ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
- አክሌድ ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ድረስ 103 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን 943 ሟቾች ደግሞ ተመዝግበዋል።
- ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ወቅት በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል ሲሆን በክልሉ 504 ሟቾች ነበሩ። ኦሮሚያ ክልል በ222 ሟቾች ሁለተኛው ከፍተኛ ሞት የተመዘገበበት ክልል ነው።
- ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 73 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 766 ሟቾች ተመዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- ከባለፈው ወር ሲነጻጸር በትግራይ፣ አማራ፣ እና አፋር ክልሎች ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በነበረው ወቅት አነስተኛ ውጊያዎች ተመዝግበዋል። ተደጋጋሚ ግጭቶች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት የተመዘገቡ ሲሆን መስከረም 1, 2014 ከተከበረው የኢትዮጵያ አዲስ አመት በኋላ ውጊያዎች ቀንሰዋል።
- ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) መካከል በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ውስጥ በተደጋጋሚ ተመዝግቧል።
- በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ሃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል ያለው ውጊያ ቀጥሏል።
- በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አሁንም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው።
በዚህ ዘገባ
- የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- በኢትዮጵያ ግጭቶች ላይ ዘገባ መስራት ላይ ያለ ችግር
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
መስከረም 1, 2014 ላይ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት አክብረዋል። ምንም እንኳን በዋና ከተማዋ እና በተቀረው የአገሪቱ ክፍል በዓሉ እንደተለመደው የተከበረ ቢሆንም በሰሜናዊ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ግጭት እና ይህም በኢኮኖሚው እና በሰዎች ደህንነት ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት ብዙ ሰዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ወቅት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በትግራይ፣ አማራ፣ እና አፋር ክልሎች ውስጥ በመንግስት ኃይሎች እና ትህነግ መካከል ከ40 በላይ ውጊያዎች የተመዘገቡ ሲሆን ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ተመዝግቧል። ከፍተኛው የሞት ቁጥር የተመዘገበው በሰሜን ጎንደር ዞን ሲሆን በጨና የአማራ ታጣቂዎች ከትህነግ ጋር ለአምስት ቀናት በተዋጉበት ወቅት ቢያንስ 120 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል (ሮይተርስ፣ ጷጉሜ 4, 2013)። በአንፃሩ እስከ መስከረም 20, 2014 ባሉት ሁለት ሳምንታት ግን ሁለት ውጊያዎች ብቻ ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የውጊያዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም የመንግስት ሃይሎችም ሆኑ ትህነግ በአሁኑ ወቅት ትህነግ ተቆጣሯቸው በሚገኙ አካባቢዎች ውጊያውን ለመቀጠል እየተደራጁ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።
ትህነግ ከሃምሌ መጀመሪያ ጀምሮ ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎች አብዛኛዎቹን የመንግስት ሃይሎች በነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ መልሰው ተቆጣጥረዋል። በአማራ ክልል አብዛኛው የሰሜን ወሎ፣ ሰቆጣ፣ ጋሸና፣ እና ላሊበላ አካባቢዎች ትህነግ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። በዚህ ወር መንግስት ሁሉንም የአፋር ክልል እንደተቆጣጠረ ነው።
ከሰኔ 2013 በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ቀውስ የሚታየው በትግራይ ክልል ውስጥ ነበር። ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ከዋግ ሐምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች የተፈናቀሉትን በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ሌሎች ዞኖች ጋር ሲነጻጸር የደቡብ ወሎ ዞን እያስተናገደ ነው። መንግስት ነሃሴ መጨረሻ ላይ በግጭቱ ምክንያት ወደ 400,000 የሚጠጉ ሰዎች ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች መፈናቀላቸውን አሳውቋል። በሁለቱም ክልሎች ያሉ ሌሎች አራት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ሰብዓዊ ዕርዳታ ሊፈልጉ ተቃርበዋል (ኢቢሲ፣ ጷጉሜ 1, 2013)። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በአማራ እና አፋር ክልሎች በተፈጠረው ግጭት 1.7 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ ዋስትና እንደሌለው ገልጿል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ነሃሴ 27, 2013)።
