በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሚያዚያ 8, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,466
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 6,760
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 3,757
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ግጭት በድጋሚ አገርሽቷል፤ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የታመነ የተደራጁ እና መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ወደ አጣዬ ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ ቦታዎች በመግባት ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል እና ፌደራል ሀይል ጋር ከባድ ውጊያ ያደረጉ ሲሆን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። በሸዋ ሮቢት፣ ካራ ቆሬ፣ መቆያ (አንፆኪያ)፣ ኤፍራታ ግድም ወረዳ፣ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ ከተማ ከባድ ውጊያ ተካሂዷል። በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ግጭት የቀነሰ ሲሆን የተመዘገቡ የተኩስ ልውውጦች ቁጥርም አናሳ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማ ውስጥ የኦነግ-አባ ቶርቤ አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በጥበቃ ሰራተኞች ላይ በወረወሩት የእጅ ቦምብ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ግለሰብ ሲገድሉ ዘጠኝ አቁስለዋል (ቪኦኤ, ሚያዚያ 4, 2013፣ DW አማርኛ, ሚያዚያ 8, 2013)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
በትግራይ ክልል ግጭት የቀነሰ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከዛ በፊት ከነበሩ ሳምንታት ያነሰ ቁጥር ያለው የተኩስ ልውውጥ ተመዝግቧል። በአድዋ ከተማ የኤርትራ ወታደሮች ቢያንስ ዘጠኝ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ሲገድሉ ከ12 በላይ ደግሞ አቁስለዋል፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን አስቁሟል (ሮይተርስ, ሚያዚያ 6, 2013)። ኤርትራ ወታደሮቿ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ያመነች ሲሆን ለማስወጣት ከስምምነት መደረሱንም አስታውቃለች (ቢቢሲ ትግርኛ ሚያዚያ 8, 2013)።
የሰብአዊ እርዳታ የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ግን ከፍተኛ ከሆነው የእርዳታ ፈላጊ ቁጥር ጋር ሲወዳደር የተወሰነ ነው። ይህም የሆነው በአካባቢው ባለው የደህንነት ስጋት እና አንዳንድ ድርጅታዊ አሰራር ምክንያት ነው።
ክልላዊ ትኩረት – ብሄር ተኮር ግጭት በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች
ምንም እንኳ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ሀይል በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞን አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎችን ባለፉት ሳምንታት ከተኩስ ልውውጥ መጠበቅ ቢችልም የተወሰነ ግዜ የዘለቀው መረጋጋት ግን አልቀጠለም። አርብ ሚያዚያ 8, 2013 ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ጋር እና የአካባቢው ኦሮሞ ሚሊሻ የተወጣጡ የተደራጁ ታጣቂዎች በአጣዬ እና ዙሪያው የሚገኙ የሸዋ ሮቢት፣ ካራቆሬ፣ መቆያ (አንፆኪያ)፣ ኤፍራታ ግድም፣ እና ማጀቴ ከተሞች እና የሚገኙ ቦታዎች ላይ ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል እና ፌደራል ሀይል ጋር ውጊያ አድርገዋል። ከዚህም አልፎ ሚሊሻዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት አድርሰዋል፣ የመኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን አውድመዋል፣ እስረኞችን ለቀዋል (ቪኦኤ ሚያዚያ 8, 2013፣ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሸን ሚያዚያ 9, 2013፣ ሪፖርተር ሚያዚያ 10, 2013)። በግጭቱ ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች ቁጥር አልታወቀም። ግጭቱ የቀጠለ ሲሆን በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
ይህ ግጭት በአካባቢው ከሳምንታት በፊት 303 ሰዎች ከሞቱበት፣ 369 ከቆሰሉበት፣ እና 1539 ቤቶች ከተቃጠሉበት ግጭት የቀጠለ ነው (አፍሪካ ኒውስ መጋቢት 26, 2013)። የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የፌደራል መንግስቱ አካባቢውን በመከላከያ ቁጥጥር ስር በማዋል ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደርግ በሚያዚያ 10, 2013 አስታውቋል (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሚያዚያ 11, 2013)።
