በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥቅምት 5, 2014)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,054
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,167
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,632
በቁጥር (ከመስከረም 29, 2014 እስከ ጥቅምት 5, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 7
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 40
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ለተወሰነ ጊዜ ከዘለቀ መቀዛቀዝ በኋላ በመንግስት እና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) መሃል ያለው ውጊያ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ጀምሯል። ሁለቱም ቡድን ሌላውን በአማራ ክልል እንደገና ውጊያውን በመጀመር ይከሳሉ። አስተማማኝ መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ውጊያዎቹን በተመለከተ ያሉት ዝርዝሮች እምብዛም አይደሉም። ባለፈው ሳምንት ግጭቶች በዋናነት የነበሩት በሰሜን ወሎ ዞን በተለይም ውርጌሳ፣ ወገልጤና፣ እና ሀሮ ከተሞች እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን ውጫሌ፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦ፣ እና ደላንታ አካባቢዎች ነበር። በውጊያዎቹ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ጨምሮ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል። ጥቅምት 3, 2014 ላይ በአፋር ክልል ትህነግ በከባድ መሳሪያ ባደረሰው ድብደባ ሰባት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሲገድል 15 ማቁሰሉ ተዘግቧል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 3, 2014)።
በኦሮሚያ ክልልም ውጊያዎች ቀጥለዋል። ከጥቅምት 1 እስከ 3, 2014 የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ ዓለም ቀበሌ ባደረጉት ውጊያ 15 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 4, 2014፤ ኢሳት፣ ጥቅምት 1, 2014፤ ኢሳት፣ ጥቅምት 2, 2014፤ ኢሳት፤ ጥቅምት 3, 2014፤ Aአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 4, 2014)። ምስክሮች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች መስከረም 29, 2014 ላይ ከቀበሌው ለቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል፤ ኦነግ-ሸኔ ወደቀበሌው በማግስቱ ገብቷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 4, 2014)። በተጨማሪም ጥቅምት 2, 2014 ላይ ኦነግ-ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ በቀላላ አካባቢ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል (ኢሳት፣ ጥቅምት 3, 2014)። በቀጣዩ ቀን በአርሲ ዞን ሙኔሳ ከተማ ከኦነግ-ሸኔ ጋር በተደረገ ውጊያ ስምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸው ተዘግቧል። ተጨማሪ 10 ወታደሮች በጥቃቱ መቁሰላቸው ተነግሯል (ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ጥቅምት 3, 2014)። በመንግስት ሃይሎች እና በኦነግ-ሸኔ መካከል ተጨማሪ ውጊያዎች በምስራቅ ጉጂ ጉራ ዶላ ወረዳ መካሄዱ ተዘግቧል (ኢቢሲ፣ መስከረም 29, 2014)። ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ሸዋ ማጄቴ ሰብል በተቃጠለበት ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ከሰዋል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 5, 2014)።
ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች የትምህርት ሚኒስቴር ወደ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ስላልመደባቸው ለመቃወም እና እንደገና የመመደብ አማራጮቻቸውን በአግባቡ እንዲያሳውቃቸው ለመጠየቅ በአዲስ አበባ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በራፍ ጥቅምት 1, 2014 ላይ ሰልፍ አካሂደዋል። በሰሜን እየተካሄደ ያለው ውጊያ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ዩንቨርስቲዎች እንዲዘጉ አድርጓል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአይኦኤም እና የዩኤንኤፍፒኤ ተወካዮች ወደ የተባበሩት መንግስትታት ድርጅት (ተመድ) ዋና መሥሪያ ቤት እንዲመለሱ እና የአስተዳደር ዕረፍት እንዲወስዱ ተደርጓል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 3, 2014)። ይህ ውሳኔ የመጣው የሁለቱ የተመድ ባለሥልጣናት የተቀረጸ ድምጽ በበይነመረብ ከተለቀቀ በኋላ ነው። በቀረጻው ላይ ባለሥልጣናቱ “አንዳንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለሚዋጉ በሰሜን የሚገኘው የትግራይ ክልል ኃይሎች ሃዘኔታ አላቸው” ሲሉ ተደምጠዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 3, 2014)። መስከረም 20, 2014 ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ በማስተላለፍ እና የሰብአዊ እርዳታን ፖለቲካዊ በማድረግ የከሰሳቸውን ሰባት ከፍተኛ የዩኒሴፍ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ባለስልጣናትን ከአገሪቷ እንዲወጡ አዟል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መስከረም 21, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት: በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በሚካሄደው ውጊያ በተዋጊ ቡድኖች የሚቀርቡ አቤቱታዎች
በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ በድጋሚ የተቀሰቀሰውን ውጊያ ሌላኛው ቡድን በፈጸመው ጥቃት እንደሆነ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ትህነግ ተናግረዋል። ምንም እንኳን የተኩስ አቁም በይፋ ባይታወጅም ውጊያው በድጋሚ በጥቅምት 1, 2014 ከመጀመሩ በፊት ውጊያው ተቀዛቅዞ ነበር። የአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረትን የማዕቀብ ማስፈራሪያዎችን ጨምሮ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እያደረገ ባለበት ወቅት ሁለቱም ወገኖች ዘገባዎችን ለመቆጣጠር እና ውጊያ በሌላኛው ወገን እንደገና እንደጀመረ ለመናገር ሞክረዋል (ጆሴፍ ቦሬል ፎንቴሌስ ትዊተር፣ ጥቅምት 8, 2014)። የትህነግ ሃይሎች የፌደራል ወታደሮች እና ተባባሪ “የአማራ ኃይሎች” ጥቅምት 1, 2014 ማለዳ ላይ ጥቃት መጀመራቸውን ትህነግ በይፋዊ መግለጫው ተናግሯል (ጌታቸው ረዳ ትዊተር፣ ጥቅምት 1, 2014)። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ከጥቂት ቀናት በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ትህነግ ጭፍራ እና ውጫሌ ከተሞችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ እና 30 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን በመግደል ውጊያውን እንደገና ማስጀመሩን አሳውቋል(የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 8, 2014)።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ባለፈው ሳምንት ያደረጓቸው ንግግሮች ቀስቃሽ የነበሩ ሲሆን በመሬት ላይም ውጊያ ነበር። ውጊያው እንደቀጠለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በፌስቡክ ገጹ እና በመንግስት ተጓዳኝ ሚዲያዎች በኩል ባወጣው መግለጫ “ሠራዊቱ በራሱ ዕቅድ መሠረት ጥቃት ከፈጸመ [ትህነግ] ጥቃት ደርሶብኛል የማለት እንኳ ጊዜ ሳያገኝ እንደሚያጠናቅቀው መታወቅ አለበት” ብሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 2, 2014)። እነዚህ መግለጫዎች በኋላ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፌስቡክ ገጽ እና ከሌሎች ድረገጾች ተሰርዘዋል።
በሰሜን ወሎ ውጊያው እንደቀጠለ ጥቅምት 1, 2014 ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የትህነግን ድርጊቶች ‘ለመቀልበስ’ በሚያደርገው ዝግጅት መሳሪያዎቹን እያዘመነ እንደሆነ ገልጸው ነበር (ኢቢሲ፣ መስከረም 1, 2014)። መጀመሪያ በፌደራል መንግሥት የተካዱ የአየር ጥቃቶች የትግራይ ክልል ዋና ከተማ ላይ የተፈጸሙ ሲሆን ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መሞታቸው ተዘግቧል። የመንግስት ምንጮች ጥቃቶቹ የመገናኛ ህንጻን ኢላማ እንዳደረጉ ተናግረዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 8, 2014)።
ሁለቱም ቡድኖች በሚያቀርቧቸው ተቃራኑ አቤቱታዎች ምክንያት ዝርዝሮች ግልፅ ባይሆኑም እንኳን በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም በአፋር/በአማራ ክልሎች ድንበር አካባቢ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ መቀጠሉ እውነታ ነው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የመጀመሪያ (ያልተረጋገጡ) ዘገባዎች ትህነግ በፍጥነት ወደደቡብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና ወገልጤና ከተማን መቆጣጠሩን ያሳያሉ (ኢትዮጵያ ማፕ፣ ጥቅምት 8, 2014፤ ጌታቸው ረዳ ትዊተር፣ ጥቅምት 8, 2014)። ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ከደሴ እና ኮምቦልቻ ውጊያው ወዳለበት ወደ ሰሜን እየተጓዙ ነው። ይህ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ የአካባቢው ተወላጆች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይልን እንዲቀላቀሉ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የተፈጠረ ነው። በቅርቡ ጋዜጠኞች ኮምቦልቻ ከተማ አቅራቢያ የተኩስ ድምጽ እንደነበረ ዘግበዋል (አይደር ፔራልታ ትዊተር፣ ጥቅምት 9, 2014)።
አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች አዲስ መፈናቀል አስከትሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 5, 2014)። በተለይም በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ከጦርነት የሚሸሹ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እያስተናገደች ነው። ትህነግ ሳምንቱን በሙሉ አማራ እና አፋር ክልሎችን በከባድ መሳሪያ ደብድቦ ተጨማሪ መሠረተ ልማት አውታሮችን ሲያፈርስ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን አደጋ ላይ ጥሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በመቀሌ ላይ የተፈጸመው የአየር ድብደባ የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ በበለጠ በአየር ሃይሉ አቅም ላይ እንደሚመረኮዝ ሊያመለክት ይችላል። ይህ ከመላው ክልል ተፈናቀለው በከተማው የተሰባሰቡ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን እና መሠረተ ልማቶችን አደጋ ላይ ይጥላል።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 20, 2014 የተካሄዱትን አጠቃላይ ምርጫዎች እና ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት አሳውቋል። ምርጫዎች አንዳንድ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልሎች የምርጫ ክልሎች3ምርጫው በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ለክልል ምክር ቤት በ31 የምርጫ ክልሎች እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ በ22 የምርጫ ክልሎች ተካሂዷል። እንዲሁም ሃረሪ እና ሶማሌ ክልሎችን ጨምሮ ከሰኔ ጀምሮ ምርጫዎች በዘገዩባቸው አካባቢዎች ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ በመስከረም 2014 ምርጫ ወቅት ለውድድር የቀረቡትን የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን በሙሉ አሸንፏል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 30, 2014 10)። በመሆኑም የብልጽግና ፓርቲ ከ547 መቀመጫዎች 457 ይይዛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች ያሉ የሶስት የምርጫ ክልሎች ላይ የቀረቡ የምርጫ አቤቱታዎችን በማጣራት ላይ በመሆኑ የሶስቱ የምርጫ ውጤቶች ባለፈው ሳምንት ይፋ አልተደረጉም (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 30, 2014)። በሶስቱም ክልሎች ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ለተደረጉት ምርጫዎች ሁሉንም ማለት በሚቻል መልኩ ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 30, 2014)።