በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥቅምት 26, 2014)1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,150
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 12,539
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,772
በቁጥር (ከጥቅምት 20, 2014 እስከ ጥቅምት 26, 2014)2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 27
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 131
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 41
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን መቆጣጠሩ የትህነግ ሃይሎች ወደ ደቡብ ተጉዘው ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን እና በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ ሌሎችን ቦታዎች ያስፈራሉ የሚል ስጋት በመላ ሃገሪቷ ተፈጥሮ ነበር። ይህም የፌደራል መንግስቱ ጥቅምት 23 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አድርጓል። ቀጣዩ ክፍል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን ወቅታዊ ስጋት በዝርዝር ይቃኛል።
ሳምንቱን በሙሉ በአማራ ክልል ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ውስጥ እና አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአማራ ታጣቂዎች ከትህነግ ጋር መዋጋት ቀጥለዋል። ጥቅምት 25 ላይ የመንግስት ሃይሎች ጥምረት ለብዙ ወራት በትህነግ ተይዘው የነበሩትን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ የሚገኘውን ቆቦ ከተማ እና በትግራይ ክልል ዋጃ ከተማን መልሰው መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።
በአፋር ክልል በአውሲ ዞን 1 ጭፍራ እና አሳጊታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአፋር ታጣቂዎች ከትህነግ ጋር ውጊያ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ጥቅምት 24, 2014 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል አዲሀገራይ (ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን) አካባቢ ትህነግ የሚጠቀምበትን የአዲቡከራይ ማሰልጠኛ ማዕከል ላይ የአየር ጥቃት ፈጽሟል። በተመሳሳይ ጥቅምት 29 ላይ በራያ እና ሀጂ ሜዳ/ኪልዋ (የአፋር/ትግራይ ክልሎች ድንበሮች አቅራቢያ) በሚገኙ ሁለት የትህነግ ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት ፈፅሟል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ጥቅምት 29, 2014)።
ጥቅምት 21 ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔም ተብሎ የሚጠራው ኦኤልኤ) ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ የቡድኑ የሰሜን እዝ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዪ ዞን ሰንባቴ እና ከሚሴ መንቀሳቀሱን ገልጸዋል (Odaaኦዳ ታርቢ፣ ጥቅምት 21, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2014)። ከሚሴ ከኮምቦልቻ ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ይህ በትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ በተያዙ አካባቢዎች መካከል የጋራ ድንበር ፈጥሯል። ጥቅምት 26 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እና የትህነግ አጋሮቹ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴ ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 26, 2014)።
በትህነግ ቁጥጥር ስር ባሉ የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተነግሯል። ከሀምሌ ወር ጀምሮ በትህነግ ቁጥጥር ስር ባለው የአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በምግብ፣ የውሃ እና የመድሃኒት እጥረት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ከ110 በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 26, 2014)። ትህነግ ከተማውን መቆጣጠሩን ተከትሎ ከሰሜን ወሎ ከተማ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉት ተፈናቃዮች እጣ ፈንታ እስካሁን አልታወቀም። ደሴ ከተማ በትህነግ ቁጥጥር ከመውደቁ በፊት ከ300,000 በላይ ተፈናቃዮች መኖሪያ ነበረ (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መስከረም 12, 2014)። ከጥቅምት 8, 2014 ጀምሮ ምንም አይነት ሰብአዊ አቅርቦቶች ባልደረሱበት እና በትህነግ ቁጥጥር ስር ባለው የትግራይ ክልልም የሰብአዊ ሁኔታው በተመሳሳይ አስከፊ ነው (ኦሲኤችኤ፣ ጥቅምት 25, 2014)።
በአዲስ አበባ የተላለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ ባሉ የክልል ባለስልጣናት ተስተጋብቷል። ጥቅምት 25 ላይ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 25, 2014)። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች በየአካባቢያቸው የሰፈር የጥበቃ ቡድን እንዲያቋቁሙ አድርጓል። ይህም መንግስት ሁሉም ሰው አካባቢውን እንዲጠብቅ ያሳወቀውን ጥሪ ተከትሎ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ መካከል ያለው ጥምረት በኦሮሞ ቡድኖች መካከል የፖለቲካ ችግር እየፈጠረ ነው። የኦነግ ፓርቲ ኦሮሞዎች መንግስት የትህነግን ጥቃት ለመመከት እንዲሰባሰቡ ያቀረበውን ጥሪ እንዳይቀበሉ የጠየቀ ሲሆን ይህ ጥሪ “በሰው በሚከፈል መስዋትነት የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናትን በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው” ሲል ገልጿል (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ/አቦ፣ ጥቅምት 24, 2014)። ይልቁንም ፓርቲው ኦሮሞዎች እንዲጠናከሩና “የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሽግግር መንግሥት መዋቅር መሬት እንዲጠነክር” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ/አቦ፣ ጥቅምት 24, 2014)። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሽግግር መንግስት በኦነግ ፓርቲ እና በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሰኔ 18, 2013 ላይ የተፈጠረ ነው(ኦነግ፣ ሰኔ 18, 2014)። በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ፓርቲው የትህነግ ሃይሎችን “የኦሮሞን ህዝብ ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ እና ወደ ኦሮሚያ ክልል በወታደራዊ ሃይል ከመግባት እንዲቆጠቡ” ጠይቋል (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ/አቦ፣ ጥቅምት 24, 2014)።
ባለፈው ሳምንት ኦነግ-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቲን ከተማ 70 ሰዎችን አፍኖ ወስዷል ተብሏል። አፈናዎቹ የተፈጸሙት በአካባቢው ለወራት የዘለቀው እና በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰቦች መካከል የሚካሄደው ግጭት በከረረበት ወቅት ነው። በምዕራብ ሸዋ ዞን ባልተነገሩ ጥቂት የገጠር አካባቢዎች ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሞ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግቷል። በተጨማሪም ጥቅምት 20 ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በጊ እና ኮንዳላ ወረዳዎች ውስጥ ኦነግ-ሼኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ተዋግቷል። በግጭቱ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች ተገድለዋል። ከ3,000 በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 23, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ጥቅምት 21 ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጠቂ ቡድን ከግልገል በለስ ወደ ቻግኒ የሚጓዙ ሁለት መኪናዎችን የካር ፍተሻ ኬላ አካባቢ በማጥቃት ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን አቁስሏል። በማግስቱ በቡለን ወረዳ አዘም ቀበሌ ታጠቂ ቡድን አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ግለሰብ ተኩሶ ገድሏል። ጥቅምት 23 ላይ ታጠቂ ቡድን አወራጎዳና ካምፕ ዙሪያ ባለሶስት ጎማ የህዝብ ማመላለሻ (ባጃጅ) አጥቅቶ የአንድ ቤተሰብ አራት አባላትን ገድሏል። በቀጣዩ ቀን ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በአንደኛው ማንነቱ ያልታወቀ ታጠቂ ቡድን ማንደን ቀበሌ ውስጥ ከፓርዜት ወደ ዲባቴ ይጓዝ የነበረ መኪና አጥቅተዋል። ሁለት ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን ሶስት ቆስለው አራት ደግሞ ታፍነዋል። በሌላ ክስተት የጉምዝ ነፃነት ግንባር በፓርዜት ሶስት ገበሬዎችን ገድሏል። ታጣቂ ቡድኑ ከ100 በላይ ከብቶችን ለመዝረፍ ሞክሯል (የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 28, 2014)። በክልሉ ውስጥ በጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖች የሚደርሱ ጥቃቶች የተለመዱ ሲሆን ማንነታቸው ባልታወቁ ፈጻሚዎች ተብለው ከላይ የተገለጹት ጥቃቶች በተለያዩ የጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖች አባላት እንደተፈጸሙ ይጠረጠራል (የኢትዮጵያ ሪፖርተር፣ ጥቅምት 28, 2014)።
