ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ህዳር 17, 2014)1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,277
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 13,004
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 5,845
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከህዳር 11, 2014 እስከ ህዳር 17, 2014)2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 27
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 174
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 23
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ እና አፋር ክልል ውጊያዎች የቀጠሉ ሲሆን የመንግስት ሃይሎች በሳምንቱ መጨረሻ በአፋር ክልል በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ላይ ድሎች መቀዳጀታቸውን ዘግበዋል። የትህነግ ሃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እንዲሁም የአፋር ታጣቂዎች ጋር በአፋር ክልል ጭፍራ፣ ካሳ ጊታ እና ቡርቃ አካባቢዎች ጋር ተዋግተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ትህነግ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአማራ ታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ቀጥለዋል። ሸዋ ሮቢት፣ ባቲ፣ እና ከሚሴ ከተሞች ውስጥ እና ዙሪያ በርካታ ውጊያዎች እንደነበሩ ተዘግቧል። ትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ በሸዋ ሮቢት፣ መሀል ሜዳ (ሰሜን ሸዋ) እና ደጎሎ (ደቡብ ወሎ) ከመንግስት ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል።
ህዳር 11 እና 17 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም የአየር ድብደባ አድርጓል። ህዳር 11 በተደረገው ጥቃት የሰው ህይወት መጥፋቱም ሆነ አካል ላይ ጉዳት መድረሱ አልታወቀም። ህዳር 17 በነበረው የአየር ጥቃት ምንም ጉዳትም ሆነ ሞት አልተዘገበም (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 17, 2014)።
ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰልፎች አካሂደዋል። ህዳር 16 ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአሜሪካ እና እንግሊዝ ኤምባሲዎች ፊት ለፊት ተሰብስበው “የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማፍረስ” የተደረጉ ሙከራዎችን በሰልፍ ተቃውመዋል (አፍሪካ ኒውስ፣ ህዳር 16, 2014)። የምዕራቡ ዓለም ለትህነግ ያደርጋሉ ተብለው የሚታመኑ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎች በተለይም በኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች ነዋሪዎች ዘንድ ብስጭት ጨምረዋል። በኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዙ መፈክሮችን የያዙ እና በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ግጭት አስመልክቶ የሚሰሩ “የውሸት” ዘገባዎችን የሚቃወሙ ሰልፎች ደቡብ አፍሪካ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካን፣ እና የተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች “ኖ ሞር” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 12, 2014፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 16, 2014)።
በአማራ እና በአፋር ክልል የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በአፋር ክልል ከ100,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ይገኛሉ (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ህዳር 18, 2014)። የትህነግ ሃይሎች ደሴን እና ኮምቦልቻን ከተቆጣጠሩበት ጥቅምት 22 ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን (ለምሳሌ በደብረ ብርሃን) እና የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ወደሆነችው ባህር ዳር ከተማ ለመሄድ ተገደዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ውስጥ በስድስት ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ወደ 9,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች አሉ (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ህዳር 16, 2014)። እነዚህ ተፈናቃዮች የትህነግ ታጣቂዎች በበርካታ የከተማ ማእከላት በኩል ወደ ደቡብ ሲጓዙ በተደጋጋሚ ወደተለያዩ ቦታዎች ለመሰደድ ተገደዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ መቀሌ የሚያደርገውን በረራ ከአንድ ወር በፊት ካቆመ በኋላ ባለፈው ሳምንት ህዳር 14 ላይ በድጋሚ ጀምሯል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ህዳር 16, 2014፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። ባለፈው ሳምንት ወደ መቀሌ ሁለት በረራዎች ነበሩ። በተጨማሪም 160 የሰብአዊ ምግብ የያዙ የጭነት መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል ደርሰዋል (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል ሰመራ በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚሄዱ የሰብአዊ እርዳታ እቃዎችን የጫኑ 353 ከባድ መኪኖች አሉ (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014። እንደ መንግስት መረጃ ከሀምሌ እስከ ጥቅምት 2014 ድረስ ሰብአዊ አርዳታ የጫኑ 1,114 መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ሲሆን እርዳታውን ካደረሱ በኋላ የተመለሱት ግን 322 የጭነት መኪናዎች ብቻ ናቸው (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ከኦሮሚያ የክልል ሃይሎች እና ከመንግስት ወታደሮች ጋር ውጊያ ማድረግ ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ወገኖች በለካ ዱለቻ ወረዳ (ምስራቅ ወለጋ) እና ዩብዶ ወረዳ (ምዕራብ ወለጋ) ተዋግተዋል። ኦነግ-ሸኔ እነዚህን ሁለት አካባቢዎች መቆጣጠሩን ተናግሯል (ኦኤምኤን፣ ህዳር 12, 2014)። ህዳር 14 ላይ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በሚዳ ቀኝ ወረዳ (ምዕራብ ሸዋ ዞን) ሶስት ባለስልጣናትን አድፍጠው ገድለዋል። በጥቃቱ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪም ቆስለዋል። የቡድኑ ቃል አቀባይ ታጣቂዎቹ እጃቸው አለበት መባሉን አስተባብሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 14, 2014)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል በመንጌ እና ሸርቆሌ ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር ተዋግተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በውጊያው ቢያንስ 30 የሚሆኑ ያልታወቀው ቡድን አባላትን መግደላቸውን ገልጸዋል (ኢሳት፣ ህዳር 13, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዳር 15 ላይ የኢትዮጵያ አስራ አንደኛው ክልል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል – ይፋዊ የምስረታ ስነስርአት አካሂዷል። መስከረም 20 ላይ የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ እና ሸካ ዞን ነዋሪዎች በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች ሥር መተዳደር ከመቀጠል ይልቅ አዲስ የኢትዮጵያ ክልል ለመመሥረት በሕዝበ-ውሳኔ ወስነዋል። አዲሱ ክልል ዋና ከተማው ቦንጋ ይሆናል። ይሁን እንጂ የቤንች ሸኮ ዞን ተወካዮች ውሳኔው ዋና ከተማ ለመምረጥ የተደረሰውን የስምምነት ሂደት የተከተለ አይደለም ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል (ኢሳት፣ ህዳር 11, 2014፤ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 9, 2014)።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በይፋ በተመሰረተበት ማግስት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የመንግስት ሰራተኞችን ጭኖ በአዲሱ ክልል በኩል ሲጓዙ የነበረን መኪና በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ የኪ ወረዳ ሰላም በር ቀበሌ ላይ አድፍጠው በማጥቃት አራት የጸጥታ ሃይሎች ሲገደሉ ስድስት የመንግስት ሰራተኞች ቆስለዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሸካ ዞን የአስተዳደር ማእከሉን ከከማሻ ወደ ቴፒ ከተማ በመቀየር የሁከት ታሪክ ባለበት ክልል ውጥረት ፈጥሯል። በሸካ ዞን የሚገኘው የመንግስት ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይህ ጥቃት ከዚህ ውዝግብ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ እንደማይታሰብ ገልጸዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 15, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት: የኢትዮጵያ የመረጃ ጦርነት
በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ቀናት የወጡ ዋና ዋና ዜናዎች የኢትዮጵያ ወታደሮች ትህነግ ላይ የወሰዱትን የተሳካ ጥቃት አጉልቶ አሳይቷል። በሳምንቱ ማገባደጃ ላይ የመንግስት ሃይሎች በኮምቦልቻ-ባቲ-ሚሌ መንገድ ላይ የካሳ ጊታ እና የቡርቃ ከተሞችን እንዲሁም በሰሜን በኩል ጭፍራ ከተማን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል (አልጀዚራ፣ ህዳር 19, 2014)። እንደ መንግስት ዘገባ የኢትዮጵያ ወታደሮች ባደረጉት ልዩ ዘመቻ በሁለቱ ግንባሮች 12 ከፍተኛ የትህነግ ወታደራዊ አመራሮች ተገድለዋል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ህዳር 15, 2014)።
እነዚህ የቅርብ ጊዜ ክንውኖች መንግስት ከትህነግ ጋር ባደረገው ጦርነት ያለ ትልቅ ለውጥ ያመለክታሉ። ወታደራዊ ድሎችን ወደ ጎን በመተው መንግስት ትህነግን በውጊያ ለመታገል ፍላጎት ያላቸውን የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ፖለቲከኞች፣ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂትነት ያላቸው የረዥም ርቀት ሯጮችን ጭምር የሚያደርጉትን የፕሮፓጋንዳ ለመጠቀም እየሞከረ ነው (ቢቢሲ፣ ህዳር 16, 2014)። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃይሎችን “ከግንባር” ለመምራት መወሰናቸውን ህዳር 15 ላይ ያሳወቁ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የመንግስት ስርጭቶች ላይ ወታደራዊ አልባሳትን አድርገው በግንባር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች ጋር ሲገናኙ ታይተዋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 21, 2014)። ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመንግስት ስራ ተረክበዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 15, 2014)።
በኢትዮጵያ ጦርነት በብዙ ግንባሮች እየተካሄደ ሲሆን ከነዚህም መካከል ስለ ግጭቱ መረጃዎችን እና ትርክቶችን መቆጣጠር ይካተታል። ሳምንቱን በተለያዩ የተወዛገቡ አቤቱታዎች እና ምላሾች የተበሳጨው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለጋዜጠኞች በማብራራት “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያልተፈቀደላቸው አካላት በጦር ግንባር እንቅስቃሴዎች ያልተረጋገጡ እንቅስቃሴዎችን እንዳያሳውቁ ይከለክላል” ሲል አስታውቋል (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጋዜጠኞች “የውሸት መረጃ” እንዳያሰራጩ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 15, 2014)። በተጨማሪም የአሜሪካ ኤምባሲ ህዳር 15, 2014 ላይ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤምባሲው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ የአየርላንድ ኤምባሲ አራት ዲፕሎማቶችም አገሪቷን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ አስተላልፏ።
በጦርነቱ ወቅት የመረጃ ቁጥጥር ለኢትዮጵያ መንግሥት ከውስጥም ሆነ የውጪ ህዝብ ግንኙነት አንፃር አስፈላጊም ጎጂም ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት በግጭቱ መጀመሪያ ላይ ለወራት የኤርትራ ኃይሎች መኖራቸውን እና የፈጸሙትን ለመደበቅ ሞክሯል (ቢቢሲ፣ ሚያዚያ 15, 2013)። መረጃ ላይ የተጣለው እገዳ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ በትግራይ ክልል ከሚገኙት ትላልቅ ከተሞች አንዱ በሆነው አክሱም ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት እና ከአንድ አመት በፊት በጠራራ ፀሀይ የተፈጸመው ግድያ አጠያያቂ ሆኖ ቆይቷል (ቢቢሲ፣ የካቲትር 19, 2014)። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ለጣለው ማዕቀብ ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ የኤርትራ ተሳትፎ ነው (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ህዳር 3, 2014) እንዲሁም ለትግራይ ነዋሪዎች ቁጣ መንስኤ ሆኗል (ትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ ጥር 12, 2013)።
ሆኖም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለአስርት አመታት በስልጣን ላይ ለነበረው ለትህነግ ያደላል የሚለው የመንግስት አመለካከት የተወሰነ ድጋፍ ያለው ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ሾልኮ የወጣ የዙም ስብሰባ የቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣናት ከትህነግ ሃላፊዎች ጋር ሲገናኙ እና ቡድኑን እንደሚደግፉ ሲገልጹ አሳይቷል (ኤሊዘር፣ ህዳር 15, 2014)። ምንም እንኳን በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ግለሰቦች በአሜሪካ መንግስት ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሃላፊነት ቦታዎች ይዘው እያገለገሉ ባይሆኑም ስብሰባው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ብዙዎች አሜሪካ ገለልተኛ ላለመሆኗ በቂ ማስረጃ ነው። ይህም አብይ እና መንግሥታቸው “የምንገነዘበው የሕዝብ ሥልጣን” እንዳላቸው እና አሜሪካ “ከትህነግ ጎን ቆማለች የሚለው ፍጹም ቅዠት ነው” ከሚለው የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን መልእክት ጋር በቀጥታ እንደመቃረኑ የግለሰቡን ሥራ ከባድ ያደርገዋል (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ህዳር 14, 2014)።
በመንግስትም ይሁን በትህነግ የሚገኙ ወታደራዊ የበላይነቶች የኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እንዱ በሌላው ላይ ያለውን አቋም የሚያጠናክር እና ውይይትን የበለጠ የሚያርቁ ይመስላሉ። ሁለቱም ወገኖች ጦርንተ መፍትሄ ነው ብለው ያመኑ የሚመስሉ ሲሆን አስተያየቶቹ እየተጠናከሩ መጥተዋል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ትህነግ የመረጃ ፍሰትን ለመገደብ እርምጃ ወስደዋል። ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ የትምህርት እና የሲቪል ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ እና በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ግጭት መንስኤ በጥልቀት ማስረዳት የሚችሉ ድምፆች በውስጥ እና በውጭ አካላት አንዱን ወይም ሌላውን ይደግፋሉ በሚል ወደ ጎን ተደርገዋል። በመሆኑም ሁለቱንም ወገኖች ወደ ድርድር ለማምጣት አሁንም ድረስ አንዳንድ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁን ባሉበት ሁኔታ ጥረቶቹ ሊሳኩ ባለመቻላቸው ግጭቶች ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።