በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ሐምሌ 9, 2013)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,648
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 8,460
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,535
በቁጥር (ከሐምሌ 3, 2013 እስከ ሐምሌ 9, 2013) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። በተለይም በወቅታዊ የትግራይ ሁኔታ ላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ጥቃት በተመለከተ ዘገባዎች ቀስ ብለው በሚቀጥሉት ሳምንታት ሊወጡ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 17
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 86
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 46
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ታጣቂዎች ወደ ትግራይ ክልል ምዕራባዊ እና ደቡባዊ ግንባሮች በመግፋት ተከዜ ወንዝን በማቋረጥ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ጋር ከተዋጉ በኻላ ማይ ፀብሪ፣ አላማጣ፣ እና ኮረም ከተሞችን ተቆጣጥረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ድንበር በስተደቡብ በምትገኘው አዲ አርቃይ የተሰባሰቡ ሲሆን በሚቀጥሉት ሳምንቶች ከትህነግ ታጣቂዎች ጋር ለመዋጋት ተዘጋጅተዋል (ፍራንስ 24፣ ሐምሌ 8, 2013)።
በትግራይ ክልል ውጊያዎች እየተካሄዱ ባሉበት ወቅት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለጉዳት እና አድሎአዊ እስር ተጋልጠዋል። ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ በተፈጠረው የደቦ ጥቃት ሦስት የትግራይ ተወላጆች መገደላቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሐምሌ 8, 2013)። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ተጠርጥረው ታስረዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 10, 2013)።
ለወራት ከዘለቀ አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ ባለፈው ሳምንት በቡሌ ወረዳ በእማንጂ ቀበሌ ውስጥ አንድ አርሶ አደር የጉሙዝ ታጣቂዎች ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ከተገደለ በኋላ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ግጭት ተቀስቅሷል። የሟች ቤተሰቦች በቀጣዩ ቀን ወደ አርሶ አደሩ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ሲጓዙ ወደ ቅዳሜ ገበያ ከመጡ የጎሙዝ ብሔር ግለሰቦች ጋር ተጋጭተዋል፡፡ ቢያንስ 15 ሰዎች ሲሞቱ ዘጠኝ ሰዎች ቆስለዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 5, 2013; የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሐምሌ 9, 2013)። በምላሹም በመተከል ዞን ያለው ኮማንድ ፖስት በወረዳው ውስጥ የሰአት እላፊ ገደብ ጥሏል። ከዚሁ ግጭት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 5, 2013)። የተጠናከረ የፀጥታ ጥበቃ ቢኖርም ሐምሌ 8, 2013 ላይ በደንቤ ቀበሌ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች በማህረሰብ ውጊያ ተገድለዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በነበረው ብጥብጥ ወደ 4,000 ያህል ሰዎች በአገር ውስጥ መፈናቀላቸውን ገልጿል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሐምሌ 9, 2013)።
ሐምሌ 4, 2013 ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ አባላት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ዞን አሙሩ ወረዳ ኢላሞ አካባቢ ዘጠኝ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሲገድሉ አራት ሕፃናትን አፍነው ወስደዋል (ዋዜማ ራዲዮ፣ ሐምሌ 6, 2013)። ከሁለት ቀናት በኋላ ሐምሌ 6, 2013 ላይ ከኦነግ-ሸኔ እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በሆሮ ጉዱሩ ዞን በጃርደጋ ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የቀበሌ ታጣቂዎች ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈፅመዋል። በጥቃቱ ስምንት የቀበሌ ታጣቂዎች እና አንድ የአከባቢው አርሶ አደር ተገድለዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 7, 2013)። ስለሆነም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የግጭቱ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ቀጥሏል። ሐምሌ 9, 2013 ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ሳዮ ኖሌ ወረዳ ውስጥ ላሊስቱ ጌቾ ቀበሌ ከኦነግ-ሸኔ ጋር በመስራት የተጠረጠሩ አንድ ወጣት ልጅ እና አባት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መገደላቸው ተዘግቧል (ኦኤምኤን፣ ሐምሌ 11, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት: የትግራይ ግጭት
ምንም እንኳን መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈ እና በትግራይ ክልል አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ቢኖርም የትህነግ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት የክልሉን አከባቢዎች በሚቆጣጠሩ የክልል እና የፌደራል ሃይሎች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል። “እያንዳንዱን የትግራይ ካሬ ነፃ ለማውጣት” ቃል የገቡት የትህነግ ታጣቂዎች ወደደቡብ በማቅናት በአማራ ክልላዊ መንግስት ድንበር ላይ የሚገኘውን እና ለረጅም ጊዜ አከራካሪ ወደሆነው ግዛት እየተጏዙ ነው (ፍራንስ 24፣ ሐምሌ 8, 2013)። ቡድኑ የቀጠለው መስፋፋት መደበኛ እና ኢመደበኛ ኃይሎች በመላው ሀገሪቱ እንዲሰባሰቡ ምክንያት ሆኗል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ የትህነግ ታጣቂዎች ግዛታቸውን በማስፋፋት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ሃይሎች ጋር በራያ (ኮረም፣ አላማጣ፣ እና ባላ ከተሞች)፤ ዋግ ህምራ (ፃግብጂ፣ ዛታ፣ እና አበርገሌ ከተሞች)፤ እና ወልቃይት ጠገዴ እና ማይ ፀምሪ አካባቢዎች (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 6, 2013) ውስጥ ውጊያ አካሂደዋል። ትህነግ ለተከታታይ ቀናት ያደረገውን መስፋፋት ተከትሎ የፌደራል ወታደሮችን ለመደገፍ የተለያዩ የክልል መንግስታት ኃይል በማሰባሰብ ላይ ናቸው። ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሀረሪ፣ አማራ፣ እና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች፣ እና ድሬዳዋ ከተማ የትህነግን መስፋፋት ለመመከት የክልል ልዩ ሀይሎቻቸውን ልከዋል (ፍራንስ 24፣ ሐምሌ 8, 2013፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ሐምሌ 12, 2013፤ አልጀዚራ፣ ሐምሌ 12, 2013)።
ሐምሌ 5, 2013 ላይ የትህነግ ታጣቂዎች በደቡባዊ ትግራይ ዞን የምትገኘው የኮረም አከባቢን መቆጣጠራቸውን አሳወቁ (ሮይተርስ፣ ሐምሌ 5, 2013)። በቀጣዩ ቀን የትህነግ ታጣቂዎች ወደ ደቡብ በመጓዝ አላማጣ እና ዙሪያውን የሚገኙ መንደሮችን ተቆጣጠሩ (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 6, 2013)። በራያ በሚገኙ የመንግስት ኃይሎች ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች ተፈፅመዋል (የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፤ ሐምሌ 7, 2013)። ሐምሌ 6, 2013 ላይ የትህነግ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አማራ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ከተዋጉ በኋላ በሰሜን ምዕራባዊ ትግራይ ማይ ፀምሪ ከተማን ተቆጣጥረዋል።
የትህነግ ቦታዎችን መያዝ በአማራ ክልል ውስጥ የሽብር ስሜት ቀስቅሷል። በግጭቱ መጀመሪያ የትህነግ ሃላፊዎችን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ የፌዴራል መንግስቱ በሾማቸው የጊዜያዊ መንግስት ሃላፊዎች ሲያስተዳድራቸው ከቆዩ ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በተለየ በአሁኑ ሰአት ውጊያ እየተካሄደ ያለው በአማራ ክልል መንግስት እየተዳደሩ በቆዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ነው (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከግንቦት 28, 2013 እስከ ሰኔ 4, 2013 ይመልከቱ)። በምላሹም የአማራ ክልል መንግስት ከትግራይ ክልል በስተደቡብ ድንበር ባሉ አካባቢዎች መደበኛ እና ኢመደበኛ ሃይሎችን በማሰባሰብ የክልል ሃይሎች የመከላከል ብቻ ሳይሆን የማጥቃት እርምጃዎችን እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል (አፍሪካ ኒውስ፣ ሐምሌ 7, 2013)።
