ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ነሃሴ 28, 2013)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,938
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 11,317
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,429
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከነሃሴ 22, 2013 እስከ ነሃሴ 28, 2013)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 47
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 426
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 51
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከተለያዩ የክልል ኃይሎች ጋር በመተባበር ከትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ጋር በአምስት ግንባሮች ውጊያ ማድረግ ቀጥሏል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በአፋር ክልል የአፋር ክልል ልዩ ሃይል እና የአፋር ታጣቂዎች በቂልባቲ ዞን 2 በራሃሌ ወረዳ ከትህነግ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በአማራ ክልል ውጊያዎች በዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተመዝግበዋል። በእነዚህ ዞኖች የትህነግ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች፣ አማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ አማራ ታጣቂዎች፣ እና ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች (በአንዳንድ ዞኖች) ጋር ተዋግተዋል። በትግራይ ክልል በምዕራብ ትግራይ ዞን በወልቃይት አካባቢ በአንድ ወገን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አማራ ክልል ልዩ ሃይል በሌላ ደግሞ ትህነግ መካከል ግጭቶች ተመዝግበዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ቀደም ሲል በትህነግ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውስጥ የትህነግ ታጣቂዎች ስለፈፀሟቸው ጉዳቶች የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች ወጥተዋል። የትህነግ ታጣቂዎች በሰቆጣ፣ አዲ አርቃይ፣ ነፋስ መውጫ፣ ጋይንት፣ ሐራ፣ ጨጨሆ፣ እና ጋሳይ ውስጥ የግል ቤቶችን፣ ንግድ ድርጅቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ እና የመንግሥት ተቋማትን መዝረፋቸው እና ማውደማቸው ተዘግቧል (ኢሳት፣ ነሃሴ 24, 2013; ኢቢሲ፣ ነሃሴ 25, 2013; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 23, 2013ሀ; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 23, 2013ለ; ኤፒ ኒውስ፣ ነሃሴ 28, 2013)። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ በአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 700 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች በትህነግ ጉዳት ደርሶባቸዋል (የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ነሃሴ 26, 2013)። ግጭቱ ከትግራይ ክልል ከመውጣቱ በፊት ብዙ ድርጅቶች የመንግሥት ኃይሎችን ትምህርት ቤቶችን እና ሌሎች የሕዝብ ሕንፃዎችን እንደ ወታደራዊ ሥፍራዎች በመጠቀም፣ ጦርነቱ በቀጠለ ወቅት በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ሁሉም የትምህርት ቤት ሕንፃዎች ወደ 25% ገደማ እንዲወድሙ ወይም እንዲጎዱ በማድረግ ተከሰዋል (ኤችአርደብሊው፣ ግንቦት 20, 2013)። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት ምክንያት 1.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርት ገበታቸው ላይ አይገኙም (የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ነሃሴ 26, 2013)።
እንዲሁም ነሃሴ 28, 2013 እንደተዘገበው የትህነግ ታጣቂዎች በጋይንት የሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለማቀፍ የሕፃናት አስቸኳይ ፈንድ (ዩኒሴፍ) የምግብ ማከማቻ ማዕከልን ዘርፈዋል (ኢሳት፣ ነሃሴ 24, 2013).። በኢትዮጵያ የዩኤስኤድ ዳይሬክተር እንዳረጋገጡት የትህነግ ታጣቂዎች በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዩኤስኤድ ማከማቻዎችን ዘርፈዋል (ኢቢሲ፣ ነሃሴ 25, 2013)። ትህነግ የዘረፋ ክሶቹን ያስተባበለ ሲሆን አብዛኛዎቹ ዘረፋዎች ‘በዋናነት የተቀነባበሩት በአካባቢው ግለሰቦች እና ቡድኖች ነው’ በማለት ገለልተኛ ማጣራት እንዲካሄድ ጠይቋል (ጌታቸው ኬ ረዳ፣ ነሃሴ 26, 2013)።