በአማራ ክልል በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ብዙ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በአግባቡ ማረስ አልቻሉም። በትግራይ ክልል ያሉ አርሶ አደሮች ባለፈው የዝናብ ወቅት ማረስ ስለመቻላቸው መረጃ የለም። መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁሙን ሲያውጅ ከሰጣቸው ምክንያቶች አንዱ አርሶ አደሮች በዝናብ ወቅት ማረስ እንዲችሉ ነበር። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት መረጃ መሠረት በትግራይ ክልል ከ1.3 ሚሊዮን ሄክታር ውስጥ 320,000 ሄክታር የእርሻ መሬት ብቻ መታረሱን አሳውቋል (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ነሃሴ 27, 2013)።
መስከረም 20 አካባቢ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዩኒሴፍ እና የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አባሯል። የኢትዮጵያ መንግሥት የተባረሩትን የተመድ ባለሥልጣናት በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ሲል ከሷል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መስከረም 21, 2014)። ይህንን ውሳኔ የአውሮፓ ህብረት፣ ተመድ፣ እና አሜሪካ ወዲያውኑ ያወገዙት ሲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ መንግስት ሰባቱ የተመድ ሰራተኞች ላይ ያተላለፈውን ከአገር ውጡ ውሳኔ እንዲቀለብስ ጠይቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ እና ተመድ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 21, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ጨምረዋል። ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በነበረው ጊዜ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ከደረሰው ጥቃት አብዛኛው የተመዘገበው በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪርሙ ወረዳ ነው (ከታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በኪርሙ ወረዳ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በኦነግ-ሸኔ ቁጥጥር ስር ናቸው። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በተደጋጋሚ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ምክንያት 300 የሚጠጉ አማራዎች ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ወደ ተፈናቅለዋል። የመንግስት ሃይሎችም በዚሁ ወር በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን በጥይት ገድለዋል። በተጨማሪም በመንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ኦነግ-ሸኔ መካከል 11 ውጊያዎች ተመዝግበዋል። እነዚህ ውጊያዎች የተከሰቱት በሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ አርሲ፣ ጉጂ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ እና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች ነው።
ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ወደ መተከል መስፋፋታቸውን ተከትሎ ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ወቅት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ቀጥሏል። ነሃሴ 28, 2013 አካባቢ በመተከል ዞን አልመሃል አካባቢ ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያለው ታጠቂ ቡድን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ጋር ተዋግቷል። ይህ ግጭት ላለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ፣ አማራ፣ እና አፋር ክልሎች የመንግሥት ኃይሎች ከትህነግ ጋር ሲያደርጉት የነበረው ውጊያ ወደ አዲስ ክልል መዛመቱን ያሳያል።
በመንግስት ኃይሎች እና ሌሎች ተገንጣይ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ሁከት ወደ ካማሺ ዞንም ተዛምቷል። የካማሺ ዞን በቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ግንባር ቁጥጥር ሥር ከቆየ በኋላ ከመስከረም 20 በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ዞኑ ገብቷል። ግንባሩ ከክልል እና ከፌዴራል ኃይሎች ጋር የሚዋጋ ተገንጣይ ቡድን ነው።
ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በነበረው ወቅት አራት ሰላማዊ ሰልፎች በኢትዮጵያ ተካሂደዋል። ሁለቱ ሰልፎች ታጠቂ ቡድኖችን በመቃወም የተካሄዱ ሲሆን ሰልፈኞቹ እንደዚህ ያሉ ቡድኖች ፍላጎታቸውን እንደማይወክሉ በግልጽ ለማሳየት ሞክረዋል። መስከረም 3, 2014 ላይ የካማሺ ዞን ነዋሪዎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ በካማሺ ከተማ በታጠቂ ቡድኖች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል። ሆኖም ግን መስከረም 14, 2014 ላይ የጉሙዝ ታጣቂዎች በሰዳል ወረዳ መርሻ እና እቅፈት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር 145 ጉሙዞችን አፍነው ሲወስዱ ቢያንስ ሁለት ገድለዋል። ቡድኑ የታገቱትን ሰዎች አልደግፋችሁኝም በሚል መክሰሱ ተዘግቧል። የፀጥታ ኃይሎች ለጥቃቱ በአቅራቢያው በሚገኝ የገጠር ሥፍራ ከታጣቂዎቹ ጋር በመዋጋት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 በነበረው ወቅት የመጨረሻ ቀናት የጭልጋ ወረዳ ነዋሪዎች የቅማንት ኮሚቴ ታጠቂ ቡድንን ተቃውመው በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር አይከል ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። የቅማንት ኮሚቴ ታጠቂ ቡድን ከትህነግ ጋር በመሆን ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ጊዜ በምዕራብ ጎንደር ዞን ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል። የቅማንት ኮሚቴ በአማራ ክልል ውስጥ ለበለጠ የራስ ገዝ አስተዳደር ይታገላል። የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ትህነግን ‘የጦር መሣሪያ እና ገንዘብ’ ዓመፀኛ ለሆነው የቅማንት ብሔርተኛ እንቅስቃሴ በማቅረብ ይከሳሉ (ቢቢሲ፣ ግንቦት 11, 2014)።
ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ጊዜ የተካሄዱት ቀሪዎቹ ሁለት ሰልፎች የተካሄዱት በሰሜን ባለው ውጊያ በተጎዱ ሰዎች በአዲስ አበባ ከተማ በተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ፊት ለፊት ነው። መስከረም 10, 2014 ላይ የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ ክልል በኤርትራ ስደተኞች ላይ በትህነግ የሚደርሰውን ጥቃት እና ወሲባዊ ጥቃት ተቃውመው አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ ወጥተዋል። በቀጣዩ ቀን በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ዩኒሴፍ ጽ/ቤቶች ፊት ለፊት በመገኘት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በግጭቱ ለተጎዱ ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ምርጫው ሰኔ 2013 ላይ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ መስከረም 20, 2014 ላይ ተካሂዷል። በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል (በ31 የምርጫ ክልሎች ለደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ወንበሮች እና በ22 የምርጫ ክልሎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) እንዲሁም በሐረሪ እና በሶማሌ ክልሎች ምርጫ ተካሂዷል። በተጨማሪም የኮንታ ልዩ ወረዳ እና ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ እንዲሁም ሸካ ዞኖች አዲስ (አስራ አንደኛ) የኢትዮጵያ ክልል ይመስርቱ ወይንስ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተዳደር ሥር መተዳደር ይቀጥሉ የሚለውን የሚወሰንበትን ሕዝበ ውሳኔ አካሂደዋል። በአጠቃላይ የምርጫው ቀን በሦስቱም ክልሎች ሰላማዊ የነበረ ሲሆን ምንም ዓይነት የአመፅ ግጭቶች አልተዘገቡም።
ወርሃዊ ትኩረት: ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶችን መዘገብ ላይ ያሉ ችግሮች
ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተሾሙበት መጋቢት 2010 ጀምሮ በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች። በኢትዮጵያ የአስተዳደር መዋቅር እና ሠራተኞች ላይ ከተደረጉ ለውጦች ጎን ለጎን የፌዴራል መንግሥት ለጋዜጠኞች እና ለዘገባዎች ያለው አመለካከት አብይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። አብይ ሲመረጡ ለመገናኛ ብዙሃን (ለብሮድካስት፣ ህትመት፣ እና በይነመረብ) ክፍት የሆነ አካባቢ እንደሚፈጠር ቃል ገብተው ነበር፤ ለተወሰነ ጊዜም ይህ ሆኖ ነበር። ዓመፅ በመላው አገሪቱ ተሰራጭቶ በስተሰሜን አስከፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ግን የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ቦታ በጣም የተገደበ እየሆነ የመጣ ሲሆን ጋዜጠኞች ከመንግስት እና አማጺ ቡድኖች ማስፋራሪያ ገጥሟቸዋል።
በኢፒኦ መረጃ ማሰባሰቢያ መንገዶች ላይ እንደተገለጸው የኢፒኦ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ የፖለቲካ ሁከት እና ሰልፎችን በተመለከተ መረጃ ለመሰብሰብ ከአካባቢ አጋሮች በተጨማሪ በየሳምንቱ በደርዘን የሚቆጠሩ የእንግሊዝኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ፣ እና ኦሮምኛ ቋንቋ ምንጮችን ይገመግማሉ።
የኢፒኦ ጥናት እንደሚያመለክተው ባለፈው አመት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሚዲያ በሀገሪቷ ባለው ከፍተኛ ክፍፍል እና ከመንግስት የሚመጣ ጫና ውጤት በሚመስል መልኩ ተቀይሯል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘገባዎች የአንዱን ወገን ብቻ የሚያሳዩ እና “የሌላውን ወገን” ሕጋዊ ሊያደርጉ የሚችሉ አስፈላጊ መረጃዎችን የማያካትቱ እየሆኑ ነው።
አደጋዎች ቢኖሩም ብዙ ማሰራጫዎች እና ጋዜጠኞች እነዚህን ተግዳሮቶች አልፈው ተጨባጭ ዘገባን ለማቅረብ ይሰራሉ። ሆኖም በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተጋረጠው አደጋ መጨመሩን ቀጥሏል እንዲሁም ገለልተኛ ዘገባ የበለጠ አደጋ ላይ እየወደቀ ነው። ውጊያዎች የወንጀለኞች እና ተጎጂዎች እንዲሁም የግጭቶች መጠን እና ውጤቶችን በእርግጠኝነት ለመዘገብ እና በጊዜ ለማቅረብ አስቸጋሪ የሆነባቸው ‘የዝቅተኛ መረጃ’ ቦታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ችግሮች የብሔር ማንነት ክፍፍል በፈጠረበት እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ሳይቀር በተዋጊዎች ወገን ሊያስቀምጡ በሚችሉበት መሆናቸው ያባብሰዋል።
የኢትዮጵያ መሠረተ ልማትም ለጋዜጠኞች ፈታኝ ነው። ጋዜጠኞች ታጣቂ ቡድኖች ወደሚንቀሳቀሱባቸው ሩቅ አካባቢዎች ለመድረስ የሚቸገሩ ሲሆን ይህ ደግሞ የመረጃ ክፍተቶችን እና እንደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ያሉ ‘ድብቅ ግጭቶችን’ አስከትሏል። ለምሳሌ በቅርቡ የመንግስት ኃይሎች ከሱዳን ድንበር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሞክሩ ታጣቂዎችን በ“መቶዎች” የሚቆጠሩ ሰዎችን መግደላቸውን ተናግረዋል (ኢሳት፣ ጷጉሜ 1, 2013፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጷጉሜ 2, 2013)። እንደዚህ ያለ ከፍተኛ የሟች ቁጥር ቢገለጽም ይህንን ለማረጋገጥ ግን ተጨማሪ ዘገባዎች እና መረጃዎች የሉም።1ኢፒኦ የሞቱ ሰዎች መኖራቸው በሚታወቅበት ሆኖም ግን እርግጠኛው ቁጥር ባልታወቀባቸው ሁኔታዎች የሟቾችን ቁጥር የሚመዘግበው 10 ብሎ ነው። በመሆኑም ይህ ክስተት በተጨማሪ መረጃ እጥረት ምክንያት መንግስት እንዳለው “በመቶዎች” ከመሆን ይልቅ 10 ተብሎ ተመዝግቧል። የግጭቱ ክብደት አነስተኛ ነው ተብሎ በሚታሰብባቸው ሌሎች ክስተቶች ያልታወቁ የሞት ቁጥሮች አብዛኛውን ጊዜ ሶስት ተብለው ይመዘገባሉ (ለበለጠ መረጃ የአክሌድን የሞት መመዝገቢያ መንገዶች በሟቾች መመዝገቢያ ጥያቄዎች እና መልሶች ላይ ይመልከቱ)።
ከነሃሴ 26, 2013 እስከ መስከረም 20, 2014 ባለው ወር በአማራ ክልል በአማራ ክልል ኃይሎች እና ትህነግ መካከል በተደረገ ውጊያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ሞት ተመዝግቧል። የአማራ የአካባቢ ባለስልጣናት 119 “ንፁህ አርሶ አደሮች፣ ካህናት፣ ሕፃናት፣ እና ሴቶች” ጨና በተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ ተገድለዋል ብለዋል (ቢቢሲ፣ ጷጉሜ 3, 2013)። አንዳንድ ዘገባዎች ግን የተገደሉት ከትህነግ ጋር በተደረገ ውጊያ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ያመለክታሉ። ይህ የክልል ባለሥልጣናት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን እንዲደራጁ የማድረጋቸው ውጤት ይሆናል፤ በዚህም ምክንያት ፖለቲካዊ የሆነው ግጭት ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ይቀየራል።
ተአማኒ እና አስተማማኝ የግጭት ዘገባ በሌለበት ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ ትረካዎችን በመጠቀም ደጋፊዎችን በማሰባሰብ ላይ ናቸው። የትህነግ መሪዎች በደል ደርሷል የሚሉ ክሶችን ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተጠቀሙ እንደሆነ ሁሉ የአማራ ልሂቃንም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ትህነግን እንዲታገሉ እያደረጉ ነው፤ በዚህም የክስ እና የማነሳሳት እሽክርክሪት ውስጥ ተገብቷል። የአማራ ክልል መንግስት የአከባቢው ሰዎች ትህነግን እንዲዋጉ እያበረታታ ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ግለሰቦች ከትህነግ የማረኩት ማንኛውንም መሳሪያ እራሳቸው ጋር እንዲያስቀሩ ፈቅዷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 10, 2013፤ አዲስ ስታንዳርድ፣ ነሃሴ 12, 2014)። የአማራ ክልል መንግስት እና ልሂቃን ትህነግን ለመመከት እንዲቻል የ“ህዝባዊ ማዕበል” ጥሪ አቅርበዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ነሃሴ 10, 2013)። ይህ ጥሪ የተደረገው ትህነግ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ትግሬዎችን (ተጋሩዎችን) ለጦርነት መመልመል እና መላክ መጀመሩን ተከትሎ መሆኑ ተዘግቧል። በመሆኑም ከመደበኛ የደህንነት ተቋማት ትዕዛዝ ውጭ የሆኑ እና ያልሠለጠኑ ግለሰቦች በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከትህነግ ጋር እየተዋጉ ነው።
የመረጃ እጥረት፣ የተዛባ ዘገባ፣ እና ዘገባ መስራት ላይ የሚጣል ገደብ የፖሊሲ ውሳኔዎች ባልተሟላ መረጃ ላይ ተመስርተው የሚተላለፉበት ሁኔታ ይፈጥራሉ። ሚዲያዎችን ከመገደብ ይልቅ የሚዲያ ነፃነት እንዲኖር በመፍቀድ ጋዜጠኞች እውነተኛ ዘገባ እንዲሰሩ እና የተሻሉ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ ለማድረግ ይቻላል።