ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጳጉሜ 5, 2013)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 1,987
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 11,792
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,434
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከነሃሴ 29, 2013 እስከ ጳጉሜ 5, 2013)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 44
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 338
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሽኔ በጉጂ ፣ በሆሮ ጉዱሩ ፣ በምዕራብ ወለጋ ፣ በአርሲ እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ጋር ተዋግቷል። በተመሳሳይ ፣ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ኃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ እና ከተለያዩ የክልል ኃይሎች ጋር በትግራይ ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች መዋጋታቸውን ቀጥለዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)።
ኦነግ-ሸኔ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ነሃሴ 29 ቀን 2013 በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን ጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ወረዳ ተዋግተዋል (ኦ.ኤም.ኤን ፣ መስከረም 1, 2014)። በሚቀጥለው ቀንም ሁለቱ ቡድኖች ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ከተማ ተዋግተዋል (ኦ.ኤም.ኤን ፣ መስከረም 1, 2014)። በተመሳሳይ ቀን ሁለቱ ቡድኖች በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ውስጥም ተዋግተዋል። ጳጉሜ 2 ቀን 2013 ኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ በኢሬሳ ሊበን አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ አምስት መኪኖች ላይ ጥቃት አድርሰዋል (ኦ.ኤም.ኤን ፣ መስከረም 1, 2014)። ከሁለት ቀናት በኋላ በአርሲ ዞን ሙነሳ ወረዳ ሁለቱ ቡድኖች ተዋግተዋል። በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የተዘገበው የሟቾች ቁጥር በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። ኦነግ-ሸኔ ከህወሓት ጋር ያለውን ህብረት በነሐሴ 2013 ካወጀ በኃላ በኦሮሚያ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች ጨምሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ, ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት የአፋር ክልል በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በአፋር ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መሆኑን ገልጿል። ነገር ግን ትህነግ/ህወሃት ተዋጊዎቹ በፈቃደኝነት ከአፋር ክልል ወጥተው ወደ አማራ ክልል እንደዘመቱ ተናግሯል (ሮይተርስ ፣ ጳጉሜ 4, 2013)። ጳጉሜ 1 ቀን 2013 የኢትዮጵያ መከላከያ በአፋር ክልል በኡዋ እና በሂዳ ወረዳዎች ከትህነግ/ህወሃት ጋር ተዋግቶ ኡዋን ተቆጣጥሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአፋር ክልል አውራ እና ሂዳ ወረዳዎች በአየር ድብደባ የትህነግ/ህወሃት ወታደሮችን አጥቅቷል። በነጋታውም በአፋር ክልል በጉሊና ፣ በያሎ ፣ በአውራ እና በከልዋን ወረዳዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ከትህነግ/ህወሃት ወታደሮች ጋር ተዋግቶ እነዚህን ወረዳዎች ተቆጣጥሯል።
