በቁጥር (ከመጋቢት 24, 20101እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ የተከሰቱ የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶችን፣ በዚህ ምክንያት የደረሱ የሞት ጉዳቶች፣ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ነው። እስከ ሐምሌ 23, 2013)2አክሌድ እስከ ነሀሴ መጨረሻ ድረስ የተመዘገቡ ኩነቶችን ህትመት ይገታል። ከሐምሌ 24, 2013 እስከ ነሀሴ 28, 2013 ያሉ መረጃዎች የኩነቶች ህትመት ጷጉሜ 1, 2013 ላይ በድጋሚ ሲጀምር የሚለቀቁ ይሆናል። በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እንዲሁም ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሁሉንም የአክሌድ መረጃዎች ማውረድ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,735
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 9,294
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 4,944
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በአፋር ክልል በፋንቲ ራሱ-ዞን 4፣ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ እና በምዕራብ ትግራይ ዞን ውጊያ ቀጥሏል። ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሀይሎች ትህነግን በመግፋት ቡድኑ ወደ አፋር ክልል የሚያደርገውን ግስጋሴ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ማቀዝቀዝ የቻሉ ይመስላል።
በአፋር ክልል የትህነግን እንቅስቃሴ ማቀዝቀዝ የተቻለ ቢሆንም በአማራ ክልል ሰሜናዊ አካባቢዎች የሚዋጉ የትህነግ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላን ጨምሮ አዳዲስ ቦታዎችን መያዝ ችለዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የትህነግ ሃይሎች ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ሲገቡ ከመንግሥት ኃይሎች መክላክል አልገጠማቸውም (ሮይተርስ፣ ሐምሌ 30, 2013)። በተጨማሪም ወልዲያ ከተማ፣ ራያ ቆቦ አካባቢ፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ እና ሀብሮ ወረዳ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ውጊያዎች ተመዝግበዋል። በተጨማሪም በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በአዲ አርቃይ እና ማይ ፀብሪ በመንግስት ሃይሎች እና በትህነግ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተመዝግበዋል። በእነዚህ ግጭቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር አይታወቅም።
በወልዲያ ከተማ ያሉ ወጣቶች ለከፍተኛ የከተማ ውጊያ እየተዘጋጁ ይመስላል። እራሳቸውን በመደርደር የትህነግን ከፍተኛ ጥቃቶች ለመከላከል ችለዋል። በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ከባድ ድብደባ ተመዝግቧል (የወልድያ ከተማ ኮሙኒኬሽን፣ ነሃሴ 3, 2013)።
ሐምሌ 29, 2013 ላይ ትህነግ በፋንቲ ራሱ ዞን-4 በጥሩ ወረዳ ጋሊ ኩማ ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች የሰፈራ ቦታን በጥይት ደብድቧል። በዚህ ጥቃት ምክንያት 107 ሕፃናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ተፈናቃዮች መገደላቸው ይገመታል (ዩኒሴፍ፣ ነሃሴ 3, 2013፤ ኢሳት፣ ሐምሌ 30, 2013)። በጥቃቱ ወቅት ወደ 30,000 የሚጠጉ የአፋር ተፈናቃዮች በጋሊኩማ አካባቢ ሰፍረው እንደነበር ይታመናል (ኢሳት፣ ሐምሌ 30, 2013)። በዚህ ድብደባ ሰብዓዊ ዕርዳታ ተቀምጦባቸው ሕንፃዎችም ወድመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት መንግስት የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል እና ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሆላንድን ለሦስት ወራት አግዷል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሐምሌ 28, 2013)። መንግስት እነዚህን ድርጅቶች የሐሰት መረጃን በማሰራጨት እና ያልተፈቀደ የውጭ አገር ዜጎችን በመቅጠር ከሷል። ከዚህ ባለፈም መንግስት ኤምኤስኤፍ ሆላንድ ያልተፈቀደ የሳተላይት መገናኛ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል ብሏል። እነዚህ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ ተሳትፈዋል። ሶስት ሰራተኞቹ በክልሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ ኤምኤስኤፍ በሐምሌ 2013 መጨረሻ በትግራይ ውስጥ የእርዳታ አቅርቦቱን አቁሟል (ፍራንስ 24፣ ሰኔ 30, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የትግራይ ክልል ተደራሽነት ለሰብአዊ እርዳታ
በትግራይ ግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ለድርጊታቸው ትክክለኛነት ማሳያ ሰብአዊ ስጋቶችን ተጠቅመዋል። በግጭቱ ምክንያት የእርሻ ወቅት መስተጓጎሉን እና ገበሬዎች መሳሪያዎቻቸውን በዝርፊያ እና በጥቃት ማጣታቸውን ተከትሎ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አቅርቦቶች ወደ ክልሉ ካልደረሱ በሚቀጥሉት 12 ወራት ውስጥ 100,000 ሕፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊሰቃዩ እንደሚችሉ ያሳያል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ሐምሌ 29, 2013)። ከዓለም የተቆረጡ ማህበረሰቦች ነዋሪዎችን “እንደ ቅጠል መውደቃቸውን” ይገልፃል (ኤፒ፣ ሰኔ 23, 2013)።
ሰኔ 21, 2013 ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ አመፅ “የማይታገስ” ደረጃ ላይ ሲደርስ ሰብዓዊ ስጋቶችን በመጥቀስ የፌዴራል ወታደሮችን ከትግራይ ክልል ክፍሎች በፍጥነት አነሳ። መንግሥት በአፋር እና በምዕራብ ትግራይ ድንበሮች ላይ የመከላከል ቦታዎችን ጠብቆ ግጭትን በማስቆም ሰላማዊ የእርሻ ወቅት ለማድረግ ያስችላል ብሎ የገለፀውን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳለፈ (ሮይተርስ፣ ሰኔ 22, 2013)። በእርግጥም ነገሮች ለተወሰነ ጊዜ ተሻሻሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የፌዴራል ኃይሎች ከትግራይ ክልል ከወጡበት ጊዜ አንስቶ “በአብዛኛው የትግራይ ክፍል የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለ ነው” ሲል ዘግቧል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ሐምሌ 2, 2013)። በሰኔ የመጨረሻ ሳምንት 40 የዓለም የምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪናዎች በአፋር ክልል በኩል ትግራይ ደርሰዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ሐምሌ 3፣ 2013)። በተጨማሪም የምግብ እና የእርዳታ ቁሳቁሶች በአውሮፕላን ተልከዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ሐምሌ 12, 2013)። በሐምሌ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ትህነግ ሐምሌ 10, 2013 ላይ በአፋር ክልል ፋንቲ ራሱ-ዞን 4 በያሎ ወረዳ በፈፀመው ጥቃት እና የመሬት ቁጥጥር ምክንያት ከ200 በላይ የአለም ምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪናዎች በአፋር ክልል በሚገኘው ሰመራ እንዲቆዩ አድርጏል (ቢቢሲ፣ ሐምሌ 16, 2013)። የአለም ምግብ ፕሮግራም 10 መኪኖቹ ሐምሌ 11, 2013 ላይ ያልታወቀ ቡድን በአፋር ክልል ከሰመራ ከተማ በ115 ኪ.ሜ.(70 ማይልስ) ርቀት ላይ በሚገኘው የአውሲ-ዞን 1 መጠቃቱን ገልዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሐምሌ 16, 2013)።
በመሆኑም የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ እፎይታ ያስገኛል የሚለው ተስፋ ግጭቱ የትግራይ ክልል ድንበርን ተሻግሮ ወደ አጎራባች የአፋር እና አማራ ክልሎችን በማመሱ ብዙም ሳይቆይ ተሰናክሏል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የትህነግ ሃላፊዎች እነዚህ ግስጋሴዎች የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በመሆናቸው አስፈላጊ ናቸው ብለው መንግስትን እርዳታ እንዳያልፍ በመከልከል ይከሳሉ (ፍራንስ 24፣ ሐምሌ 30, 2013፤ ቢቢሲ፣ ሐምሌ 26, 2013)። መንግሥት እነዚህን ውንጀላዎች አስተባብሎ ይልቁንም ትህነግን መንገድ በመዝጋትና የተኩስ አቁሙን በመጣስ ግጭት በመቀስቀስ ከሷል።
ወደ ትግራይ ክልል የሚጓዙ የትራንስፖርት መስመሮች ለመቋረጣቸው ብዙ ቡድኖች ተጠያቂ እንደመሆናቸው በአንድ ቡድን ላይ ሃላፊነትን ማስቀመጥ ይህንን እጅግ የተወሳሰበ እና ተቀያያሪ የሆነ ግጭት ከመጠን በላይ ማቃለል ይሆናል። በተለያዩ የጦርነቱ ወገኖች ገፋፊነት የቀጠለው ግጭት፣ የመሠረተ ልማት ውድመት፣ ደካማ የግንኙነት አወቃቀሮች፣ ተጠራጣሪ እና ውጥረት ያለበት ሕዝብ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የተከሰቱ የውጭ ግንኙነት ስህተቶች “የከፋ ሁኔታ” አስከትለዋል።
የቀጠሉ ውጊያዎች
በመጀመሪያ የግጭቱ የመቀጠል ሁኔታ እና የዕለት ተዕለት የግዛት ለውጦች ለእርዳታ አድራሾች ለማለፍ አደገኛ የሆነ መገመት የሚያዳግት አካባቢ ፈጥሯል። ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ውጊያው በዋናነት እየተደረገ ያለው ከሦስት ወራት በፊት እንደነበረው በገጠር አካባቢዎች ሳይሆን በመንገዶች ላይ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ትህነግ ተጨማሪ ግዛቶችን ለመያዝ ሙከራ እያደረገ በመሆኑ ነው። የትህነግ ታጣቂዎች አፋር ክልል ውስጥ የሚገኘውን የፋንቲ-ራሱ ዞን 4 ያሎ ወረዳ ካጠቁ በኋላ የተከተለው ከፍተኛ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች የህይወት እና ንብረት የማጣት ስጋት እያለ ሰመራ (አፋር) ላይ እንዲቆዩ አስገድዷል (ቢቢሲ፣ ሐምሌ 16, 2013)። በደቡብ ወደ ወልዲያ እና ላሊበላ አካባቢዎች እየተስፋፋ ያለው ትህነግ ታጣቂዎቹ ከአማራ ክልል የአካባቢ ታጣቂዎች እና ሃይሎች ጋር በመዋጋታቸው ትግራይ እና አማራን የሚያገናኙ መንገዶችን ለማለፍ የማይቻሉ ሆነዋል።
ትህነግ እነዚህ ጥቃቶች በትግራይ ክልል ላይ ያለውን “የእርዳታ መተላለፍ አለመቻልን” ለመስበር መሆኑን ገልጿል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ሐምሌ 26, 2013፤ ፍራንስ 24፣ ሐምሌ 30, 2013)። የትህነግ ታጣቂዎች በስተምስራቅ ባደረሱት ጥቃት የኢትዮጵያ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ከጅቡቲ የሚያገናኘውን የባቡር እና የመንገድ መስመር መቆጣጠር ይፈልጋሉ። የጅቡቲ-አዲስ አበባ መንገድ የሰብአዊ አቅርቦቶች የሚደርሱበት ዋና መንገድ ነው። ይኸው መንገድ አዲስ አበባን ከጅቡቲ ዋና ወደብ ጋር ያገናኛል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሐምሌ 29, 2013)።
የግንኙነት ብልሽቶች
ምንም እንኳን የእርዳታ መኪኖች ከፌደራል መንግስቱ ድጋፍ እና ፈቃድ ሊኖራቸው ቢችልም ወደ ትግራይ መግባት ግን በመንገዱ ላይ በሚንቀሳቀሱ አጋር ሀይሎች ምክንያት የተወሳሰበ ነው።
አጥቂውን ትህነግ ለመመከት የፌዴራል ኃይሎች በተወሰነ ሁኔታ የመከላከል ቦታዎችን በማስጠበቅ ላይ ቢሆንም የአማራ እና የአፋር ክልሎች ትህግን ለመዋጋት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችንና የክልሉን ልዩ ሀይሎች አሰባስበዋል። እነዚህ ሀይሎች በፌዴራል ሠራዊት ሥር አይደሉም። ለክልል ባለስልጣናት ታማኝ፣ በብሔር የተመሰረቱ፣ እና በአጠቃላይ ያልዳበሩ እና በደንብ ያልሰለጠኑ ናቸው። በአንድ አዛዥ ስር የማይወድቁ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች መኖራቸው ለመተላለፍ የሚደረጉ ሙከራዎችን ውስብስብ ከማድረግ ባለፈ ረጅም መዘግየቶችን አስከትለዋል። እንደተገለጸው ሐምሌ 11, 2013 ላይ ማንነቱ ባልታወቀ ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ለመድረስ የሚሞክሩ 10 የጭነት መኪናዎችን ከሰመራ ከተማ 115 ኪ.ሜ. (70 ማይል) ላይ በአፋር ክልል አውሲ-ዞን 1 ጥቃት አደርሶባቸዋል (ቢቢሲ፣ ሐምሌ, 16፣ 2013)።
