በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ታህሳስ 1, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,340
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 13,494
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,037
በቁጥር (ከህዳር 25, 2014 እስከ ታህሳስ 1, 2014) 2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 22
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 155
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 57
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባሳለፍነው ሳምንት የፌዴራል መንግስቱ እና ተባባሪ ሃይሎች በሰሜናዊ የአማራ ክልል ክፍል የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የመጀመሪያው ምዕራፍ ኦፕሬሽን በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል” (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ህዳር 29, 2014) ካሉ በኋላ ከጦር ሜዳ ወደ ጽ/ቤታቸው ለተወሰኑ ቀናት ተመልሰዋል (ኦል አፍሪካ፣ ታህሳስ 4, 2014)። በሰሜን ወሎ በጋሸና ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ከተራረፉ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ) ታጣቂዎች ጋር አልፎ አልፎ የሚካሄዱ ውጊያዎች ተዘግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ጦርነቱ እየቀነሰ ሲሄድ የዘረፋ እና የፆታዊ ጥቃት ክስተቶች ተዘግበዋል፤ የጅምላ መቃብሮችም ተገኝተዋል። የትህነግ ሃይሎች በገለልተኛም ሆነ በመንግስት ሚዲያዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን በመግደል እና አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ-ልማቶችን በማውደም ተከሷል። ትህነግ በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸማቸው ድርጊቶች ከዚህ በታች ባለው የሳምንታዊ ትኩረት ክፍልበሰፊው ይብራራል።
በሌላ በኩል በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከ1,500 በላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመጣስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች እና በፌደራል እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ሃይሎች መካከል አጭር ግጭት እንደነበረ ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ እና ጉጂ ዞኖች የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ እና ታጣቂዎች ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል (የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ፣ ህዳር 29, 2014)። በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ በርካታ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች ተፈናቅለዋል። በምዕራብ ኦሮሚያ በኦሮሞ እና አማራ ብሄር ታጣቂዎች መካከል በአከራካሪ አካባቢዎች ላይ ከባድ ግጭት ቀጥሏል። የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር እንዲሁም አናሳ ብሄረሰቦችን በማጥቃት የሚከሰስ ሲሆን ቡድኑ ብዙ ጊዜ ይህንን ውድቅ ያደርጋል ይልቁንም የመንግስት ደጋፊ ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደርጋል።
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ ኢንሴኖ ከተማ ውስጥ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ አንድ ሰው ገድሏል። በማግስቱ ማንነታቸው ያልታወቁ ሁለት ታጣቂዎች በአካባቢው ተዋግተዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የዚህ ግጭት ምክንያት አይታወቅም። ከሁለት አመት በፊት በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ ወረዳዎች መካከል የድንበር ግጭት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን በኋላ በሃገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች እልባት አግኝቷል (ኢሳት፣ ህዳር 30, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች ትህነግን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ሲሆን ቡድኑ ለመንግስት እጁን እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች “ትህነግ አይወክለንም። ኩሩ ኢትዮጵያውያን ነን። ትግሬዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው”ን ጨምሮ ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ነበር (የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ፣ ህዳር 26, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡- መንግስት እና አጋሮቹ የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ አማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የተጋለጡ ጥቃቶች
ባለፈው ሳምንት ለፌደራል መንግስት ታማኝ የሆኑ ሃይሎች በአማራ ክልል ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሃይቅ፣ እና ውጫሌ ከተሞችን ጨምሮ አስር ከተሞችን እንደገና መቆጣጠር ችለዋል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ህዳር 27, 2014፤ የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ህዳር 29, 2014)። ሁለቱም ወገኖች የቁጥጥር ለውጡ እንዴት እንደመጣ የሚጋጩ አስተያቶች ሰጥተዋል። የመንግስት ሃይሎች ቦታዎቹን በውጊያ ማስለቀቃቸውን ሲገልጹ የትህነግ ሃላፊዎች ደግሞ ሃይላቸው ወደ ትግራይ ክልል ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረጋቸውን ተናግረዋል (ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ ህዳር 26, 2014)። በሳምንቱ ውስጥ በጋሸና እና ላሊበላ ዙሪያ ቀሪ የትህነግ ታጣቂዎች በማጥፋቱ ሂደት በመንግስት ሃይሎች እና ትህነግ መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል።
