በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሚያዚያ 29, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,518
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,095
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 3,948
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ካለፉት ሳምንታት በቁጥር ያነሱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ተመዝግበዋል። የ2013 ጠቅላላ ምርጫ መድረሱን ተከትሎ የፖለቲካው ድባብ ውጥረት ቢነግስበትም ባለፈው ሳምንት በአክሌድ የተመዘገበው የአለመረጋጋት ኩነት አንድ ብቻ ነው፤ ይህም ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ የተወሰደ አላስፈላጊ ሀይል ነው።
ሚያዚያ 25, 2013 የአዲስ አበባ ፖሊስ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር የሆኑ ግለሰብ ቤት ውስጥ በሀይል በመግባት ቤቱን የሚጠብቁ የደህንነት ሰራተኞችን አስሮ በቤቱ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ሁሉ ስልኮች እና ላፕቶፖች ወስዷል (ቪኦኤ፣ ሚያዚያ 29, 2013; አዲስ ስታንዳር፣ ሚያዚያ 26, 2013)።. ፖሊስ ይህንን ድርጊት ለመቃወም ከቤቱ ውጪ ተሰብስበው የነበሩ ወጣቶች ላይ ተኩሷል፤ አስሯል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 26, 2013)።
ሚያዚያ 27, 2013 አካባቢ የፌደራል ሀይሎች የአማራ ወጣቶች ማህበር አባላትን በጅምላ አስረዋል። በተጨማሪም የተወሰኑ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል አባላትን ባህር ዳር ውስጥ በነበረው ሰልፍ ወቅት ለነበረው ግጭት ተጠያቂ በማድረግ አስረዋቸዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 26, 2013; ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 9, 2013 እስከ 15, 2013)።
ሚያዚያ 29, 2013 ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኦነግ ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ የወሰነውን ውሳኔ ሽሯል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 30, 2013). ምርጫ ቦርድ በአራርሶ ቢቂላ የተመራው ጠቅላላ ጉባኤ በፓርቲው የውስጥ ህግ መሰረት አልተካሄደም በማለት አዲስ የተመረጡትን የፓርቲ አመራሮች አልቀበልም ያለ ሲሆን ፓርቲውንም ለምርጫ አልመዘገበም (ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መጋቢት 19, 2013)።
ኦነግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳን ካገደበት ነሀሴ, 2012 ጀምሮ የአመራር ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ዳውድ ኢብሳ የታገዱት በሌሉበት ነበር። የአንድ ታዋቂ የኦሮሞ ሙዚቀኛን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በሰፊው ከተከሰተው ግጭት የተወሰኑ ቀናት በፊት በቤታቸው በቁም እስር ላይ እንዲሆኑ ተደርገው ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ታህሳስ 21, 2013)።
አራርሶ ቢቂላ የሚመሩት ኦነግ ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ በመጪው ምርጫ ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆኑን አስታውቋል። ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው ኦነግ በምርጫው የማይሳተፈው መንግስት ባደረሰበት ጫና ነው ብለው ነበር (ዲደብሊው፣ የካቲት 12, 2013)። ይህንን የውስጥ ሽኩቻ ተከትሎ ኦነግ ምርጫ ለመወዳደር አልተመዘገበም (ሪፖርተር፣ ነሀሴ 9, 2012; ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መጋቢት 19, 2013)።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የህዝበ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሀት) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ የሽብርተኛ ድርጅቶች እንዲባሉ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሀሳብ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፅድቆታል (የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ሚያዚያ 28, 2013)። መንግስት ይህ ውሳኔ በህግ አግባብ መንግስት የድርጅቶቹን ተግባር ለመቆጣጠር እና ለመከላከል እንዲችል ያደርገዋል ብሏል (የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ-ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 23, 2013)።
የሰብአዊ ድጋፎች እንቅስቃሴ በትግራይ ክልል እና አማራ ክልል
በትግራይ ክልል ምንም እንኳን ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ ድርጅቶች የተሰጠው ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ ግንኙነቶች ማስተባበሪያ ቢሮ በመአከላዊ፣ ሰሜን ምዕራባዊ፣ ምስራቃዊ፣ ደቡብ ምስራቃዊ፣ እና ደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች ሰባዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ወደ ገጠራማው የትግራይ አካባቢዎች ላይ ከመድረስ አግዷቸዋል ሲል ገልጿል (የተመድ ሰብአዊ ግንኙነቶች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሚያዚያ 29, 2013)። በተጨማሪም የመገናኛ መስመሮች አለመኖር የቁጥጥር ስራዎችን እና የእርዳታ ማድረስ ጥረቶችን ሂደት ምዘናን እንዲዘገይ አድርጏል። መንግስት የተወሰኑ አካባቢዎች ከወታደራዊ እጀባ ጋር ክፍት መሆናቸውን አስታውቋል (ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ-ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 30, 2013). ሆኖም መንግስት እነዚህ አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ ግልፅ አላደረገም።
ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ (ሜዲሲንስ ሳንስ ፍሮንቲዬርስ-ኤምኤስኤፍ)ም ´´ገጠራማ አካባቢዎች በአብዛኛው እርዳታ አይደርሳቸውም እንዲሁም በቅርብ ሳምንታት የእርዳታ ድርጅቶች ለተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ያላቸው ተደራሽነት የበለጠ ተደናቅፏል´´ ብሏል (ኤምኤስኤፍ፣ ሚያዚያ 27, 2013)። አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማት የሚገኙት በከተማ ውስጥ ነው። በገጠራማው ክፍል የሚገኙት የጤና ጣቢያች በመጎዳታቸው ወይም በመዘረፋቸው ምክንያት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት 60 የሚደርሱ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች በትግራይ ውስጥ መቋቋማቸውን ገልጿል (የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ-ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 30, 2013)።
በተጨማሪ በክልሉ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል (የተመድ ሰብአዊ ግንኙነቶች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሚያዚያ 29, 2013)። የተመድ ሰብአዊ ግንኙነቶች ማስተባበሪያ ቢሮ የአውሮፓውያን አዲስ አመት ከገባ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በክልሉ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ከሶስት ድርጅቶች እንደደረሳቸው ገልጿል። መንግስት ይህንን ቁጥር ወደ 2.7 ሚሊዮን ያደርሰዋል (ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ-ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 30, 2013)።
በኦነግ-ሸኔ (በአካባቢ የኦሮሞ ሚሊሻዎች በመታገዝ) እና አማራ ልዩ ሀይል መካከል ያለውን ግጭት በመሸሽ በአማራ ክልል ከአጣዬ እና ዙሪያው ካሉ አካባቢዎች ከሚገኝ መኖሪያቸው የተፈናቀሉ ግለሰቦች (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013) ተጨማሪ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሸን፣ ሚያዚያ 27, 2013; ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 28, 2013)። የተፈናቀሉ ግለሰቦች ቁጥር ባይታወቅም ወደ 50,000 እንደሚደርስ ይገመታል (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 28, 2013)። በግጭቱ በአጣዬ ከተማ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለመኖሪያ አይሆኑም። አንድ ምስክር እንዳሉት ከሆነ ”አጣዬ ከተማ 01 ቀበሌ ሙሉ በሙሉ ወድሟል” (ኢቢሲ፣ ግንቦት 2, 2013)። የበቀል ጥቃት ፍራቻ የተፈናቀሉ ግለሰቦች ወደ መኖሪያቸው እንዳይመለሱ አድርጏል (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 29, 2013)።