ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
-
- አክሌድ ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ድረስ 94 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 346 ሟቾች ደግሞ መዝግቧል።
- ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ባለው ወቅት በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች በ250 የተዘገቡ ሟቾች አንደኛውን ቦታ የሚይዘው አማራ ክልል ሲሆን ኦሮሚያ ክልል በ93 የተዘገቡ ሟቾች ሁለተኛውን ቦታ ይይዛል።
- ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 49 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 182 ሟቾች ተመዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- በአፋር እና አማራ ክልሎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) መካከል የሚካሄደው ውጊያ በድጋሚ አገርሽቷል።
- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ባለው ጊዜ በትግራይ የአየር ጥቃቶችን የፈጸመ ሲሆን የአየር ጥቃቶቹ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ካወጀበት ሰኔ 2013 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄዱ ናቸው።
- ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)–ሸኔ ታጣቂዎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- በአማራ ብሄርተኞች እና የፌደራል መንግስቱ መሃል ያለው ውጥረት
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
እስከ መስከረም አጋማሽ በነበሩት ሳምንታት አንጻራዊ መረጋጋት ከታየ በኋላ በአማራ እና አፋር ክልሎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ትህነግ መካከል ውጊያ በድጋሚ ተቀስቅሷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። እያንዳንዱ ወገን ግጭቱን አነሳስቷል በማለት ሌላውን ከሷል። ትህነግ ወሩን በሙሉ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና የአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። የትህነግ ሃይሎች የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ማዕከል የሆነችውን ደሴ ከተማን እንዲሁም የዞኑ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችውን ኮምቦልቻ ከተማን መቆጣጠር ችለዋል። በአፋር ክልል በትህነግ እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይል በሚታገዘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል በአፋር ክልል የተካሄደው አብዛኛው ውጊያ የተካሄደው የአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞንን በሚያዋስነው የጭፍራ ከተማ ነበር። ከተማው የአማራ ክልልን ከሚሌ መገንጠያ እና ከጅቡቲ ወደብ ባሻገር በሚያገናኘው ዋና መንገድ ላይ ያለ ስትራተጂያዊ ስፍራ ነው።
ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ባለው ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአፋር፣ አማራ፣ እና ትግራይ ክልሎች በትህነግ ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ አድርጓል። በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ውርጌሳ ከተም እና በደቡብ ወሎ ዞን ወገልጤና ከተማ አካባቢ (ሁለቱም በአማራ ክልል) የአየር ድብደባ ተፈፅሟል። በተጨማሪም የአፋር ክልልን ከአማራ ክልል ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ተካሂደዋል (ሮይተርስ፣ መስከረም 29, 1014)። ሰኔ 2013 ላይ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ በወሰደው የአየር ጥቃት ከጥቅምት 8, 2014 እስከ 12, 2014 በነበሩት ቀናት በትግራይ አምስት የአየር ጥቃቶችን አድርሷል። ጥቅምት አጋማሽ ላይ በነበሩት ቀናት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተጨማሪ አምስት የአየር ጥቃቶች ያደረገ ሲሆን ሁለት በመቀሌ እንዲሁም በማይ ጸምሪ፣ አዳዋ፣ እና አጓሌ በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ አድርጓል።
በወሩ ውስጥ የትህነግ ሃይሎች በከባድ መሳሪያ ስላደረሷቸው ድብደባዎች ተዘግቧል። ጥቅምት 3, 2014 ላይ በአፋር ክልል ትህነግ ባደረሰው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ሰባት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መሞታቸው እና 15 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 3, 2014)። ጥቅምት 7, 2014 ላይ ትህነግ በሰሜን ጎንደር ዞን ዛሪማ ከተማ የሚገኝን ጥንታዊ መስጊድ በከባድ መሳሪያ በመምታት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ጥቅምት 8, 2014 አካባቢ የትህነግ ሃይሎች በሰሜን ወሎ ዞን አምባሰል ከተማ ባደረሱት የከፍተኛ መሳሪያ ድብደባ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች ሞተዋል። ጥቅምት 20 እና 21, 2014 ላይ ትህነግ ደሴ ከተማን አራት ጊዜ በከባድ መሳሪያ ደብድቧል።