የኢትዮጵያ ሁኔታ እየተባባሰ እየሄደ ባለበት ወቅት ሰልፎችም ባሳለፍነው ሳምንት ጨምረዋል። ሰልፎቹ በመላው ሃገሪቱ የተካሄዱ ሲሆን ትህነግን፣ ኦነግ-ሸኔን፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት፣ እና በኢትዮጵያ ላይ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚዘገቡ አድሏዊ ዘገባዎችን አውግዘዋል። ጥቅምት 26 ላይ በዘጠኝ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ እነዚህ ሰልፎች ተካሂደዋል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 26, 2014)፤ በርካታ በመንግስት የሚደገፉ ሰልፎችም ተካሂደዋል። ተመሳሳይ ሰልፎች በድሬዳዋ ከተማ እና በጋምቤላ ክልል ተካሂደዋል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ጥቅምት 26, 2014)። ሰልፎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀጥለዋል።3 የአክሌድ መረጃ እስከ ጥቅምት 26 2014 ያለውን ብቻ ያሳያል። በሳምንቱ መጨረሻ የተካሄዱ ሰልፎች በቀጣዩ ሳምንት የመረጃ ቋት ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት በርካታ ጉልህ ፖለቲካዊ ለውጦች ነበሩ። ጥቅምት 24 ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ወራት ማለትም ከጥቅምት 24, 2013 እስከ ሰኔ 21, 2013 በነበረው ጊዜ የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የጋራ ጥናት አውጥተዋል (የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ጥቅምት 24, 2014)። ጥናቱ ሁሉም በግጭቱ የሚሳተፉ ወገኖች ሰብአዊ መብቶችን፣ የጦር፣ እና የስደተኞች ህጎችን ጥሰዋል እንዲሁም በደል ፈጽመዋል ሲል ደምድሟል። የኢትዮጵያ መንግስት “ከአንዳንድ የጥናቱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እርግጠኝነት ባይኖረውም” ጥናቱን እንደሚቀበለው ያሳወቀ ሲሆን (አብይ አህመድ አሊ፣ ጥቅምት 24, 2014) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ክሶቹን አጣርቶ ወንጀለኞችን ለህግ የሚያቀርብ እንዲሁም ለተጎጂዎች ካሳ እና የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ የሚሰጥ የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ለማቋቋም ቃል ገብተዋል (አብይ አህመድ አሊ፣ ጥቅምት 24, 2014)። ትህነግ የኢሰመኮን ገለልተኛ አለመሆን በመጥቀስ የጥናቱን መደምደሚያዎች እንደማይቀበል አስታውቋል። በተጨማሪም ምርመራው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላሳተፈ ነው ብሏል (ጌታቸው ኬ ረዳ፣ ጥቅምት 23, 2014)። የኤርትራ መንግስት ምርመራው “ብዙ ወሳኝ የህግ፣ ዘዴዊ፣ እና እውነታ ጉዳዮችን እንዲሁም የቀዳሚ ጉዳዮችን እና አለም አቀፍ ደንቦችን እና ተግባራትን ያነሳል” በማለት ምላሽ ሰጥቷል (የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 24, 2014)።
ጥቅምት 25 ላይ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያን ለሁለት ቀናት ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅት ፌልትማን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከመከላከያ ሚኒስትር፣ እና ከገንዘብ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተዋል። ፌልትማን ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች “ለሰላም እድል” እንዲሰጡ ጠይቀው አሜሪካ “ትህነግ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣትም ሆነ ለመክበብ የሚያደርገውን ማንኛውንም ሙከራ” እንደምትቃወም ተናግረዋል (ቪኦኦኤ፣ ጥቅምት 24, 2014)።
በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጥቅምት 26 ላይ በአሜሪካ የተሰባሰቡ ዘጠኝ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች4እነዚህ ዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር፣ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ሰራዊት፣ አለምአቀፍ የቅማንት ህዝብ መብትና ፍትህ ንቅናቄ/የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ኦነግ-ሸኔ፣ የሲዳማ ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር፣ የሶማሌ ክልል ተቃዋሚዎች እና ትህነግ ናቸው። “የተባበሩት የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት እና ኮንፌደራሊስት ኃይሎች ግንባር” የተባለ አዲስ ጥምረት ፈጥረዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 26, 2014)። የቡድኑ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በኃይልም ሆነ በድርድር ከስልጣን በማውረድ የሽግግር መንግስት መመስረት ነው። ይህንን ማስታወቂያ ተከትሎ የእነዚህ ቡድኖች ትክክለኛነት እና የእነሱ ውስጣዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ።
ሳምንታዊ ትኩረት: የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የአዲስ አበባ ወቅታዊ ሁኔታ
