 2021)።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሳረፈውን ተፅእኖ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያን ለቀው እንደሚወጡ መጋቢት 17, 2013 ላይ አሳውቀዋል (BBC, 26 March 2021)። ብዙም ሳይቆይ፣ በመጋቢት 21, 2013 የኤርትራ ወታደሮች ቢያንስ ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ገድለዋል ተብሏል (Sudan Tribune, 30 March 2021)። ከሽሬ ሰሜን ምስራቅ (በምአራባዊ ትግራይ) እርምጃ መውሰዳቸውን እንደቀጠሉ ነው።
ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግስቱ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ቦታዎች ላይ እንኳን የፌደራል መንግስቱ አመፅን መቆጣጠር አለመቻል የጊዜያዊ መንግስቱ ችግር ሆኗል። ህይወትን ወደቀድሞ ቦታው መመለስ ፍፁም የማይቻል አስኪመስል አስቸጋሪ የሆነ ሲሆን መቀሌ ከመአከላዊ እና ደቡባዊ የክልሉ ክፍል ውጊያ ሸሽተው በመጡ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ተሞልታለች።
ከት.ህ.ነ.ግ. ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች አካባቢውን ለመግዛት እንዲያስቸግር በክልሉ ውስጥ አመራሮችን እያጠቁ ይገኛሉ። መጋቢት 19 ላይ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችው መቀሌ ጊዜያዊ ከንቲባ የፈንጂ ጥቃት ደርሶበታል (Addis Standard, 2 April 2021)። ራሱን ከዚሁ የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ ከሃላፊነት ቦታው ማግለሉ ተዘግቦ ነበር (Addis Standard, 30 March 2021)። ሆኖም ግን ከንቲባው መጋቢት 24 ላይ ሀላፊነቱን የለቀቀው በክልሉ የሽግግር መንግስት ከስራ በመባረሩ መሆኑን ገልፇል፤ይህም በጊዜያዊ መንግስቱ ውስጥ ያለውን ጥልቅ ችግር ያሳየ ሲሆን በመጪወቹ ወራት በአስተዳደር ጉዳይ ላይም ተጨማሪ ችግሮች ሊከሰቱ እንድሚችል የሚያሳይ ነው። የቀድሞው ከንቲባ በታህሳስ 2013 የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን ያመነ የመጀመሪያው ከፍተኛ ባለስልጣን ሲሆን (Addis Standard, 4 January 2021) ት.ህ.ነ.ግ. የ2013ቱን ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት 165 ግለሰቦችን ለመግደል ዝርዝር አዘጋጅቶ እንደነበር ተናግሮ ነበር። የካቲት 2013 ላይ የፈንቅል እንቅቃሴ መሪ የሆነ ግለሰብ ከሁለት ጠባቂዎቹ ጋር ባልታወቁ ግን ከት.ህ.ነ.ግ. ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በታመኑ ታጣቂዎች ህዋኔ በተባለ ቦታ ተገሏል። ት.ህ.ነ.ግ. ተቺዎችን እና የፌደራል መንግስቱን የሚወክሉ ግለሰቦችን የነፍስ ማጥፋት ኢላማ እንዳደረገ ይታመናል።
ሳምንታዊ ትኩረት – ከፍተኛ ሞት የተከሰተባቸው ግጭቶች የመንግስትን ታጣቂ ቡድኖችን የመመከት ችሎታ ጥያቄ ውስጥ ከቷል።
መጋቢት 21, 2013 ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሽኔ ተዋጊዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቦኔ ቀበሌ ባቦ ገምበል ወረዳ (ምእራብ ወለጋ ኦሮሚያ) ውስጥ 28 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል (ከታች የሚገኘውን ካርታ ይመልከቱ)። ጥቃቶቹን አድርሷል የተባለው የኦነግ ተገንጣይ ቡድን የሆነው እና የፌደራል መንግስቱን በትጥቅ ትግል የሚገዳደረው ኦነግ-ሽኔ በአካባቢው ላይ የእንቅስቃሴ እና ግዛት ቁጥጥር እንዳለው አስታውቋል። ኦነግ-ሽኔ የመንግስት ተቃዋሚ ከሆነው የቀረው የኦነግ ክፍል በመለየት ትጥቅ አልፈታም ያለ ቢሆንም በሁለቱ መሀል ያለው ልዩነት በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ የደበዘዘ ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህም በአካባቢው ከሚገኘው የቄሮ ጋር በመሆን ቦታውን ከፍ አድርጓል። የመንግስት ሀይሎች መጋቢት 21 ለደረሰው ግድያ ተዋጊዎቹ ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን የገለፁ ሲሆን በጥቃቱም 3 ግለሰቦች ተገለዋል (EBC, 31 March 2021)። መንግስት ባሳለፍነው አመት 1947 ኦነግ-ሽኔ አባላትን መግደሉን ገልፃል (EBC, 31 March 2021)።
በቅርቡ የደረሰው ጥቃት በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳትፎ በሌላቸው አማራዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት የተከተለ ነበር። ባለፈው ወር ብቻ አክሌድ በዘራቸው አማራ የሆኑ እና በኦሮሚያ ክልል በመኖር እና በመስራት ያሉ ግለሰቦች ላይ ከደረሱ ጥቃቶችን ውስጥ 70 ሞት መዝግቧል፤ ይህ የተወሰነ ግምት ነው። እነዚህ ጥቃቶች የተከሰቱት በዳቢስ እና በጃሬት ጃርገዳ ሆሮ ዳዲ ቀበሌዎች ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ቦኔ ቀበሌ ባዶ ገምበል ወረዳ (ምእራብ ወለጋ) ነው (Addis Standard, 12 March 2021)። ምንም እንኳ የቡድኑ ተዋጊዎች በግጭት ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ላይ ግድያ ፈፃሚዎች ለመሆናቸው ብዙ ባያጠራጥርም ጃል መሮ በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው የቡድኑ መሪ ኩምሳ ድሪባ በአልጀዚራ ቀርቦ ክሱን አውግዞ ማንም አማራ በቡድኑ ቁጥጥር ስር ባለ ቦታ እንዳልተገደሉ ገልፇል። (Al Jazeera, 28 March 2021). ለአልጀዚራ በተላከ ደብዳቤ ግድያው ከመንግስት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሚሊሺያዎች የተፈፀመ መሆኑን ቡድኑ አስታውቋል (Al Jazeera, 28 March 2021). ። ምንም እንኳን የገዳዮቹ ማንነት ባይረጋገጥም እየጨመረ በመጣው የትጥቅ ትግል ውስጥ ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት በመጪዎቹ ወራትም መቀጠሉ የማይቀር ነው።
በተጨማሪም በኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰቦች መካከል በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን እና አካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ሁለተኛ ሳምንታቸወን ይዘዋል፤ ማጀቴ፣ አጣዬ እና ዱሙግ ከተሞች ውስጥ ተኩስ ነበር። ከመጋቢት 9 እስከ 22 ድረስ በግጭቱ ቢያንስ 67 ሰዎች ሲሞቱ 80000 ደግሞ መፈናቀላችው ተዘግቧል። (BBC News, 31 March 2021). ከብሄርተኝነት ማደግ እና የት.ህ.ነ.ግ.ን መውደቅ ተከትሎ ከመጣው የፖለቲካው ሜዳ መከፈት ጋር ተያይዞ በዞኑ ውስጥ በኦሮሞ ብሄር ሚሊሻ እና በልዩ ዞኑ ዙሪያ የደህንነት ማስጠበቅ ስራ በሚያካሂዱት አማራ ልዩ ሀይል መካከል ግጭት ተፈጥሯል። ግጭቱ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ እና አማራ ክፍሎች መካከል አደገኛ ክፍፍል ከኖረበት አጋጣሚ ጋር ተገጣጠመ። በየአካባቢያቸው በብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች የሚገፉት ሁለቱ ፓርቲዎች ለግጭቱ እርስ በእርስ ታካሰዋል። የአማራ ክልል ሃላፊዎች የከባድ መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ መዋል በማንሳት ለግጭቱ ኦነግ-ሸኔን ተጠያቂ አድርገዋል (Amhara Communications, 21 March 2021)። የኦሮሚያ ክልል ሃላፊዎች በበኩላቸው የአማራ ሀይሎችን ወንጅለዋል (BBC 24 March 2021)።
ባሳለፍነው ሳምንት የደረሱት ጥቃቶች እና ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም። ታጣቂዎች ጉራፋርዳ ወረዳ በቤንች ሻኮ ዞን በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ባደረሱት ጥቃት 10 ሰዎች ተገድለዋል። ከ2010 ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ ብዙ ወረዳዎች ዞን ለመሆን፣ ዞኖች ደግሞ ክልል ለመሆን ጠይቀዋል። አንዳንዶች ጉራፋርዳ ዞን መደረጉን ሲደግፉ ሌሎች ደግሞ ወረዳው ከቤንች ሼኮ አልያም ምእራብ ኦሞ ዞኖች ጋር እንዲቀላቀሉ ፈልገው ነበር። በ2012 ዓ.ም የሲዳማ ዞን የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል መሆኑን ተከትሎ ሌሎች ብሄሮችም ጥቃቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ የሚያገኝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ሆኖም ግን የክልሉ ምክር ቤት ለጥያቄዎቹ ምላሽ አልሰጠም፤ ይልቁንም ክልሉን ፈራርሶ ወደብዙ ክልሎች ከመቀየር ለመታደግ የፈለገ ይመስላል። ይህ ውሳኔ ግጭት የነበረባቸው ሰልፎች እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም መጋቢት 20, 2013 ላይ ቢያንስ 7 በግጭት ላይ የማይሳተፉ አማራዎች መተከል ዞን ማንዱራ ውስጥ ባልታወቁ ቡድኖች ተገድለዋል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ኮማንድ ፖስት ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አጥቂዎቹን ተከታትሎ በወሰደው እርምጃ 10 ግለሰቦች ተገድለዋል። መተከል ውስጥ ከሚገኝ የመኖሪያ አካባቢያቸው በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ አማራዎች በምእራብ ኦሮሚያ ግጭት ውስጥ የማይሳተፉ አማራዎች ካስተጋቡት ጭንቀት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ኮማንድ ፖስት ቢኖርም በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልፀዋል (VOA, 2 April 2021)። ከ2010 ጀምሮ በአክሌድ ምልከታ በመተከል ዞን ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ግለሰቦች 1052 – የተወሰነ ግምት ነው– ናቸው። በምእራብ ኦሮሚያ ውስጥ ድርጊቶችን ማን እንደፈፀ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። መንግስት ቡድኖቹን ´ፀረ–ሰላም´ ሀይሎች ሲል የሚጠራቸው ሲሆን ከሱዳን ጋር ግኝኙነት አላቸው ሲል ይከሳቸዋል።(AFP, 12 February 2021)። አንድ አንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ቡድኑን ከኦነግ–ሸኔ ጋር ያገናኙታል፤ ሆኖም ግን ቡድኑ ይህንን ውድቅ አድርጏል። ቢሆንም ግን የታጣቂ ቡድኑ በአብዛኛው የሚያቅፈው የጉሙዝ የብሄር ሚሊሻዎችን ሲሆን ምናልባትም ከተደራጁ የብሄር እንቅስቃሴዎች ጋር ሊገናኝ ይችላል። አብዛኛዎቹ የጉሙዝ ብሄር አባላት ከመሬታቸው እንደተገፉ ያምናሉ (BBC, 31 March 2021)።
በሀገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እንደመኖራቸው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የደህንነት ሀይሎች በብዙ ጉዳዮች መያዛቸው አያጠራጥርም። ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች መንግስት ምርጫ የሚያካሂድ ከሆነ እንዴት እንደሚያካሂድ ግልፅ አይደለም። ምንም እንኳን የተለያዩ የመንግስት ክፍሎች ግጭት ላይ የማይሳተፉ ግለሰቦችን የሚገሉ ቡድኖችን ለማሸነፍ ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም በሂደት ላይ ያለው ግጭት አለመረጋጋት እንደሚቀጠለ የሚያሳይ ነው (EBC, 31 March 2021; XINHUA 25 February 2021; BBC, 10 November 2020)።