4 ለሐረሪ ክልል ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 36 መቀመጫዎች አሸንፏል። ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት ፓርቲው ከ72 መቀመጫዎች 70 ያሸነፈ ሲሆን አንድ ገለልተኛ እጩ ደግሞ አንድ ወንበር አሸንፈዋል። በሶማሌ ክልል የሁለት ምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤት ባልተፈቱ የምርጫ ውዝግቦች ምክንያት እስካሁን አልተገለጸም። በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምርጫ ለ30 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካሂዷል። የብልፅግና ፓርቲ 27 መቀመጫዎችን ያሸነፈ ሲሆን የቀሪዎቹ መቀመጫዎች ውጤት ያልተፈቱ የምርጫ አለመግባባቶች በመኖራቸው ምክንያት አልተፈቱም (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 30, 2014)። ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት ለሁለት የምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤቶች እስካሁን ባልተፈቱ የምርጫ አለመግባባቶች ምክንያት ገና አልታወቁም።
ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት በስተቀር በሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ማለት ይቻላል አብዛኛው መቀመጫ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከ99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ምርጫ የተደረገው ለ34 ብቻ ነበር። በፀጥታ ምክንያት በመተከል እና ካማሺ ዞኖች ምርጫ አልተካሄደም። ከእነዚህ 34 መቀመጫዎች ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ 28 ወንበሮችን አግኝቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የስድስት የምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤት ተሽሯል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ባለው ውጊያ ምክንያኛት ምርጫው አልተካሄደም፤ በክልሉ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ ግልፅ አይደለም። የትግራይ ክልል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 መቀመጫዎች አሉት። እንዲሁም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባሉና ምርጫዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት በተጓተቱባቸው አካባቢዎች ምርጫዎቹ መቼ እንደሚካሄዱ አሁንም አልታወቀም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሥር የሚተዳደሩትን የኮንታ ልዩ ወረዳ እንዲሁም የምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ እና ሸካ ዞኖችን ያካተተ አዲስ የኢትዮጵያ ክልል ይቋቋም ወይ የሚለውን ውሳኔ ለማሳለፍ የተካሄደውን ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት አስታውቋል። ሕዝበ-ውሳኔው ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተብሎ የሚጠራውን አስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ክልል መስርቷል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መስከረም 29, 2014)። አዲሱ ክልል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውጤቱን ከተቀበለ በኋላ ጥቅምት 29, 2014 ላይ በይፋ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል። ክልሉ በስተምስራቅ ከደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ በስተሰሜን ከኦሮሚያ፣ በስተምዕራብ ከጋምቤላ፣ እንዲሁም በስተደቡብ ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል። ነገር ግን የክልሉን የአስተዳደር ማዕከልን መወሰንን ጨምሮ አሁንም ያልተፈቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሉ። ገና ባልተጠናቀቀው እና በክልሉ ምክር ቤት ባልጸደቀው የክልሉ ህገ-መንግስት መሰረት በርካታ የአስተዳደር ማዕከላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ይቋቋማሉ (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 2, 2014)።
ክልሉን በሚፈጥሩት ዞኖች ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ አለመግባባቶች እንዴት እንደሚፈቱ ግልፅ አይደለም። መሰል አለመግባባቶች በቤንች ሸኮ ዞን ባለፈው አመት በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ግጭቶች መነሻ ናቸው። ዞኑ በቦታው ላይ ቀደም ብለው የነበሩ በሚባሉ እና እንደ ሰፋሪዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከሀብት እና የአስተዳደር መብቶች ጋር በተገናኘ ግጭት ሲፈጠርበት የነበረ ቦታ ነው። ባለፈው ዓመት5ከመስከረም 21, 2013 እስከ መስከረም 21, 2014 አክሌድ በቤንች ሸኮ ዞን 99 ሰዎችን ለሞት የዳረጉ 8 የተደራጁ የፖለቲካ ሁነቶችን መዝግቧል (የኢፒኦን ቤንች ሸኮ (ቤንች ማጂ ዞን) ግጭት ይመልከቱ)። በመሆኑም በአዲሱ ክልል የሚፈጠሩ እነዚህን አይነት ግጭቶች የሚፈቱ የአስተዳደር መዋቅሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል።