በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 11, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,591
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 7,984
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,301
በቁጥር (ከሰኔ 5, 2010 እስከ ሰኔ 11, 2013)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 8
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 42
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 12
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በኦሮምያ ክልል የፀጥታ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ባለፈው ሳምንት ሙሉ ውጊያ ተካሂዷል። ሚያዚያ 23, 2013 ላይ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሽብር ቡድን” ተብሎ የተሰየመው ኦነግ-ሸኔ ከውሳኔው ወዲህ በምዕራባዊና ደቡባዊ ኦሮሚያ ያለው ግጭት ጨምሯል፡፡ በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጉጂ፣ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ትልልቅ ውጊያዎች ነበሩ (ጠቅላይ ሚኒስትር ጽቤት፣ ሚያዚያ 23, 2013)። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሰኔ 11, 2013 እንደገለጸው ባለፉት ሁለት ወራቶች አንድ የቡድኑን ከፍተኛ መሪ ጨምሮ 295 የኦነግ-ሸኔ አባላት በምዕራብ ኦሮሚያ ተገድለዋል (የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ሰኔ 11, 2013)።
ሰኔ 9, 2013 አካባቢ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በጅማ ዞን ሊሙ ቆሳ ወረዳ ላይ በኦነግ-ሸኔ ላይ በወሰደው እርምጃ 23 ታጣቂዎችን ገድሏል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ሰኔ 11, 2013)። ሰኔ 10, 2013 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የቡሌ ሆራ ደህንነት ጽ/ቤት ሃላፊ እና ሶስት የአካባቢው ታጣቂዎችን ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ መጋዳ ደን ልማት አካባቢ ገድለዋል (ኢሳት፣ ሰኔ 12, 2013)። በተጨማሪም ሰኔ 11, 2013 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ ቀበሌ ውስጥ ዘጠኝ የፌዴራል እና ኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞችን እና አንዲት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነች ሴትን በጥይት ገድለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 11, 2013)። ከዚህም በተጨማሪ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ማና ሲቡ አካባቢ ሁለት የአፍጋኒስታን ዜጋ የሆኑ የማዕድን ሠራተኞችን ማሰራቸውን ተናግረዋል (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ሰኔ 10, 2013)። የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የተባለውን ውድቅ አድርገዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 10, 2013)። ግንቦት መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ወለጋ መንዲ አካባቢ ኦነግ-ሸኔ በማዕድን ማውጣት ስራ ላይ የተሰማሩ ሶስት የቻይና ዜጎችን አፍነው ከወሰዱ በኻላ (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 7, 2013) ከሶስት ቀናት በኻላ ለቀዋቸዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 14, 2013 እስከ ግንቦት 20, 2013 ይመልከቱ)።
የመንግስት ሃይሎች የኦነግ-ሸኔ አባላት ናችሁ አልያም ቡድኑን ትደግፋላችሁ ተብለው የተጠረጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን መግደላቸውን ቀጥለዋል። ሰኔ 7, 2013 የኦሮሞ ክልል ልዩ ፖሊስ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ ውስጥ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነን ግለሰብ ተኩሰው ገድለዋል (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ሰኔ 10, 2013)። ከአንድ ሳምንት በፊት ግንቦት 29, 2013 ላይ አንድ ወጣት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ላሎ አሳቢ ቀበሌ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተተኩሶበት ተገድሏል (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ሰኔ 3, 2013)።
ባለፈው ሳምንት በቱሉ ጉሌድ (ምስራቅ ሀረርጌ፣ ኦሮሚያ) አከባቢዎች በሚገኙ የኦሮሞ እና የሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉ ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን 580 ቤተሰቦች ተፈናቅለው ያልታወቀ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሞተዋል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ ፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 7, 2013)። በአካባቢው ግጭት ሰኔ 1, 2013 ላይ እንደገና አገርሽቷል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 28, 2013 እስከ ሰኔ 4, 2013 ይመልከቱ)። የቱሉ ጉሌድ አካባቢ በጣም አጨቃጫቂ ሲሆን ቦታው የኔ ነው በሚሉ የኦሮሞ እና ሶማሌ ጎሳዎች መካከል በተደጋጋሚ ከፍተኛ ግጭት ይታያል።
በትግራይ ክልል በምዕራብ ትግራይ ዞን በወፍ አርግፍ እና ዳንሻ ከተሞች ሰኔ 5 እና 6, 2013 ላይ በሰልፎቹ ላይ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን እና በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ተቃውመው ሁለት ተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 5, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 6, 2014)። ስለሆነም ከሰኔ 2, 2013 እስከ 6, 2013 ድረስ ህወሓትን እ በኢትዮጵያ የውስጣዊ ጉዳዮች ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ በጠቅላላው አምስት ሰላማዊ ሰልፎች በምእራብ ትግራይ ዞን ተካሂደዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 28, 2013 እስከ ሰኔ 4, 2013 ይመልከቱ)። በ1980ዎቹ የሕወሃት አስተዳደር ወቅት ከምዕራብ ትግራይ ዞን የተገፉ 270 አማራዎች ምዕራብ ትግራይ በአማራ ክልል ኃይሎች ስር ከሆነ ጀምሮ በስደተኝነት ይኖሩበት ከነበረው ሱዳን ወደ ሁመራ ከተማ ተመልሰዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 8, 2013)። በሀይል የተወሰደው የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ገና በሕጋዊ መንገድ መፍትሄ መገኘት ያለበት ጉዳይ ሲሆን አስተዳደሩ በአዲሱ ተመራጭ የኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ዋነኛ አከራካሪ ጉዳይ ይሆናል። ባለው ግጭት ምክንያት በየትኛውም የትግራይ አካባቢ ምርጫ አይካሄድም።
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በአጣዬ እና አካባቢው ባህላዊ የእርቅ መርሃግብሮች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በአጣዬ እና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች የፀጥታ ጉዳይ የኦሮሞ ታጣቂዎች እና ከኦነግ ሸኔ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች እና የፌደራል ወታደሮች ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ሚያዚያ 10, 2013 በተቋቋመው የፌደራል ኮማንድ ፖስት ይመራል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 2, 2013 እስከ ሚያዚያ 8, 2013፤ ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 29, 2013)። ሰኔ 9, 2013 ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን በአርጡማ ፋርሲ ወረዳ ጭሬ አካባቢ ላይ ባህላዊ የእርቅ ተግባራት ተካሂደዋል። በእነዚህ ባህላዊ የማስታረቅ ሂደቶች ወቅት ከአርጡማ ፋርሲ፣ አንፆኪያ ጋምዛ፣ እና ማጀቴ የመጡ ሽማግሌዎች ተገኝተዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 9, 2013)። ተመሳሳይ ባህላዊ የዕርቅ ሂደቶች በደሴ ከተማ ደዋ ጨፌ ወረዳ ጠረፍ ቀበሌ ግንቦት 25, 2013 ላይ ተካሂደዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 21, 2013 እስከ ግንቦት 27, 2013 ይመልከቱ)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
በትግራይ ክልል ግጭቶች በክልሉ ማዕከላዊ፣ ደቡብ ምስራቃዊ፣ ምስራቃዊ፣ ሰሜን-ምዕራባዊ፣ እና ደቡባዊ ዞኖች አሁንም ድረስ የቀጠሉ ሲሆን የተራዕዶ ድርጅቶችን ስራ እያደናቀፉ ነው። የተራዕዶ ድርጅቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ወታደሮች ፍቃድ ቦታዎች ጋር እንዳይደርሱ መከልከላቸውን እና የተለያዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች እንደተያዙባቸው ገልፀዋል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሰኔ 10, 2013)። ምንም እንኳን የመንግሥት ባለሥልጣናት በመላ ክልሉ ለሰብአዊ ድርጅቶች ያልተገደበ ተደራሽነት እንዳለ ቢናገሩም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ግን በደቡብ ምስራቅ ትግራይ ዞን ዋጂራት ወረዳ የሚገኙ አከባቢዎች ከአንድ ወር በላይ ተደራሽ እንዳልተደረጉ አስታውቋል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሰኔ 10, 2013)።
አገር በቀል አጋሮች በአሁን ወቅት ያለው የግጭት አዝማሚያ “በእንቅስቃሴ ላይ ያለ” እና “የማይገመት” ሲሉ ገልጸውታል፣ ይህም ህወሃት የትጥቅ ስትራቴጂውን በአጋጣሚ ወደሚፈፀሙ ጥቃቶች መቀየሩን የበለጠ ያረጋግጣሉ፡፡ የታጠቁ ቡድኖች እርስ በእርስ ፍጥጫ ውስጥ በመግባታቸው እና የአከባቢው ህዝብ እንዲሰደድ በማስገደዱ የትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች የበለጠ አደገኛ ሆነዋል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ግንቦት 23, 2013)። ግጭቱ በገጠር አርሶ አደሮች ላይ የከፋ ሲሆን 2020 (እ.አ.አ.) አመት 90% ሰብል ውድሟል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 7, 2013)። ለተራእዶ ድርጅቶች ተደራሽነትን ለማሻሻል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ሰብአዊ ድርጅቶች በወታደራዊ ፍተሻዎች የሚያልፉበትን መንገድ የሚያቀሉ አዳዲስ አሰራሮችን ማፀደቁን አስታውቋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 12, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት – የቅድመ-ምርጫ ችግሮች ላይ የተነሱ ጥያቄዎች በድህረ-ምርጫ ወቅት
የ2013 አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርጫ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ረቡዕ ሰኔ 9 2013 አብቅቷል፡፡ ሰኔ 14, 2013 ከሚደረገው የድምጽ መስጠት ሂደት በፊት በነበሩት አራት ቀናት በምርጫ ህጉ መሰረት “የጥሞና ጊዜ” ሲሆን የምርጫ ቅስቀሳ ክልክል ነው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ፣ ሰኔ 9, 2013)።
የቅስቀሳ ተግባራት ከማቆማቸው በፊት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቅድመ-ምርጫው ወቅት የተከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን የዘረዘሩባቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሰጥተዋል። እነዚህ ክሶች ድምጽ መሰጠት ከመጀመሩ በፊት መፍትሄ ባለማግኘታቸው ከድህረ-ምርጫ በኋላ ለሚነሱ ክርክሮች መሠረት ሊሆኑ ይችላሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥያቄያቸውን ለተመረጡት የምርጫ አለመግባባት መፍቻ ተቋማት በምርጫ ደንቡ መሠረት ማስገባታቸው ግልጽ አይደለም።
ሰኔ 5, 2013 ላይ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲ ግንባር (ዎሕዴግ) እና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) በመራጮች ምዝገባ ወቅት በወላይታ ዞን በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የአከባቢው ባለሥልጣናት የምርጫ አስፈጻሚ ሆነው እየሠሩ እንደነበር ተናግረዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 5, 2013)። በአቤቱታው መሰረት እነዚህ የአካባቢ ባለሥልጣናት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች የምዝገባ ካርድ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። በተጨማሪም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የአካባቢው ባለሥልጣናት በወላይታ ዞን በማይኖሩ ሰዎች ስም የተሞሉ የምዝገባ ካርዶች ይዘዋል ብለዋል። የአካባቢው ባለሥልጣናት የአከባቢውን አርሶ አደሮች ለገዥው ፓርቲ ድምጽ እንዲሰጡ እንዳስፈራሩ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎችን አስረዋል በሚል ወቅሰዋቸዋል፡፡ የተቃዋሚ መሪዎች እነዚህ ችግሮች ከምርጫው በፊት መፍትሄ ካላገኙ በምርጫው ላለመሳተፍ እንደሚገደዱ ገልፀዋል።
በቀጣዮ ቀን አምስት ፓርቲዎች – ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ እና እናት ፓርቲ – የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጡ ሲሆን በእጩዎች ምዝገባ፣ በመራጮች ምዝገባ፣ እና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የነበሩ ችግሮችን ዘርዝረዋል (ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ ሰኔ 6, 2013)። በእነዚህ ፓርቲዎች መሠረት እጩዎች በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ከተጠየቁት ሰነዶች ተጨማሪ እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል። በመራጮች ምዝገባ ወቅት የምርጫ ጣቢያዎች በመጀመሪያ የምዝገባ ወቅት እና የመራጭ ቁጥር ከመሙላት ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ጣቢያዎች ከተከፈቱ በኻላ መዘግየት አሳይተዋል። የጋራ መግለጫው አብዛኛዎቹ መራጮች በተለይም በተወሰኑ የተቃዋሚ ድጋፍ ባለባቸው አካባቢዎች አለመመዝገባቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም ፓርቲዎቹ ከአዲስ አበባ በስተቀር በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ሊባል በሚቻል መልኩ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አግባብ ያልሆኑ ገደቦች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል። ወከባ፣ ድብደባ፣ ማስፈራሪያ፣ እስራት፣ አልፎ ተርፎም አንዳንድ እጩዎች ላይ ግድያ እንደደረሰባቸውም ስሞታቸውን አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ሰኔ 9, 2013 ላይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በእጩዎች ምዝገባ፣ መራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ ዝርዝርን ማጣራት፣ እና የምርጫ ዘመቻዎች ወቅት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ – ኢዜማ፣ ሰኔ 9, 2013)። አብዛኛዎቹ የኢዜማ ፓርቲ ተግዳሮቶች እና በእጩዎች ምዝገባ፣ መራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ ዝርዝርን ማጣራት፣ እና የምርጫ ዘመቻዎች ወቅት ያጋጠሙ ዝርዝር ችግሮች ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቀሷቸው ችግርች ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ የኢዜማ ባለሥልጣናትም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ግለሰቦች የመራጭ ምዝገባ እንዳካሄዱ ማረጋገጥ የቻሉባቸውን ክስተቶች በዝርዝር ገልጸዋል። ፓርቲው ምርጫ ቦርድ እነዚህን ችግሮች መፍታት አልያም ለችግሮቹ መልስ መስጠት ካልቻለ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ እንደሚገደድ አስረድቷል ፡፡
ከ673 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ከ71 በስተቀር ምርጫው በእላው ኢትዮጵያ ሰኔ 14, 2013 ላይ ተካሂዷል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 15, 2013; ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ , 22 May 2021; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎችን ይመልከቱ)። በቀሪዎቹ 71 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምርጫው ወደ ጷጉሜ 1, 2013 ተሸጋግሯል። በእነዚህ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ። እነዚህም የደህንነት ምክንያቶች፣ የሎጂስቲክ ችግሮች፣ እና በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ክርክሮች ናቸው። ከ71 ውስጥ 26 የምርጫ ክልሎች የደህንነት ስጋት ዋና ምክንያት ነው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)። በምርጫ ወረቀቶች ላይ የተከሰቱ ስህተቶች 27 የምርጫ ክልሎች በምርጫ ቀን በራቸውን እንዳይከፍቱ አስገድዷቸዋል። 16 የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ላይ ባጋጠሙ ችግሮች እና ከምርጫ ጋር የተዛያያዙ ክርክሮች ጋር ተያይዞ እየተደረጉ ባሉ ምርመራዎች ላይ ይገኛሉ። ከ71 የምርጫ ክልሎች በሁለቱ ውስጥ ምርጫው በምርጫ ካርድ እጥረት ምክንያት ተቋርጧል፡፡
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የመተከል፣ ሺናሻ፣ ካማሽ፣ ዳሊት፣ አሶሳ ሁሃ፣ እና አሶሳ መንገሌ ምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫው አልተካሄደም። በአሶሳ ሁሃ እና አሶሳ መንጌሌ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ምርጫው በምርጫው እለት በምርጫ ካርዶች እጥረት ምክንያት ተስተጏጉሏል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 15, 2021; ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2013)። በአራት የምርጫ ክልሎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ አልተከናወነም (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)።
በኦሮሚያ ክልል ምርጫው በ7 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በፀጥታ ምክንያቶች አልተካሄደም። እነዚህ የምርጫ ክልሎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ እና ሰኞ ገበያ የምርጫ ክልሎችን፤ በምስራቅ ወለጋ ዞን አያና እና ገሊሌ የምርጫ ክልሎች፤ እና በሆሮ ጉዱሩ ዞን አሊቦ፣ ጊዳ፣ እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልሎች ናቸው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)። በተጨማሪም በምርጫው እለት ኦሮሚያ ውስጥ በምዕራብ ሸዋ ዞን የምርጫው ሂደት በደህንነት ችግሮች ምክኛት ተቋርጧል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 15, 2013; ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2013; የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 15, 2013)።
በአማራ ክልል ምርጫው በስምንት የምርጫ ክልሎች ከፀጥታ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት አልተካሄደም፡፡ እነዚህ የምርጫ ክልሎች ማጆዬ (ማኮይ)፣ አርጎባ ልዩ ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ አርማጭሆ፣ እና አንኮበር የምርጫ ክልሎች ናቸው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምርጫው በአራት የምርጫ ክልሎች በፀጥታ ምክንያት አልተካሄደም። እነዚህ የምርጫ ክልሎች ዘልአለማዊ፣ ሱርማ ልዩ፣ ዲዚ ልዩ፣ ሙርሲ ልዩ፣ ማጀት፣ ሸኮ፣ እና የቴፒ የምርጫ ክልሎች ናቸው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)። በተጨማሪም በድምጽ መስጫ ወረቀቱ ህትመት ላይ በተፈጠረ ስህተት ምክንያት በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሚገኙ አሥር የምርጫ ክልሎች እና በአፋር ክልል በሚገኙ ሦስት የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫው ጷጉሜ 1, 2013 ይካሄዳል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 4, 2013)፡፡ ምንም እንኳን በሲዳማ እና ጋምቤላ ክልሎች በሎጅስቲክ ችግሮች ምክንያት ሰኔ 14, 2013 ላይ ቢቋረጡም ምርጫው በማግስቱ ሰኔ 15, 2013 ላይ ተካሂዷል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)።
ምርጫው በሶስት ክልሎች ማለትም በትግራይ ፣ በሶማሌ፣ እና በሐረሪ ሙሉ በሙሉ አልተካሄደም፡፡ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ላይ በምትገኘው ትግራይ ክልል በክልሉ እየተካሄደ ባለው እና ሕወሓት በሚሳተፍበት ግጭት ምክንያት ምርጫ ማካሄድ አልተቻለም። በሶማሌ እና ሐረሪ ክልሎች አጠቃላይ ምርጫው በመራጮች ምዝገባ ላይ በተፈጠሩ ክርክሮች፣ ችግሮች፣ እና በታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ በተፈጠሩ ስህተቶች ምክንያት ወደ ጷጉሜ 1, 2013 ተዘዋውሯል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሰኔ 4, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 24, 2013; የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ግንቦት 14, 2013)።