ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
- አክሌድ ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 በነበረው ጊዜ 182 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 1844 የሟቾች ቁጥር መዝግቧል።
- ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 በነበረው ጊዜ በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ትልቁ የተዘገበ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል ሲሆን ቁጥሩም 816 ነበር። ኦሮሚያ ክልል በ388 የሟቾች ቁጥር ይከተላል።
- ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 152 ኩነቶች እና 1350 ሟቾች ተመዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 የነበረው ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ወቅት ከጥቅምት 2013 ወዲህ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት (የተደራጀ የፖለቲካ ግጭትን በተመለከተ) ነው።
- በአማራ እና አፋር ክልሎች የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) የተሳተፈባቸው ውጊያዎች ቁጥር ጨምሯል።
- ትህነግ አዳዲስ ቦታዎችን በመያዙ አልያም የፌደራል መንግስት ግዛቶችን መልሶ በመቆጣጠሩ ምክንያት ያሉ የቦታ ለውጦች በወሩ ውስጥ የተደጋገሙ ነበሩ።
- ሰላማዊ ሰልፎች የቀነሱ ሲሆን አብዛኛዎቹ የተመዘገቡ ሰልፎች መንግስትን የሚደግፉ እና ትህነግን ወይም ኦነግ-ሸኔን የሚቃወሙ ነበሩ።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት: የሰላም እድሎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ
ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ወቅት ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25,2013 የነበረው ጊዜ ከጥቅምት 2013 ወዲህ ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት (የተደራጀ የፖለቲካ ግጭትን በተመለከተ) ነበር። በኦሮሚያ ክልል እና ሌላ በትግራይ ክልል እስካሁንም ያሉት ሁለት ሁከቶች ከፍተኛውን የግጭት ቁጥር ቢወስዱም በወሩ ውስጥ የተለያዩ ግጭቶች ነበሩ (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
በወሩ መጀመሪያ ላይ ትህነግ በአማራና በአፋር ክልሎች ግዛት ማግኘቱን ቀጥሎ ነበር። የትህነግ ታጣቂዎች ጋሸና እና ላሊበላን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን ሰፊ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል። በተጨማሪም የትህነግ ታጣቂዎች በወሩ አጋማሽ አካባቢ በደቡብ ጎንደር የሚገኙ አካባቢዎችን ቢቆጣጠሩም የፌዴራል ወታደሮች እና የአማራ ክልል ሀይሎች አዲስ ጥቃት በመሰንዘራቸው በወሩ መጨረሻ አካባቢ ነፋስ መውጫ፣ መርሳ፣ እና ደብረዘቢጥ ከተማዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጥተዋል።
ከቦታ ለውጦች ጎን ለጎን ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25,2013 በነበረው ወቅት ከባድ ድብደባ የጨመረ ሲሆን የመንግስት ሃይሎችን ሆነ የትህነግ ታጣቂዎች ከባድ መሳሪያዎች ተጠቅመዋል። የትህነግ ሃይሎች ሃምሌ 29, 2013 ላይ በአፋር ክልል ጋሊኩማ በሚገኝ አንድ የተፈናቃዮች መጠለያ ማእከል ላይ ከባድ ድብደባ በመፈፀም ቢያንስ 150 ተፈናዋዮች ህይወታቸው አልፏል። በተመሳሳይ የትህነግ ሃይሎች በወልዲያ፣ ነፋስ ማወጫ፣ እና ደብረታቦር ከባድ ድብደባ አድርገዋል። ትህነግ በቁጥጥሩ ስር የነበሩ አካባቢዎችን መዝረፉ በሳምንቱ ሲዘገብ ነበር።
ኦነግ-ሸኔ በወሩ ውስጥ በርካታ ትናንሽ ከተማዎችን ተቆጣጥሬያለሁ ማለቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልልም በተመሳሳይ እንዲሁ የመሬት ለውጦች ተከስተዋል። ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በበርካታ የትራንስፖርት መስመሮች ላይም ይንቀሳቀስ ነበር። የታጣቂዎች እንቅስቃሴ የቡድኑ መሪ ጃል ማሮ (ኩምሳ ድሪባ) ከትህነግ ጋር ወታደራዊ ህብረት መፍጠራቸውን ካሳወቀበት ነሐሴ 5,2013 በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል (ቪኦኤ፣ ነሐሴ 5,2013) ።
ነሃሴ 12,2013 ላይ የኦነግ-ሸኔ ሀይሎች በኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ጊዳ ኪራሙ ውስጥ በአማራ ሰፈራዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 150 ሰዎችን ገድለዋል ተብሏል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ነሃሴ 20, 2013)። በኋላ የፌዴራል ኃይሎች በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ድንበር አቅራቢያ በጉጂ-ሞያሌ መንገድ ላይ ባደረጉት እንቅስቃሴ 40 የኦነግ -ሸኔ ታጣቂዎችን ገድለው ተጨማሪ 35 ማቁሰላቸውን ተናግረዋል (ቪኦኤ፣ ነሃሴ 22, 2013)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25,2013 በነበረው ጊዜ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ግጭት በድጋሚ ያገረሸ ሲሆን በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ነበሩ። በክልሉ ውስጥ ያለው የግጭት ተለዋዋጭነት ከዚህ በታች በዝርዝር ይብራራል።
ወርሃዊ ትኩረት: የሰላም እድሎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ
በኢትዮጵያ ውስጥ በትህነግ እና ማዕከላዊ መንግሥት መካከል ያለው ግጭት ዋና ቦታ ቢወስድም በመላ አገሪቱ ያሉ ትንንሽ ግጭቶች ምንም እንኳን መንግሥት ግጭቶችን በሰላም ፕሮግራሞች እና የፀጥታ ጥበቃን በመጨመር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም ተጠናክረዋል። ከእነዚህ ግጭቶች አንዱ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ነው። ሌሎች አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቡድኖች ተሳታፊ መሆናቸውን ተከትሎ ክርክር ባለባቸው መሬቶች ላይ ያሉ ግጭቶች ተባብሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ከያዙበት መጋቢት 24, 2010 ጀምሮ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ወደ 60 የሚጠጉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የደረሱ ጥቃቶች የነበሩ ሲሆን 640 ሰዎች ሞተዋል። በተጨማሪም ከ40 በላይ ውጊያዎች የነበሩ ሲሆን ወደ 970 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው የግጭት ተለዋዋጭነት በኢትዮጵያ ፒስ ኦብዘርቫቶሪ የክልሎች መገለጫ ገጽ ላይ የበለጠ ተብራርቷል (ኢፒኦ-ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል)።
በፀጥታና ሎጅስቲክ ጉዳዮች ምክንያት የሰኔ ወር አጠቃላይ ምርጫ በአብዛኛዎቹ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የምርጫ ክልሎች አልተከናወነም። ይልቁንም ምርጫው ገና በሚወሰን ቀን ይካሄዳል (ኦልአፍሪካ፣ ነሃሴ 18, 2013)። ግንቦት እና ሰኔ 2013 ላይ ግጭት ሲቀዘቅዝ የፌደራል መንግስት በቻግኒ (አማራ ክልል) የሚገኝ የተፈናቃዮች ማረፊያን ዘግቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰውች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወደሚገኝ መኖሪያቸው መለሰ (ቪኦኤ፣ ሰኔ 21, 2013)። ብዙ ከስደት ተመላሾች በክልሉ ወደሚገኝ አዲስ የማቋቋሚያ ማዕከል በመመለሳቸው ደስተኛ አልነበሩም። ቻግኒ ውስጥ መቆየት አልያም ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ወደሚገኝ መኖሪያቸው ሁከቱ ሲበርድ ለመመለስ ፈልገው ነበር። ከተመለሱ ጀምሮ ሁከት በክልሉ በድጋሚ አገርሽቷል። ምክንያቱም የግጭቱ መንስኤዎች – በአከባቢ ያሉም ሆነ በዙሪያው ከሚገኙ ክልሎች የሚመጡ – አልተቀረፉም።
ምንም እንኳን የጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖችን ያገናኛል የሚሉ አንዳንድ የመንግስት ክሶች ግልፅ ባይሆኑም እንዲሁም ያለውን ውስብስብ ጉዳይ ከልክ በላይ ቢያቃልልም በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ቡድኖች በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከሚከሰተው ግጭት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሏል (አዋሽ ፖስት፣ ነሃሴ 18, 2013)። ሆኖም ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ባለስልጣናት ከፍተኛ እርምጃ ወስደዋል እንዲሁም በወሩ ውስጥ በርካታ ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል።
ነሐሴ 4, 2013 ላይ ያልታወቁ ታጣቂዎች (አንዳንድ ምንጮች ጉሙዝ ናቸው ያሏቸው) ቤንሻንጉል/ጉሙዝ መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ጊዲጋ ቀበሌ ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚጓዝ አውቶቡስ ላይ ጥቃት አድርሰው ቢያንስ ስድስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሲገድሉ ሌሎች 14 ደግሞ አፍነው ወስደዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ነሃሴ 5, 2013)። ከቀናት በኋላ የመንግስት ሃይሎች በሱዳን ድንበር በኩል ወደ ጉባ ወረዳ ለመውረር የሞክሩ 12 የትህነግ አባላትን ጨምሮ ከ170 በላይ ያልታወቁ የትጥቅ ቡድን አባላት መግደላቸውን ተናግረዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 8, 2013)።
ከትህነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ተጨማሪ 32 ሰዎች በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ከሱዳን ወደ ክልሉ ለመግባት ሲሞክሩ ተይዘዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ነሃሴ 11, 2013)። በወሩ መጨረሻ ላይ የፀጥታ ኃይሎች ከባድ እርምጃ የወሰዱ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከፀረ-መንግስት ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ተጠርጥረው ታስረዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሃሴ 13, 2013)። በወሩ ውስጥ ታጣቂዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ግፊት ለማድረግ 19 ሴቶች ከሕፃናት ጋር በፌደራል ኮማንድ ፖስት መታሰራቸው ከተረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ስጋቱን ገልጿል (ኢሰመኮ፣ ነሃሴ 29, 2013)። 19 ሴቶች በኋላ ተለቀዋል (ኢሰመኮ፣ ነሃሴ 29, 2013)።
መንግስት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በመልሶ ማቋቋም ሥልጠና ለተሳተፉ በክልሉ ውስጥ ላሉ ታጣቂዎች መሬት እና የፖለቲካ ቦታዎችን በመስጠት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብዙ ጥረት አድርጓል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 28, 2013)። ግንቦት 2013 ላይ በቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ተወካዮች እና በክልሉ የመልሶ ማቋቋም ሥልጠና በሚወስዱ የትጥቅ ቡድን አባላት መካከል ስምምነት ተፈርሟል። እንደመንግስት ባለስልጣናት ገለፃ ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉት የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባላት ናቸው (ቢቢሲ አማርኛ፣ ግንቦት 11, 2013)። ሆኖም የጉሙዝ ነፃ አውጪ ግንባርን ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ቡድኖች በዚህ የሰላም ስምምነት እና ስልጠና ውስጥ አልተካተቱም። ስለሆነም እነዚህ ቡድኖች በክልሉ ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ማጥቃት እና ከመንግስት ኃይሎች ጋር መጋጨታቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም የመንግሥት ሥልጠናዎች የተፈለገውን ውጤት እያመጡ አይመስሉም። ኢትዮጵያ ኢንሳይት ያወጣው አንድ ዘገባ ነሃሴ 2013 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ከደረሱ ጥቃቶች ቢያንስ አንዱ የተፈጸመው በአከባቢው በተቋቋመው የፌዴራል ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት በተካሄደው የመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሮች ተመራቂዎች የተመራ መሆኑን አመልክቷል (Eኢትዮጵያ ኢንዳይደር፣ ነሃሴ 5, 2013)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ የብዙ የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቀን ሲቃረብ እየተባባሰ የመጣው የፀጥታ ሁኔታ ለአገሪቱም ሆነ ለክልሉ ከፍተኛ መዘዝ ይኖረዋል። ቤንሻንጉል/ጉሙዝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የሚሊዮኖችን ሕይወት መለወጥ የሚችለው እና የ5 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለበት ክልል ነው (ሮይተርስ፣ ነሃሴ 19, 2013)። በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ መገንባቱ የተፋሰስ ሃገራት የሆኑትን ሱዳን እና ግብፅን የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ ነው። በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን ያቀረበችውን ከትህነግ ጋር ላደራድራችሁ ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ሱዳን አምባሳደሯን ጠርታ ነበር (ሮይተርስ፣ ነሃሴ 2, 2013)። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የሱዳን ባለስልጣናት ውድቅ ያደረጉትን ሱዳን የታጣቂዎችን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ትደግፋለች የሚል ክስ ካቀረበ ቡሃላ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ሻክሯል (የሱዳን ጦር ኃይሎች፣ ነሃሴ 29, 2013)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መረጋጋት መኖት ወይም አለመኖሩ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር በሰሜን ከሚገኘው ዋና የግጭት ቀጠና ውጭ ምን ያህል እየሠራ እንደሆነ ቁልፍ አመላካች ሆኖ ይቀጥላል። በመላው ኢትዮጵያ መረጋጋት እስኪመለስ ድረስ ግን እንደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ያሉ የአገሪቱ ዳርቻዎች ውስጥ ያለው የከፋ የፀጥታ ሁኔታ የመቀጠል እድሉ ከፍተኛ ነው።