ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
- አክሌድ ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014 ድረስ 158 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን 705 ሟቾች ደግሞ ተመዝግበዋል።
- ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014 ባለው ወቅት በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን በክልሉ 243 ሟቾች ነበሩ። አፋር ክልል በ200 እንዲሁም አማራ ክልል በ199 አካባቢ የተዘገቡ ሟቾች ቁጥር ይከተላሉ።
- ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 127 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 557 ሟቾች ተመዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) በአማራ ክልል ዋግ ሀመራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሚያ ልዩ፣ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖችን ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹን ቦታዎች ተቆጣጥሮ ነበር። በወሩ መገባደጃ ላይ የመንግስት ሃይሎች በጣም ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን መልሰው ተቆጣጥረዋል።
- በወሩ መጀመሪያ ላይ በትህነግ ሃይሎች እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ አፋር ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአፋር ታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ ውጊያዎች በአፋር ክልል ካሳጊታ፣ ጭፍራ፣ እና ቡርቃ ተመዝግበዋል።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ውጊያ አካሂዷል።
- ትህነግና ኦነግ-ሸኔን እንዲሁም የውጭ ሀገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በመላ ሀገሪቱ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል።
- የትህነግ ሃይሎች በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ እና ቡርቃ ከተሞች ከተቆጣጠሩ በኋላ በዚህ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
- ብዙ ሰዎች ከትህነግ ወይም ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ታስረዋል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባር
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በጥቅምት ማገባደጃ ላይ የትህነግ ሃይሎች በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ተቆጣጥሯል። ከትህነግ ጋር ጥምረት የፈጠረው የኦነግ-ሸኔ አባላት በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ የሚገኙትን ሳንባቴ እና ከሚሴ ከተሞችን ተቆጣጠሩ (ኦዳ ታርቢ፣ ጥቅምት 21, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2014)። ይህም በመላ ሀገሪቱ የትህነግ ሃይሎች ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመንቀሳቀስ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን እና ሌሎች አካባቢዎችን አደጋ ላይ ይጥላሉ የሚል ስጋት ፈጠረ። በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግስቱ ጥቅምት 23 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጸጥታ ሃይሎች ግለሰቦችን ያለፍርድ ቤት ማዘዣ መፈተሽ እና ማሰር እንዲችሉ ይፈቅዳል። እንዲሁም መንገዶችን መዝጋት እና የአስተዳደር መዋቅሮችን በከፊል ወይም በሙሉ መታገድ እና የጸጥታ ስጋት ካለ አስተዳዳሪዎችን መተካት ያስችላል (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014)። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር መንግስት ማንኛውም መሳሪያ የያዘ ወይም ቀደም ሲል ወታደራዊ አገልግሎት የሰጠ ሰው ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስድ እና ወደ ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲገባ ማዘዝ ይችላል፤ መንግስት ውትድርና መቀላቀል ያልቻሉትን መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ማስገደድ ይችላል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ብዙ ሰዎች ከትህነግ ወይም ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው ተከሰው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ታስረዋል። በተጨማሪም የመንግስት አካል የሆነው የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለግል መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መዘገብ ያለውን አንድምታ እንዲያጤኑት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር “መገናኛ ብዙሃን ከልማዳዊ የዘገባ አቀራረብ በመውጣት በምትኩ ኢትዮጵያውያን እያጋጠሟቸው ካሉ ችግሮች እንዲያልፉ በሚረዱ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል” (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 3, 2014)። በተጨማሪም ባለስልጣኑ ለሲኤንኤን፣ ቢቢሲ፣ ሮይተርስ፣ እና አሶሼትድ ፕሬስ “ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ” አለበለዚያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የመንቀሳቀስ ፈቃዳቸውን እንደሚሰርዝ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጽፏል (የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፣ ህዳር 10, 2014)። የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር በውጭ ሚዲያዎች የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች “በአገራቸው ላይ የሚነዛውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንዲቃወሙ” እና ሀገራቸው ያለችበትን እውነታ ለአለም እንዲያሳዩ ጠይቀዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 3, 2014)።
በወሩ መገባደጃ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን የተመለከቱ መረጃዎችን ፈቃድ የተሰጣቸው ሰዎች እና ተቋማት ብቻ እንዲያጋሩ ወስኗል። በተጨማሪም ህዳር 15, 2014 ላይ የአሜሪካ ኤምባሲው የሽብር ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ ማስጠንቀቂያው መሬት ላይ ካለው እውነት የራቀ ነው ያለው መንግስት ለኤምባሲው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 16, 2014)። የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ የአየርላንድ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ አራት ዲፕሎማቶች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ አስተላልፏል።
ህዳር 15, 2014 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን “ከግንባር” ለመምራት መወሰናቸውን አስታወቁ (ኢቢሲ፣ ህዳር 21, 2014)። ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንግስትን የመቆጣጠር ስራ ተረክበዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 15, 2014)። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአማራም ሆነ አፋር ክልሎች የሚገኙ በርካታ አካባቢዎችን መንግስት መልሶ መቆጣጠር ችሏል። በወሩ መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቹ በአፋር ክልል ጭፍራ፣ ካሳ ጊታ፣ እና ቡርቃን ተቆጣጥረዋል። በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን በባቲ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ተራራማ ቦታዎችን መንግስት በድጋሚ ተቆጣጥሯቸዋል።
በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች እየተስፋፉ ሲሄዱ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ቀውስም ጨምሯል። ከሃምሌ ጀምሮ በትህነግ ቁጥጥር ስር የነበረው በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ዞን በዚህ ወቅት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ከ110 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በምግብ፣ በውሃ፣ እና በመድሃኒት እጥረት ለህልፈት ተዳርገዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 26, 2014)። በተጨማሪም በአማራ እና አፋር ክልሎች በትህነግ እና ኦነግ-ሸኔ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ መድፈሮች፣ እና የንብረት ውድመቶችን የተመለከቱ ዘገባዎች ወጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለው ግጭት ምክንያት በአማራ ክልል ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ህዳር 28, 2014)። እንዲሁም በአፋር ክልል “ከ17 ወረዳዎች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አፋጣኝ የሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል እንዲሁም 376,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል” (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ህዳር 28, 2014)። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ መሰረት “በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት 9.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል” (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ህዳር 23, 2014)።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥቅምት 13 ላይ አቁሞት የነበረውን በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ መቀሌ የሚያደርገውን በረራ ህዳር 14 ላይ በድጋሚ ጀምሯል (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ህዳር 16, 2014፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። በወሩ መጨረሻ ላይ “በክልሉ ያለው የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት የተወሰነ ተሻሻለ” (የተመድ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ህዳር 23, 2014)። ወደ ህዳር መጨረሻ ላይ 160 የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል የደረሱ ሲሆን 353 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በአፋር ክልል ሰመራ በኩል ወደ ትግራይ ክልል እያመሩ ነበር (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)። እስከ ህዳር 28, 2014 203 የጭነት መኪናዎች ትግራይ ደርሰዋል (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ህዳር 28, 2014)። እንደ መንግስት ከሆነ ከሃምሌ 2013 እስከ ጥቅምት 2014 ድረስ ወደ 1,114 የሚጠጉ የጭነት መኪናዎች ሰብአዊ እርዳታ ይዘው ወደ ትግራይ ክልል ገብተዋል። ሰብአዊ እርዳታውን ካደረሱ በኋላ የተመለሱት ግን 322 የጭነት መኪናዎች ብቻ ናቸው (የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት፣ ህዳር 21, 2014)።
በዚህ ወር ትህነግን፣ ኦነግ-ሸኔን፣ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት፣ እና አለም አቀፍ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚሰሯቸውን የተዛቡ ዘገባዎችን የሚያወግዙ 27 ሰልፎች ተካሂደዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። እነዚህ ሰልፎች በጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ተካሂደዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተቃውሞ የተካሄደው በኦሮሚያ ክልል ነበር። በአዲስ አበባ ህዳር 16, 2014 ላይ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የከተማዋ ነዋሪዎች የአሜሪካ ኤምባሲ ፊትለፊት በመገኘት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን የአሜሪካ መንግስትን በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ በመግባት እና የሃሰት መረጃ በማሰራጨት ከሰዋል። ቡድኑ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲም ተጉዟል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ህዳር 16, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል ውጊያዎች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወሩን ሙሉ ቀጥለዋል። በምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና ከኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በወሩ መጀመሪያ ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቲን ከተማ 70 ሰዎችን አፍነው ወስደዋል በሚል ተከሰዋል። እገታው የተከሰተው በአካባቢው ለወራት በዘለቀው በኦሮሞ እና በአማራ ማህበረሰብ መካከል ከፍተኛ ውጊያ በሚካሄድበት ወቅት ነው። ህዳር 10 ላይ በመቱ ስላሴ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በአማራ ታጣቂዎች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ በተባለ ቦታ የአማራ ታጣቂዎች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው ቢያንስ 20 ሰዎች ሞተዋል። ህዳር 14 ላይ ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚዳ ቀኝ ወረዳ ሶስት ባለስልጣናትን አድፍጠው ገድለዋል። በጥቃቱ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪም ቆስለዋል። የቡድኑ ቃል አቀባይ ታጣቂዎቹ እጃቸው መኖሩን አስተባብሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 14, 2014)።
በተመሳሳይ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውጊያዎች እና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ቀጥለዋል። በጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖች እና የቤንሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ የሚደርሱ ጥቃቶች በክልሉ የተለመዱ ናቸው። የመንግስት ምንጮች ብዙ ጊዜ ታጣቂዎቹ በትህነግ እንደሚደገፉ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ባለፈው ወር የመተከል ዞን ግንኙነት ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ የክልሉ ፀረ ሽምቅ ሃይሎች ሀላፊ፣ እና የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰፍረው በሚገኙ የፌደራል ወታደሮች መታሰራቸው ተነግሯል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይሎች በአሶሳ ዞን መንጌ እና ሸርቆሌ ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው ከተባሉ ያልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ተዋግተዋል። ህዳር 2 ላይ የኢትዮጵያ ጦር ከክልሉ የፖሊስ ሃይሎች ጋር በመተባበር ከቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ጋር በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ ጌመድ ቀበሌ ተዋግቷል። የመንግስት ሃይሎች ከ200 የሚበልጡ የአማፂ ቡድን አባላትን መግደላቸውን እና በአማፂያኑ የታገቱ 12 ሴቶችን ጨምሮ 19 ሰዎችን መታደግ መቻላቸውን ገልጸዋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 3, 2014)። ጉዳቱን በግል ማረጋገጥ አልተቻለም።
ባለፈው ወር በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ በርካታ ውጊያዎች መካሄዳቸው ታውቋል። ህዳር 10 ላይ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይሎች “የሱዳን ድንበር አካባቢ” ተብሎ በተገለጸ ስፍራ ላይ “ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያለው ታጣቂ ቡድን” ጋር ተዋግተዋል (ኦቢኤን፣ ህዳር 10, 2014)። የፖሊስ ሃይሉ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ታጣቂዎችን መግደሉን እና ፀረ ታንክ ፈንጂዎችን ጨምሮ ትጥቅ መያዙን ተናግሯል። በወሩ መገባደጃ ላይ የሱዳን መንግስት የሱዳን ጦር እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም “የኢትዮጵያ ታጣቂዎች” መካከል በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በተፈጠረ ግጭት በትንሹ 20 የሱዳን ወታደሮች መሞታቸውን ዘግቧል (ቪኦኤ፣ ህዳር 18, 2014፤ ብሉምበርግ፣ ህዳር 19, 2014)። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ውንጀላ ውድቅ አድርጎ የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ታጣቂዎችን ይረዳል ሲል ወቅሷል (ኢሳት፣ ህዳር 18, 2014)። በሌላ ዘገባ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ደለሎ ቁጥር 6 እና ጢሃ አካባቢዎች ከትህነግ ጋር ግንኙነት ያለው የሳምሪ ቡድን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና የአማራ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል (ኢሳት፣ ህዳር 18, 2014)። የሱዳን ወታደሮች ከሳምሪ ቡድን ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ሲዋጉ እንደነበር ተዘግቧል (ኢሳት፣ ህዳር 18, 2014)።
በመጨረሻም ባለፈው ወር የኢትዮጵያ አስራ አንደኛው ክልል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል – በይፋ ተመስርቷል። መስከረም 20 ላይ የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ዳውሮ ዞን፣ እና ሸካ ዞን ነዋሪዎች ህዝበ-ውሳኔ አካሂደው አብዛኞቹ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ስር ከመቀጠል ይልቅ በኢትዮጵያ አዲስ ክልል ለመመስረት መርጠዋል። አዲሱ ክልል ቦንጋ ከተማን ዋና ከተማ አድርጎ መርጧል። የቤንች ሸኮ ዞን ተወካዮች ውሳኔው ዋና ከተማ ለመምረጥ የተደረሰበት መንገድ ስምምነት ላይ የነበሩትን ሂደቶች የተከተሉ አይደሉም በማለት ተከራክረዋል (ኢሳት፣ ህዳር 11, 2014፤ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ህዳር 9, 2014)።
ወርሃዊ ትኩረት: የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባር
ጥቅምት 26, 2014 ላይ በዋሽንግተን ዲሲ ዘጠኝ ፀረ-መንግስት አንጃዎች “የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባር” የተባለ ጥምረት ፈጠሩ (ዘ ጋርዲያን፣ ጥቅምት 26, 2014)። በስብሰባው ላይ የተገኙ ተወካዮች እንዳሉት አዲሱ ጥምረት ዓላማው “በኃይል ወይም በድርድር ያለውን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ማፍረስ… ከዚያም የሽግግር መንግሥት ማስገባት” ነው (ሮይተርስ፣ ጥቅምት 26, 2014)።
ከዘጠኙ አንጃዎች መካከል ሁለቱ ቀደም ሲል ጥምረት የመሰረቱት ትህነግ እና በመንግስት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ የሚባለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ይገኙበታል (ኤፒ፣ ነሃሴ 5, 2013) 1አክሌድ በዘገባዎቹ ውስጥ ኦነግ-ሸኔን ይጠቀማል። ነገር ግን ቡድኑ ስምምነቱን ሲፈጠር ከተጠቀመበት ስያሜ ጋር ወጥነት እንዲኖረው በዚህ ክፍል ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሲባል ተገልጿል።። የተቀሩት የጥምረቱ አባላት ትንሽ እና አነስተኛ እንቅስቃሴ ያላቸው ናቸው። ስሙ እንደሚያመለክተውም እያንዳንዱ ቡድን ባህላቸውን፣ መሬታቸውን፣ ወይም ማንነታቸውን ለማጥፋት ይደረጋል በሚሉት ጥረት የየራሳቸውን ብሄረሰብ ቡድን አባላት መብቶች የፌዴራሊዝም/የኮንፌደራሊዝም ሥርዓት አካል በመሆን ለማስከበር ይተጋሉ።
የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው ለሚያውቁ ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተወጣጡ “የነጻነት ግንባሮች” ፀረ-መንግስት ጥምረት መመስረታቸው 1983 ላይ የመንግስቱ ሀይለማርያምን መንግስት ያፈረሰውን የአንድነት ግንባር ያስታውሳሉ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)2ህዳር 21, 2012 ላይ ኢህአዴግ ፈርሶ በብልጽግና ፓርቲ ሲተካ ትህነግ ወደ ብልፅግና ፓርቲ ላለመቀላቀል ወሰነ። የተቀሩት የኢህአዴግ ጥምረት አባላት ራሳቸውን በትነው ወደ ብልፅግና ፓርቲ ለመቀላቀል ወሰኑ። የትህነግ፣ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፣ እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕአፓ)31986 ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ስያሜውን ወደ ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ቀይሯል። ጥምረት ግንቦት 20, 1983 ላይ ወደ አዲስ አበባ በመግባት ግንቦት 24, 1983 ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሟል (ዘ ጋርዲያን፣ ግንቦት 21, 2014)።
ከዚህ በታች ባለው ወርሃዊ ትኩረት የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት እና የኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባር አባላት መካከል ስለስምንቱ የተገኘውን መረጃ የምንመረምር ሲሆን በመጨረሻም ትህነግ ይህንን አጋርነት የማስቀጠል እድሉን እንገመግማለን። ይህ ጥምረት ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን በማስፈራራት የኢትዮጵያን ታሪክ ሊደግም እንደማይችልም እንደመድማለን።
ዞሮ ዞሮ ታሪካዊም ሆኑ የቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ታሪካዊም ሆነ የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን በመገምገም ይህ አዲስ የተቋቋመው ጥምረት አሁን ባለበት ሁኔታ የፌደራል መንግስቱን የማስፈራራት አቅም እንደሌለው ግልፅ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ምንም እንኳን ትህነግ ለቅንጅቱ ወታደራዊ ሃይል እየሰጠ ቢሆንም የማጥቃት እና የመጨቆን ታሪኩ በብዙ መልኩ ከእነዚህ ቡድኖች እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጦበታል። ይህ በተለይም በአፋር እና አገው አካባቢ እውነት ነው። በተጨማሪም አሁን ያለው በአብይ የሚመራው መንግስት እንደ ደርግ ሳይሆን ከመላው ሃገሪቱ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ አለው።
1. በአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር፣ በመሐመድ ኢብራሂም የተወከለው
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር በሰሜናዊ አፋር የተመሰረተ ሲሆን ለብዙ አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ድርጅቱ በ1985 የተመሰረተ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ህብረት፣ የአፋር ኡማታህ ዲሞክራሲያዊ ፎካ፣ እና የአፋር አብዮታዊ ሃይሎች የተባሉ የሶስት የአፋር ድርጅቶች ጥምረት ነበር። ትብብሩን ደጋግሞ ቢቀይርም አላማው በሦስት አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ እና ኤርትራ) የሚኖሩ የአፋር ብሔረሰቦች በሙሉ በአንድ ባንዲራ ስር ማድረግ ሆኖ ቀጥሏል (ያሲን ዋይ ኤም፣ 2000)። ትህነግ ከፌዴራል መንግስት በ2010 ከመውጣቱ በፊት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አንዳንዴ በአፋር ምህፃረ ቃል ኡጉጉሞ) በትህነግ መራሹ ኢህአዴግ ላይ አነስተኛ ትግል አድርጓል።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሊቀመንበር ሙሳ ኢብራሂም 1999 ላይ ትህነግን “በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጨቋኙ አገዛዝ” ብለውታል (ኦልአፍሪካ፣ መጋቢት 11, 1999)። 2004 ላይ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር በአፋር ክልል በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃይሎች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ወረራ ወቅት ለተከሰቱ የበርካታ ጎብኚዎች አፈና እና ሞት ተጠያቂ ነበር (የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር፣ ጥር 3, 2004)። በ2009 የደረሰ ሁለተኛ ኩነት ሌላ ጎብኚን ለሞት ዳርጓል (ቢቢሲ፣ ህዳር 26, 2014)።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር የፖለቲካ አቋም ውስብስብ ነው ምክንያቱም እራሱን ከአፋር ክልል መንግስት ጋር አድርጎ በተመሳሳይ ጊዜ የፌዴራል መንግስቱን በመቃወም ላይ ነው። በቅርቡ ለአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ታማኝ የሆኑ ታጣቂዎች በሶማሌ/አፋር ድንበር ላይ ለተከሰቱ ደም አፋሳሽ ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ላይ ተሳትፈዋል። በ2013 የተደረገው አገራዊ ምርጫ አካባቢ የነበረው ግጭት ከኢሳ ጎሳ የመጡ የሶማሌ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው ሦስት ቀበሌዎች ላይ ነበር። በነዚህ ውጊያዎች ወቅት የሱማሌ ታጣቂዎች እና ልዩ ሃይሎች በአፋር መሬት ላይ የሱማሌ ሰፈራዎችን ለማስፋፋት እያመቻቹ ነው ያለው የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ከአፋር ክልል መንግስት ሃይል ጋር በመቀናጀት ከአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ተዋግቷል ተብሏል። ለበለጠ መረጃ የኢፒኦን አፋር-ሶማሌ ድንበር ግጭት ገፅን ይመልከቱ። ሃምሌ 2013 ላይ በሶማሌ ብሄር ተወላጆች የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች በአሁኑ ወቅት ትህነግ ሊቆጣጠረው እየሞከረ ያለውን የኢትዮ-ጅቡቲ አውራ ጎዳናን ዘግተዋል (ሮይተርስ፣ ሃምሌ 21, 2013)።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሌሎች ፖለቲካዊ ውስብስብ ቦታዎችን ይይዛል። ልክ እንደሌሎቹ አዲስ የተቋቋመው ፀረ-መንግስት ጥምረት አባላት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ለአስርት አመታት በትህነግ ላይ ሽምቅ ውጊያን ሲያካሂድ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ከቡድኑ ጋር ያለው ጥምረት በአፋር ህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት እንደሌለው ማስረጃ ያለው የፖለቲካ ምሰሶ ያሳያል። ይልቁንም ሃምሌ 2013 ላይ ትህነግ አፋር ላይ ያደረሰው ወረራ ለፌዴራልና ለክልላዊ መንግስታት የሚደረገው ድጋፍ እንዲጨምር ያደረገ ይመስላል። መንግስት በአፋር ህዝብ ዘንድ ያለውን ፀረ-ትህነግ ስሜት ለመጠቀም ያደረገው ጥረት የተሳካ ሲሆን ትህነግን ከክልሉ ለማስወጣት ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ከአፋር የተውጣጡ ታጣቆዎችና የክልሉ ልዩ ሃይሎች ናቸው። ስለዚህም የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ከትህነግ ጋር በቅርቡ መፈራረሙ ተወዳጅም ስኬታማም አልነበረም።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር በፌዴራል መንግስት እና በትህነግ ዙሪያ የህዝብን አስተያየት ለመያዝ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ነሃሴ 2013 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በጋሊኮማ፣ ፋንቲ ራሱ ዞን በክልሉ ለደረሰው እና ቢያንስ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞቱበት ጥቃት ተጠያቂ የሚያደርግ መግለጫ የወጣ ሲሆን መንግስት በበኩሉ የትህነግን ታጣቂዎች ተጠያቂ አድርጓል (አያንቱ፣ ነሃሴ 3, 2013)። ክስተቱ አሁንም አከራካሪ ቢሆንም ትህነግ በአፋር ክልል የሚገኙ የኢትዮጵያ እና የአፋር ክልል ሃይሎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መወሰኑ እና ይህም መሰረተ ልማቶችን በማውደሙ እንዲሁም በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ መፈናቀልና ጉዳት በማድረሱ ቡድኑ ላይ ተቃውሞ እንዲፈጠር አድርጓል። አክሌድ ከሃምሌ 2013 ጀምሮ በአፋር ክልል አምስት ጸረ-ትህነግ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መዝግቧል።
ከአካባቢያዊ ድጋፍ ጋር ከተያያዙ ችግሮች በተጨማሪ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ለፌዴራሊዝም ጥምረቱ ተጨማሪ የፖለቲካ ራስ ምታት ያመጣል። የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሁሉንም የአፋር ብሄረሰቦች አንድ ለማድረግያለው ሃሳብ ከኤርትራ እና ከጅቡቲ ጋር የግዛት ማስተካከያ እንዲኖር ያስገድዳል። ይህ ዓይነቱ ፍላጎት እንዲሳካ ሁለቱም ሀገራት ላይ የሚያስፈልገው የዲፕሎማሲ እና የወታደራዊ ሃይል ፍላጎት አዲሱ ህብረት ሊቋቋመው የሚችል አይደለም።
2. የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ በአድማሱ ጸጋዬ የተወከለ
ስለ አገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብዙም መረጃ የለም እንዲሁም ስለ እንቅስቃሴያቸው የሚያሳዩ ገለልተኛ ዘገባዎች የሉም። የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች (በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ እና አገው አዊ ዞን) ከትህነግ ጋር በሚረገው ጦርነት እርግጠኛ መሆን በሚቻል መልኩ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች የተሳተፉባቸው ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል።
አገው ኩሽቲክ ተናጋሪ ህዝቦች ሲሆኑ የተወሰኑት ከሀምሌ 2013 ጀምሮ በትህነግ ቁጥጥር ስር የነበሩት በአማራ ክልል በዋናነት በዋግ ሃምራ እና አገው አዊ ዞኖች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። የቢቢሲ አማርኛ እና የዲደብሊው አማርኛ ዘገባዎች እንደሚያሳዪት የዋግ ሃምራ ነዋሪዎች በግጭቱ ምክንያት ተሰቃይተዋል፤ የአካባቢው ባለስልጣናትም በትህነግ ወረራ ምክንያት ረሃብ እና መፈናቀል እንደተፈጠረ ዘግበዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 10, 2014፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ መስከረም 25, 2014)።
ፓርቲው የአባልነት መስፈርቶችን ማሟላት ባለመቻሉ ታህሳስ 13, 2013 ላይ የአገው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምዝገባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰርዟል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ታህሳስ 13, 2014)። በዋሺንግተን ዲሲ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ አቶ አድማሱ ፀጋዬ ሃምሌ 2013 በአግባቡ ያልተወከሉ ብሄሮች እና ህዝብ ድርጅት ባዘጋጀው የምርጫ መግለጫ ላይ ላይ የአገው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድንን ወክለው ተገኝተዋል። ‘‘አገዎች በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ላይ እምነት አጥተዋል እንዲሁም ከምርጫዎች በኋላ እንደተገለሉ እና እንደተጨቆኑ ይሰማቸዋል” ሲሉ በመግለጫ አውጥተዋል (በአግባቡ ያልተወከሉ ብሄሮች እና ህዝብ ድርጅት፣ ሰኔ 24, 2013)።
ሚያዚያ 18, 2013 ላይ ከአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች እና ከትህነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በኒራክ ከተማ (ዋግ ኽምራ፣ አማራ ክልል) ላይ በአማራ ልዩ ሃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽመው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ጨምሮ 11 ሰዎችን ገድለዋል። የትህነግ ምንጮች ከከተማዋ ከመውጣታቸው በፊት የጦር መሸጫ ሱቅን በተሳካ ሁኔታ ተቆጣጥረው ስንቅ ማግኘታቸውን ሲገልጹ የመንግስት ግንኙነት የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች ጥቃቱን በተሳካ ሁኔታ መመከታቸውን ገልጸዋል። ነሃሴ 2013 ላይ በአበርገሌ አካባቢ የአገው ታጣቂዎች ሳይሳተፉባቸው ያልቀሩ ተጨማሪ ጦርነቶች ተካሂደዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ነሃሴ 7, 2014)።
3. የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፣ በዩሱፍ ሃሚድ ናስር የተወከሉ
የቤንሻንጉል/ጉምዝ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ሆኖ ቀጥሏል፤ ይህም በከፊል የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ካወጀው አመፅ ጋር ይያያዛል። በአካባቢው የጉሙዝ፣ ሺናሻ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አገው፣ እና ሌሎች ብሄረሰቦች ይኖራሉ። የጉሙዝ፣ በርታ፣ እና ሺናሻ ብሄረሰብ ተወላጆች በአካባባው ከመጀመሪያውም የነበሩ ሲባሉ አማራዎች እና ኦሮሞዎች ደግሞ ከ1976-1977 በነበረው ከባድ ድርቅ ምክንያት ወሎ ከሚገኙ አካባቢዎች ወደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ወደሚገኙ ለም መሬቶች እንዲሰፍሩ ተደርገዋል።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የተፈጠረው ግጭቶች ሥር የሰደዱ እና በመሰረቱ ለመፍታት አስቸጋሪ ናቸው። የሀገሬው ተወላጆች “የደጋማ ነዋሪዎችን” (ኦሮሞ እና አማራ) በግዳጅ መሬት ወስደዋል በማለት ይከሳሉ ለዚህም የሃይል ምላሽ ሰጥተዋል። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን በሀገሪቱ ውስጥ በየጊዜው ከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በመሆኑም ዞኑን በማረጋጋት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጥር 15, 2013 ላይ በመንግስት በኩል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። በግብፅና ሱዳን ውዝግብ ያለበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባው በዚህ ዞን ነው።
የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ የትጥቅ ትግልን ለማቆም ከኢህአዴግ ጋር በ2004 የሰላም ስምምነት ተፈራርሟል (ሪሊፍዌብ፣ ነሃሴ 14, 2014)። በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ብሔር ተኮር ግጭት ተባብሶ የቡድኑ አዛዦች ወደ ትጥቅ ግጭት ተመልሰዋል። ከተካሄደው አገራዊ ምርጫ (ባለው አለመረጋጋት ምክንያት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ያልተካሄደ) መዳረሻ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የንቅናቄው ፖለቲከኞች ያለፍርድ ተይዘው ታስረዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይት፣ ጷጉሜ 5, 2013)።
በክልሉ በተስፋፋው የጎሳ ግጭት ውስጥ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ሚና ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም። የመንግስት ምንጮች አሁንም በግጭቱ ውስጥ ያሉትን አካላት ያላሳወቁ ሲሆን ይልቁንም “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ወይም “የትህነግ-ተላላኪዎች” በማለት ይሰይሟቸዋል። ሰኔ 29, 2013 ላይ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ላልተገለጸ “25 የቀድሞ የትጥቅ ቡድን አባላት” በርካታ የመንግስት የስራ ቦታዎችን መስጠቱን አስታውቋል – ከነዚህም አንዳንዶቹ በእርግጠኝነት የቀድሞ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ አባላት ነበሩ (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 28, 2013)።
ዛሬ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በአመፅ ተግባር ላይ የተሰማሩት ክፍሎች በ2004 የቡድኑን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ያልተስማሙ የዋናው የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ቡድን ታማኝ የሆኑ የአካባቢ አዛዦች ናቸው። ከትህነግ ጋር የሚደረገው ውጊያ ከተጀመረ ጀምሮ ቡድኑ የበለጠ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከመስከረም 2014 ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ግዛት ተቆጣጥሯል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 14, 2014)።
በዋሽንግተን ዲሲ ቡድኑን ወክሎ ለህብረቱ የፈረመው የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ተወካይ ዩሱፍ ሃሚድ ናስር በጣም የታወቀ ግለሰብ ነው። በ1978 የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄን ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በትህነግ የሚመራው ኢህአዴግ የመንግስቱ ሀይለማርያምን (ደርግ) መንግስት ከገለበጠ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት አባል ሆነዋል። በ1984 ዩሱፍ በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል (አፍሪካን ኢንተሌጀንስ፣ ህዳር 17, 2014)። የ1987 የኢትዮጵያ ምርጫ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄን ፖለቲከኞችን ወደ ከኢህአዴግ ወደ ዳር ካደረገ በኋላ በየመን የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሱዳን ድንበር ላይ በአሸባሪዎች ላይ ዘመቻ ማድረጉን በየጊዜው ይዘግባል። መንግስት እነዚህ ቡድኖች ስልጠና እና የጦር መሳሪያ ከሱዳን እንደሚያገኙ ተናግሯል (ኢቢሲ፣ ህዳር 10, 2014፤ ኢቢሲ፣ ሃምሌ 21, 2013)። በቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ እና በማንኛውም የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት መካከል ያለው ግንኙነት አልተረጋገጠም።
4. የጋምቤላ ሕዝብ ነፃ አውጪ ሰራዊት፣ በኦኮክ ኦጁሉ ኦኮክ የተፈረመ
የጋምቤላ ህዝቦች ነፃ አውጪ ሰራዊት ከ2013 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫዎች በኋላ ጥቅምት 2014 ላይ የተመሰረተ አዲስ ድርጅት ነው። ቡድኑ የምርጫውን “ችግሮች እና ብልሹ አሰራር” በመጥቀስ እራሱን በማስታጠቅ የጋምቤላ ክልል መንግስትን ለመጣል ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል (የኢትዮጵያ ኦውቶኖመስ ሚዲያ፣ ጥቅምት 21, 2014)።
ቡድኑ ልክ እንደ ሌሎች በህብረቱ ውስጥ ያሉ ቡድኖች የተያያዥ ድርጅታዊ ችግሮች አሉበት። ህብረቱ በዋሽንግተን ዲሲ ከተፈራረመ ብዙም ሳይቆይ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ሰራዊት በስሙ ስምምነቱን የፈረመው ተወካይ አባሉ እንኳን እንዳልነበር የሚጠቅስ መግለጫ አውጥቷል (የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ሰራዊት፣ ህዳር 8, 2014)። የመንግስት የዜና ማሰራጫ ኢቢሲ ህዳር 9 ላይ ለጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ሰራዊት ይዋጉ የነበሩ በርካታ ወጣቶችን እጃቸውን መስጠታቸውን መቀበሉን አስታውቋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 9, 2014)።
5. አለም አቀፍ የቅማንት ህዝቦች መብትና ፍትህ ንቅናቄ/ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
ቅማንት በአማራ ክልል ቋራ፣ ጭልጋ፣ ላይ አርማጭሆ፣ ደንቢያ፣ መተማ፣ እና ጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች ውስጥ የሚኖር የብሄረሰብ ቡድን ነው። በርካታ የቅማንት ብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች ያሉ ሲሆን በአማራ ክልል ውስጥ በበለጠ ራስን በራስ የማስተዳደር ቅስቀሳቸው ብዙ ጊዜ ወደ ግጭት ይመራል። 2009 ላይ በአማራ ክልል በአብላጫው ቅማንቶች ይኖሩባቸው ከነበሩት ስምንት ቀበሌዎች ውስጥ ሰባቱ በአማራ ክልል እንዲቀጥሉ በህዝበ-ውሳኔ በመፍቀድ በወቅቱ በልዩ ዞን ማዕረግ የላቀ የራስ ገዝ አስተዳደር የማግኘት ተስፋን አጨልሟል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥር 30, 2011)።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት ትህነግን የቅማንት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲን ጨምሮ አመጸኛ የቅማንት ብሄርተኛ እንቅስቃሴዎችን “መሳሪያ እና ገንዘብ” በመስጠት በመደገፍ ይከሳሉ (ቢቢሲ፣ ግንቦትር 11, 2013)። በምላሹ የቅማንት ቡድኖች እንደ ፋኖ ያሉ የአማራ ብሄርተኛ የወጣቶች እንቅስቃሴዎችን አለመረጋጋት ባለበት ወቅት በቅማንት ቤተሰቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይፈጽማሉ ሲሉ ይከሳሉ።
በ2010 ትህነግ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከታህሳስ 2011 እስከ መስከረም 2012 ድረስ በተካሄዱ የእርስ በእርስ ግጭቶ 130 ሰዎች መሞታቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ይገምታል (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ 2012)።