ሐምሌ 8, 2013 ላይ የአማራ ክልል ሃይሎች የትህነግ ታጣቂዎች በሳምንቱ መጀመሪያ የያዙትን ግዛት መቆጣጠራቸውን አሳወቁ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ሐምሌ 10, 2013፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 9, 2013)። ይህ ገና ያልተረጋገጠ ሲሆን ውጊያ አሁንም ቀጥሏል።
ግጭቱ ከፍተኛ የሆነ የብሔር መልክ ያለው ስለሆነ በሁለቱም ወገን ያሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የግጭቱ ተጠቂ ሆነዋል። ሐምሌ 6, 2013 ላይ የትህነግ ታጣቂዎች የኮረም ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ 18 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል (ቦርከና፣ ሐምሌ 6, 2013)። እንዲሁም ሐምሌ 7, 2013 አካባቢ በሰሜን ምዕራባዊ ትግራይ ዞን ማይ አይኒ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ቢያንስ አንድ ኤርትራዊ ስደተኛ በተኩስ ልውውጥ ወቅት ተገድሏል። ምንጮች ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋል፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ዝርፊያ፣ እና አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ የታመኑ ዘገባዎችን ማሳየታቸውን ገልፀዋል (የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ፣ ሰኔ 28, 2013)። በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የኤርትራ ስደተኞች ተገድለዋል አልያም በእስር ላይ ይገኛሉ (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሐምሌ 14, 2013፤ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ መግለጫ፣ ሐምሌ 6, 2013)።
ሐምሌ 6, 2013 ላይ በአማራ ክልል መንግስት እየተዳደረ በሚገኘው የምዕራብ ትግራይ ዞን ሁመራ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የቀጠለውን አለመረጋጋት በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 7, 2013)። በተጨማሪም 323 የትግራይ ተወላጆች ትህነግን በመደገፍ ተጠርጥረው በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 10, 2013)። ሐምሌ 4 , 2013 ላይ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ወረታ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በደቦ ተገድለዋል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሐምሌ 8, 2013)። ጥቃቱ የደረሰው ትህነግ ከፎገራ አካባቢ የሆኑ ከመንግስት ጋር የተያያዙ ታጣቂዎችን በፍየል ውሃ አካባቢ መግደሉን ተከትሎ ነው (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ሐምሌ 8, 2013)። በመጪዎቹ ሳምንታት ከፍተኛ የሆነ የብሔር መልክ ባለው ግጭት ውስጥ በሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች መሃል ያሉ በግጭት ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው የሚቀጥል ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአለም ምግብ ፕሮግራም የተላከ 1,000 ሜትሪክ ቶን ምግብ በአፋር ክልል በኩል መቀሌ ገብቷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 5, 2013)። ተጨማሪ የምግብ እና የእርዳታ ቁሳቁሶች በአውሮፕላን እንዲደርሱ ተደርጏል። በሳምንቱ መጨረሻ በአፋር ክልል በኩል ወደ መቀሌ በሚወስደው መንገድ ላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎችን የጫኑ 60 ተሽከርካሪዎች የትህነግ ታጣቂዎች በመንገዱ አካባቢ ያሊ ቦታዎችን በመዝጋታቸው ዘግይቷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 10, 2013፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 9, 2013)። ሐምሌ 10, 2013 ላይ የአፋር ክልል መንግስት እንዳስታወቀው ትህነግ በያሎ ወረዳ በፋንቲ ራስ ዞን 4 በአርብቶ አደሮች ካምፕ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል (የአፋር ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ሐምሌ 10, 2013)። እስካሁን የሟቾች ቁጥር ላይ ዘገባ የለም።3ይህ ኩነት በመጪው ሳምንት የአክሌድ መረጃ እና የኢፒኦ ሳምንታዊ ዘገባ ውስጥ የሚካተት ይሆናል።