በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 13, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,545
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,491
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 3,981
በቁጥር (ከሚያዝያ 30, 2013 እስከ ግንቦት 13, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 20
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 385
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 24
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ጠቅላላ ምርጫው እየተቃረበ እና ከብሄር ክፍፍል ጋር የተያያዙ ውጥረቶች የሀገሪቱን የፀጥታ ኃይሎችን እየተፈታተኑ ባሉበት በአሁኑ ሰአት የፀጥታ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል/ጉምዝ፣ ትግራይና፣ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ግጭቶች ተዘግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ምስል ይመልከቱ)። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለሥልጣናት በትግራይ ግጭት ውስጥ ባላቸው ሚና ምክንያት የቪዛ ገደቦችን መጣሉን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፎች ተካሂደዋል (ኤንፒአር፣ ግንቦት 16, 2013)።
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም መርዓዊ በተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሰልፍ ያካሄዱ ተማሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመጋጨታቸው ተኩስ ተከፍቶ አራት ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ቆስለዋል(ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 13,2013)። ባለፈው ወር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሰባሰብ በክልሉ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችን ያደራጀው የአማራ ብሄርተኛ ፓርቲ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ድርጊቱን በማውገዝ ምርመራ እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል (አብን፣ ግንቦት 13,2013)።
በቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልል በቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልል መንግስት ተወካዮች እና በክልሉ የመልሶ-ውህደት ስልጠና በሚያካሂዱ የታጠቁ ቡድን አባላት መካከል ስምምነት ተፈርሟል። የመንግስት ባለስልጣናት እንዳሉት ስልጠናውን የሚወስዱት የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባላት ናቸው (ቢቢሲ አማርኛ፣ ግንቦት 11,2013)። የክልሉ መንግስት የትጥቅ ቡድኑን አባላት የስልጣን እርከኑ ላይ ለማካተት እና የእርሻ መሬት እና ለቤት ግንባታ የሚሆን መሬት ለመስጠት ተስማምቷል። ምንም እንኳን እነዚህ ጥረቶች ቢኖሩም በክልሉ ውስጥ እሁንም ድረስ አለመረጋጋት ይታያል። ግንቦት 9, 2013 ላይ ከጉሙዝ ነፃ አውጪ ግንባር የሆኑ ታጣቂዎች መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አድፍጠው በማጥቃት 20 የፌደራል ወታደሮችን እና ሁለት አሽከርካሪዎችን ገድለዋል(ኢሳት፣ ግንቦት 10,2013)።
በሶማሌ ክልል ከሲጢ በስተምዕራብ በሚገኙ የቢርታ ድሂር አካባቢ እና ታራይኔ ውስጥ ግንቦት 12, 2013 ላይ የአፋር ታጣቂዎች የሶማሌ ታጣቂዎችን በማጥቃታቸው ግጭት ተቀስቅሷል። በግጭቱ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል (ቮስ ቲቪ፣ ግንቦት 12, 2013)። በጠቅላላ ምርጫው መዳረሻ በሶማሌ እና አፋር ክልሎች መካከል ክርክር ባስነሱ አካባቢዎች ላይ የተቀሰቀሱ ግጭቶች የመቶዎችን ህይወት ቀጥፈዋል።
ግንቦት 1, 2013 ላይ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ወደ መስቀል አደባባይ (አብዮት አደባባይ) እየተጏዙ የነበሩ አማኞች ወደኢፍጣር ዝግጅቱ እዳይሄዱ መንገድ በመዝጋት አስለቃሽ ጭስ ተኩሶባቸዋል(ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 2,2013)። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተፈጠረው መስተጏጎል ይቅርታ ጠይቋል(የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 2,2013)። ከተማ አቀፍ የኢፍጣር ዝግጅት ግንቦት 3, 2013 ላይ ያለምንም ችግር ተካሂዷል። ግንቦት 13, 2013 በአዲስ አበባ የተሰበሰቡ ሰልፈኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትን አውግዘዋል። በሰልፈኞቹ ከተስተጋቡ መፈክሮች ውስጥ “ከኢትዮጵያ ላይ እጅ አንሱ” እና “የእኔ ግድብ ነው” የሚሉ ይገኙበታል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13,2013)።
በመጨረሻም በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ወረዳ ግንቦት 10, 2013 ላይ ያልታወቁ ግለሰቦች ዘጠኝ የፀጥታ ሀይሎችን ገድለው ሶስት ሰዎችን አቁስለዋል። ባለፉት ወራት ውስጥ ዞኑ ከፍተኛ የብሄር ግጭት የሚከሰተበት ስፍራ ሆኗል(ቪኦኤ፣ ግንቦት 11,2013)። በክልሉ አማሮ ልዩ ዞን ውስጥ ተጨማሪ ግጭት ተከስቷል (ተጨማሪ መረጃ ከታች ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት: በኦሮሚያ ክልል የጨመረው ግጭት
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በመንግስትም እና ፀረ-መንግስት ታጣቂ ሀይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚፈፅሙትን ግጭት እና ጥቃት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት መጨመሩን ቀጥሏል (ከዚህ ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ሚያዚያ 23, 2013 ላይ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት ኦነግ-ሸኔ ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን አሸባሪ ድርጅት ብሎ ሰይሟል(የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ሚያዚያ 23,2013)። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በሰጠው ምላሽ “ህጋዊ ያልሆነውን ቡድን ከስልጣን ለማስወገድ ጦርነት ውስጥ ለመግባት” ቃል ገብቷል(የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ከፍተኛ እዝ መግለጫ፣ ሚያዚያ 27, 2013)። ከሚያዚያ አጋማሽ አንስቶ በምዕራባዊ እና ደቡባዊ ኦሮሚያ ውስጥ በኦነግ-ሸኔ እና የፌደራል ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት የጨመረ ሲሆን ውጊያዎች በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጉጂ፣ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ ተካሂደዋል። በተጨማሪም በክልሉ የተፈጠፉ እንደጋዜጠኛ መገደል፣ በህዝብ ፊት የተፈፀመ ግድያ እና የውጪ ዜጎች መጠለፍ የመሳሰሉ ትልልቅ ኩነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ውጥረት ያሳያሉ።
በጉጂ ዞን ጎራ ዶላ እና ሊበን ወረዳዎች የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ስምንት የኦነግ-ሸኔ አባላትን መግሰሉን ተከትሎ ግንቦት 9 እና 10, 2013 ላይ ውጊያዎች ተካሂደዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 10, 2013፤ ኢሳት፣ ግንቦት 11, 2013)። በአካባቢው በሚገኙ ብሄሮች መካከል ተደጋጋሚ የትጥቅ ግጭት የሚያስተናግደው ከምዕራብ ጉጂ ጋር በሚዋሰነው እና በደቡብ ክልል በሚገኘው የአማሮ ልዩ ወረዳ ግንቦት 4, 2013 ላይ ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የተገደሉ ሲሆን ሁለት ቆስለው ከ6000 በላይ ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 6, 2013)። ሚያዚያ መጨረሻ ላይ የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ፅሁፍ እንደሚያሳየው በአካባቢው ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች በአካባቢው ባለ ከፍተኛ አለመረጋጋት ምክንያት እየተስተጏጎሉ ነው (ሪሊፍ ዌብ፣ ሚያዚያ 22, 2013)።
በምዕራብ ኦሮሚያም ግጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል። ግንቦት 1, 2013 የመንግስት የሆነው የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋዜጠኛ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ የኦነግ-ሸኔ አባ ቶርቤ ቡድን ታጣቂ መሆናቸው በተጠረጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቱ አካባቢ ተተኩሶበት ተገድሏል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 2, 2013)። የአባ ቶርቤ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ በመደበኛ ግድያ በማካሄድ ይከሰሷል። በዛው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ከኮንዳላ ወደ ሜንዲ ከተማ በሁለት መኪኖች ከሹፌራቸው እና ሶስት ጠባቂዎቻቸው ጋር ሲጏዙ የነበሩ የምዕራብ ወለጋ ዞን የመንገድ ባለስልጣን ሀላፊ በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በጥይት ተገድለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 10,2013)።