በአይከል ከተማ ከተካሄደው የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስብሰባ በኋላ ግጭት ከተቀሰቀሰ ቡኋላ ሚያዚያ 2013 ላይ ውጊያዎች በድጋሚ አገርሽተዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሚያዚያ 14, 2014)። ግንቦት 2013 ላይ ምርጫ ቦርድ በቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ሃይሎች መካከል ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ሰርዟል (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መጋቢት 10, 2014)። በጎንደር ከተማ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች በ2013 ጸደይ እና ክረምት ወቅቶች ተደጋጋሚ ነበሩ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 20, 2013)። በአልጀዚራ የደረገ ምርመራ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ከቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር በሚያደርጉት ውጊያዎች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ የቅማንት ብሄረሰብ አባላት ወደ ሱዳን ተፈናቅለዋል (አል ጀዚራ፣ መስከረም 26, 2014)።
6. የኦሮሞ ነጻነት ግንባር- የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ በጃላ ኦዳ የተፈረመ
ከትህነግ ቀጥሎ በህብረቱ ውስጥ ካሉት እንቅስቃሴ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ነው። አክሌድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ያለፈው አመት ብቻ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በአሁኑ ሰአት ኦነግ-ሸኔ ተብሎ የሚመዘገብ) የተሳተፈባቸው 201 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ክስተቶችን መዝግቧል። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ከትህነግ እና ከጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የግዛት ትስስር ያለው ግንኙነት ፈጥሯል (ኦዳ ታርቢ፣ ጥቅምት 21, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥቅምት 22, 2014).።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመላው የኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀስ ሲሆን በምዕራብ እና በደቡብ ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ግዛት ይዟል። ቡድኑ ለፌዴራል መንግስቱም ሆነ ለኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ትልቅ የጸጥታ ችግር ቢፈጥርም እስካሁን በክልሉ ውስጥ ምንም አይነት ትልቅ የከተማ ማእከል አልያዘም። የኢፒኦን የምዕራብ እና ቄለም ወለጋ ግጭት ገጽን ይመልከቱ።
በአዲሱ ህብረት ውስጥ እንዳሉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከውስጥ አደረጃጀት እና ከማህበረሰብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ ችግሮች አሉበት። ቡድኑ ሲጀመር በ2010 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአብይ አህመድ በተደረገለት ጥሪ ትጥቅ ሲፈታ የተፈጠረ ነው (ዘ ሪፖርተር፣ መስከረም 26, 2014)። ከመንግስት ጋር በሚያደርገው የትጥቅ ትግል በኦሮሚያ ክልል አናሳ ብሄረሰቦች ላይ ከፍተኛ ወንጀሎችን ፈጽሟል በሚል የሚከሰስ ሲሆን የቡድኑ አመራሮች ክሱን ውድቅ ያደርጋሉ።
ቡድኑ ከትህነግ ጋር ለመፍጠር የወሰነው ጥምረት እንዲሁ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል። አብዛኞቹ የቡድኑ ወጣት ታጣቂዎች ከ2006 እስከ 2010 በትህነግ ላይ ሰላማዊ የተቃውሞ ንቅናቄን የመራው እና ለአብይ ወደ ስልጣን ሚና አለኝ የሚለው ቄሮ እንቅስቃሴ አባላት ነበሩ። በነዚህ ተቃውሞዎች ላይ በተሳተፉ የኦሮሞ ወጣቶች ላይ ትህነግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ብዙ ጊዜ እጅግ ከባድ የነበሩ ሲሆን በመላው ኦሮሚያ ያሉ ማህበረሰቦች ለትህነግ አመራሮች መጥፎ ስሜት አላቸው።
ኦነግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂ ክንፉ የነበረ ሲሆን የሚታዘዘው የሸኔ ምክር ቤት በሚባል በሸኔ ማዕከላዊ እዝ ክፍል ነው። ምንም እንኳን በመላው ኦሮሚያ ክልል እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ትህነግ ካለው የውጊያ አቅም ትንሹም ቢሆን የለውም። ትህነግ በኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ወንበሮች ላይ ለአስርት አመታት ያሳለፈ ሲሆን በዚህም የገንዘብ ሃብትና የጦር መሳሪያ ክምችት አግኝቷል። በ1984 ከትህነግ ጋር የተቃቃረው ኦነግ ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣን ስላልነበረው እስከ 2010 ድረስ ትህነግን በመቃወም የሚታገል ታጣቂ ሃይል ይመራ ነበር። ኦነግ ከስደት ከተመለሰ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከኦነግ ሲለያይ ታጣቂዎቹ የወረሱት የጦር መሣሪያም ሆነ የሕዝብ ድጋፍ አነስተኛ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የመዋጋት አቅሙ ከትህነግ ጋር እኩል ወይም የሚስተካከል ነው የሚለው ትንታኔ ከመሰረቱ ስህተት ነው።
7. የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር፣ በተስፋዬ ወዳጆ ሂሎ የተፈረመ
የሲዳማ ነጻነት እንቅስቃሴ በ1983 በኢህአዴግ የተመሰረተው የሽግግር መንግስት አካል ነበር። በወቅቱ ለቡድኑ ሁለት መቀመጫዎች ተሰጥተው ነበር (አዲስ ስታንዳርድ፣ ሰኔ 26, 2013)። የድርጅቱ ስም ሰኔ 1991 ላይ ወደ ሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ተቀይሯል (የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር)።
የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ትህነግን የሚደግፉ እና የሲዳሞ ወጣቶችን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሲዳማ ልዩ ፖሊስ አባልነት መመልመል የሚያወግዙ ጥቂት መግለጫዎችን ከማውጣት በስተቀር ከ2010 እስከ 2014 ድረስ ብዙም አይታይም ነበር (Tiየትግራይ ሚዲያ ሃውስ፣ ሃምሌ 8, 2014)።
ሲዳማ 98% ነዋሪዎቿ ከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ለቀው የኢትዮጵያን 10ኛ ክልላዊ መንግስት ለመሆን መምረጣቸውን ተከትሎ ሰኔ 11, 2012 በይፋ ክልላዊ እውቅና ተሰጥቷታል (አፍሪካ ኒውስ፣ ህዳር 13, 2012)። ይህ በመሆኑ ለኢትዮጵያ መሪ መንግስት ብልጽግና ፓርቲ ታማኝ የሆነው የሲዳማ ክልል መንግስት የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የኢትዮጵያ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ታማኝ የሆነው የሲዳማ ክልል መንግስት የሲዳማ ህዝብ ብሄራዊ የጠቀሰውን የራስን እድል በራስ የመወሰን አላማን አስገኝቷል። በመሆኑም የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር በራሱ ማህበረሰብ ዘንድ እንኳን የታወቀም ሆነ የዳበረ አይደለም።