ባለው ውጊያ ምክንያት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በእርሻ እና መሰብሰቢያ ወቅት ላይ የምግብ እጦት እና መፈናቀል አሳሳቢ የሆነ ሰብአዊ ሁኔታ አስከትለዋል። በሚቀጥሉት ወራት የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ወር የሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖችን ለመከላከል የአማራ ክልል መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በርካታ ግለሰቦች በደቡብ ወሎ ዞን ትህነግን ለመታገል የአማራ ታጣቂዎችን ተቀላቅለዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 11, 2014; የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥቅምት 8, 2014)። ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 ባለው ወቅት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች የቅጥር ዘመቻዎች ተካሂደዋል።
በኦሮሚያ ክልል በጉጂ፣ ምስራቅ ጉጂ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና የመንግስት ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 በሰሜናዊ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ኦነግ-ሸኔ ከአካባቢ የኦሮሞ ታጣቂዎች ጋር በመሆን ከአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። ከመስከረም 30, 2014 እስከ ጥቅምት 3, 2014 በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሮ አዲስ አለም ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ-ሸኔ እና የአማራ የብሄር ታጣቂዎች ተዋግተዋል። ጥቅምት 8 ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ከተማ የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ተዋግተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰብ መካከል ግጭቶች በየጊዜው ተከስተዋል። ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደሮች በማስፈለጋቸው የክልሉ ሃይሎች ወደ ሰሜን እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን ተከትሎ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አቅም በመቀነሱ እነዚህ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተባብሰዋል።
ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በአካባቢው በሚገኙ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ መሆናቸውን ከኦሮሚያ የሚወጡ በርካታ መረጃዎች ሲያመላክቱ ቡድኑ ክሱን ውድቅ አድርጓል። ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 በነበረው ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። ጥቅምት 2 ላይ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ ከላላ አካባቢ ጥቃት ሰንዝረዋል። ጥቅምት 8 እና 9 ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ ቤኮ ጅማ ቀበሌ መርካቶ አካባቢ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብሏል። ጥቅምት 16 እና 17 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ጎልቦ ቢቲም ቀበሌ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል አራት ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል። ጥቅምት 17 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ልጃቸውን ወደ ኦነግ-ሸኔ ልከዋል ያሉትን የአንድ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ማቃጠላቸው ታውቋል።
በመጨረሻም የጉሙዝ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ በሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲሁም በእነዚህ ቡድኖች እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል ውጊያዎች በመኖራቸው ከመስከረም 21, 2014 እስከ ጥቅምት 21, 2014 በነበረው ወቅት የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አለመረጋጋት ታይቷል። እንደክልሉ መንግስት ከሆነ ከ490,000 በላይ ተፈናቃዮች በክልሉ ውስጥ ይኖራሉ (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 26, 2014).
ወርሃዊ ትኩረት፡ በአማራ ብሄርተኞች እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለው ውጥረት
ባለፈው አመት በፌዴራል መንግስት እና ትህነግ መካከል ከጀመረው ውጊያ ጀምሮ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ከፌዴራል መንግስቱ የጦርነት ጥረቶች ጋር በቅርበት ሲተባበሩ ቆይተዋል። የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰነውን ግዛት የሚቆጣጠሩ ሲሆን ቀድሞ በትህነግ ስር የነበረው ግዛት ላይ ጥያቄ አላቸው። የክልሉ ልዩ ሃይሎች፣ የቀበሌ ታጣቂዎች፣ እና የፋኖ ታጣቂዎች1“ፋኖ” በአማራ ክልል ያሉ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎችን (በክልሉ መንግስት ከተደራጁ ታጣቂዎች በተቃራኑ) የሚያመለክት ቃል ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ከወጣት ወንዶች እና ሴቶች የተውጣጡ እና በመንደር/በጎረቤት መስመር የተደራጁ ናቸው። ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ከትህነግ ጋር እየተፋለሙ ይገኛሉ። እነዚህ የአማራ ክልል ሃይሎች ጦርነቱ ጥቅምት 2013 ላይ ሲጀምር በምዕራብ ትግራይ የሚገኘውን መሬት ከትህነግ ቁጥጥር ለማውጣት ቁልፍ ነበሩ። ትህነግ ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ ወዲህ ደግሞ የአማራ ሃይሎች በአብዛኛዎቹ ግንባሮች ዋና ሚና ተጫውተዋል።
