በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 27, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,566
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,747
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,223
በቁጥር (ከግንቦት 21, 2013 እስከ ግንቦት 27, 2013)
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 3
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 3
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 1
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ካለፉት ሳምንት ጋር ሲወዳደር ባለፈው ሳምንት የነበሩት የተደራጁ ግጭቶች ኩነቶች እና ሟቾች ቁጥር አነስተኛ ነበሩ (ከዚህ በታች ያለውን ይመልከቱ)። ሳምንቱ የተጀመረው የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በሚቃወሙ ሰልፎች ነበር። ግንቦት 22, 2013 ላይ ሰልፈኞች “ድምፃችን ለነፃነታችን እና ሉአላዊነታችን” በሚል መሪ ቃል አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ በማውገዝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችውን የቪዛ ገደብ እንደገና እንድታጤን ጥሪ አቅርበዋል (ፋና ብሮድካቲንግ፣ ግንቦት 22, 2013)። በአዲስ አበባ ከ50,000 በላይ ሰዎች የተሳተፉበት ሰልፍ መካሄዱ ተዘግቧል (ኢሳት፣ ግንቦት 22, 2013)። በተመሳሳይ ቀን በአሶሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር፣ ሆሳእና፣ ስልጤ፣ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 22, 2013ሀ, የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 22, 2013ለ). በአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት ሁለተኛ ሰልፍ ግንቦት 24, 2013 ላይ ተካሂዷል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጉጂ፣ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ውስጥ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዝያ 30, 2013 እስከ ግንቦት 13, 2013፤ እና ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013 ይመልከቱ)። ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ኃይሎች መካከል በሚደረገው ውጊያ መሀል የወደቁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ኦሮምኛ ያልሆነ ቋንቋ በሚናገሩ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከባድ እርምጃ እንደተወደባቸው ቅሬታ አሰምተዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 23, 2013)።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአጣዬና አካባቢው በፌደራል ወታደራዊ ኃይል የሚመራው ኮማንድ ፖስት የተለያዩ ተግባራትን አካሂዷል። ኮማንድ ፖስቱ የተቋቋመው በአጣዬ እና አካባቢው ባሉ አካባቢዎች ኦነግ-ሸኔ እና የአካባቢው የኦሮሞ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሀይል እና ፌደራል ወታደሮች ጋር ከተዋጉ በኻላ ነበር (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013ን ይመልከቱ)። ግንቦት 25, 2013 ላይ በደሴ ከተማ ደዋ ጨፌ ወረዳ ጠረፍ ቀበሌ ባህላዊ የእርቅ ተግባራት ተካሂደዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 25, 2013)። ሆኖም ግን በአጣዬ ከተማ ውስጥ በነበረው ግጭት የተጎዱት አብዛኛዎቹ ሰዎች አብዛኛው ንብረት በግጭቱ ሙሉ በሙሉ በመውደሙ አሁንም ድረስ ግዜያዊ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከሚያዚያ 23 2013 እስከ ሚያዚያ 29 2013ን ይመልከቱ)።
ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች አድፍጦ ማጥቃታቸውን ቀጥለው ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የፀጥታ ኃይሎችን ገድለዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013 ይመልከቱ)። ግንቦት 27, 2013 ላይ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ወጀምታ ቀበሌ ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን አድፍጦ በማጥቃት ስድስት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፀጥታ ኃይል አባላትን ሲገድል አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ግለሰብን አቁስሏል። ከዚህ ጥቃት በኋላ ወደ 4000 ያህል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ከአካባቢውን ሸሽተው ሄደዋል። ግንቦት 28 እና 29, 2013 ላይ ማንነቱ ያልታወቀው ቡድን በጉራፈርዳ ወረዳ የጋቢታ እና ሰመርታ ቀበሌዎች ውስጥ ቤቶችን እና እርሻዎችን አቃጥሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 30, 2013)።2ይህ ኩነት በአክሌድ በሚቀጥለው ሳምንት ይመዘገባል። በአክሌድ በአሁኑ ሰአት የመዘገበው እስከ ግንቦት 27, 2013 የተከሰቱትን የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ኩነት የተዘገበው ግንቦት 30, 2013 ላይ ነው። ከዚህ ጥቃት ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ግንቦት 10, 2013 ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ውስጥ አድፍጠው በማጥቃት ዘጠኝ የደህንነት ሀይሎችን ሲገድሉ ሌሎች ሶስት ሰዎችን አቁስለዋል።
ግንቦት 25, 2013 ላይ የአፋር ክልል መንግስት ላለፉት 30 ዓመታት ከትግራይ ክልል በሆኑ ሀላፊዎች ሲተዳደር የቆየውን የሳውኔ ቀበሌ አስተዳደርን እንደተረከበ ገልጿል (ዋዜማ ሬዲዮ፣ ግንቦት 25, 2013)። በተመሳሳይ ከህዳር, 2013 ጀምሮ የአማራ ክልል መንግስት የተወሰኑ ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎችን እያስተዳደረ ይገኛል። የፌደራል መንግስቱ ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ጋር ባለው ግጭት ወቅት የተፈጠሩትን እነዚህን መሰል የአስተዳደር ፉክክሮችን እንዴት እንደሚፈታ ግልፅ አይደለም።
ሳምንታዊ ትኩረት: መንግስት የትግራይ ክልልን ለማረጋጋት የሚያደርገው ጥረት
ባለፈው ሳምንት መንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ውጊያ በርካታ ሪፖርቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ እነዚህ ሪፖርቶች ያተኮሩት መንግስት “መሠረተ ቢስ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸው” ሲል የጠራቸው ሪፖርቶችን መመለስ ላይ ነበር (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)። መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግስት በክልሉ ውስጥ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገለፃ ተደርጓላቸዋል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 26, 2013)።
በሪፖርቶቹ ውስጥ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በክልሉ ውስጥ እየተወሰደ ያለውን እርምጃው ለማጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም ከህወሃት ኃይሎች ጋር ቢያንስ በሁለት አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆኑን አምኗል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)። የመንግስት ወታደሮች ተጨማሪ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የህወሃት ሀይሎች ወደሽምቅ ውጊያ እና ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎችን እና ተጓዦችን የጥቃት ኢላማ ወደማድረግ ቀይረዋል። ይህ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቅጠል እና በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎች ላይ መንግስት ለመመስረት የሚደረጉ ጥረቶችን በጣም አወሳስቧል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 24, 2013)።
የመንግስት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ2013 ከጥቅምት እስከ ግንቦት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች 22 የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላትን ገድለዋል፣ ሌሎች 4 አባላትን አቁስለዋል፣ እንዲሁም 20 ከጊዜያዊ መንግሥቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችን ክልሉ ውስጥ አፍነው ወስደዋል (የኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማረጋገጫ፣ ግንቦት 18, 2013)። ግንቦት 20, 2013 ላይ የህወሃት ሀይሎች በምስራቅ ትግራይ ዞን አዲግራት ውስጥ በሚገኝ የመንግስት ህንፃ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የከተማውን ጊዜያዊ ከንቲባ እና አንድ ያልተገለፀ ረዳታቸውን ገድለዋል። በተኩስ ልውውጡ አንድ የአለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አባልም ተገድሏል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ, ግንቦት 26, 2013)። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግንቦት 26, 2013 ላይ የህወሃት አባላት በራያ አዘቦ ወረዳ አንድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባል ገድለዋል (ኢሳት፣ ግንቦት 28, 2013)።
ምንም እንኳን በትግራይ ክልል ላይ የተጣለው የስድስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ በይፋ ቢያበቃም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ “በፌዴሬሽን ምክር ቤት የታዘዘው የፌደራል ጣልቃ ገብነት አሁንም በሥራ ላይ ነው” ሲሉ ገልፀዋል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)። ይህ ማለት በህጉ የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልልን ማስተዳደር መቀጠል ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ውሳኔ የክልሉ ሀላፊዎች ወደስልጣን እንዲመለሱ ከሚፈልገው የጊዜያዊ መንግሥቱ ተቃውሞ ገጥሞታል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 24, 2013)። በተጨማሪም መንግስት የኤርትራ ኃይሎች ከክልሉ መውጣት መጀመራቸውን አመልክቷል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)።
በክልሉ ውስጥ በታጣቂ ኃይሎች የተፈፀሙ ወንጀሎች እንዲጣሩ የደረሰውን ከፍተኛ ጫና ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ “ያለ ወታደራዊ አስፈላጊነት” በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን በመግደል የተጠረጠሩ 28 ወታደሮች እና በጾታዊ ጥቃት እና አስገድዶ መድፈር የተጠረጠሩ 25 ወታደሮች ላይ ክስ መመስረቱን በዝርዝር አቅርበዋል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)። ሌሎች ምርመራዎችም በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በማይካድራ አካባቢ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ግድያ ላይ እንደተሳተፉ የታመኑ 23 ሰዎች ለፍርድ መቅረባቸውን ገልፀዋል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)። በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጥረዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአራት የተለያዩ ቡድኖች እየተመረመሩ ይገኛሉ። እነዚህም የወታደራዊው ፍ/ቤት፣ ትግራይ ፖሊስ እና ፍትህ ቢሮ ፣ ፌደራል ፖሊስ ከተመደቡ መርማሪዎች ጋር በመሆን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ናቸው።
እነዚህ መሻሻሎች ቢኖሩም መንግስት በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ የደህንነት እና የገንዘብ ችግሮች እያጋጠሙት መሆኑን አምኗል፡፡ ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሀይሎች በተደጋጋሚ በተጏዦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፣ ይህም አቅርቦት ለማድረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አዘግይቷል። እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ቁጥር ካለው የገንዘብ አቅም በላይ ነው። የመንግስት ምንጮች አለማቀፍ የዜና አውታሮች ‘’የሚያዛቡት መረጃ’’ በክልሉ ውስጥ ያለውን ችግር እንዳይፈታ ተግዳሮት ፈጥሯል ብለዋል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት-ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 26, 2013)።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶች ወቅታዊ ሁኔታ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሠረት አራት የባልደራስ አባላት ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) አባላትን ባለፈው ሳምንት ለመጪው ምርጫ ዕጩ አድርጎ መዝግቧል (አዲስ አበባ ባልደራስ፣ ግንቦት 26, 2013; የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 27, 2013፤ ኢፒኦ ሳምንታዊ:- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013 ይመልከቱ)። ይህንን ውሳኔ ለማስፈፀም ምርጫ ቦርድ 1.3 ሚሊዮን የምርጫ ወረቀቶችን አጥፍቷል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 27, 2013)። ውሳኔው ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምርጫ በአራት የምርጫ ክልሎች ውስጥ 843 የምርጫ ጣቢያዎችን እና በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ 14 የምርጫ ክልሎችን ነክቷል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 27, 2013)።
በተጨማሪም ምርጫ ቦርድ በአምስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 37 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች እንደማይካሄድ አስታውቋል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)። ከ37ቱ የምርጫ ክልሎች በ26ቱ ውስጥ ምርጫው እንዳይካሄድ የደህንነት ጉዳይ እንደዋና ምክንያት ተጠቅሷል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)። እነዚህ 26 የምርጫ ክልሎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ የሚገኙ አራት የምርጫ ክልሎችን፣ በአማራ ክልል ያሉ ስምንት የምርጫ ክልሎችን፣ እና በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በእያንዳንዳቸው ሰባት የምርጫ ክልሎች ናቸው (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)።
ሁለት ሳምንት ብቻ በቀረው ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ላይ ማስፈራራት እንደደረሰባቸው እየተዘገበ ነው፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን በይላም እና ዴንሳ ወረዳ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚደግፉ አርሶ አደሮች እንዳሉት የአከባቢው አስተዳዳሪዎች ለወቅቱ የመዝራት ወቅት አስፈላጊ የሆነውን ማዳበሪያ ማግኘት ከልክለዋቸዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 26, 2013)። በተጨማሪም የኢትዬጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአማራ ክልል ቻግኒ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰሬ የምርጫ ክልል ውስጥ የአከባቢው አስተዳደሮች በጣሉት ገደብ ምክኛት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አልቻለም (ኢዜማ፣ ግንቦት 21, 2013; ኢዜማ፣ ግንቦት 20, 2013)። ኢዜማ በቢሾፍቱ (ኦሮሚያ ክልል) እና በአጣዬ የደረሱትን የሁለት እጩዎቹን ግድያ ጨምሮ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ማስፈራሪያ እና ግጭት ገጥሞታል።