የኢትዮጵያ መንግስት ህዳር 4 ላይ ከትህነግ ወይም ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ታጣቂዎች በሲዳማ ክልል በሃዋሳ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል (ኢቢሲ፣ ህዳር 4, 2014)። እነዚህ ከሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ይሁኑ አይሁኑ የታወቀ ነገር የለም።
8. የሶማሌ ክልል ተቃውሞ፣ ተወካይ ማሃሙድ ኡጋስ
በሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች እንደተረዱት የሶማሌ ክልል ተቃውሞ በዋሽንግተን ዲሲ ከተደረገው የፊርማ ስነስርአት በፊት አልነበረም። ተወካዩ መሃሙድ ኡጋስ ከ1983 እስከ 1987 የፕላን እና ኢኮኖሚ ልማት የክልል ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከ1987 እስከ 1992 ኡጋስ ለተለያዩ የሰብአዊ እርዳታ የሚያደርጉ ድርጅቶች በአማካሪነት እና በመስክ ተመራማሪነት ሰርተዋል። በህይወት ታሪካቸው መሰረት መሃሙድ በ1992 ከኢትዮጵያን ለቀው ከሄዱ በኋላ በካናዳ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀዋል (መሃሙድ ኡጋስ፣ አካደሚያ.ኢዲዩ)። ምንም እንኳን የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በሆነ መንገድ ሊሳተፍ ቢችልም መሃሙድ ኡጋስም ሆኑ የሶማሌ ክልል ተቃውሞ ከኦብነግ ጋር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም። እንዲሁም መሃሙድ ኡጋስ በ2004 በናይሮቢ በመንግስት እና በወቅቱ ኦብነግ መካከል በተካሄደው የሰላም ድርድር ላይ የኦብነግ የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ተወካይ ሆነው ተገኝተዋል (ቶባይስ ሃግማን፣ 2006)።
እንደ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሁሉ የሶማሌ ክልል ተቃውሞ የሶማሌ ህዝብን (በተለይ በኦጋዴኒያ ያሉ) እራሱን ከትህነግ ጋር ማሰለፉን እንደጥሩ ሀሳብ ለማሳመን ያስቸግረዋል። ኡጋስ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ትህነግ በሶማሌ ክልል የረዥም ጊዜ ግፍና በደል የማድረስ ታሪክ ስላለው በአስርት አመታት የተፈጠረው ምሬት አዲስ ህብረት በመፍጠር ብቻ አይረሳም። የሶማሌ ክልል ተቃውሞ የኦብነግ ግንባር ይሁን ሙሉ በሙሉ ከገዥው የብልጽግና ፓርቲ ክልከላ ውጭ ቦታ ለመፍጠር ባለ የፖለቲካ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አዲስ ድርጅት መሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ነው።
ማጠቃለያ፡ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር ታሪክን የመድገም እድል
ከሌሎቹ አባል ድርጅቶች እጅግ የላቀ ልምድም ሆነ አቅም ያለው ትህነግ ከፍተኛ መጠን ያለው ግዛት በመያዙ በቁጥጥሩ ስር ያሉ ቦታዎችን ማስተዳደር ይችላል። ሌሎቹ ድርጅቶች (ከኦነግ-ሸኔ በስተቀር) በእውነቱ የሚያበረክቱት ብዙ ነገር እንዳለመኖሩ በዚህ ህብረት ውስጥ ትህነግ የአደራጅ እና አቅራቢ ቦታ እንዳለው ግልፅ ነው ።
ሆኖም ግን የትህነግ ያለፈ ታሪክ እጅግ በጣም ጎጂ በመሆኑ በወረቀት ላይ ብቻ እንኳን ያሉ ጥምረቶች ደካማ ናቸው። ትህነግ የመንግስቱ ሃይለማርያምን መንግስት በ1983 መገልበጥ የቻለ ቢሆንም አሁን ማዕከላዊ መንግስቱን የመጣል አቅማቸው በነበራቸው ደካማ የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ምክንያት የተገደበ ነው። ሌሎችም ሊታሰቡ የሚገቡ ምክንያቶች አሉ።
ትህነግ በ1983 ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ያስወገደው “በጣም ተወዳጅነት የሌለውን” አገዛዝ ነበር (ዘ ኮንቨርሴሽን፣ ህዳር 12, 2014)። ምንም እንኳን አብይ አህመድ ጠንካራ አቋም ባለው ባህሪያቸው ምክንያት በመላው ሃገሪቱ ብዙ ጠላት ያላቸው ቢሆንም በአብዛኛው የማህበረሰቡ ክፍል ድጋፍ ስላላቸው ተመሳሳይ ነገር ማለት አይቻልም። በተጨማሪም ከላይ የተገለጹት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ለደካማነት እና ለመንግስት ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ሥር የሰደዱ ችግሮች አሏቸው።
ይህ ማለት ግን መንግስት የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እራሱ ከሚያደርገው ነገር በላይ ነው ማለት አይደለም። በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች እና በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚወስደው የእስር እና የኃይል እርምጃ ወደፊት አንድ ቀን የራሱ ዋጋ ይኖረዋል። በተጨማሪም በየክልላቸው ለሚስተዳድራቸው ሃይል ታማኝ የሆኑ የኢትዮጵያ ክልላዊ ልዩ ሃይሎች አቅም እያደገ መምጣቱ የፌዴራል መንግስት ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ የሆነ ብጥብጥ ሊያስከትል የሚችል አደገኛ ክስተት ነው።
ከምንም በላይ ግን የፀረ-መንግስት ጥምረት ቡድኑ አባላት ችላ ሊባል የማይችል ከባድ የሆነ ግፍና በደል ትህነግ በራሳቸው ማህበረሰብ ላይ በመፈፀሙ እየታገለ ነው። በአፋር ክልል የትህነግ ሃይሎች ወደኋላ ከማፈግፈጋቸው በፊት ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል እንዲሁም በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ላልሆኑ ሰዎች ምንም አላደረጉም። ከሰሞኑ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ጦርነቱ የዛሬ አመት ሲጀመር የትህነግ አመራሮች የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሃይሎችን የከሰሱባቸው አይነት ተግባራት በአማራ ክልል በትህነግ ታጣቂዎች ተፈፅመዋል (ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ህዳር 30, 2014)። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ትህነግ ወደ ኦሮሚያ የሚያደርገውን ጉዞ እንዲያቋርጥ ጠይቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥቅምት 27, 2014)። አንዳንዶች የፌደራሊዝም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ለሚያራምደው ሃሳብ ሃዘኔታ ቢኖራቸውም አልያም የብሔር ራስን በራስ ማስተዳደርን ሊደግፉ ቢችሉም በትህነግ ላይ በቸልታ ሊታለፍ የማይችል ቁጣ አለ እንዲሁም የሚወክሏቸውን ማኅበረሰቦች ስሜት መወከል ባለመቻላቸው የእነዚህን ቡድኖች ተቀባይነት ጎድቷል።
በ1983 የተከሰቱት ኩነቶች እንደገና ሊከሰቱ የሚችሉ አይመስልም። የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት አንድነት ሃይሎች ግንባር ከኢህአዴግ በብዙ መሰረታዊ መንገዶች የሚለይ ሲሆን ያለው አቅምም በእጅጉ ያንሳል። ያለፈውን የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙም ግምት ውስጥ ሳያስገባ በአንድ ላይ የመጣ ነው። ሆኖም ግን መንግሥት የሀገሪቱን ጉዳዮች በእውነት አሳታፊ በሆነና ክብር ባለው መንገድ እስኪያስተካክል ድረስ ግጭት በኢትዮጵያ የወደፊት የፖለቲካ መንገድ ላይ ለመደራደር እንደመፍትሄ መወሰዱ ይቀጥላል።