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ፍላቂት ገርገራ በትህነግ/ህወሃት እና በአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና በአማራ ሚሊሻዎች መካከል ከነሃሴ 29 እስከ ጳጉሜ 3 ድረሰ የዘለቀ ውግያ ተመዝግቧል። ነሃሴ 29 ቀን 2021 የኢትዮጵያ መከላከያ አካል የሆነው የሪፐብሊካን ጋርድ በድሬ ሮቃ በጮቤ ፣ በቀለልቲ ፣ በሰርቲ እና በቄላ ተራሮች ላይ ከትህነግ/ህወሃት ወታደሮች ጋር ተዋግቶል። የሪፐብሊካኑ ጋርድ መደበኛ ሃላፊነት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከማንኛውም ማስፈራሪያ እና ጥቃቶች መጠበቅ ነው። ሆኖም ከነሃሴ 2013 ጀምሮ የተለያዩ የመንግስት የፀጥታ አካላት በግጭቱ ውስጥ እየተሳትፉ ይገኛሉ። ባለፈው ሳምንት በሰሜን ወሎ ፣ በደቡብ ወሎ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች የኢትዮጵያ መከላከያ ከተለያዩ የክልል ኃይሎች ጋር በመተባበር ከትህነግ/ህወሃት ጋር መዋጋታቸው ተመዝግቧል።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ወር በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር ዞኖች ሲዋጉባቸው በነበሩበት ቦታ ውጊያ ቀንሷል። መንግሥት ከነሃሴ መጨረሻ (ሴፕቴምበር መጀመሪያ) ጀምሮ አንዳንድ ቦታዎችን መልሶ በመቆጣጠሩ በግጭቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት የሚያመላክቱ ሪፖርቶች መውጣት ጀምረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት የትህነግ/ህወሃት ወታደሮች በሰሜን ጎንደር ዞን ከዳባት አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጭና ከተማ ላይ ነሃሴ 26 እና 27 2013 ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 120 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል (ሮይተርስ ፣ ጳጉሜ 4, 2013)። ይህንን ክስ ትህነግ/ህወሃት ውድቅ በማድረግ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል (ጌታቸው ኬ. ረዳ ፣ ጳጉሜ 3፣ 2021)።
በተጨማሪም ፣ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 የትህነግ/ህወሃት ወታደሮች እና የቅማንት ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ፣ ከአማራ ክልል ሀይሎች እና ከአማራ ሚሊሻዎች ጋር በቲሃ መጋጨታቸውን ቀጥለዋል (ኢሳት ፣ ጳጉሜ 4, 2013) ። በማግስቱ በሺንፋ እና በጉባይ የተዋጉ ሲሆን ቁጥራቸው በውል ያልተረጋገጠ የሞት አደጋ ደርሷል። ሁለቱ ቡድኖቹ በሺንፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋጩት ነሃሴ 26 ቀን 2013 ነበር። መንግሥት የትህነግ/ህወሃት ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ከሱዳን መንቀሳቀሳቸውን ተናግሯል።
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በማይ ፀምሪ ወቀን አካባቢ በትህነግ/ህወሃት እና በአማራ ክልል ልዩ ሃይል ፣ በአማራ ሚሊሻ እና በፋኖ ሚሊሻዎች መካከል ውግያ ቀጥሏል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በጉሙዝ ታጠቂ ቡድን የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት ጳጉሜ 3 ቀን 2013 የጉሙዝ የታጠቀ ቡድን በመተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ አምስት የፀጥታ አካላትን (አራት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና አንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት) እና ቻይናዊ ዜጋን ጨምሮ ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ተኩሶ መግደሉ ተነግሯል። በዚህ ጥቃት ሁለት ተጨማሪ የፀጥታ አካላትም ቆስለዋል። ይህንን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ እና የክልሉ ልዩ ኃይሎች በጉሙዝ ታጠቂ ቡድን ላይ በፈፀሙት ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የጉሙዝ ታጣቂዎችን ተገድለዋል። ከሐምሌ ወር ጀምሮ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የሚደርሰው ግጭት ጨምሯል። በክልሉ ውስጥ ስላለው ግጭት ተጨማሪ ዝርዝሮችን ለማግኘት የኢፒኦ ወርሃዊ:- ሃምሌ 25, 2013 እስከ ነሃሴ 25, 2013 ዘገባን ይመልከቱ።
ሳምንታዊ ትኩረት – ሰብአዊ ቀውስ በሰሜን