መንግስት እንደኢትዮጵያውያን አቆጣጠር አዲሱ አመት ከገባ ወዲህ ኦነግ-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል 18 ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሀላፊዎችን ገድሏል ብሏል (ዋልታ፣ ግንቦት 2,2013)። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአቢ ዶንጎሮ ወረዳም ጥቃቶች የተከሰቱ ሲሆን ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሶስት አማራዎችን ገድለዋል (ኢሳት፣ ግንቦት 11,2013)። በኢትዮጵያ መንግስት ኦነግ-ሸኔ ተብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ቃል አቀባይ የቡድኑ አባላት በወለጋ ሆሮ ጉዱሩ አማራዎች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ የሚለውን ውድቅ አድርገዋል። ይልቁንም ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጏል።
በመላው ምዕራባዊ እና ደቡባዊ ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መዋቅር ያሉ ጉድለቶች እየታዩ እና ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ተለዋዋጭ ለሆነ ሁኔታ እየተጋለጡ ነው። በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች አክሌድ ቃለምልልስ ያደረገላቸው ዳኞች በአብዛኛው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደማይፈፀሙ ቅሬታቸውን ገልፀው ማህበረሰቡ የፌደራል የፍትህ ስርአት ላይ እምነት እንዳይጥሉ ስለሚያደርግ አደገኛ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ አካሄድ በተለያዩ ደረጃዎች የታየ ሲሆን የካቲት ላይ የዋስትና መብት ቢሰጠውም እስከአሁን ድረስ በእስር ላይ የሚገኘው የጅማ ዩንቨርስቲ ምሩቅን ጉዳይ ይጨምራል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 12,2013)። የኦሮሞን ክልል ልዩ ኃይሎች አንድ የኦነግ-ሸኔ አባል ነው ተብሎ የተጠረጠረ ወጣትን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ፋንታ በአደባባይ መግደላቸው የደምቢ ዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል(ቢቢሲ አማርኛ፣ ግንቦት 4,2013)። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ሲሆን የመንግስት ሀላፊዎች እና ጋዜጠኞች ላይ ግድያ ፈፅመዋል። ይህ ግድያ ከመፈፀሙ ጥቂት ቀናት በፊት ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያለው የሚዲያ የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋዜጠኛ የኦነግ-ሸኔ አባላት ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ ታጣቂዎች በደምቢ ዶሎ መኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ተገድሏል(የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 2,2013)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
በትግራይ ክልል ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር በሚደረገው ግጭት ላይ ባላቸው ሚና የተነሳ በርካታ አለም አቀፍ አካላት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ ጫና ማሳደራቸውን ጨምረዋል። የዚህን ግፊት ውጤት ተከትሎ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲደረጉ ቢያደርግም በትግራይ ክልል ውስጥ ግን እስካሁን ድረስ ወደ ድርጊት አልተቀየረም። ምንም እንኳን የሕወሃት ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተጣለው የቪዛ ማእቀብ ላይ የተካተቱ ቢሆኑም ግጭቱን ለማራዘም፣ ዕርዳታን ማደናቀፍ ላይ፣ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ያላቸው ሚና ግን ብዙም አልተባለበትም።
ግብረሰናይ ድርጅቶች አሁንም ድረስ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ዕርዳታ እንዳያደርሱ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዳሉባቸው ይናገራሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች እና የእርዳታ አቅርቦቶች በተለያዩ የግጭቱ አካላት እየተያዙ ናቸው ብሏል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ግንቦት 12,2013)። በተጨማሪም ግብረሰናይ ድርጅቶች በተለያዩ ወታደራዊ ኬላዎች ውስጥ እንዲያልፉ ይገደዳሉ። ሰውነታቸው እና መኪኖቻቸው ይፈተሻሉ እንዲሁም ከአከባቢው ባለሥልጣናት የተሰጠ የፍቃድ ደብዳቤ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። እነዚህ ድርጅቶች ወደገጠራማ አካባቢዎች በቀላልሉ እንዳይደርሱ እንቅፋት ፈጥረዋል።