በተጨማሪም የትህነግ ታጣቂዎች የጨጨሆ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያንን (በጨጨሆን) እና መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያንን (በጋሳይ፣ ደቡብ ጎንደር) በከባድ መሳሪያ ደብድበዋል። በጨጨሆ የቤተክርስቲያኑ የተወሰነ ክፍል መውደቅ አንድ ልጅን ገድሏል (ኤፒ ኒውስ፣ ነሃሴ 28, 2013)። እንዲሁም ባለፈው ሳምንት የትህነግ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ አስገድዶ መድፈር እና ግድያ መፈጸማቸው ተዘግቧል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 27, 2013፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 24, 2013፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 23, 2013)።
ባለፈው ሳምንት ትህነግ የፌደራል መንግስት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለ52 አገራት ልኳል (ትግራይ ቲቪ፣ ነሃሴ 29, 2013)። በደብዳቤው ትህነግ ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር እና ፌዴራል መንግሥት ነዳጅ እና አቅርቦቶች ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ጠይቋል።
በሰሜን ከተከሰተው ግጭት በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ነሐሴ 24, 2013 ላይ ከጋምቤላ ከተማ በ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ አምስት የአንድ ታጠቂ ቡድን አባላት አንድ ሰው በጥይት ገድለው ሁለት ተጨማሪ ሰዎችን አቁስለዋል። ተከትለው በተከሰቱ ውጊያዎች ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል (ኢሳት፣ ነሃሴ 25, 2013)። እንደ ጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ገለፃ ጥቃቱ የተፈጸመው ቀድሞ የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ በመባል በሚታወቀው የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ነው (ሪፖርተር፣ ነሃሴ 30, 2013)። ፓርቲው ሰኔ 2013 በተካሄደው ስድስተኛው የክልል ምርጫ መቀመጫ ማግኘት ባለመቻሉ ሁከት ለማነሳሳት እንደፈለገ ተዘግቧል። ምንም እንኳን ጋምቤላ ክልል ውስጥ ያሉ ግጭቶች አዲስ ባይሆኑም ክልሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰላማዊ ከሆኑ ክልሎች አንዱ ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም ግን ከሰኔው ምርጫ ጀምሮ አክሌድ ለሞት የዳረጉ በርካታ ጥቃቶችን መዝግቧል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሞት ቁጥር የተመዘገበባቸው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ነሐሴ 24 እና 25 2013 ላይ ከጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በካሚሺ ዞን ቤሎ ጂጋንፎይ ከተማ ላይ ጥቃት ፈፅመው ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይሎች ጋር መዋጋታቸው ተዘግቧል። ፖሊስ ታጣቂዎቹ በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ከ 50 በላይ ሰዎችን (አብዛኛዎቹ ሴቶች) ገድለዋል ብሏል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ነሃሴ 27, 2013፤ ኢሳት፣ ነሃሴ 28, 2013)። በተመሳሳይ ቀናት ቡድኑ በካማሺ ዞን በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ቁጥራቸው ያልታወቀ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ገድሏል (ኢሳት፣ ነሃሴ 28, 2013)። ነሃሴ 25, 2013 በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ እሪ በከንቱ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አምስት የቀበሌ ታጣቂዎችን በጥይት ገድለው ሌሎች ሁለት አቁስለዋል (ኢሳት፣ ነሃሴ 25, 2013)። የቀበሌ ታጣቂዎቹ ቀበሌያቸውን ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎችን ለመቀበል ወደ ቡለን ወረዳ እያቀኑ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ነሐሴ 25, 2013 ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ አባላት በምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሰው 40 ያህል ፖሊሶችን ሲያቆስሉ ቢያንስ ስድስት እስረኞችን ደግሞ አስለቅቀዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ነሃሴ 27, 2013)።
ከዚህ ባለፈ የአፋር እና የሶማሌ ታጣቂዎች በሁለቱ ክልሎች ድንበሮች ላይ የሚያደርጉት ውጊያ ቀጥሏል። ነሐሴ 23, 2013 ላይ የአፋር እና ሶማሌ የብሄር ታጣቂዎች በአዋሽ እና ጋርባ-ሲሴ መካከል በሚገኘው ጋውራካን መንደር ውስጥ ተዋግተዋል(ራዲዮ ቁሊሚዬ፣ ነሃሴ 23, 2013)። በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ያለው ግጭት የአፋር የብሄር ታጣቂዎች እና ከአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ጋር የተቆራኙ ታጣቂዎች በአፋር ክልል ጋቢ ዞን 3 ጋዳማይቱ ከተማ ውስጥ ያሉ ሶማሌ ነዋሪዎችን ማጥቃታቸውን ተከትሎ ሃምሌ 17, 2013 ላይ አገርሽቷል (ሮይተርስ፣ ሃምሌ 20, 2013፤ ብሉምበርግ፣ ሃምሌ 20, 2013፤ ሶማሌ ኮሚዩኒኬሽን፣ ሃምሌ 19, 2013)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትህነግ ጋር ግኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች መታሰራቸው ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት 284 ሰዎች በአዲስ አበባ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል። የፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ሰዎች የመኖሪያ እና ሥራ ቦታ ሲፈትሽ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን መያዙ ተዘግቧል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ነሃሴ 25, 2013)።
ሳምንታዊ ትኩረት: አዳዲስ የግጭት አዝማሚያዎች በኢትዪጵያ
ጥቅምት 2013 ላይ የተቀጣጠለው የትግራይ ግጭት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቷል። በሐምሌ 2013 የትህነግ ታጣቂዎች ወደደቡባዊ ክፍል በመስፋፋት በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል። በመላ አገሪቱ አከራካሪ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የነበሩ ግጭቶች ሲቀጥሉ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ አዳዲስ የግጭት አዝማሚያዎች ይታያሉ።
ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ አማራ፣ እና አፋር ክልሎች የነበሩት አብዛኛዎቹ ውጊያዎች በሰለጠኑ ወታደሮች እና ታጣቂዎች መካከል ነበሩ። ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ግን ግለሰቦች – ከመደበኛው የትእዛዝ እርከን ውጪ የሆኑ አርሶ አደሮች ወይም ቡድኖች – በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ከትህነግ ታጣቂዎች ጋር እየተዋጉ ነው። እነዚህ ግለሰቦች የትህነግን ታጣቂዎች ለመውጋት የተለያዩ መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ2013 በትግራይ ክልል እንደተከሰተው በአማራ ክልል ያሉ ልሂቃን የዘረፋ እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ግድያን በተለምዶ በጦርነት ውስጥ ተሳፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ወደ መደበኛ የትጥቅ ትግል እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየተጠቀሙባቸው ነው። በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ሁሉም ሰው የትህነግን ሀይሎች እንዲዋጋ እያበረታታ ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ግለሰቦቹ ከትህነግ ሃይሎች የሚይዙት ማንኛውንም መሳሪያ እንዲያስቀሩ ፈቅዷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 10, 2013፤ አዲስ ስታንዳርድ፣ ነሃሴ 12, 2013)።
ባለፈው ሳምንት የቅማንት ኃይሎች ከትህነግ ኃይሎች ጋር በጋራ ከተሳተፉባቸው የመጀመሪያ አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። ነሃሴ 26, 2013 ላይ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ሺንፋ የትህነግ ታጣቂዎች እና የቅማንት ታጣቂ ቡድን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ አማራ ክልል ሀይሎች፣ እና አማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል (ኢሳት፣ ነሃሴ 26, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 26, 2013)። የትህነግ እና ቅማንት ታጣቂዎች ከሱዳን ወደ ሺንፋ ለመግባት ሞክረዋል ተብሎ ተዘግቧል። ከ30 በላይ የትህነግ እና ቅማንት ታጣቂዎች በውጊያው ሞተዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 27, 2013)። የቅማንት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ውስጥ ለሚኖረው የቅማንት ብሄረሰብ የበለጠ የራስ ገዝ አስተዳደርን ለማግኘት እየታገሉ ነው።
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያለው ሌላ ታጣቂ ቡድን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክር በቤንሻንጉል/ጉሙዝ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አልመሃል አካባቢ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አማራ ክልል ሃይሎች ጋር ተዋግቷል (ኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ ነሃሴ 28, 2013፤ ኢሳት፣ ነሃሴ 28, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 28, 2013)። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የቡድኑ ዋና ዓላማ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 50 የታጣቂ ቡድኑን አባላት ገድሎ 70 ማቁሰሉን ገልጿል (የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሰራዊት፣ ነሃሴ 28, 2013)። ስለዚህ ከትህነግ ጋር የሚተባበሩ ቡድኖች የሚፈጽሙት ጥቃት አሁንም ሊቀጥል ይችላል።