የእርዳታ መኪኖች መሳሪያ እና ምግብ ለታጣቂዎች ያሳልፋሉ የሚለውን ጥርጣሬ ተከትሎ የክልል ልዩ ሃይሎች፣ የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ እና የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች የፍተሻ ቦታዎችን በማዘጋጀት መኪኖች እንዳያልፉ ይከለክላሉ። የአለም አቀፍ ድርጅቶች አለመታመን ከመንግስት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሚዲያዎች ዋና ተረክ ሲሆን ድርጅቶቹን “አሸባሪ ቡድኑን እንደገና ለማነቃቃት እና ለራሳቸው አጀንዳ ለመጠቀም” ትህነግን እንደሚደግፉ ይከሳሉ (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ነሃሴ 4, 2013)። ምንም እንኳን ከፌደራል መንግስት ፈቃድ ቢያገኙም የአለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ የጫኑ 29 መኪኖች ሰኔ 22, 2013 በአማራ ክልል እንዲቆሙ ከተደረገ በኋላ እንዲመለሱ ተገደዋል (ቢቢሲ፣ ሰኔ 22, 2013)። በሰኔ ወር አጋማሽ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሰባት የትግራይ መኪኖችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ሹፌሮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለአንድ ቀን አሳድሯል (ኤንዋይቲ፣ ሰኔ 22, 2013)።
እርዳታ የማድረስ ፍቃድን በሚመለከት ተመሳሳይ ችግሮች ትህነግ ትግራይን ከመቆጣጠሩም ቀደም ብሎም በግጭቱ ወቅት ያጋጥሙ ነበር። ምንም እንኳን ብልሽቶች ሕወሓት ከመያዙ በፊት በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት በሙሉ ተከስተዋል። ምንም እንኳን ጋዜጠኞች ትክክለኛ የመዘገብ ፍቃድ ቢኖራቸውም እና አስቀድመው እንዲገቡ የጠየቁ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሰራዊት የሰጠውን ወረቀት የኤርትራ ኃይሎች ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጉዞ በተደጋጋሚ ታግዶ ነበር (ሲኤንኤን፣ ግንቦት 5, 2013)።
በምዕራብ ትግራይ ዞን በሱዳን በኩል የሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ መንገዶችን ለመክፈት የቀረቡት ጥያቄዎች ውድቅ ተደርገዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የአማራ ክልል ትህነግን ሱዳን ውስጥ ቁጥራቸው ላልታወቀ ታጣቂዎች ስልጠናዎችን በመስጠት ከሰዋል (ኢሳት፣ ሐምሌ 27, 2013፤ ኢቢሲ፣ ግንቦት 6, 2013)። ይህ በሱዳን ውስጥ 30,000 የትግራይ ተወላጆች ለቡድኑ ለመዋጋት ዝግጁ ናቸው ባለው ትህነግም የታመነ ነው (ፋይናንሺያል ታይምስ፣ ሰኔ 28, 2013)። ዘገባዎች እንደሚያሳዪት በሱዳን በኩል መንገድ ለመክፈት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ትህነግ ከአማራ ልዪ ሃይል ጋር 11 ጊዜ በምዕራብ ትግራይ ተዋግቶ ያልተሳካ ሙከራ አድርጏል (ኢሳት፣ ሐምሌ 30, 2013)። ግንቦት 2013 ላይ መንግስት ከሱዳን በኩል በምዕራባዊ ድንበር ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት የሞከሩ 320 ያህል የትህነግ አባላትን መግደሉን አሳውቋል (ኢቢሲ፣ ግንቦት 6, 2013)።
የወደሙ መሰረተ ልማቶች
በትግራይ ክልል ግጭት ወቅት የመሠረተ ልማት ውድመትም ከፍተኛ ሥጋት ሆኖ ቆይቷል። በመላው ትግራይ ክልል የሚገኙ መንገዶች በጦርነቱ ተጎድተዋል። በአመቱ መጀመሪያ የትህነግ ሀይሎች አካባቢውን መቆጣጠር ባቃታቸው ወቅት የአክሱምን አውሮፕላን ማረፊያን አውድመውት ወጥተዋል (ሮይተርስ፣ ህዳር 13, 2013)። ትህነግ በጎንደር እና ባህር ዳር አይሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ሚሳኤሎች ተኩሷል። የፌዴራል ኃይሎች ከትግራይ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተከዜ ወንዝ ድልድይ (ምዕራባዊ ትግራይን ከሌላው የክልሉ ክፍል ጋር የሚያገናኘው) ባልታወቀ ቡድን ፈርሷል (ሮይተርስ፣ ሰኔ 24, 2013)።
በግጭቱ ምክንያት ሌሎች ወሳኝ መሠረተ ልማቶችም ተጎድተዋል። ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ የካቲት ማገባደጃ ድረስ የድንበር የለሽ ሀኪሞች ቡድን በትግራይ ክልል ከጎበኛቸው 106 የጤና ተቋማት ውስጥ 70 በመቶው ተዘርፈዋል ከ30 በመቶ በላይ ደግሞ ተጎድተዋል (ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን፣ መጋቢት 6, 2013)። በትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ሕንፃዎች፣ እና መጋዘኖች በግጭቱ ወቅት ተጎድተዋል። ለተፈጸመው አብዛኛው ዘረፋ ከትህነግ ጋር የተዋጉት የኤርትራ ወታደሮች ተጠያቂ ይደረጋሉ (ኤፒ፣ ግንቦት 20, 2013)።
የህዝብ ምላሽ
የሰኔ መጨረሻ ሳምንት ላይ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሙቀት ወረዳ ላይ ሰዎች ወደ ትግራይ ክልል የሚወስዱ መንገዶችን በመዝጋት 8 የአለም ምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪኖችን ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ ከልክለው ይልቁንም እርዳታው በክልሉ ላሉ ተፈናቃዮች እንዲከፋፈል ጠይቀዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ሐምሌ 1, 2013)።
እነዚህ ድርጊቶች ለዓመታት ሲገነቡ የቆዩ የንግግር ውጤቶች ናቸው – በብሔረሰቦች መካከል ግጭትን የሚያመቻቸው የኢትዮጵያ የብሔር–ፌደራሊዝም የአስተዳደር ሥርዓት ለዚህ ረድቷል። ትህነግ በመንግስት የታወጀውን የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ አሻፈረኝ በማለቱ እና በምትኩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ወደ ደቡብ ለመቀጠል በመምረጡ በግጭቶች ቀጥተኛ ተጠቂ የሆኑ ህዝቦች ዕርዳታ እንዲያልፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እየጨመረ ይመጣል። ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች 150,000 አማራዎች ከራያ ቆቦ አካባቢ እንዲሁም ከዋግ ኽምራ ዞን አበርገሌ ደግሞ 18,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል ተብሎ ይገመታል። በአፋር ክልል ከአባላ፣ ዳሎል፣ ጎልባ፣ እሬብቲ፣ መጋሌ፣ እና አፈዴሬ አካባቢዎች ከ70,000 በላይ አፋሮች በቅርቡ በተፈጠረው ግጭት ተፈናቅለዋል ተብሎ ይታሰባል (ኢሳት፣ ሐምሌ 27, 2013)።
ከላይ ባሉ ደረጃዎች የዲፕሎማሲ መክሸፍ
ዲፕሎማሲ እና ከትህነግ ጋር በተደረገው ጦርነት አውድ ውስጥ መካከለኛ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተደረጉ ሙከራዎች ሙሉ በሙሉ አልተሳኩም። ሐምሌ መጨረሻ ሀገሪቱን የጎበኘችው የዩኤስኤአይዲ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ሳትገናኝ ሀገሪቱን ለቃለች (ሮይተርስ፣ ሐምሌ 23, 2013)። በቅርቡ የሱዳን መንግሥት ያቀረበው የማደራደር ጥያቄ የሱዳን መንግስትን ገለልተኛ ባለመሆን በከሰሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት አላገኘም (ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት – ኢትዮጵያ፣ ሐምሌ 29, 2013)። በዚህ ምክንያት የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን አምባሳደር ወደ አገሩ ጠርቷል (ሮይተርስ፣ ነሃሴ 2, 2013)።
አብይ አህመድ የኤርትራን መኖር በመካዳቸው እና ከአንድ ወር በፊት “በትግራይ ረሀብ የለም” በማለታቸው ዓለም አቀፉ እራሱን ከአብይ አርቋል (ኤፒ፣ ግንቦት 29, 2013)። አብይ በበኩሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል” በማለት ወንጅለዋል (ሮይተርስ፣ ግንቦት 16, 2013)። መንግሥት የክልል ኃይሎቹን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመመደብ መብት እንዳለው አጥብቆ ሲከራከር አሜሪካ ደግሞ የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ አጥብቃ ጠይቃለች (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ግንቦት 9, 2013፤ ;የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን፣ ግንቦት 7, 2013)።
የሆነ ሆኖ ሁሉም አካላት የትግራይ ክልል በከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ እንዳለ እና ሰዎች በምግብ እና የመንግስት አገልግሎቶች እጦት እየተሰቃዩ መሆናቸውን አምነዋል። የጦርነት ጀብደኝነት እና ወታደራዊነትን መሰረት ያደረገ ስር የሰደደ ልዩነት ባለበት አካባቢ ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የግጭት ሰለባ መሆናቸውን ይቀጥላሉ።