ምንም እንኳን የተለያዩ የአማራ ፖለቲካ እና ወታደራዊ ሃይሎች ለጊዜው ከፌዴራል መንግስት ጋር የተቆራኙ ቢሆኑም ባለፈው ወር የአማራ ብሄርተኞች የፌደራል መንግስት የትህነግን ተጨማሪ ግስጋሴዎች ለማስቆም ባለመቻሉ አልያም ባለመፈለጉ ቅር በመሰኘታቸው በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ላይ ያሉ መሸራረፎች እየተስፋፉ መጥተዋል። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መንግስትን በብቃት ማነስ እና “ትህነግ ላይ ያለውን ወታደራዊ ብልጫ ወደውጤት መቀየር ባለመቻል” ከሶታል (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ጥቅምት 7, 2014)። አብን በፌደራል መንግስቱ ላይ ያቀረበው ክስ በአማራ ክልል ብዙዎች ላይ ያለውን ስሜት ያሳያል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቦታዎችን እያጣ በመጣ ቁጥር መንግስት የአማራ ህዝብን ደህንነት ዋስትና ሊሰጥ አይችልም ወይም አይሰጥም የሚል ስሜት እየተበራከተ መጥቷል።
ይህ አስተሳሰብ በመላ ሀገሪቱ በአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ተከትሎ (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ) ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ ከአጠቃላይ ምርጫው መጀመር በፊት በመላው አማራ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሰሙ ቅሬታዎችን የሚያስተጋባ ነው። ሚያዚያ 2013 ላይ በባህር ዳር ከተማ ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በመቃወም መፈክሮችን አሰምተው የብልጽግና ፓርቲ ፖስተሮችን አቃጥለዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ :- ከሚያዚያ 9, 2013 እስከ ሚያዚያ 15, 2013ን ይመልከቱ)። ብዙዎቹ እነዚህ ተቃዋሚዎች አሁን እንደ ታጣቂ አባል ሆነው ወደ ትግሉ የተቀላቀሉ ሲሆን ተመሳሳይ በፌዴራል መንግስት የመተው እና የመከዳት ስሜታቸውን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ከመታገል ይልቅ (አሁንም ድረስ ብዙዎች እንደሚሉት) አንዳንዶች “በህልውና፣ በማንነት እና ለዚህች ምድር በሚያምኑበት” ላይ ተመስርተው የመታገል ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ ሲሆን ይህም እንደ ጥንቱ ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር በጥብቅ የማይያያዝ ልዩ እና የተለየ የአማራ ብሔርተኝነት አመለካከት የበለጠ እውቅና እያገኘ እንዳለ ያሳያል (ቻናል 4 ዜና፣ ጥቅምት 18, 2014)።
የአማራ ብሄርተኝነት መነሳሳት የተመዘገበ ክስተት ሲሆን ደጋፊዎቹ “ከፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እና ማህበረ-ባህላዊ ጉዳዮች በጋራ መምጣት ጋር የሚገናኝ ሲሆን የእንግዳነት፣ ‘ሀገር አልባነት’፣ የደህንነት እጦት፣ እና የአማራ መኖር (አካላዊ እና ባህላዊ) ላይ የተጋረጠ አደጋ፣ እንዲሁም ድሀነት እና የኢኮኖሚ ተጸኖ ጋር ተያይዞ” የተፈጠረ ሲሉ ይገልጹታል። የአማራው ህልውና (አካላዊ እና ባህላዊ) እና አስከፊ ድህነት እና ኢኮኖሚያዊ መገለል” (ታዘበው፣ ጥር 12, 2013)። የፌዴራል መንግሥቱ የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር ያለውን ተመሳሳይነት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሟል። ይህ አሁን እየተቀየረ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ። የመንግስት እርምጃ አለመውሰድ እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ የፈጠረው ብስጭት አብይ ከተጠቀመበት የተለየውን የአማራ ብሄርተኝነት አጠናክሮታል።
በትህነግ ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታዎች ላይ ያሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንዳሉ ዘገባዎች ያሳያሉ። በዋግ ኽምራ ዞን ያሉ አስተዳዳሪዎች የምግብ ዋስትና እጦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ረሃብ በህብረተሰቡ ላይ መከሰት መጀመሩን ገልጸዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 26, 2014)። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ያወጣው ዘገባ የትህነግ ታጣቂዎች በንፋስ ማውጫ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራውችን ኢላማ በማድረግ “በቡድን ደፍረዋል፣ ዘርፈዋል፣ እና አካላዊ ጥቃት አድርሰዋል” ብሏል (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ጥቅምት 30, 2014)። በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ በግጭት ወስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች የኦሮሞ ታጣቂዎች እና የኦነግ- ሸኔ ሃይሎችን እርሻዎችንና እና የገጠሩን ማህበረሰብ በማጥቃት ከሰዋል።
በአማራ ብሔርተኞችና በፌዴራል ባለስልጣናት መካከል እየተጠናከረ ያለው ፍጥጫ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ወታደራዊ አጋርነታቸውን በማዳከም ትህነግ ለወታደራዊ ጥቅም እንዲያውለው ሊያደርግ ይችላል። የአማራ ብሄርተኞች ከፌደራል መንግስቱ ቡራኬ ውጭ ምን ያህል ወታደራዊ እርምጃ ሊወስዱ ወይም ከትህነግ ጋር ድርድር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ግልፅ አይደለም። የፋኖ ታጣቂዎች የአማራ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ተጽእኖ ያለባቸው ሲሆን በመደበኛነት የተደራጁ የክልል ልዩ ኃይልና የቀበሌ ታጣቂዎችን ደግሞ ማዕከላዊ መንግሥቱ በአማራ ክልል ባለው የብልጽግና ፓርቲ መዋቅር በኩል ይቆጣጠራል። ትህነግ ሲገፋ ግን የአማራ ብሄርተኞች ከባድ እርምጃ የሚደግፉበት ጫፍ ላይ ሊደርስ ይችላል።