በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መስከረም 21, 2014)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,031
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,093
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,603
በቁጥር (ከመስከረም 15, 2014 እስከ መስከረም 21, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 6
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 16
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ሕወሓት) ኃይሎች እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው የአካባቢ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ቀጥሏል (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአማራ ክልል በተፋላሚ ወገኖች መካከል ያሉ ውጊያዎች የቀነሱ ቢሆንም በመንግስት የሚደገፉ ኃይሎች በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ አዲስ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ያለ ሲሆን ይህም በመጪዎቹ ሳምንታት ግጭት እንዲጨምር የማድረግ እድል አለው (ስካይ ኒውስ፣ መስከረም 25, 2014)።
እንዲሁም በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ባቲ አካባቢ ከአፋር ብሄር የሆኑ ታጣቂዎች የኦሮሞ ተወላጆች በሆኑ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰሰቦች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ተብሎ ተዘግቧል። በባቲ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች በአርብቶ አደር የኦሮሞ እና አፋር ማህበረሰቦች መካከል ያሉ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በዱግዳ ወረዳ የወረዳውን አስተዳዳሪ ገድለዋል። በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ የተለመደ የግጭት አይነት ነው።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ማንነታቸው ያልታወቁ የጉሙዝ ታጣቂዎች በሴዳል ወረዳ መርሻ እና እክፈት ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን አጥቅተው 145 የጉሙዝ ብሄር ተወላጆች አፍነው ሲወስዱ ቢያንስ ሁለት ገድለዋል። ቡድኑ የታገቱትን ሰዎች አልደግፋችሁንም ማለቱ ተዘግቧል። የፀጥታ ኃይሎች በአቅራቢያው በሚገኝ የገጠር ሥፍራ ከታጣቂዎቹ ጋር በመዋጋት ለጥቃቱ ምላሽ ሰጥተዋል። ከ2010 ጀምሮ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሁከት ካለቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ የተከሰተው ግጭት በአማራ፣ ትግራይ፣ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባሉ በፖለቲካ ውስጥ ቦታ ባላቸው ግጭቶች በመሸፈኑ ብዙውን ጊዜ ችላ ይባላል። ይህ በክልሉ ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ታጣቂዎች ጥልቅ መረጃን ጨምሮ ስለሁኔታው በቂ መረጃ ባለመኖሩ የተከሰተ ነው።
ሳምንታዊ ትኩረት: የኢትዮጵያ እና አለማቀፉ ማህበረሰብ ግንኙነት
መስከረም 20, 2014 ላይ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰባት ከፍተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሥልጣናት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ 72 ሰዓታት ሰጥቷል (ሮይተርስ፣ መስከረም 21, 2014)። ከዩኒሴፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ተባረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ተወካዮች መካከል ያለው የቅርብ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ክርክር ለወራት የዘለቀ ውጥረት ውጤት ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳሰቢያውን ከማውጣቱ በፊት የተለቀቀ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሁኔታዎች ዘገባ የኢትዮጵያን መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ እገዳ በማድረግ እንዲሁም ነዳጅ፣ ገንዘብ፣ እና የህክምና አቅርቦቶች እንዳይሰጡ በማድረግ ከሷል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መስከረም 13, 2014)። የኢትዮጵያ መንግትሥት በበኩሉ የተባረሩትን የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ሰብአዊ እርዳታዎችን ወደ ትህነግ በማዘዋወር፣ የመገናኛ መሳሪያዎችን ለትህነግ በመስጠት፣ በትህነግ ለወታደራዊ ጥቅም የተያዙ 400 የጭነት መኪናዎችን እንዲመልሱ ከመጠየቅ በመታቀብ፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ እና የሰብአዊ ዕርዳታን ፖለቲካዊ በማድረግ ከሷል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መስከረም 21, 2014)።
ባለሥልጣኖቹን የማባረሩ ውሳኔ በአውሮፓ ህብረት እና በአሜሪካ የተወገዘ ሲሆን ሁለቱም “ውሳኔው እንዲቀለበስ” ጥሪ አስተላልፈዋል (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መስከረም 20, 2014)። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መስከረም 7, 2014 ላይ በግጭቱ ቦታ ያላቸውን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ኢላማ ለማድረግ አዲስ ማዕቀቦችን የተመለከተ የህግ ማዕቀፍ አውጥተዋል። ባለፈው አመት የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የበጀት ድጋፍ ሰርዘዋል።
በአንፃሩ የቻይና ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 21, 2014)። የአሜሪካ ማዕቀብ እንደምትጥል ባሳወቀችበት ወቅት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ምክትል ቋሚ ተወካይ በሰጠው መግለጫ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከትግራይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ እንዲያከብር” አሳስቧል (ሺንዋ፣ ሰኔ 25, 2013)።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እና የብልጽግና ፓርቲያቸው አዲስ መንግሥት እየመሰረቱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአሜሪካ፣ እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላቸው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ ዝቅ ያለ ነው። በትግራይ ያለው ግጭት (ብዙ አስፈላጊ የማምረቻ እና የማዕድን ማዕከላት ያሉበት ቦታ)፣ በዓለም ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ እና ከዋጋ ግሽበቱ ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ ድምር ውጤት አብይ እና ሌሎች በቅርቡ የተሾሙት ባለሥልጣናት አሉታዊ ምልከታ ያለው ኢኮኖሚ እንዲወርሱ ያደርጋቸዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 14, 2014)። አዲሱ አመራር ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶች ከፍተኛ ናቸው።
በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በአዲስ አበባ መካከል ያለው ውጥረት ምንም ይሁን ምን የአፍሪካ መንግስታት መሪዎች እና የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት መስከረም 24, 2014 ላይ የሚደረገው የአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት በአለ-ሲመት ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ገብተዋል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መስከረም 23, 2014)። መስከረም 23 እና 24 ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያረፉት አውሮፕላኖች የሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮ እንዲሁም የአልጀሪያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይዘው ነበር። ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከቱ አለመግባባቶች ላይ ከሱዳንና ግብፅ ጋር በምታደርገው ድርድር የአፍሪካ ኅብረትን መርጣለች። ከትግራይ ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም በህብረቱ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የመደገፍ እድል አላት።
የፌዴራል መንግሥቱ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናትን በማባረር ሕወሓትን በወታደራዊ ኃይል ማሸነፍ እንደሚችል እያመላከተ ሲሆን ይህን ለመፈጸም የሚያደርጉትን ጥረት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ማንኛውንም የውጭ አካላት ድርጊት እንደማይታገስ ያሳያል። የማባረሩ ውሳኔ ምናልባትም የግንኙነቱ መሻከር መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በግልጽ ውድቅ ቢያደርገውም በአዲስ አበባ ያሉ ባለሥልጣናት የተባበሩት መንግሥታት ትህነግን እየረዳ ነው ብለው እስካመኑ ድረስ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶች ቀላል ምላሽ አያገኙም።
የአዲስ አበባ ትህነግን በወታደራዊ ሃይል የማሸነፍ አቅሟ የትህነግ ታጣቂዎች አሁንም በአማራ ክልል በበርካታ ዞኖች ውስጥ ትልቅ የሆነ ቦታ ይዘው እንደመገኘታችቸው ገና አልተረጋገጠም። የኢትዮጵያ ወታደሮች እና የአማራ ክልል ኃይሎች ትህነግን ወደ ትግራይ መልሰው መግፋት ቢችሉ እንኳ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ጊዜያዊ ባለሥልጣናት በሾመበት ወቅት እንደታየው ክልሉን ማስተዳደር አይቻልም። የቀድሞ ጊዜያዊ ባለሥልጣን (እና በትግራይ ውስጥ ትህነግን የሚቃወም የተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት ፓርቲ አባል) ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሁከት በማነሳሳት ተከሷል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 23, 2014)። በትግራይ የሚኖሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ሲሰቃዩ በመንግሥት ኃይሎች እና በትህነግ መካከል የሚደረገው ውጊያ መቀጠሉ አይቀርም።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች
ባለፈው ሳምንት መስከረም መስከረም 20, 2014 ላይ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በሐረሪ፣ ሶማሌ፣ እና በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች (ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች በ31 የምርጫ ክልሎች እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች በ22 የምርጫ ክልሎች) ተካሂዷል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 6, 2014)። በተጨማሪም የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ እንዲሁም ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ እና ሸካ ዞኖች አዲስ (11ኛ) ክልል ይሁኑ ወይንስ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ውስጥ የአስተዳደር ዞኖች እና ልዩ ወረዳ ሆነው ይቀጥሉ ወይ የሚለውን ለመወሰን ሕዝበ-ውሳኔ አካሂደዋል። መስከረም 30, 2014 ላይ የሕዝበ-ውሳኔው ውጤት ሲገለጽ ተቀባይነት ካገኘ አዲሱ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን ይባላል።
በምርጫው እና ቀጣዩ ቀን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ 42 ከምርጫ ቀን ጋር የተያያዙ ስሞታዎች ቀርበዋል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 21, 2014)። በተጨማሪም በሞያሌ የሚገኘው የዱኩቺ የምርጫ ጣቢያ ከደህንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ተዘግቷል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 20, 2014)። በአጠቃላይ በሶስቱም ክልሎች የምርጫው ቀን ሰላማዊ የነበረ ሲሆ ምንም አይነት የተዘገበ የግጭት ኩነት አልነበረም።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በክልሉ አልተካሄደም። በተመሳሳይ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ያሉትን የመተከል እና ካማሺ ዞኖችን በመሳሰሉ አካባቢዎች ከፀጥታ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ምርጫው አልተካሄደም። በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ግልፅ አይደለም። ይህ ደግሞ ከ99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ለ34 ብቻ ምርጫ በተካሄደበት የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አዲስ መንግሥት ለመመስረት እንቅፋት ፈጥሯል። ገዥው ፓርቲ 28 ወንበሮችን ብቻ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በስድስት የምርጫ ክልሎች ደግሞ የምርጫው ውጤት ተሰርዟል። ከመስከረም 24, 2014 ጀምሮ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ስልጣን ያበቃል። የክልሉ መንግሥት ክልሉን በምን ስልጣን ማስተዳደር እንደሚቀጥል አከራካሪ ነው።
ባለፈው ሳምንት ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና የአማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ ምክር ቤቶች አዲስ መንግስት አቋቁመዋል። በተመሳሳይ የሶማሌ እና ሃረሪ ክልሎች የመስከረም 20, 2014 የምርጫ ውጤት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተገለጸ በኋላ የየራሳቸውን መንግሥት ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል። የመጨረሻው የምርጫ ውጤት ከመስከረም 21 እስከ መስከረም 30, 2014 በየእለቱ ይፋ ይደረጋሉ። ማንኛውም ከመስከረም 20, 2014 ምርጫ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች እስከ መስከረም 29, 2014 ድረስ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሊቀርቡ ይችላሉ።