በአጣዬ የሚከሰቱ ግጭቶች ተደጋጋሚነት እና ከፍተኝነት በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ናቸው። በሀገሪቱ ከፍተኛው ቁጥር ባላቸው የሁለቱ ብሔሮች ማህበረሰቦች መካከልም ካለው በላይ መቃቃር የሚጭር ነው። በመላው ኢትዮጵያ በአማራዎች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች የመንግስት ምላሽ አለመስጠት ወይም የዘገየ ምላሸ መስጠትም ቁጣ ያስነሳ ሲሆን ለደህንነቱ ክፍተት በሚወነጃጀሉት የአማራ አና ኦሮሞ ክልላዊ መንግስታት መካከል ስር የሰደደ ክፍፍል ፈጥሯል። ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች መካከል ለብሄርተኝነት ቅስቀሳዎች በር ከፍቷል።
በዚህ ሳምንት የተከሰቱ ኩነቶች ያወገዘው የአማራ ብሄርተኛ ፓርቲ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲን ለኦነግ-ሸኔ ድጋፍ በማድረግ አና አማራዎችን በማጥቃት ተጠያቂ አድርጏል። አብን እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ አማራዎችን ከጥቃት የሚጠብቅ መንግስት አለመኖሩን በመጥቀስ አማራዎች እንዲደራጁ እና ራሳቸውን እዲከላከሉ ጥሪ አቅርቧል (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሚያዚያ 10, 2013)። ከኦሮሞ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ያለው የሚዲያ ተቋም የአማራ ፖሊስ እና መከላከያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ኦሮሞዎችን አጥቅተዋል ሲል ተመሳሳይ ክስ ያቀረበ ሲሆን (ኦኤምኤን ሚያዚያ 10, 2013)።
በምዕራብ ኦሮሚያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ላይ እየደረሱ ባሉ ጥቃቶች የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ወደአማራ ክልል መግባታቸውን ተከትሎ ውጥረት ጨምሯል (ዋዜማ ሬዲዮ ሚያዚያ 1, 2013)። ሚያዚያ 8, 2013 ላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎችን መሰደድን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ግለሰቦች በፍኖተ-ሰላም ከፖሊስ እና የአማራ ልዩ ሀይል ጋር የተጋጩ ሲሆን አንድ ፖሊስ ሲሞት አንድ ደግሞ ቆስሏል። አዚሁ ቦታ ላይ አንድ የጭነት መኪና ሹፌር ሰልፈኞች መኪናውን በእሳት በማያያዛቸው ቆስሏል (የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ ሚያዚያ 9, 2013፣ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 8, 2013፣ ሪፖርተር ሚያዚያ 10, 2013)። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አማራዎች እርግጠኛ ቁጥር አይታወቅም።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች ወቅታዊ ሁኔታ
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በክልሉ ውስጥ የማይኖሩ የሀረሪ ተወላጆች ለክልሉ ምክር ቤት የሚደረገው ምርጫ ላይ መምረጥ እንደማይችሉ ያሳለፈውን ውሳኔ (ለዝርዝሩ የባለፈው ሳምንት ኢፒኦ ሳምንታዊ ይመልከቱ) የሀረሪ ክልላዊ ምክር ቤት በሚያዚያ 3, 2013 ተቃውሟል። ምክር ቤቱ ውሳኔው ከክልሉ ህገመንግስት እንዲሁም የምርጫ ህጎች እንደሚቃረን በመግለፅ ጉዳዩን ገለልተኛ አካል እንዲያጣራው ጠይቋል (የሀረሪ ሕዝብ ክልላዊ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚያዚያ 3, 2013)። ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ እስከአሁን እንዳልተካሄደ የገለፀው የክልሉ ምክር ቤት ለምን የሚለውን ግን ግልፅ አላደረገም።
በተጨማሪም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኦሮሞ ነፃነት ዲሞክራሲ ግንባር መካከል ለነበረ ክርክር ውሳኔ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ምርጫ ቦርድ በታህሳስ 6, 2013 የኦሮሞ ነፃነት ዲሞክራሲ ግንባርን ከፓርቲነት የሰረዘበትን ውሳኔ አፅድቋል። ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ህጎች መሰረት የተመረጡ የፓርቲው አባላትን አድራሻ ለማጣራት ጥረት አድርጏል። አድራሻቸው ከተጣራ ግለሰቦች ውስጥ አብዛኛዎቹ በተመዘገበ አድራሻቸው አልተገኙም (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 5, 2013)።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ሆሮ ጉዱሩ፣ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ፣ አርጎባ፣ እና ዋግሜራ ዞኖች፤ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ መተከል እና ካማሺ ዞኖች፤ እንዲሁም በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ጉራ ፈረዳ፣ ሱርማ፣ እና ዘሌማም ዞኖች የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ እንዳልሆነ አስታውቋል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 6, 2013)። በአሁኑ ወቅት ካልተከፈቱ 24,849 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 4126ቱ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ከትራንስፖርት፣ ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ለወታደራዊ መኮንኖች ለመክፈት ከመዘግየት፣ እና ሌሎች ምክንያቶች የተዘጉ ናቸው (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 6, 2013)።