ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መስከረም 14, 2014)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,023
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,075
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,595
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመስከረም 8, 2014 እስከ መስከረም 14, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 10
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 98
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 15
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በፌዴራል ኃይሎች መካከል ውጊያዎች ነበሩ። በአማራ ክልል ምስራቅ በለሳ ወረዳ የአማራ ታጣቂዎች እና የትህነግ ሃይሎች ተዋግተዋል። በአማራ ክልል አዲስ ዘመን፣ ኢቢናት፣ እና አምደወርቅ ከተሞችን የሚያገናኘውን ድልድይ የትህነግ ታጣቂዎች ማውደማቸው ተዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መዘገባቸው ቀጥሏል። ምንም እንኳን የሞቱት ሰዎች እርግጠኛ ቁጥር እስከ አሁን ባይረጋገጥም የትህነግ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ ዙሪያ ከጷጉሜ 4, 2013 ጀምሮ ከ12 እስከ መቶዎች የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን መግደላቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች ባለፈው ሳምንት ወጥተዋል (ኤፒ፣ መስከረም 15, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ መስከረም 14, 2014)። በተጨማሪም የትህነግ ታጣቂዎች ቤቶችን፣ የመንግስት ተቋማትን፣ እና እርሻዎችን አውድመዋል እንዲሁም ዘርፈዋል።
ባለፈው ሳምንት ሁለት ሰልፎች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል። መስከረም 10, 2014 ላይ የኤርትራ ስደተኞች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጽ/ቤት ፊት ለፊት በመገኘት በትግራይ በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና ወሲባዊ ጥቃቶችን አውግዘው ትህነግ ላይ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 10, 2014)። ሰልፈኞቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጽ/ቤት የኤርትራ ስደተኞችን ከትግራይ ክልል ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንዲያዘዋውራቸው ጠይቀዋል። ሰልፉ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2013 ባለው ወቅት በትህነግ እና የኤርትራ መንግስት ሃይሎች በኤርትራ ስደተኞች ላይ የደረሰውን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እና ሌሎች ጥሰቶችን አስመልክቶ በቅርቡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የለቀቀውን ዘገባ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የተደረገ ነው (ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ መስከረም 6, 2014)።
መስከረም 11, 2014 ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች በአዲስ አበባ የሚገኙት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኒሴፍ ጽ/ቤቶች ፊት ለፊት አለም አቀፍ ድርጅቶች በግጭት ለተጎዱ ግለሰቦች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ሰልፈኞቹ ለትግራይ እርዳታ የሚያደርሱ ድርጅቶች ከሰሜን ወሎ ዞን ለተፈናቀሉ ግለሰቦችም እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል (ኢሳት፣ መስከረም 11, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሽኔ በኦሮሚያ ክልል ከክልሉ ኃይሎች ጋር መዋጋት ቀጥሏል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። መስከረም 12, 2014 አካባቢ በሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ፣ ደግም፣ እና ያያ ጉለሌ ወረዳዎች ውስጥ የኦነግ-ሽኔ ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር ግንኙነት ካላቸው ሃይሎች እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሀይሎች ጋር መጋጨታቸው ተዘግቧል (ኦኤምኤን፣ መስከረም 12, 2014)። እንዲሁም መስከረም 7 እና 8, 2014 ላይ በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ቦክዓ ቀበሌ ውስጥ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረው በሁለት ቀናት ውስጥ 11 ሰዎችን ገድለዋል (ኢሰመኮ፣ መስከረም 14, 2014)። ዘገባው ጥቃቱን የፈጸሙት እነማን እንደሆኑ ባይገልጽም በአካባቢው የኦነግ-ሽኔ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በመጨረሻም በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የካማሺ ዞን ለሳምንታት በቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር ቁጥጥር ሥር ከቆየ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባለፈው ሳምንት ወደ ዞኑ ገብቷል። እርምጃው የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር ኃይሎችን ወደ ኋላ መግፋት አለመቻላቸውን ተከትሎ የመጣ ነው። የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር በኦነግ-ሽኔ እንደሚረዳ (ቪኦኤ አማርኛ፣ መስከረም 14, 2014) እንዲሁም በአካባቢው ንብረት እንደሚዘርፍ እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን እንደሚያጠቃ ይነገራል።
ሳምንታዊ ትኩረት: ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና አዲስ መንግስት
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲ የሚመራ አዲስ መንግሥት መስከረም 24, 2014 ላይ ከመካሄዱ በፊት የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ (በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሰኔ 2013 ጀምሮ የዘገየው) ድምጽ መስጠት በሐረሪ፣ ሶማሌ፣ እንዲሁም ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ እና ሕዝቦች ክልሎች መስከረም 20, 2014 ላይ ይካሄዳል። በተጨማሪም ምርጫው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ በወሰኑባቸው አራት የምርጫ ክልሎችም ይካሄዳል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 13, 2014)። በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመጪው ምርጫ ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን ይህም ሁከት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። ሆኖም አሁንም የፀጥታ ችግሮች የምርጫ አስፈፃሚዎች እንዳይሠሩ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች ምርጫው መቼ (ወይም እንዴት) እንደሚካሄድ አሁንም ግልፅ አይደለም።
ምንም እንኳን በቅርቡ በኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በመጪው ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ በኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ በዋናነት ግጭት ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የሶማሌ ክልልን ወደ ግጭት ቀጠናነት ሊመልስ ቢችልም በሌሎች ክልል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫ ራሳቸውን ማግለል የምርጫ ሁከት አልፈጠረም (አዲስ ስታንዳርድ፣ መስከረም 7, 2014)። የኦብነግ ታጣቂዎች በ2010 ከኢትዮጵያ የሽብርተኛ ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ ተሰርዘው በ2011 ትጥቅ ፈትተው ወደ ሶማሌ ክልል የደህንነት መስመር ውስጥ ተጠቃለዋል (አፍሪካኒውስ፣ ነሃሴ 27, 2011)። እንደ ኦብነግ እና ከሶማሌ ክልል ራሳቸውን እንዳገለሉ ሌሎች ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ምዝገባ ላይ የተነሱ የቅድመ-ምርጫ አለመግባባቶችን ‘‘አልፈታም’’ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መስከረም 7, 2014)። በመሆኑም በሶማሌ ክልል በመጪው ምርጫ የሚሳተፉት የብልጽግና ፓርቲ እና የምዕራብ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ብቻ ናቸው። የኦብነግ ከምርጫው መውጣት በሶማሌ ክልል የፖለቲካ ምህዳር ላይ በሰላም ለመሳተፍ መቻሉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫው ባልተካሄደባቸው ሌሎች ክልሎች ውስጥ ተጨማሪ የፖለቲካ ለውጦች ታይተዋል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ባሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ባሳለፍነው ሳምንት ምርጫ ገና ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል/ጉሙዝ አንዳንድ ክፍሎች ምርጫ ከማድረግ ይልቅ ክልላዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጥሪ አቅርቧል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መስከረም 12, 2014)። የባሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪዎች የአሁኑ የክልል መንግስት ከመስክረም 24, 2014 በኋላ እንደ ክልላዊ መንግስት ለመቀጠል ሕጋዊነት እንደማይኖረው ገልፀዋል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከ99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ የተደረገው ለ34 መቀመጫዎች ብቻ ነው። በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ምርጫ አልተካሄደም። ከነዚህ 34 መቀመጫዎች ውስጥ ገዥው የብልፅግና ፓርቲ 28 መቀመጫዎችን አግኝቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የስድስት የምርጫ ክልሎች ምርጫ ውጤት ተሽሯል። ምንም እንኳን ምርጫዎቹ በድጋሚ መስከረም 20, 2014 ላይ ይካሄዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም የደህንነት ስጋቶች እነዚህን ምርጫዎች የበለጠ አዘግይተዋል። ቢሆንም የአሁኑ የመተከል ዞን አስተዳዳሪ (እና የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣን) ዞኑ አሁን በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋ በመሆኑ ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጁ ነው ብለዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 13, 2014)። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሕገ-መንግሥታዊ ክለሳዎች ከሌሉ በክልሉ በቀጣይ ሁከት የመፈጠር ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
ምርጫው በዘገየባቸው ክልሎች እና ሌሎች አካባቢዎች ድምጽ መስጠት ሲጀመር የምርጫ ሁከቶች ሊፈጠሩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የፖለቲካ ብጥብጥ የመጨመር እድሉ አሳሳቢ ሆኖ ሳለ ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉ ሃላፊዎች የክልል ባለሥልጣናትን በቀጥታ በመቃወም ሰልፎችን ሊጠሩ ይችላሉ።