በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሰኔ 18, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,616
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 8,136
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,373
በቁጥር (ከሰኔ 12, 2013 እስከ ሰኔ 18, 2013)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 20
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 121
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 71
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው አጠቃላይ ምርጫ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ተካሂዷል፡፡ ብዙዎች የምርጫው ሂደት በሰፊ ግጭት የታጀበ ይሆናል ብለው ቢጠብቁም በምርጫ ቀን የነበሩ የምርጫ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ በሚገኙ የከተማ አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ ሲያልፍ በተወሰኑ የገጠር ከተሞች ደግሞ አልፎ አልፎ ግጭት ተስተውሏል፡፡ ግጭቶቹ በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እና የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን በሚያጓጉዙ ሰራተኞች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ይጨምራሉ፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ሰሜን ሸዋ፣ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ክስተቶች ተመዝግበዋል እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ አንድ ጥቃት ደርሷል።
በትግራይ ክልል ያለውን ግጭት ተከትሎ ድምጽ መስጠት ያልተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አጋር በሆኑት የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና ለህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ታማኝ በሆኑ ተዋጊዎች መካከል ግጭቶች ተፋፍመዋል። ውጊያው የህወሃት ወታደሮች የክልሉን መዲና መቀሌን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አብቅቷል (ሬውተርስ፣ ሰኔ 21, 2013)።
በተጨማሪም ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልልን ለማረጋጋት የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል። በግብርና ሰፈራዎች ላይ ለረዥም ጊዜ የዘለቁ ጥቃቶችን ተከትሎ አማራ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት 16,531 ተፈናቃዮች ወደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወደ ዳንጉር፣ ድባቴ፣ ማንዱራ፣ ቡለን፣ እና ወንበራ ወረዳዎች እንደመለሷቸው አስታውቀዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 16, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 16, 2013)። ሆኖም ግን የተመለሱት ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት መኖሩን እና በመተከል ዞን አዲስ ያረፉበት ስፍራ ላይ ተጨማሪ ጥበቃ እንዲደረግላቸው በመጠቆም ያልተፈቱ ችግሮችን አሳይተዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2013)።
ወቅታዊ የትግራይ ግጭት ሁኔታ
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ሰሜን-ምዕራብ እና ደቡብ ዞኖች ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) መካከል የሚደረጉ የትጥቅ ግጭቶች ተጠናክረው ነበር። የግልፅ መረጃ አለመኖር በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የሞቱትን ግለሰቦች ቁጥር በትክክል ለመገመት አስቸጋሪ ቢያደርገውም ጉዳቱ ግን ከፍተኛ የነበረ ይመስላል። በእነዚህ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች በሰኔ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ወራት ውስጥ እየጨመሩ የመጡ ናቸው።
ተደራሽነትን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ ሰብዓዊ አቅርቦቶችን የሚያከናውኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየጊዜው ኬላዎችን ሲያልፉ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፣ የተወሰኑ የክልሉን አካባቢዎችም እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም። ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ኃይሎች በሰሜን-ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ውስጥ የአለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ቡድን ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረሳቸው ተገልጿል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሰኔ 17, 2013)፡፡ በተጨማሪም ሰኔ 17, 2013 በማእከላዊ ትግራይ ዞን በአቢ አዲ ወረዳ ሶስት የዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ (ኤምኤስኤፍ) ሰራተኞች የሆኑ ሁለት ኢትዮጵያውያን እና አንድ የስፔን ሀገር ዜጋ ተገድለዋል (ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ፣ ሰኔ 18, 2013)። ግድያውን የፈፀመው ያልተረጋገጠ ሲሆን ኤምኤስኤፍ በግድያው ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል (ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ፣ ሰኔ 30, 2013)። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለግድያው የሕወሃት አጋር የሆኑ ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርጏል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሰኔ 18, 2013; ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሰኔ 19, 2013)።
ሰኔ 15, 2013 ላይ የህወሃት ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰራዊት ጋር በምስራቅ ትግራይ ዞን አዲግራት ከተማ ውጊያ ካደረጉ በኻላ ቦታውን ለተወሰነ ግዜ ተቆጣጥረዋል፡፡ በውጊያዎቹ ወቅት የተከሰተው የሟቾች ቁጥር አልታወቀም (ቢቢሲ፣ ሰኔ 15, 2013)። መንግሥት ግን በምርጫ ወቅት ደህንነትን ለማረጋገጥ ወታደሮቹን እንዳስወጣ ገልጿል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 17, 2013)። በዚሁ እለት በደቡብ ምስራቅ ዞን ቶጎጋ ውስጥ በሚገኝ የገበያ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አውሮፕላኖች የአየር ድብደባ በማካሄድ በትንሹ 64 ሰዎች ሲገድሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ አቁስለዋል ቆስለዋል (ኤፒ ዜና፣ ሰኔ 17, 2013)። የኢትዮጵያ ሰራዊት ጥቃቱ በግጭት ውስጥ የማይሳተፉ ግለሰቦችን ልብስ የለበሱ እና የሰማእታት ቀን ለማክበር የተሰበሰቡ የህወሃት ሀይሎች ላይ ያንነጣጠረ መሆኑን አሳውቋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 17, 2013)፤ የህክምና እና የአከባቢው ምንጮች ኝ ምንም አይነት የህወሃት ተዋጊዎች እንዳልነበሩ እና ተጎጂዎቹ በዋናነት ለገበያ የወጡ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መሆናቸውን አሳውቀዋል (ኤፒ ዜና፣ ሰኔ 17, 2013)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይሎች ጥቃቱ ወደደረሰበት ቦታ ለመድረስ የሞከረ አምቡላ ላይ ጥይት በመተኮሳቸው የህክምና ተደራሽነትን ለሰዓታት ተገቷል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ሰኔ 17, 2013)።
ሰኔ 16, 2013 ላይ ህወሃት እና አጋር ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰራዊት ጋር በምስራቅ ትግራይ ዞን ውቅሮ ከባድ ተኩስ ልውውጥ አድርገዋል (ፍራንስ24፣ ሰኔ 16, 2013)። በተመሳሳይ ቀን አንድ አውሮፕላን ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ 25 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው አዲ ቃላ አካባቢ ተከስክሷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2013)። የህወሃት ሃይሎች አውሮፕላኑን እንደጣሉ ሲናገሩ የመንግስት ምንጮች ደግሞ አውሮፕላኑ በቴክኒክ ችግር መውደቁን ገልፀዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2013)። ሰኔ 16, 2013 ላይ የትግራይ ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ የሆነ እና የጊዜያዊ መንግስቱ አባል ወደ መቀሌ አየር ማረፊያ እየተጏዘ ባለበት ወቅት ታፍኖ ተወስዶ በህወሃት ሀይሎች ተገድሏል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሰኔ 18, 2013)። በፌደራል መንግስቱ የተዋቀረው የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት አስተዳደር ሰራተኞች እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ግንኙነት አላቸው ከተባሉ ግለሰቦች ውስጥ እስከአሁን ድረስ 38 የሚሆኑት በህወሃት በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ውስጥ ተገድለዋል (ኢቢሲ፣ ሰኔ 20, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት: ከምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶች እና የድህረ-ምረቃ ክርክሮች
ብዙዎች የኢትዮጵያን ግጭት የተቀላቀለባቸው ምርጫዎች ታሪክ እና ያለፉትን ሁለት አመታት የነበረውን ውጣ ውረድ ከግምት በማስገባት የ2013 ጠቅላላ ምርጫ ሲቃረብ ፍራቻ ነበራቸው። በ2012 እና 2013 በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የነበረው ሰፊ ሁከት፣ በአማራ ክልል የተከሰቱ የብሔር ግጭቶች፣ እና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚጠበቁ የድንበር ለውጦች ሁሉ ባለፈው ሳምንት በነበረው ድምጽ መስጫ ወቅት ወደ ከፍተኛ የአመፅ ስጋት አመላክተው ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫው ቀን በመላ ሀገሪቱ የተጠናከረ ግጭት በነበረበት ውስጥ የተካሄደ ቢሆንም በምርጫ ጣቢያዎች፣ መራጮች፣ ወይም ምርጫ አስፈፃሚዎች ላይ ላይ የተቃጡ ጥቃቶች ቁጥር አነስተኛ ነበር (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)፡፡ በማፈን፣ ማግለል፣ እና ቅድመ-ደህንነት ጥበቃ ግንባታዎች; የኢትዮጵያ መንግስት በምርጫ ቀን የተስፋፋ ሁከትና ብጥብጥን ማስቀረት ችሏል።
ሆኖም በምርጫ ቀን የተከሰቱ ሁከቶች ለኢትዮጵያ መንግስት ከፊት ለፊቱ ረጅም እና አስቸጋሪ ጉዞ እንዳለ የሚያመላክቱ በመሆናቸው ወሳኝ ተግዳሮቶች ይቀራሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ቡድን በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ኩነቶች ተደጋጋሚ ነበሩ፡፡ በምርጫው እለት ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ ያሉ ባለሥልጣናትን በማጥቃታቸው ሶስት ሰዎችን ለህልፈት ሲዳረጉ የሁለት ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደት ተስተጏጉሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2013)። በተመሳሳይ በዲጋ ነቀምት (ምስራቅ ወለጋ) በአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ በደረሰ ተመሳሳይ ጥቃት አንድ ሰው ሲሞት ሶስት ሰዎች ቆስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 19, 2013)። ሁለት የፌደራል ፖሊሶች በምዕራብ ሐረርጌ ሚኢሶ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲጓዙ ተገድለዋል (ኢሰመኮ፣ ሰኔ, 2013)። በምዕራብ አርሲ ዞን አንድ የምርጫ አስፈፃሚ በታጣቂዎች ተገድሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 19, 2013)። ከድምጽ መስጠት ሂደቱ የተወሰኑ ቀናት ቀደም ብሎ ባለፉት ሳምንታት ከፍተኛ ብጥብጥ በተስተዋለበት የምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ የቡሌ ሆራ ደህንነት ጽህፈት ቤት ሃላፊ እና ሶስት ታጣቂዎች በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ተገድለዋል (ኢሳት፣ ሰኔ 12, 2013)። እነዚህ ክስተቶች በምዕራባዊ እና ደቡባዊ የኦሮሚያ ገጠራማ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን ያመረጋጋት አዝማሚያ እና በቀጣዮቹ ወራት የክልሉ መንግሥት የሚያጋጥመውን ፈተና ያሳያሉ፡፡
ሆኖም ግን ባለፈው አመት ከፍተኛ የሆነ ሁከት፣ ግጭት፣ እና ጥቃት ያስተናገዱ የኦሮሚያ ከተሞች ከተሞች ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ አካሂደዋል። ከአምቦ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የድምፅ አሰጣጡ ቀን ምንም አይነት ችግር እንዳልነበር ያሳያሉ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 15, 2013)። ሌሎች ዋና ከተሞች – ሻሸመኔ፣ ነቀምት፣ ዝዋይ፣ እና አዳማ – በድምጽ አሰጣጡ ሂደት ወቅት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሆኑት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የመንግስትን ጭቆና በመጥቀስ ምርጫው ‘‘የህዝባችንን የዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እና ራስን ማስተዳደር ትግል ለሁለተኛ ግዜ መክዳት ነው’’ በማለት ከምርጫው በመውጣታቸው ነው (የኦፌኮ መግለጫ፣ ሰኔ 16, 2013)፡፡ ይህ ማለት በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ክልል የምርጫ ክልሎች የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች የተወዳደሩት ያለተቀናቃኝ ነበር፡፡
የምርጫ ቀን ችግር ላለመፈጠሩ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ። እነዚህም:- የወጣቶች ንቅናቄ በብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ በመከፈሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ሀላፊዎች እና ወጣቶች በስፋት መታሰራቸው፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የተጠናከረው የልዩ ኃይሎች የፀጥታ ጥበቃ ናቸው (ኢትዮጵያ ኢንሳይት፣ መጋቢት 29, 2013; አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሐምሌ 11, 2013)። በተለይም የፀጥታ ኃይሎች መበራከት የአከባቢውን የብልፅግና ባለሥልጣናት በየክልሎቻቸው ላይ ከፍተኛ ሀይል እንዲኖራቸው እና የምርጫ ብጥብጥ እንዲቀንስ አድርጏል።
በአገሪቱ ባሉ “ተቃዋሚ የያዟቸው ዋና ቦታዎች” ላይ ተመሳሳይ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመላ ሀገሪቱ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው እና የምርጫ ጥሰቶች መፈፀማቸውን ቅሬታ አቅርበዋል (የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፣ ሰኔ 14, 2013; ኦነግ፣ ሰኔ 18, 2013; ቪኦኤ አማርኛ፣ ሰኔ 18, 2013; ኢዜማ፣ ሰኔ 17, 2013)። እስሮች የተለመዱ ነበሩ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሰኔ 16, 2013) እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ቁጥር ይገኙ ነበር (ኢሰመኮ፣ ሰኔ 18, 2013)። የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተሻለ የአካባቢ ነፃነት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ በነበሩባቸው የአማራ እና ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች አካባቢዎች ምርጫው በግጭት ፍራቻ ምክንያት እንዲዘዋወር ተደርጏል (ለበለጠ መረጃ ያለፈውን ሳምንት የኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሰኔ 5, 2013 እስከ ሰኔ 11, 2013 ይመልከቱ)።
የ2013 የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ለገዢው የብልጽግና ፓርቲ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድል እንደሚያመጣ ጥርጥር የለውም፡፡ ውጤቱ ይፋ በሚሆንበት ጊዜ ከምርጫ በኋላ ለሚከሰቱ ሁከቶች ምክንያቶች ከምርጫ ቀን ብጥብጥ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተገለሉባቸው አካባቢዎች ቅሬታዎች ሊበዙ ቢችሉም፣ በከባድ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቶች እና በሃላፊነት ላይ ላሉ ባለሥልጣናት ያለው ከፍተኛ ድጋፍ ለተቃዋሚዎች ያለውን በመካፈሉ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ግጭት የሚያስከትሉ መሰባብሰቦች የመከሰታቸው እድል እጅግ ዝቅተኛ ነው። ስለሆነም ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስሞታቸውን ለፍርድ ቤቶች አቅርበው የፍርድ ቤቶችን ውሳኔዎች በፀጋ እንደሚቀበሉ ይጠበቃል።
ከዚህ አዝማማያ የተለየ የሚሆነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተገዳዳሪ የሆነ የምርጫ ዘመቻ ያካሄዱባቸው ቦታዎች ናቸው። ለምሳሌ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች አካባቢ ጠንካራ የሆነ የምርጫ ዘመቻ አካሂዷል ስለሆነም በመንግስት ምስረታው ውስጥ የማይካተት ከሆነ የድህረ ምርጫ ሁከት የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ነው። ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሁከቶች ምርጫው ገና ባልተደረገባቸው የሶማሌ ክልል፣ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል፣ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝበ-ውሳኔ በሚካሄድበት የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሊከሰቱ ይችላሉ። ሕዝበ-ውሳኔው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኙ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ (ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ) 11ኛውን የኢትዮጵያ ክልል ይመስርቱ አልያም በክልሉ ውስጥ ይቀጥሉ የሚለው ላይ ውሳኔ ያሳልፋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶችን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ዘገባ ለማንበብ የአክሌድን ልዩ ዘገባ ይመልከቱ።