ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2013 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
-
- አክሌድ 134 ጠቅላላ ኩነቶች እና 556 ሟቾች መዝግቧል።
- ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል ሲሆን የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን ተከትሎ 172 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል። ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች በ159 እና 102 ሟቾች ተከታዩን ቦታ ይዘዋል።
- በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት የጦርነት ግጭት ሲሆን 49 የጦርነት ግጭቶች እና 317 ሟቾች ተመዝግበዋል። 29 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የደረሱ ግጭቶች የተመዘገቡ ሲሆን ይህንን ተከትሎ የ216 ግለሰቦች ህይወት አልፏል። 39 ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ዋና ሂደቶች
- በመላው ሀገሪቷ የተለያዩ ቡድኖች አማራዎችን ኢላማ በማድረግ የሚያደርሱትን ግድያዎች እና መፈናቀሎች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ አለመውሰዱን ተከትሎ በአማራ ክልል ያለው አሉታዊ አመለካከት እየጨመረ ነው። .
- መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራዎች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ምላሽ አለመስጠቱ አልያም ማዘግየቱ ባስከተለው ቅሬታ ምክንያት በኦሮሞ እና አማራ ክልል መንግስታት መካከል ያለው ክፍፍል ስር እየሰደደ መጥቷል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- የመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22, 2013 (መጋቢት/ሚያዚያ) የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
- ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች እና ግጭቶች
- ወርሀዊ ትኩረት: ከምርጫ በፊት ያለው የሰልፍ ሁኔታ በኢትዮጵያ
የመጋቢት/ሚያዚያ ሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በመላ አገሪቱ በርካታ ግጭቶች መቀጠላቸውን ተከትሎ መአከላዊ መንግስቱ ላይ ያለው ጫና እየጨመረ ነው፡፡ ከእነዚህ ግጭቶች አብዛኛዎቹ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ አማራዎችን የጥቃት ኢላማ ያደረጉባቸው ናቸው። መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራዎች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ምላሽ አለመስጠቱ አልያም ማዘግየቱ ባስከተለው ቅሬታ ምክንያት በኦሮሞ እና አማራ ክልል መንግስታት መካከል ያለው ክፍፍል ስር እየሰደደ መጥቷል። ይህ ሁኔታ የብሔርተኝነት ጥቃቄዎች ከሁለቱም ጎራዎች እንዲነሳ በር ከፍቷል። በመላው ሀገሪቷ አማራዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች ብልፅግና ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ በክልሉ ሊያገኝ የሚችለውን የመራጭ እምነት እያሳጣው ነው።
በአፋር ክልል በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች መካከል በነበሩ ውጊያዎች ምክንያት መጋቢት/ሚያዚያ ላይ ከ300 በላይ ግለሰቦች ህይወት አልፏል። አብዛኛዎቹ ውጊያዎች በአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች (በአፋር የብሔር ታጣቂዎች የታገዘ) እና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች መካከል በአፋር ክልል ዞን 3 ባሉ የገዋኔ፣ ሀንሩክ፣ እና ገላሉ ወረዳዎች ውስጥ የተካሄዱ ነበር፡፡ መጋቢት መጨረሻ ላይ አክሌድ በአንድ ሳምንት ብቻ 100 ግለሰቦች መሞታቸውን መዝግቧል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ውጥረት የጨመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአፋር ክልል ዞን 3 ውስጥ የሚገኙ 30 የምርጫ ጣቢያዎችን በሶማሌ ክልል ስር ከመዘገበ በኋላ ነው፡፡ የአፋር ክልል መንግስት ይህንን ውሳኔውን ሲቃወም ምርጫ ቦርድ ጣቢያዎቹን ለመዝጋት ወስኖ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን በአጎራባች ቀበሌዎች እንዲመዘገቡ እና ድምጽ እንዲሰጡ መክሯል። የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ አድርጏል፡፡ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ያለው ተቃውሞ በመቀጠሉ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ውጥረቱ አሁንም ከፍተኛ ነው፡፡
በመጋቢት/ሚያዚያ ተደጋጋሚ ግጭቶች እና ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር በአማራ ክልል ውስጥ ተዘግበዋል። በክልሉ ውስጥ በተደራጀ የፖለቲካ ግጭት ምክንያት ህይወታቸው ካለፈ 172 ግለሰቦች መካከል 116ቱ በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ዞኖች የተመዘገቡ ናቸው። የተደራጁ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እና ፌደራል ወታደሮች ጋር በአጣዬ እና አካባቢው ባሉ የሸዋ ሮቢት፣ ካራቆሬ፣ መቆያ (አንጾኪያ)፣ ኤፍራታ ግድም፣ እና ማጀቴ ያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ በአማራ ክልል የኦሮሚያ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ ግጭት ሚያዚያ 8, 2013 ላይ በድጋሚ አገርሽቷል (ቪኦኤ፣ ሚያዚያ 8, 2013; Aአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 9, 2013; ሪፖርተር፣ ሚያዚያ 10, 2013)። ታጣቂዎቹ ከኦነግ-ሸኔ እና ከአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች የተወጣጡ መሆናቸው ይታመናል፡፡ በተጨማሪም የኦነግ-ሸኔ እና የአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት አድርሰዋል፣ የመኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ድርጅቶችን አውድመዋል፣ እንዲሁም እስረኞችን ፈተዋል፡፡
በአማራ ክልል አጣዬ እና ዙሪያው ባሉ ከተሞች የተከሰቱት ግጭቶች መጋቢት 2013 ውስጥ ከተከሰቱ እና አክሌድ ወደ 300 የሚጠጉ ሟቾችን ከመዘገበባቸው ውጊያዎች የቀጠሉ ናቸው። በዚህ ምክንያት የፌደራል መንግስቱ በአካባቢው ዘላቂ ደህንነት ለማስፈን በማሰብ ሚያዚያ 10, 2013 ላይ ኮማንድ ፖስት አቋቁሟል። ሚያዚያ 21, 2013 በክልሉ ልዩ ኃይል እና ከቅማንት ብሔር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚሊሻዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በጭልጋ እና ዙሪያውን በሚገኙ የመአከላዊ ጎንደር አካባቢዎች ላይ ሁለተኛው ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። በክልሉ ልዩ ሀይሎች እና ከቅማንት ብሔር ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚሊሻዎች መካከል ግጭቱ የተነሳው ሚያዚያ 6, 2013 የከተማው ማዘጋጃ ቤት የነበረ ስብሰባ ወደ ብጥብጥ ከተቀየረ በኋላ ነው። ግጭቱ በአይከል ከተማ እና የመአከላዊ ጎንደር ሰራባ ከተማ ውስጥ በሚገኙት ኳስ ሜዳ፣ ጌታ ፈረስ ፣ እና ቲዉዲብ አካባቢዎች 35 ለሚደርሱ ሰዎች ሞት እና 38 ሰዎች የአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ሆሮ ጉድሩ ዞኖች ውስጥ በኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች እና በፌደራል ኃይሎች (በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል የታገዙ) መካከል ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ የመንግሥት ምንጮች 14 የኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን እና 143 ተጨማሪ ተዋጊዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ኩዩ እና ዳግም ወረዳዎች ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመለክታሉ (ኢቢሲ፣ ሚያዚያ 2, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 4, 2013)። ምንም እንኳን እነዚህ እርምጃዎች ቢወሰዱም ሚያዚያ 20, 2013 ላይ ከዚሁ ቡድን እንደሆኑ የተጠረጠሩ ያልታወቁ ታጣቂዎች በዚያው አካባቢ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማጥቃት አምስት ሰዎችን ገድለዋል፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ የኦነግ–ሸኔ አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በአሙሩ ቀበሌ (ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን) ውስጥ ከአውቶቡስ አስወርደው 15 ሰዎችን በጥይት ሲገሉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን አቁስለዋል ፡፡ አንድ ምስክር ኦነግ–ሸኔ ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎችን እንደወሰደ ገልጿል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሚያዚያ 23, 2013)። ሆኖም ግን ሟቾቹ ከኦሮሞም ሆነ ከአማራ ብሄረሰቦች ናቸው፡፡
በወሩ ውስጥ ኦነግ–ሸኔ በአማራ ክልል ግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በተለይም የአማራ ብሄር ተወላጆችን ማጥቃቱን ቀጥሏል። መጋቢት 27, 2013 የኦነግ–ሸኔ ተዋጊ መሆናቸው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በሆሮ ጉዱሮ ዞን በቢላ እና ጉዶሮ ወረዳዎች የሚገኙ የአማራ ነዋሪዎችን አጥቅተዋል። መጋቢት 29, 2013 አካባቢ የኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች በጃርደጋ (ሆሮ ጉዱሮ) የሚገኙ የአማራ ነዋሪዎችን በማጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ገድለዋል። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሚያዚያ 13, 2013 አካባቢ ከጉቲን ውጪ መንደር 8፣ መንደር 9፣ መንደር 10፣ እና አርኩምቢ አካባቢዎችን ጨምሮ ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ አማራዎች በኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ ያልታወቀ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ተገድለዋል። ሚያዚያ 15, 2013 የኦነግ–ሸኔ ታጣቂዎች በጅማ ዞን በሊሙ ቆሳ ወረዳ በቄቾ ኪርኪራ እና ጋሌ ቀበሌዎች ውስጥ የአማራ ብሄረሰብ ተዋላጅ የሆኑ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው እንዲሰማሩ አደረጉ። የአከባቢው ባለሥልጣናት በጥቃቱ 20 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መገደላቸውን ቢገልፁም አንዳንድ ምንጮች የሟቾችን ቁጥር 29 ያደርሱታል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 20, 2013; ሬውተርስ፣ ሚያዚያ 22, 2013)።
በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ቤተሰቦች ወደ አማራ ክልል እንዲሰደዱ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት ሚያዚያ 8, 2013 ፍኖተ ሰላም የሚኖሩ ግለሰቦች በአማራ ክልል በመሰብሰብ በሀገሪቷ ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎችን መፈናቀል አውግዘዋል። ከፖሊስ እና አማራ ክልል ልዩ ኃይል ጋር የተጋጩ ሲሆን አንድ ፖሊስ ህይወቱ ሲያልፍ አንድ ደግሞ ቆስሏል። በአካባቢው አንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪ በአመፅ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች መኪናውን ባቃጠሉበት ወቅት የመቁሰል አደጋ ደርሶበታል (የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ፣ ሚያዚያ 9, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሚያዚያ 8, 2013; ሪፖርተር፣ ሚያዚያ 10, 2013)። በተጨማሪም በአጣዬ እና ዙሪያዊን በሚገኙ አካባቢዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)–ሸኔ እና የአካባቢው ኦሮሞ ሚሊሻዎች ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ በአማራዎች ላይ የተለያዩ ቡድኖች የሚያደርሱትን ጥቃት እና መፈናቀል የሚቃወሙ ሰልፎች በአማራ ክልል ለሳምንት ተካሂደዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሚጠይቁ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን አንዳንዶች በስልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ከኦሮሞ አክራሪ ቡድኖች ጋር አለው የሚባለውን ግንኙነት አውግዘዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሰልፎቹ ፀረ–ኦሮሞን አቋም የነበራቸው ሲሆን አንዳንድ ሰልፈኞች “ኦሮሙማ ይጥፉ” የሚሉ ምልክቶችን ይዘው ነበር። ይህ ድርጊት በአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ አባ ገዳ አመራሮች (የኦሮሞ ባህላዊ ሽማግሌዎች)፣ እና በአማራ ክልል መንግስት ተወግዟል (የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ፣ ሚያዚያ 16, 2013; ኦኤምኤን, ሚያዚያ 13, 2013; ታዬ ደንደአ አሬዶ፣ ሚያዚያ 12, 2013; አማራ ኮሚዩኒኬሽን፣ ሚያዚያ 13, 2013; አማራ ኮሚዩኒኬሽን፣ ሚያዚያ 15, 2013)። አብዛኛዎቹ ሰልፎች ሰላማዊ የነበሩ ቢሆንም በሶስተኛው ቀን በባህርዳር ከተማ ሰልፈኞች ሊበትኗቸው ከሞከሩ የፀጥታ አካላት ጋር ተጋጭተዋል ፡፡
የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጥያቄ ጋር የተያያዙ ግጭቶች የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልልን ሰላምና ፀጥታን እየተፈታተኑ ይገኛሉ። መጋቢት 29, 2013 አካባቢ ከጉማይዴ ህዝቦች ልዩ ወረዳ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚሊሻዎች በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አማሮ ወረዳ ቡኒት፣ አልፋቾ፣ እና አቡሎ ቀበሌዎች ባደረሱት ጥቃት 12 ሰዎች ሲገደሉ ስምንት ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ከ11,000 በላይ የቆሬ ብሄረሰብ አባላት ተፈናቅለዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 30, 2013)። በተጨማሪም ሚያዚያ 14, 2013 ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በአማሮ ልዩ ዞን ዳኖ ቀበሌ ስድስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በጥይት ገድለዋል። ሚያዚያ 22, 2013 ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በቤንች ሸኮ ዞን ዳንቹ ወረዳ ስድስት ሰዎችን በጥይት መተው ገድለዋል።
ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ የጉሙዝ እና አማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚያደርሱት ጥቃቶች እንዲሁም በፌደራል ኃይሎች እና ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መካከል ያለውን ግጭት ተከትሎ አሁንም አለመረጋጋት እያስተናገደ ነው። ሚያዚያ 11, 2013 ከጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር ኝኙነት ያለው ታጣቂ ቡድን በካማሺ ዞን የሴዳል ወረዳን “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ” ተቆጣጥሯል (የኢትዮጵያ ሰባዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሚያዚያ 13, 2013)። በተጨማሪም መጋቢት 29, 2013 ማምሻ ላይ መተከል ዞን ድባቴ ወረዳ ሲርበን ቀበሌ ከአዋሳኝ የአማራ ክልል እንደሆኑ በተጠረጠሩ ታጣቂዎች ቢያንስ ሰባት ሰዎችን መግደላቸው ተገልጿል።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
በትግራይ ግጭቶች ቀንሰዋል። አክሌድ በማእከላዊ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ከ50 በላይ ሟቾች መዝግቧል፡፡ የክልሉ ተደራሽነት በተለይም የገጠር አካባቢዎች አሁንም አነስተኛ በመሆኑ እነዚህ ቁጥሮች ዝቅተኛ ግምት ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን የህዝበ ወያነ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ሀይሎች መሬት ለመያዝ የሚያደርጊትን ጥረት ማቆማቸው እና በምትኩ ጥፋት አድርሶ የመሸሽ ሂደት ለመከተል መምረጣቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
ሆኖም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች አሁንም ድረስ በህወሀት ሀይሎች፣ ኤርትራ ወታደሮች፣ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አልፎ አልፎ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ከህወሀት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሀይሎች በመጋቢት/ሚያዚያ ወር በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል፣ አምቡላንስ አቃጥለዋል፣ በተጨማሪም የግል እና የመንግስት ተሽከርካሪዎችን አውድመዋል። መጋቢት 20, 2013 ከህወሀት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች በአድዋ እና ተምቤን ከተሞች (ማአከላዊ ዞን) መካከል የሚጓዙ መኪኖች ላይ የደፈጣ ጥቃት በመሰንዘር ቁጥራቸው ያልታወቁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል (ኢቢሲ፣ መጋቢት 30, 2013)። ሪፖርቶች በሰሜን ትግራይ በሰለቅለቃ ከተማ ውስጥ ቢያንስ 33 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች መገደላቸውን ያሳያሉ። ሚያዚያ 4, 2013 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ጣልቃ በመግባት እስከሚያስቆሟቸው ድረስ የኤርትራ ኃይሎች በአድዋ ከተማ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ተኩስ ከፍተው ቢያንስ 9 የገደሉ ሲሆን ከ12 በላይ አቁስለዋል (ሬውተርስ፣ ሚያዚያ 6, 2013)። ምንም እንኳን ኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ቢስማሙም ሚያዚያ 22 ድረስ የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ ይንቀሳቀሱ ነበር።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ካለፉት ወራት አንፃር ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ቁጥር አንፃር አሁንም ቢሆን የሰብዓዊ ዕርዳታ የተገደበ ነው። ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት አሁንም የቀጠሉ የፀጥታ ችግሮች እና አንዳንድ የድርጅት አሰራሮች በክልሉ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ የወሰኑ ምክንያቶች ናቸው ፡፡
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮች እና ግጭቶች