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ አዲሱን ዓመት አክብራለች። በተለምዶ አዲስ ዓመት ለወደፊቱ ተስፋን ይዞ ያመጣል። ነገር ግን ብዙዎች በሰሜናዊው ግጭት ምክንያት እየተባባሰ ስለመጣው ሰብዓዊ ቀውስ እየተጨነቁ ይገኛሉ። በፌዴራል መንግሥት እና በትህነግ/ህወሃት መካከል የነበረው ግጭት እስከ ሰኔ 2021 ድረስ በትግራይ ክልል ውስጥ የተገደበ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ግን ግጭቱ ወደ ጎረቤት አፋር እና አማራ ክልሎች ተስፋፍቷል። በተጨማሪም በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች የትህነግ/ህወሃት ወታደሮች ከኦነግ-ሸኔ እና ከጉሙዝ የታጠቁ ቡድኖች ጎን ለጎን የመንግስት ኃይሎችን እየተዋጉ እንደሆነ ይነገራል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ሙሉ በሙሉ እየደረሰ አይደለም። በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (UNOCHA/ዩንኦሲኤችኤ) መሠረት ከሐምሌ 5 ቀን 2021 ጀምሮ “ከሚያስፈልገው ከ10 በመቶ በታች የሆነ የሰብአዊ እርዳታ ጭነት” ወደ ክልሉ ደርሷል (ኦሲኤችኤ ፣ ነሃሴ 27, 2013)። መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን ሲያሳውቅና ከትግራይ ክልል ሲወጣ ከሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ አርሶ አደሮች የዝናባማ ወቅቱን ለእርሻ እንዲጠቀሙ ነው። ሆኖም በዚህ የዝናብ ወቅት አርሶ አደሮች ማረስ መቻላቸው ወይም አለመቻላቸው አይታወቅም። በዩንኦሲኤችኤ መሠረት ከ 1.3 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ 320,000 ሄክታር የእርሻ መሬት ብቻ ታርሷል (ኦሲኤችኤ ፣ ነሃሴ 27, 2013)። በትግራይ ክልል 5.2 ሚሊዮን ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይገመታል (ኦሲኤችኤ ፣ ነሃሴ 27, 2013)። በመሆኑም ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለክልሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ መንግስት የሚደረገውን ጥረት እንዲያፋጥን የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ መስከረም 1, 2014)። መንግስት የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል በማለት የትህነግ/ህወሃት ኃይሎችን መውቀሱን ቀጥሏል (ኢቢሲ ፣ ጳጉሜ 1, 2013)።
በተጨማሪም ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመስፋፋቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በአማራ ክልል በወያኔ እና በመንግስት ወታደሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት አርሶ አደሮች መሬታቸውን በአግባቡ ማረስ እንዳልቻሉ ባለፈው ሳምንት የተለቀቁ የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በተጨማሪም ትህነግ/ህወሃት ወታደሮች በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የአርሶ አደሩን ከብቶች መግደላቸው ተነግሯል። እንደ መንግስት ገለጻ በግጭቱ ምክንያት ወደ 400,000 የሚጠጉ ሰዎች ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ተፈናቅለዋል። ሌሎች አራት ሚሊዮን ሰዎችም በሁለቱ ክልሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚሹ ተገልጿል (ኢቢሲ ፣ ጳጉሜ 1, 2013)። በሁለቱም ክልሎች በተፈጠረው ግጭት 1.7 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትና እንደሌላቸው ዩንኦሲኤችኤ ገልጿል (ኦሲኤችኤ ፣ ነሃሴ 27, 2013)። ባለፈው ሳምንት የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በአማራ ክልል ባለው ግጭት አካባቢዎች የተፈናቀሉ 40,000 ተፈናቃዮችን በሰሜን ጎንደር ዞን እያስተናገደ መሆኑን አሳውቋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ፣ ጳጉሜ 1, 2013)። በተመሳሳይ የደቡብ ወሎ ዞን ከአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ እና ከዋግ ሐመራ ዞኖች እና ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ 233,400 ተፈናቃዮችን እያስተናገደ ይገኛል (ኢሳት ፣ ጳጉሜ 1, 2013) ።
በትህነግ/ህወሃት እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት እየቀጠለ በሄደ ቁጥር፣ የተጎዱ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ስዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። በግጭቱ ምክንያት የተፋናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው መሬታቸውን እስካላረሱ ድረስ አሁንም በዚህ በአዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት ብዙዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይገመታል።