በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥቅምት 12, 2014)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,091
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,303
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,711
በቁጥር (ከጥቅምት 6, 2014 እስከ ጥቅምት 12, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 28
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 117
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 79
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የአየር ጥቃቶች ቀጥሏል። ከጥቅምት 8, 2014 እስከ ጥቅምት 12, 2014 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል አምስት የአየር ጥቃቶች አድርጓል። የአየር ጥቃቶቹ መንግስት ሰኔ 2013 ላይ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ካወጀ ወዲህ የመጀመርያው የዚህ አይነት ጥቃቶች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል የትህነግ ሃይሎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአማራ ታጣቂዎች ጋር በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ውጊያ አድርጓል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ጥቅምት 7, 2014 ላይ ትህነግ በሜን ጎንደር ዞን ዛሪማ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊ መስጊድን በከባድ መሳሪያ ደብድቧል። ጥቅምት 8, 2014 አካባቢ የትህነግ ሃይሎች በሰሜን ወሎ ዞን አምባሰል ከተማን በከባድ መሳሪያ የደበደቡ ሲሆን ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎችን ገድሏል። በተጨማሪም በሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ በውርጌሳ የትህነግ ሃይሎች 13 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መግደላቸውን እማኞች ገልጸዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 10, 2014)። ትህነግ ግለሰቦቹን ተኩሶ ከመግደሉ በፊት ቤንዚን በማፍሰስ ማቃጠሉ ተዘግቧል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 10, 2014፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ፣ ጥቅምት 10, 2014)።
የአማራ ክልላዊ መንግስት በመላው ክልሉ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ግለሰቦች ወደ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች በመጓዝ አካባቢውን ከተጨማሪ የትህነግ ጥቃቶች እንዲከላከሉ አበረታቷል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 11, 2014)። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ባለስልጣናት ለህዝቡ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 8, 2014)።
በአፋር ክልል ውጊያዎች በመስከረም ወር ጋብ ካለ በኋላ ቀጥሏል። የአማራ ክልል አዋሳኝ በሆነው ጭፍራ አካባቢ ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች በሚታገዘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ትህነግ መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል።
በውጊያዎች ወቅት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች መጎዳታቸውን ይቀጥላሉ። በአማራ ክልል ባለፈው ሳምንት በጊራና ከተማ የተደረገ ውጊያን ተከትሎ 250 አካባቢ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን የትህነግ ታጣቂዎች ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳን ለቀው እየወጡ የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 13, 2014)። በተጨማሪም የትህነግ ሃይሎች በአማራ ክልል የሚገኙ የእርሻ ምርቶችን እየሰበሰቡ ወደ ትግራይ ክልል እየወሰዱ ነው ተብሏል። በመሆኑም በሚቀጥሉት ወራት የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ በአፋር ክልል በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ወደ 45,000 የሚጠጉ ሰዎች ከጭፍራ እና መጋሌ ወረዳዎች ተፈናቅለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 10, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ሃይሎች እና እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ጥቅምት 6, 2014 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳ በርጋ ወረዳ የቀታደር ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተዘግቧል። ጥቅምት 7, 2014 ላይ በምስራቅ ጉጂ በጉሚ ኢዳሎ ወረዳ ቦባ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በቀጣዩ ቀን በጉጂ ዞን በሳባ ቦሩ ወረዳ ሲሬ ቡኪ እና ኡቱሉ ቀበሌዎች ሁለቱ ቡድኖች ግጭት ተዋግተዋል። በተጨማሪምበኦሮሚያ ክልል የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 8, 2014 እና 9, 2014 ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ወለጋ ዞን በሲቡ ሲሬ ወረዳ በቤኮ-ጅማ ቀበሌ መርካቶ አካባቢ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብሏል።
እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 8, 2014 ላይ የኦሮሞ እና አማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ከተማ ውስጥ ተዋግተዋል። ባለፉት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል ውዝግብ የሚያስነሱ አካባቢዎች ላይ በኦሮሞ እና አማራ የብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል በርካታ ግጭቶች መከሰታቸው ተዘግቧል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጥቅምት 8, 2014)። በእነዚህ አካባቢዎች በኦሮሞ እና አማራ ማህበረሰቦች መካከል ግጭቶች አልፎ አልፎ ተከስተዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደሮች በማስፈለጋቸው ምክንያት የመንግስት የጸጥታ አቅም ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ እነዚህ ግጭቶች ተባብሰዋል። ቡድኑ ቢያስተባብልም ከአካባቢው የሚወጡ በርካታ ዘገባዎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በአካባቢው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎችን ኢላማ እንደሚያደርጉ ያሳያሉ።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ዲባቴ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ጥቅምት 9, 2014 ላይ ተኩሰው ገድለዋል። በተመሳሳይ ቀን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በመተከል ዞን ዲባቴ ወረዳ በጋሌሳ ቀበሌ ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ተኩሰው ገድለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 10, 2014)። በጋሌሳ ቀበሌ ለተፈፀመው ጥቃት የጸጥታ ሃይሎችን የከሰሱ አሉ። ነገር ግን በአካባቢው የሰፈረው የኮማንድ ፖስት ሃላፊ ክሱን ውድቅ አድርገው ለጥቃቶቹ ተጠያቂዎቹ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ናቸው ብለዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት: በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች
በትህነግ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሃይሎች ጋር ያለው ውጊያ እየተባባሰ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከዝናብ ወቅት ማብቃት ጋር በትግራይ ክልል በትህነግ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ጀምሯል። በውጊያው ወቅት በሙሉ በትህነግ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ሲደረግ መቆየቱ ተዘግቧል። ሆኖም ግን ውጊያው ከጀመረበት ጥቅምት 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ጄቶች በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ ከተማ የትህነግን ኢላማዎች ሲመቱ ይህ የመጀመሪያው ነው። ለመጨረሻ ጊዜ መቀሌ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸመው የተዘገበው ህዳር 10, 2013 ላይ ነበር። በውጊያው ወቅት ከገጠር ከተሞች በነበረ መፈናቀል ምክንያት የመቀሌ ነዋሪ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የተሳሳተ ጥቃት ቢፈጸም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች አደጋ ላይ ይወድቃሉ።
ትህነግ በአማራ ክልል በኩል ወደ ደቡብ የሚያደርገው ግስጋሴ ጋብ ካለበት ነሃሴ 2013 ጀምሮ በኢትዮጵያ ጦርነት ላይ የአየር ጥቃቶችን ጨምሮ የርቀት ጥቃቶች እየጨመሩ የመጡ ባህሪዎች ናቸው (ከዚህ በታች ያለውን ምስል ይመልከቱ)። በግጭቱ ወቅት ጥቅም ላይ ከሚውሉት ሌሎቹ የርቀት ጥቃቶች መካከል በተለይም በትህነግ ጥቅም ላይ የሚውለው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ይገኝበታል። በቅርቡ በውጫሌ (ደቡብ ወሎ) እና ጭፍራ (በአፋር/አማራ ክልል ወሰን) ከተሞች ላይ በደረሰው የከባድ መሳሪያ ጥቃት 30 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በቅርቡ ትህነግ ያወጣው መግለጫ ላይ ደሴ ከተማ በሃይሉ የመድፍ ወሰን ውስጥ መሆኗን መግለጹን ተከትሎ በከተማው ውስጥ ሽብር የተፈጠረ ሲሆን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ለመሸሽ መሞከራቸውን ተከትሎ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ የትራንስፖርት ዋጋ ንሯል (ኢትዮጵያን ኢንሳይደር፣ ጥቅምት 11, 2014)። የርቀት ጥቃት ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት በመላው ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የሚገኙ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተጎድተዋል።
በጦርነቱ ወቅት ከተመዘገቡት የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ጥቃት መጠቀም መጀመሩ አዲስ አዝማሚያ ነው። ጥቅምት 12, 2014 ላይ የኢትዮጵያ ጀቶች መቀሌ ላይ የአየር ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን ይህም የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን የጫነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በረራ ሊገባ በታቀደበት ወቅት የነበረ በመሆኑ የተመድ በረራ እንዲቋረጥ ተገዷል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 13, 2014)። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተመድ አውሮፕላኖች ላይ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ባለው ስጋት ምክንያት ወደ ትግራይ የሚያደርጋቸውን ሁሉንም በረራዎች አቋርጧል (ሪሊፍ ዌብ፣ መስከረም 26, 2014)።
የትህነግ አመራሮች የኢትዮጵያ ጦር የተመድ አውሮፕላንን ከፀረ-አይሮፕላን መሸፈኛ አድርጎ ተጠቅሞበታል ያሉ ሲሆን የተመድ በረራ ከመነሳቱ በፊት ከአዲስ አበባ ባለስልጣናት ፍቃድ ተሰጥቶት የነበረ በመሆኑ በተወሰነ ደረጃ አሳማኝ የሆነ ክስ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በመቀሌ የሚገኙ ተቆጣጣሪዎች የበረራ ሰራተኞቹን እንዳያርፉ ማስገደዳቸውን እና የአየር ጥቃቱ “በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት” ሁኔታ መካሄዱን ገልጸዋል (የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 13 , 2014)።
ትህነግ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚያደርገው የቅርብ ጊዜ ግስጋሴም ሆነ መንግስት በትህነግ ኢላማዎች ላይ የሚያደርሰው የአየር ጥቃት በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እየተጠናከረ እንደሆነ ያሳያል። ሁለቱም ወገኖች ማዕቀብ የመጣል ማስፈራሪያዎች ያላሳሰባቸው ይመስላሉ። መንግስት የአየር ጥቃቱ የተዘጋጀ የሰብአዊ እርዳታ በረራ በነበረበት ወቅት ጊዜ ላይ ለማድረግ መፍቀዱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ባለስልጣናት መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ግንኙነት ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ሆነ ትህነግ ከርቀት የሚደረጉ ጥቃቶችን መፈጸም የሚቀጥሉ ይመስላል። የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ትህነግ የተአማኒነት ታሪክ ስለሌላቸው ይህ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችንም ሆነ እነዚህን ንብረቶች ስጋት ላይ ይጥላል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 9, 2014፤ ፍራንስ 24፣ ነሃሴ 20, 2013)።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሰኔ ወር ሊካሄድ ታቅዶ ለዘገየው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ባለፈው ሳምንት አውጥቷል። ምርጫው በመተከል እና ካማሺ ዞኖች በጸጥታ ችግር ምክንያት ዘግይቷል። በአዲሱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሚገኙ 17 የምርጫ ክልሎች ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታህሳስ 21, 2014 ላይ የሚካሄድ ይሆናል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 9, 2014)። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል እና ካማሺ ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች የምርጫ ጣቢያዎችን ለማቋቋም አቅዷል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 9, 2014)። ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ለአብላጫው የክልል ምክር ቤት ወንበሮች ምርጫ ባለመካሄዱ አዲስ መንግስት ያልተመሰረተበት ብቸኛው ክልል ነው። ሰኔ 2014 በተካሄደው ምርጫ ወቅት ከ99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ የተካሄደው ለ34 ብቻ ነው።