ምርጫው እየቀረበ ሲመጣ የቅድመ ምርጫ ውዝግቦች በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች እየተዳኙ ነው። ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ ውሳኔዎች በምርጫ ቦርድ የተደረጉ የመጀመሪያ ውሳኔዎችን የሚሽሩ እንደመሆናቸው ምርጫ ቦርድ እነዚህን ውሳኔዎች እንዴት እንደሚተገብራቸው ግልፅ አይደለም። የእጩዎች ምዝገባ በመጠናቀቁ እና የምርጫ ካርዶች ህትመት እየተካሄደ በመሆኑ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ለውጦች የሚካሄዱት ከፍተኛ አለመተማመን ባለበት ሁኔታ ነው ፡፡ በቅርቡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች የምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ገዳ ነፃነት ፓርቲ – ገዳ ቢሊሱማ እና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት (ኦዳፓርቲ) ከምዝገባ ለመሰረዝ ያደረገውን ጥረት ውድግ አድርገውታል። በተመሳሳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫ ቦርድ ከሐረሪ ክልል ውጭ የሚኖሩት ሐረሪዎች የክልሉን ምክር ቤት አባላት እንዳይመርጡ ያስተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነፃነት ዲሞክራሲ ግንባር ከፓርቲነት የሰረዘበትን ውሳኔ አፅድቋል።
ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22 ባለው ጊዜ በአጠቃላይ ሶስት የምርጫ እጩዎች ተገድለዋል። በቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ለክልሉ ም/ቤት የሚወዳደሩ አንድ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዕጩ ተወዳዳሪ ሚያዝያ 1, 2013 ላይ መተከል ዞን ካርባር አካባቢ ተገደለ ፡፡ ሚያዚያ 13, 2013 ላይ የወጣቶች አደረጃጀት መሪ የሆነ ሌላ የአብን ፓርቲ አባል በመተማ (ምዕራብ ጎንደር፣ አማራ ክልል) በጥይት ተመቶ ተገድሏል። ሚያዚያ 1, 2013 አካባቢ በኤፌራታና ግድም ወረዳ (ሰሜን ሸዋ፣ አማራ ክልል) አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ እጩ በኦነግ–ሽኔ (እና የአከባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች) እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል መካከል በነበረ ግጭት ወቅት ማንነቱ ባልታወቀ የታጠቀ ቡድን ተገድሏል።
በተጨማሪም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፀጥታ ሥጋቶች ምክንያት በአራት ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ ክልል (በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ፣ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች)፣ አማራ ክልል (በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ልዩ ዞን፣ አርጎባ ዞን፣ እና ዋገራ ዞን)፣ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ (በመተከል እና ካማሺ ዞኖች)፣ እና ደቡብ ክልል (በጉራ ፈርዳ፣ ሱርማ፣ እና ዘልማም ዞኖች) የሚገኙ 4,126 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምዝገባ እየተካሄደ አለመሆኑን አስታውቋል። በድሬዳዋ ከተማ በአንዳንድ የምርጫ መኮንኖች ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን እና መራጮች ለምርጫው እንዳይመዘገቡ ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ተዘግቧል።
በአፋር እና በሶማሌ ክልል ድንበር ዙሪያ ያሉ ክርክር ያለባቸውን የምርጫ ጣቢያዎችን ለመዝጋት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በሶማሌ ክልል ተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል። ውሳኔን ተቃውመው የሚካሄዱ ላይ የተቃውሞ ሰልፎች የጀመሩት መጋቢት አጋማሽ ላይ ነው። ጠቅላላ ምርጫው እየተቃረበ እንደመምጣቱ የተሰረዙትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች በተመለከተ ያለው አለመግባባት በውይይት ካልተፈታ በስተቀር በአካባቢው ግጭት እንደሚፈጠር ትልቅ ስጋት አለ።
በወቅታዊው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሚያዚያ አጋማሽ ላይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ እና በመንግስት ኦነግ–ሸኔ በመባል የሚታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ምርጫው እንዲሰረዝ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በምትኩ ብሔራዊ የውይይት ጉባኤ ጠይቀዋል። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ሀሳብ አቅርቧል (ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ ሚያዚያ 21, 2013; ኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ ሚያዚያ 20, 2013; አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 21, 2013)። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ኦነግ እና ሕወሃት የሽብር ድርጅቶች ተብለው እንዲሰየሙ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 23, 2013)።
ወርሀዊ ትኩረት: ከምርጫ ቀደም ብሎ ያለው የሰልፍ ሁኔታ በኢትዮጵያ
ሕዝባዊ አመጾች የወቅቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ለመቅረፅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከ2006 እስከ 2010 የነበሩ መንግስትን የተቃወሙ ሰልፎች የገዢው ጥምረት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ላይ ለውጥ እንዲደረግ ምክንያት ሆኗል። ይህንን ተከትሎ ቀደም ሲል ኢህአዴግን በበላይነት የሚቆጣጠረው ህወሃት የነበረው ሀይል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ብልጽግና ፓርቲ ተተክቷል።
ከአብይ አህመድ አመራር በፊት የተቃውሞ ሰልፎችን በዋናነት የነበራቸው ገፅታ በተለያየ ጊዜ የሚዘጋጁ መሆናቸው እና የመንግስት ወታደሮች ደግሞ ሰልፎቹን ለማፈን ውጤታማ ያልሆኑ ሙከራዎች የሚያደርጉባቸው መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን ከፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ሰልፈኞች ይህንን በመተላለፍ የውጤታማ እቅድ እና ማስተባበር ውጤት የሆኑ ድርጊቶችን ይፈፅሙ ነበር (አፍሪካኒውስ፣ የካቲት 27, 2013)። ይህ ቅንጅት የአሰላለፍ ውጤት ነበር – የመንግሥት ቁልፍ አባላት ቦታቸውን ለማሻሻል እና ከቅሬታ የተወለደውን ስብስብ ወደተሻለ የሀላፊነት ቦታ ለመግባት እንደ እድል ተመልክተውታል።
ከታህሳስ 2013 ወዲህ በመላ ኢትዮጵያ የተካሄዱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እነዚህ ባህሪዎች አይታዩባቸውም። ሰልፎቹ ለድርጊት ምላሽ ከመስጠት የሚወለዱ ሲሆን በአብዛኛው ከፍተኛ ሁከት ይታይባቸዋል። ምንም እንኳን ከፍተኛ ቅሬታዎች ቢኖሩም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ቀጣይነት የላቸውም፣ የሚሸፍኑት አካባቢም ስፋት ውስን ነው። የአሰላለፍ ድጋፍ በሚኖርበት ጊዜ እንኳን ያለው ሁኔታ ልሂቃን ተቃውሞዎችን ለማድረግ እና የኢኮኖሚ አድማን ለመጣል የሚያደርጏቸውን ሙከራዎች በአብዛኛው ያልተቀናጀ እና ውጤታማ እንዳይሆን ያደርጋል። ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቅ እና ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ሹመት በፊት የነበሩት አይነት ቀጣይነት ያላቸውን የተቃውሞ ሰልፎች የመኖር እድል ጠባብ ነው።
ኦሮሚያ ክልል: የፍቃደኝነት ማነስ፣ እድል፣ እና አሰላለፍ ቦታ
ምንም እንኳን በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ከፍተኛ የተደራጁ ግጭቶች ያሉበት ቦታ ቢሆንም በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ወር የተካሄዱት ሰልፎች ሶስት ብቻ ነበሩ። ይህም ሊሆን የቻለው በሰልፈኞች ላይ መንግሥት ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ሥጋት በመፍጠሩ፣ ለመደራጀት ባለው ዝቅተኛ ፍላጎት፣ እና ልሂቃን ሰፊ የተቃውሞ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት ያላቸው አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ነው።
በታሪክ ውስጥ ኦሮምያ ክልል በሀገሪቱ ውስጥ ሰልፈኞች የሚደራጁበት ዋና ስፍራ ሆኖ ቆይቷል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ – ከነዚህም መካከል ብዙ የቄሮ ወጣቶች የኢኮኖሚ አድማ ማድረግ እንዲችሉ፣ መንግስት ድጋፍ ያደረገባቸውን ዝግጅቶች እንዲጠልፉ፣ እና የመንግስት እንቅስቃሴዎችን በቋሚነት እንዲያውኩ የገንዘብ እና የተለያዩ ድጋፎችን የሚሰጡ የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅቶች መኖር ነበር። ከፍተኛ ፈቃደኝነት መኖሩ እና ትልቅ ዕድል በአንድ ላይ መኖራቸው የተቀናጁ ተቃውሞዎችን ለማድረግ በጣም ምቹ የሆነ ሁኔታ ፈጥሯል።
ባለፈው ዓመት ኦሮሚያ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ይህንን ሂደት ሊያሳይ ይችላል ፡፡ ሰኔ 2012 የተከሰተውን የታዋቂው የኦሮሞ ሙዚቀኛ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ተከትሎ በነበሩ ሞት የተከሰተባቸው አመፆች ጋር ተያይዞ የመንግስት ወታደሮች በኦሮሞ ወጣቶች እና ልሂቃን ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ርምጃ ወስደዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ (በአመፅ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች የገደሏቸውን አናሳ ብሄረሰቦችን ጨምሮ) ተገድለዋል እና በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል። የፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋቱን ተከትሎ ከዚያ በኋላ ሰልፍ ለማካሄድ የተደረጉት ሙከራዎች በአብዛኛው አልተሳኩም – አብዛኛዎቹ ሙከራዎች ላይ መንግስት ፈጣን እርምጃ ወስዷል።
ፈቃደኝነት ከምንግዜውም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመላው ኦሮሚያ በተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ የቄሮ ወጣቶች ጋር የተደረገ ቃለ–ምልልስ እንቅስቃሴው በከፍተኛ ሁኔታ መከፋፈሉን የሚያመለክት ሲሆን የተወሰኑ ወጣቶች ለመንግስት ብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ፣ ሌሎች ለኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት፣ እና ሌሎች ደግሞ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮችን ይደግፋሉ። ይህ ክፍፍል ለመደራጀት ያለውን ፍላጎት ዝቅተኛ አድርጏል – ወጣቶች በጥር እና የካቲት ወራት ውስጥ የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎችን እስር ለመቃወም ታስበው የነበሩ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ የተሞከሩ ጥረቶችን “ትርምስ እና ግራ መጋባት” የሞላባቸው በማለት ገልፀዋል።1አክሌድ በአምቦ፣ ሻሸመኔ፣ እና ነቀምት ከተሞች ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በመጋቢት እና ሚያዚያ 2013 የተደረጉ ቃለምልልሶች ሰልፉን ለማካሄድ የቻሉትም ቢሆን በፖሊስ ኃይሎች ከመበተናቸው ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው መቆየት የቻሉት። በ“ቢጫ ንቅናቄ” ወቅት በሻሸመኔ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት የኦፌኮ አመራሮችን ለመደገፍ የተዘጋጁ ሰልፎች ለማድረግ የተደረገው ሙከራ ወዲያው በፖሊስ እይታ ውስጥ የወደቀ ሲሆን የነበረውን ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ተከትሎም በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ሆስፒታል እንደተላኩ በርካታ ወጣቶች ተናግረዋል። በአምቦ እና ነቀምት ከተሞችም ተመሳሳይ ታሪኮች እንደነበሩ ምላሽ ሰጪ ወጣቶች ተናግረዋል። 2 አክሌድ በአምቦ እና ነቀምት ከተሞች ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በመጋቢት እና ሚያዚያ 2013 የተደረጉ ቃለምልልሶች
በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አዛውንት ነዋሪዎችም ለወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የሚያደጉት የነበረውን ድጋፍ ያነሱ ይመስላል። ብዙ ነዋሪዎች አለመረጋጋት የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በመጥቀስ ድጋፋቸውን አቋርጠዋል (ኢቢሲ፣ የካቲት 11, 2013)።
በዝቅተኛ ፈቃደኝነት ፣ ዝቅተኛ ዕድል፣ እና የተቃዋሚ ልሂቃን ሰልፍ ለማዘጋጀት ያላቸው አቅም ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በምርጫው ወቅት የማያቋርጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የመኖር እድሉ ዝቅተኛ ነው። ሆኖም ግን ፈቃደኝነት ወይም ዕድልን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች በመኖራቸው ምክንያት እነሱን ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው።
የኦሮሚያ የፖለቲካ ምኅዳር በጣም ተለዋዋጭ ነው እና ለውጦች ፈቃደኝነት፣ እድል፣ እንዲሁም የተቃዋሚ ልሂቃን ሰልፍ የማዘጋጀት አቅም ሊጨምሩ እና የሰልፍ እንቅስቃሴዎችን ወደ ክልሉ ሊመልሱ ይችላሉ። ፈቃደኝነት በከፍተኛ ሁኔታ ልዩነት በሚፈጥር ኩነት ምክንያት – ለምሳሌ የታዋቂ መሪ ሞት – ምክንያት ሊጨምር ይችላል። የብልፅግና ሀላፊዎች በኦሮሞ እና አማራ የብልፅግና ክፍሎች መካከል ባለው ልዩነት ምክንያት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሰልፍ እንዲደረግ ፍቃድ የሚሰጡ ከሆነ እድል በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀየራል። ወጣቶች አዳዲስ የመገናኛ መረቦችን እንደመፍጠራቸውና በወራት ክፍተኛ ደረጃ የመድረስ እድል ስላላቸው ሰልፍ የማዘጋጀት አቅም እየጨመረ ነው። የዋና ዋና አዘጋጆች ከእስር መለቀቅም የማዘጋጅት አቅም በቀላሉ በድጋሚ እንዲገኝ ያደርጋል።
አማራ ክልል: ትልቅ እድል፣ ከፍተኛ ፍቃደኝነት፣ እና የተደበላለቀ የማዘጋጀት ብቃት
የአካባቢ ባለስልጣናት ሰልፍ እንዲካሄድ ፈቃደኛ ካልሆኑበት የኦሮሚያ ክልል በተቃራኒው ባለፈው ወር በአማራ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ፈቃደኝነት፣ ዕድል፣ እና አሰላለፍ የታየባቸው ብዙ ሰልፎች ተካሂደዋል። ሆኖም ግን በ2010 ከሽግግር በፊት እንደነበሩት ሰልፎች የተሳታፊ ብዛትም ይሁን ቀጣይነት አልነበራቸውም። እንዲሁም መጨረሻ ላይ በተካሄዱ ሰልፍች ላይ ሁሉም በሰልፎቹ ዓላማ ባለመስማማታቸው ምክኛት እርግጠኛ ያለመሆን ነበር። የተለያዩ ወገኖች “ጠለፋ” እንደነበር እና የተደባለቀ መልእክት መተላለፉን አውስተዋል። ይህም ሊደረግ የነበረው የኢኮኖሚ አድማ እንዲሰረዝ ምክንያት ሆኗል።
በአማራ ክልል ውስጥ ለወራት ያህል ውጥረት እየጨመረ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም በአማራ ክልል በወሎ አካባቢ በሚገኘው በአጣዬ ከተማ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት አለመረጋጋት ተቀስቅሷል። በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በኦሮሚያ፣ አማራ፣ እና ቤንሻንጉል/ጉምዝ ውስጥ እየተደጋገሙ እና እየጨመሩ የመጡ አማራዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች እና መፈናቀሎች ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል ፡፡ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ሃላፊነቱን ለመወጣት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተሰማቸውን ብስጭት የሚገልፁ መፈክሮችን አሰምተዋል።
ከላይ እንደተገለፀው ሚያዚያ 8, 2013 ፍኖተ ሰላም ውስጥ የጀመረው ሰልፍ ላይ አመፅ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ከፖሊስ እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ጋር የተጋጩ ሲሆን አንድ ፖሊስ ሞቶ አንድ ቆስሏል። በተመሳሳይ ቦታ አንድ የጭነት መኪና ሹፌርም አመፅ ላይ የተሳተፉ ሰዎች መኪናው በእሳት ባያያዙበት ወቅት ቆስሏል (ምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ፣ ሚያዚያ 9, 2013)። ዝግጅቱ በኃላ ወደ ደሴ እና ደብረ ማርቆስ የተስፋፋ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ሁሉም የክልሉ ዋና ከተሞች ተሰራጭቷል። ምንም እንኳን ሰልፉ መጀመሪያ ላይ ግጭት የነበረበት ቢሆንም ወሩን በሙሉ በክልሉ የተካሄዱ አብዛኛዎቹ ሰልፎች ሰላማዊ ነበሩ።
ሰልፎቹ የአማራ ብሄርተኛ እንቅስቃሴዎችን ጥንካሬ ያሳዩ ቁልፍ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይህ የክልሉን ባለሥልጣናት አስደንግጧል። በባህር ዳሩ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች የብልፅግና ፓርቲ ማስታወቂያዎችን ካቃጠሉ እና ከፖሊስ ጋር ከተጋጩ በኻላ በርካታ የአማራ ወጣቶች ማህበር አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄደው መጪው ምርጫ አካባቢ ግጭት ለማነሳሳት በሚል የአማራ ብሄርተኛ እንቅስቃሴዎችን ላይ በመንግስት ሀላፊዎች እርምጃ ተወስዷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 28, 2013, ዲደብሊው አማርኛ፣ ሚያዚያ 26, 2013)።
በአማራ ክልል የተካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያሳየው አንድ ዋና አዝማሚያ አለ። ሰልፉ እንዲካሄድ ያበረታቱ ሀላፊዎች በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ባሳዩን መንግስትን የሚቃወም አቋም ተገርመዋል። ከሽግግሩ ወቅት በፊት እንደነበረው አይነት የአሰላለፍ ሥርዓቶች ገና መቋቋም ያለባቸው ሲሆን የአከባቢው ባለሥልጣናት ስለብሔርተኛ ቡድኖች የማግኘት እድላቸው አናሳ ነው። በዚህም ምክንያት በመጪዎቹ ወራት የአማራ ክልል ባለሥልጣናት እንደ አብን ያሉ ብሔርተኛ ቡድኖችን ኃይል ለማዳከም መሞከራቸው እና የመደራጀት እድሎችን ለመቀነስ መሞከራቸው የማይቀር ነው። በሚያነሳሳ ኩነት ምክንያት ፍቃደኝነት የሚጨምር ከሆነ ከፍተኛ መንግስት ከፍተኛ ሀይል መጠቀሙ ሊጠበቅ ይችላል።
ማጠቃለያ
በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን ማሰባሰብ የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው። በምርጫ ሂደት ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰልፍ/አመጽ ድርጊቶች በሚጠበቅበት ሁኔታ የተዘገቡት ቁጥር የተወሰነ ነው። ይህ የሆነው በቅርብ የተከሰቱ ኩነቶች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ሰልፍ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ከፍተኛ ምላሽ እንደሚጠብቃቸው በግልጽ መልእክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት የቅስቀሳ ሥራዎችን ያቀናጁ እንቅስቃሴዎች በውስጣዊ ክፍፍሎች እና የአደረጃጀት መዋቅር ባለመኖር ምክንያት ተሽመድምደዋል። እነዚህን እውነታዎች ከግምት በማስገባት አሁን ባለው የቅድመ–ምርጫ ሂደት ወቅት ከ2006 እስከ 2010 በነበረው ወቅት የነበሩ ሰልፎች ደረጃ ላይ የመድረስ እድሉ ጠባብ ነው።