የመንግስት ሃይሎች እነዚህን ቦታዎች እንደገና ከተቆጣጠሩ በኋላ በትህነግ የተፈፀሙ ግድያዎችን፣ አስገድዶ መድፈሮችን፣ እና የንብረት ውድመቶችን የሚያሳዩ ዘገባዎች መውጣት ጀመሩ። የመገናኛ መስመሮች ወደ ነበሩበት የተመለሱት ገና በቅርብ ጊዜ በመሆኑ በግጭት ውስጥ ያልተሳተፉ ግለሰቦች ሞት እና አስገድዶ መድፈር ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን አልታወቀም። ነገር ግን በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ሁከትና ብጥብጥ የተስፋፋ እንደነበር ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር እየገሰገሰ በነበረበት ወቅት የትህነግ አባላት 10 ወጣቶችን በጥይት ተኩሰው ከገደሉ በኋላ በኮምቦልቻ ከተማ በሚገኘው የቱርክ ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ በእሳት ማቃጠላቸው ተነግሯል (ኢሳት፣ ህዳር 29, 2014)። ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ እና አረጋውያን ሴቶች ላይ ያነጣጠሩ ተመሳሳይ ጥቃቶች ተዘግበዋል። ባለፈው ሳምንት በጋሸና፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ እና ኮምቦልቻ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 30, 2014)።
በተጨማሪም የአማራ እና አፋር ክልሎች በትህነግ ቁጥጥር ስር በነበሩበት ወቅት በግል ንብረቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጤና ማዕከሎች፣ እና ሃኪም ቤቶች ላይ ደረሱ ዝርፊያዎች እና ውድመቶች እየታወቁ ነው። መንግስት ባለፈው ሳምንት እንደገለጸው የትህነግ ሃይሎችን 10 የምግብ ማቀነባበሪያ፣ 11 የቆዳና ጨርቃጨርቅ፣ ሶስት የብረታ ብረት፣ 11 የግብርና ማብላያ፣ እና 10 የኬሚካል ኢንዱስትሪዎችን ዘርፈዋል እንዲሁም አውድመዋል (ኢሳት፣ ህዳር 28, 2014፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 4, 2014)። ኮምቦልቻ ከተማ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ማዕከል ነች። በአፋር ክልል የትህነግ ሃይሎች በአራት የኢንዱስትሪ ህንፃዎች ላይ ዘረፋና ጉዳት አድርሰዋል (ኢሳት፣ ህዳር 28, 2014)።
በአማራ ክልል አምስት ዞኖች እስከ ህዳር 18 ድረስ 1,660 ትምህርት ቤቶች በትሀነግ ሃይሎች የተዘረፉ እና የወደሙ መሆናቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ 1,660 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 277ቱ ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ የተቀሩት ደግሞ በከፊል ወድመዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 18, 2014)። በአፋር ክልል 455 ትምህርት ቤቶች በትህነግ ታጣቂዎች መዘረፋቸውና መውደማቸው ተረጋግጧል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 18, 2014)።
የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው እስከ ህዳር 28 ድረስ በአማራ እና አፋር ክልሎች 34 ሃኪም ቤቶችን ጨምሮ ከ2,219 በላይ የጤና ማዕከላት በትህነግ ሃይሎች ተዘርፈዋል እንዲሁም ወድመዋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 28, 2014)። በየአካባቢው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ የነበሩ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ዋና ዋና ሃኪም ቤቶች በዘረፋ እና ውድመት ምክንያት አገልግሎት መስጠት አልቻሉም (የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ታህሳስ 4, 2014፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 26, 2014፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 28, 2014፤ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 3, 2014)።
በተጨማሪም በአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ሕንፃዎች በትህነግ ታጣቂዎች ተዘርፈዋል፣ ወድመዋል። ዘገባዎች የትህነግ ሃይሎች የሃይማኖት መሪዎችን መግደላቸውን እና ከአካባቢው ቤተክርስትያን ቀሳውስት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦችን እንደደፈሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 4, 2014፤ ኢሳት፣ ታህሳስ 4, 2014)።
እነዚህ የዘረፋ፣ ውድመት፣ ግድያ፣ እና አስገድዶ መደፈር ዘገባዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ብዙዎች የትህነግ ሃይሎች ዋና አላማ ከተማዎችን ማፍረስ እና የበቀል እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ያላቸውን አመለካከት አረጋግጧል። ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች እንደተናገሩት የተያዙ የትህነግ ታጣቂዎች በአፋር እና አማራ ክልሎች ዘረፋ፣ ውድመት፣ እና መድፈር እንዲፈጽሙ ትእዛዝ መቀበላቸውን አምነዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ህዳር 10, 2014)።
ይህ በትህነግ ደርሰዋል የተባሉ ጥቃቶች እና ውድመቶች ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የፌደራል መንግስትን ለመደገፍ ግለሰቦችን ለማሰባሰብ እና ለማደራጀት እየዋለ ነው። በተጨማሪም አሜሪካ እና አውሮፓ መንግስት ከትህነግ ጋር እንዲደራደር ግፊት በማድረግ ኢትዮጵያን አሳንሰዋል የሚሉ ጸረ-ምዕራባውያ ስሜታቸው እንዲጠናከር አድርጓል። ሚያዚያ 28, 2013 ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትህነግን በአሸባሪ ድርጅትነት ፈርጇል (አፍሪካኒውስ፣ ሚያዚያ 28, 2013)። ለብዙዎች የዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ግድያ ዘገባዎች እንደ የጅምላ እስራት እና የሚዲያ ቁጥጥር የመሳሰሉ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ተቀባይ ያደርጋል። እነዚህ ዘገባዎች የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባርን ጨምሮ ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ፀረ-መንግስት ቡድኖች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድረዋል (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 26, 2014)።
በትህነግ ሃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የጥፋት እና መብት ረገጣዎች በመላ ሀገሪቱ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እምነት እንዲታ አድርጓል። በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ የተደረገ ዘገባ በአንድ ሳምንት ውስጥ አንድ ሺህ ሰዎች በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ግለሰቦች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታሰራቸውን አሳውቋል (ዲደብሊው፣ ህዳር 7, 2014)።
በአማራም ሆነ አፋር ክልሎች በትህነግ ታጣቂዎች የተፈጸሙ ከባድ በደሎች ዝርዝር መውጣት በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ማህበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት መሰበሩ ግልጽ ነው። ከወደሙ መሠረተ ልማት አውታሮች ጎን ለጎን በብሔር ብሔረሰቦችን መካከል ሰላም ያስከብሩ የነበሩ የሲቪል ማኅበራት ተቃራኒ ጥጎች ይዘዋል። በፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሁም በዕርቅ ዙሪያ ከባድ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል።