አክሌድ በመላ አገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ግጭቶች እና የተቃውሞ ሰልፎች አዝማሚያ ላይ መረጃን ከየአከባቢው መሰብሰብ እና ትንታኔ መስጠትን ለማሳደግ የሚያስችለውን ኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ (ኢፒኦ) መለቀቅ በደስታ ያበስራል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። ሰፊ የሕዝብ አመፆች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያመጡትን ከፍተኛ ለውጥ ተከትሎ አሁን መንታ መንገድ ላይ በምትገኘው ሀገር የብሄር-ፌዴራሊዝም ስርአት ስር ባለው የማንነት እና አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ ከፍተኛ ክርክር እየተደረገ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩ መከፈት ብሔርተኛ ቡድኖች ብሔርን መሰረት ባደረገው የክልል መዋቀር ውስጥ እውቅና፣ ሥልጣን፣ እና ግዛት ለማግኘት ሀይል የተቀላቀለበት የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ እንዲገቡ አድርጏል። ሀገሪቷ በቀጣዩ ወር ወደሚደረገው ምርጫ እየተቃረበች መሆኑ እነዚህ ግጭቶች እንዲባባሱ አድርጏል።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ሁከት በነገሠበት የአፍሪካ ቀንድ ላይ ለሰላም ወሳኝ ሚና ቢኖራትም በሀገሪቷ ውስጥ የሚካሄዱ በርካታ ግጭቶች ላይ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። አክሌድ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የፖለቲካ ግጭቶች እና የተቃውሞ ሰልፎች ተአማኒነት ያላቸው መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ለመንግስታት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ሲቪል ማህበራት፣ እና ጠቅላላ ማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ መድረክ ሆኖ እንዲያገለግል ኢፒኦን አቋቁሟል። መረጃዎች እና ትንታኔዎችን በቀላሉ እንዲገኙ በማድረግ ኢፒኦ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች፣ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሲቪል ማህበራት፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ፣ እና ሌሎችም መካከል ግንኙነቶች እዲፈጠሩ እና መግባባት እንዲኖር ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመገናኛ ብዙሃን ምህዳር በአድሎአዊ ምንጮች እና በውሸት መረጃዎች ምክንያት የተዛባ ነው። ኢፒኦ ይህንን መሰናክል ለማቅረፍ በመላ አገሪቱ ላይ የተዘገቡ ግጭቶችን በዝርዝር ይመረምራል፣ እንዲሁም ያመሳክራል። ኢፒኦ የሚያዘጋጃቸው መረጃዎች እና ትንታኔዎች ትክክለኛ እና በወቅቱ በተረጋገጠ መረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆኑን ለማረጋገጥ ጥብቅ በሆነ ውስጣዊ አሰራር ይገመገማል። በኢፒኦ የሚሰበሰቡ ሁሉም መረጃዎች አዳዲስ መረጃዎች ሲወጡ ከስር ከስር የሚሻሻሉ ናቸው። አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የውሸት መረጃዎች መንሰራፋትን ለመግታት ኩነቶች በኢፒኦ የሚያካተቱት አስፈላጊ የሆኑ ቀኖች፣ ቦታዎች፣ እና የጥቃት አድራሾች ማንነት በተለያዩ ምንጮች ሲገለፁ ብቻ ነው።
ሁሉም መረጃዎች ለዚሁ በተዘጋጀው የኢፒኦ ድህረ-ገፅ ላይ የሚገኙ ሲሆን በየሳምንቱ የሚሻሻሉ ወቅታዊ መረጃን በሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ካርታዎች እና ወቅታዊ ግጭቶችን፣ በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ አካላትን፣ ክልላዊ ጉዳዮችን፣ እና የትብብር ሙከራዎችንና ግምገማዎችን ያካትታል። በተጨማሪም ኢፒኦ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች መደበኛ የግጭት ዜናዎችን፣ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች ላይ ሳምንታዊ ግምገማዎችን፣ በዋና ዋና ለውጦች ዙሪያ ወርሀዊ ትንተናዎችን፣ እንዲሁም በአዳዲስ አዝማሚያዎች እና ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ልዩ ፅሁፎችን ያዘጋጃል።
በመላው ሀገሪቷ የሚደረጉ በመረጃ የተደገፉ የሰላም ግንባታ ሙከራዎችን ለማገዝ በማሰብ ኢፒኦ ግጭቶችን ከመከታተል በተጨማሪ በመንግስት ወይም በሲቪል ማህበረሰብ አካላት ተነሳሽነት የሚደረጉ የትብብር እና የሰላም ሂደቶች መረጃዎችን ይከታተላል። ኢፒኦ የፕሮጀክቱ መረጃዎች እና ትንታኔዎች እንዲሁም ወቅታዊ የግጭት ለውጦች ላይ ለመላው ማህበረሰብ ክፍት የሆኑ የተለያዩ አውደ-ጥናቶች፣ የውይይት መድረኮች፣ እና ቃለ-ምልልሶችን ያደርጋል።
ኢ.ፒ.ኦ. መቀመጫውን በአሜሪካ ሀገር ውስጥ ያደረገው ዓለምአቀፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግጭቶች የሚከታተለው አክሌድ ፕሮጀክት ነው። የኢ.ፒ.ኦ. መረጃዎች በአክሌድ የሚሰበሰቡ ሲሆን መረጃዎቹ በአማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ኦሮምኛ፣ እና ትግርኛ ቋንቋ ምንጮች የሚሰበሰቡ ናቸው። የአክሌድ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎች ከአካባቢ፣ ብሄራዊ፣ እና አለምአቀፍ ምንጮች የተገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ታሪካዊ መረጃዎችን እና በየሳምንቱ የሚጨመሩ አዳዲስ መረጃዎች የሚያካትት ነው። አክሌድ ተአማኒነት፣ ጥንካሬ፣ ጥልቀት ያላቸውን መረጃዎችን ከታመኑ ምንጮች ብቻ ይጠቀማል። አክሌድ ለመዘገብ እና ትንታኔ ግልፅ፣ ያልተዛባ፣ እና ተደራሽነት ያለው መረጃ ለመስጠት ያለመ ነው። መረጃን ለማውረድ እና ተጨማሪ ትንታኔዎችን እና የአሰራር ዘዴዎችን ለማግኘት ዋናውን የአክሌድ ድረ-ገፅን ይጎብኙ። ኢፒኦን ለተመለከተ ዝርዝር መረጃ የኢፒኦን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ገፅ ይመልከቱ.።
ለሚዲያ ጥያቄዎች እና ተጨማሪ መረጃዎች እባክዎ መልእክትዎን [email protected] ላይ ይላኩ።.