እንደተገለጸው ባለፈው ሳምንት የትህነግ ሃይሎች ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። በዚሁ ወቅት ኦነግ-ሸኔ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴን መቆጣጠሩን አስታውቋል። የእነዚህ ቦታዎች መያዝ የትህነግ ሃይሎች ወደ ደቡብ በ235 ኪሎ ሜትር ወደ ምትገኘው አዲስ አበባ ላይ ይንቀሳቀሳሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል። አንዳንድ አለማቀፍ ሚዲያዎች አዲስ አበባ በትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ ሃይሎች እንደተከበበች የተሳሳተ ዘገባ ሰርተዋል (ሲኤንኤን፣ ጥቅምት 25, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 26, 2014)። የኢንተርኔት መቆራረጥ የውጊያውን ትክክለኛ ቦታ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ቢያደርገውም የመንግስት ምንጮች ሰራዊታቸው ከተባባሪ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ጋር “በደሴ ግንባር” አከባቢዎች ከትህነግ ሃይሎች ጋር በመዋጋት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።
ትህነግ በአሁኑ ወቅት በሶስት የአማራ ክፍሎች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች እየተንቀሳቀሰ ይገኛል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በአውሲ ዞን 1 ጭፍራ እና አሳጊታ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ አፋር ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና አፋር ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ቀጥለዋል። የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ከኦሮሞ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር “በምዕራብ ሸዋ ዞን ባልተገለጹ ጥቂት የገጠር አካባቢዎች” እየተዋጉ ነው። ከዚህ ቀደም ኦነግ-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ እና ጉጂ ዞኖች ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ትህነግ እና ኦነግ-ሼ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባይሆንም በአዲስ አበባና ሌሎች ዋና ከተሞች ላይ ያለው ስጋት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
መንግስት ጥቅምት 23 ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግስት ሀይሎች ግለሰቦችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲፈትሹ እና እንዲያሰሩ ይፈቅዳል። እንዲሁም የጸጥታ ስጋት ካለ መንገዶችን መዝጋት እንዲሁም የአስተዳደር መዋቅር በከፊል ወይም በሙሉ ማገድ ወይም አስተዳዳሪዎችን መተካት ይፈቅዳል (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014)። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት መሳሪያ ያለውን ወይም በቀደምት ጊዜያት ወታደራዊ አገልግሎት የሰጠን ማንኛውንም ግለሰብ ወታራዊ ስልጠና እንዲወስድ እና ወደ ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲፈጽም አልያም መከላከያን መቀላቀል ካልቻለ መሳሪያውን እንዲያስረክብ ሊያዝ ይችላል። እስካሁን ድረስ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ሐረሪ፣ አማራ፣ እና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ የክልል ባለስልጣናት ተመሳሳይ ትዕዛዝ አውጥተዋል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ጥቅምት 28, 2014፤ አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 26, 2014)።
ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ከመስከረም 28, 2009 እስከ ሰኔ 2010 ድረስ የህወሓት የበላይነት በነበረበት የቀድሞው መንግስት ስር መንግስት ባወጃቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ስር ኖረዋል። በዚያ ጊዜ ውስጥ፣ የጸጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ስዎችን በእስር ቤቶች ውስጥ ገድለዋል (አልጀዚራ፣ መጋቢት 22, 2013)። በቅርቡ የተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ብዙዎች ላይ የጸጥታ ሃይሎች “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በማንነት ላይ የተመሰረተ” እስራት ፈጽመዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል (ኢሰመኮ፣ ጥቅምት 28, 2014፤ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ጥቅምት 29, 2014)። በጸጥታ ሃይሎች ላይ በተለይ የትግራይ ተወላጆችን እና የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ኢላማ የማድረግ ተጨማሪ ክስ ቀርቧል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 30, 2014)። መንግስት ይህን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያላቸው ብቻ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 29, 2014)። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ትህነግ አዲስ አበባን ለመያዝ መንቀሳቀሱን ያከበሩ፤ ወታደራዊ ስልጠና፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ፣ እና የውሸት መታወቂያ የወሰዱትን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል (Faፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ጥቅምት 27, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 29, 2014)።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቡድን ተደራጅተው በየአካባቢያቸው የማታ ቅኝት እያደረጉ ነው (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 26, 2014)። በሐረሪ እና ደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሌሊት የሰዓት እላፊ ገደቦች ተጥለዋል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ጥቅምት 28, 2014፤ ኢቢሲ፣ ጥቅምት 27, 2014)። በድሬ ዳዋ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና የጸጥታ ሴክተር ዩኒፎርሞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፤ ከ208 በላይ ሰዎች በአሸባሪነት ህጉ ተይዘዋል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ጥቅምት 27, 2014)። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ፍተሻ እና ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን መያዝ እንደቀጠለ ነው። ባለፈው ሳምንት በጋምቤላ ከትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 17 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 25, 2014)። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 98 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (ኢቢሲ፣ ጥቅምት 25, 2014)።
በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የጸጥታ ጉዳዮችን በመጥቀስ ከወሎ ዞኖች ወደ ዋና ከተማዋ የሚጓዙ ተፈናቃዮች ለማስቆም መንገዶችን ዘግተዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 26, 2014)። ወደ ከተማ መሄድ የሚችሉት የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ ያላቸው ብቻ ናቸው። በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያሉ ተፈናቃዮች እንዲመዘገቡና በተመደቡባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ብቻ እንዲቆዩ አዟል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 29, 2014)። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት መንግስት ለጊዜው የመታወቂያ ካርድ መስጠትን አግዷል።
ከምርጫ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ሁኔታዎች
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጪውን የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ ምርጫ በአዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አግዶታል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 26, 2014)። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፀጥታ ችግር ምክንያት ለተዘዋወረው የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ ምርጫ ጥቅምት ላይ አዲስ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ነበር። በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሚገኙ 17 የምርጫ ክልሎች ታህሳስ 21 ለማካሄድ አቅዶ ነበር (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 9, 2014)። አሁን ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ አይታወቅም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዴ ከታወጀ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማራዘም ይፈቀዳል።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 2014 አጠቃላይ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቀረቡ የምርጫ ክርክሮች ላይ ውሳኔውን አሳውቋል። ምርጫ ቦርድ ሙዬ ሙሉቄ የምርጫ ክልል (ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት) የምርጫ ካርዶች በድጋሚ እንዲቆጠሩ እና በሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ በ13 የምርጫ ጣቢያዎች (ለሶማሌ ክልል ምክር ቤት) አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 23, 2014)። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሌሞ 1 እና መስቃንና ማረቆ 2 የምርጫ ክልሎች (ለተወካዮች ምክር ቤት እና ክልል ምክር ቤት) በምርጫው እለት በነበረው ማስፈራሪያ እና እንግልት ምክንያት ምርጫ ቦርድ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ወስኗል። ይህም በመስቃንና ማረቆ 2 ምርጫ ክልል ምርጫው ለሶስተኛ ግዜ ይካሄዳል ማለት ነው (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ጥቅምት 23, 2014)። ይሁን እንጂ እነዚህ ምርጫዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መቼ እንደሚካሄዱ አይታወቅም።