ግንቦት 2,2013 ላይ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ከዚህ ጉብኝት በኋላ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፈ ሲሆን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል። የውሳኔ ሃሳብ በኋላ በም/ቤቱ ሲፀድቅ የተኩስ አቁም እንዲኖር፣ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ፣ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲፈቀድላቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ፣ እና እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል(S.Res.97፣ ግንቦት 11,2013; Secretary የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን፣ ግንቦት 7,2013)። በተጨማሪም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን የጊዜው እና ቀድሞ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ፀጥታ ኃይል አባላት፣ አማራ ክልል ኃይሎች፣ እና ሕወሓት አባላት ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ የቪዛ ገደቦች መጣሉን አስታውቀዋል። ከዚህም ባለፈ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ማንኛውንም የኢኮኖሚ እና የፀጥታ ድጋፍ መስጠት ለጊዜው ለማቆም የወሰነች ሲሆን ሌሎች መንግስታትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቃለች (የቃል አቀባዩ ጽ/ቤት፣ ግንቦት 15, 2013)።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን ገልፀው ´´በራሷ ሀላፊነት በሁሉም የወሰኗ ማእዘናት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ማንኛውንም አስፈላጊ የደህንነት መዋቅሮች እና መንገዶችን´´ የመጠቀም መብት እንዳላት ገልፀዋል(የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ግ ንቦት 9,2013)። የኢትዮጵያ መንግስት ብሄራዊ መግባባትን እና ሰላምን ለማምጣት በህግ እውቅና ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ፈቃደኝነቱን አሳይቷል። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት ህወሓትን “የሀገርን ሉዓላዊነት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ” የሽብር ቡድን ብሎ በመሰየሙ ”ከዚህ ቡድን ጋር ውይይት አያደርግም”(የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ግንቦት 9, 2013)።
በተጨማሪም መንግሥት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በህግ መሰረት እያጣራ መሆኑን ተከራክሯል። መንግስት ወታደራዊ አስፈላጊነት ባልነበረበት ሁኔታ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በመግደል ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ወታደሮችን እና ጾታዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተጠረጠሩ 25 ወታደሮች ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል። የፍርድ ቤት ክርክሮች በመካሄድ ላይ ናቸው። በዚሁ ወቅት በወሲባዊ ጥቃት እና በመድፈር የተከሰሱ 3 ወታደሮች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነን ግለሰብ በመግደል የተጠረጠረ 1 ወታደር ወንጀለኛ ተብለው ተፈርዶባቸዋል(የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ግንቦት 13,2013)። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም እና የውይይት ጥሪዎችን ውድቅ አድርጓል። በተጨማሪም ግንቦት 13, 2013 ሰልፈኞች በአዲስ አበባ በኢትዮያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጪ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትን በመቃወም “ከኢትዮጵያ ላይ እጅ አንሱ” የሚሉ ምልክቶች ይዘው ሰልፍ አድርገዋል(አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13,2013)። አሁን በአማራ ክልል ሀይሎች ቁጥጥር ስር ባሉ የምዕራብ ትግራይ ዞን በሁመራ ከተማ ላይም ለወልቃይት ነፃነት ለታገሉ የአማራ ሀይሎች አድናቆት እና ምስጋና የሚያቀርብ ዝግጅት ተካሂዷል(አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 14,2013)።