ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ታህሳስ 29, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,430
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 14,078
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,355
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከታህሳስ 2, 2014 እስከ ታህሳስ 29, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 81
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 478
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 222
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፉት አራት ሳምንታት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች ላይ የለኢትዮጵያ መንግስት ታማኝ የሆኑ ሃይሎች ቁጥጥራቸውን ባጠናከሩበት ወቅት በፌደራል ወታደሮች እና በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) መካከል በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያዎች ተዘግበዋል። የሰብአዊ እርዳታ መኪኖች በቀጠለው ግጭት ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት ዘግይተዋል። በአፋር እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ ላይ ከምትገኘው አባላ ከተማ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከታህሳስ 14 እስከ 16 በትህነግ ሃይሎች እና በአፋር ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ተካሂደዋል (ኢሳት፣ ታህሳስ 16, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ታህሳስ 18, 2014)። ታህሳስ 16, 2014 ላይ የትህነግ ሃይሎች በአፋር ክልል አባላ ወረዳን በከባድ መሳሪያ ደብድበው ህጻናትን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎችን ገድለዋል (የአፋር ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ ታህሳስ 16, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ታህሳስ 18, 2014)። የትህነግ ምንጮች እንደሚሉት በአፋር በተካሄደው ጦርነት 250 የትግራይ ተወላጆች በፌደራል ሃይሎች የተገደሉ ሲሆን 900 ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ታህሳስ 26, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፋር እና የአማራ ክልል መንግስታት የሰአት እላፊ ሰዓቶችን በመቀነስ እና የመንግስት አገልግሎትን እንደገና በመጀመር አካባቢያቸው ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ጥረት አድርገዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 14, 2014)። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትም በተመሳሳይ መልኩ ሀገሪቱን ወደ መደበኛ ሁኔታ የመመለስ እቅድ እንዳለው አመልክቷል። ታህሣሥ 14 ላይ መንግሥት በትህነግ ላይ የሚወስደው የመጀመሪያው ዙር ወታደራዊ እርምጃ ማብቃቱን አስታውቆ ወደ የትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ እንደማይሄድ አመልክቷል (የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ታህሳስ 14, 2014)።
መንግስት የሰጠው መግለጫ ቢኖርም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ባደረገው በሰው አልባ አይሮፕላን የተደገፈ ጥቃት የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ታህሳስ 7 ላይ በአላማጣ ከተማ በሰው አልባ አውሮፕላን በደረሰ ጥቃት 38 ሰዎች ሲሞቱ 86 ተጨማሪ ሰዎች ቆስለዋል (ሮይተርስ፣ ታህሳስ 2014)። እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ባወጣው ዘገባ መሰረት በትግራይ ክልል ከታህሳስ 10 እስከ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ በአላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መኮኒ፣ እና ሚላዛት ከተሞች በደረሰ የአየር ድብደባ “በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል” (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ታህሳስ 21, 2014)። ታህሳስ 29 የተደረገ ጥቃት በማይ አይኒ (በማይ ፀብሪ አቅራቢያ) የሚገኝ የስደተኞች መጠለያ በመምታት ሶስት ኤርትራውያን ስደተኞችን ገድሏል፤ በርካቶችን አቁስሏል (ሮይተርስ፣ ታህሳስ 29, 2014)። ከአንድ ቀን በኋላ በደደቢት ከእኩለ ሌሊት በኋላ በተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተደረገ ድብደባ 56 ሰዎች ሲሞቱ ተጨማሪ 30 ቆስለዋል (ቪኦኤ፣ ታህሳስ 30, 2014)። ጥር 3 ላይ በማይ ፀብሪ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት 17 ተጨማሪ ሰዎች ተገድለዋል (ሮይተርስ፣ ጥር 3, 2014)።
በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ፖሊስ ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ጠርጥሮ የያዛቸውን በርካታ እስረኞች ለቋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ታህሳስ 28, 2014)። ምን ያህል እስረኞች እንደተፈቱ ግልፅ አይደለም:: ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ የገና በአል ላይ መንግስት የትህነግ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ 33 ታዋቂ ፖለቲከኞችን ከ”ጤና እና እድሜ” ጋር በተገናኘ ለቋል (ኢትዮጵያን ኢንሳይደር፣ ታህሳስ 29, 2014)። የፍትህ ሚኒስቴር እንደገለጸው በእቅድ በተያዘው የብሄራዊ እርቅ ሂደት አንድ ክፍል መሰረት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችም ተለቀዋል (ኢፌዴሪ ኡእፍትህ ሚኒስቴር፣ ታህሳስ 29, 2014)። ታህሳስ 20 ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ የውይይት ኮሚሽን ለማቋቋም አዋጅ አጽድቋል።
በመጨረሻም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እንቅስቃሴ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ከፍ ያለ ሲሆን ከዚህ ቀደም እንቅስቃሴው ውስን በሆነባቸው አካባቢዎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል የሚታዪ የቅርብ ጊዜ የግጭት አዝማሚያዎችን ከዚህ በታች ባለው ሳምንታዊ ትኩረት እንመረምራለን።
ሳምንታዊ ትኩረት: በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ግጭት
በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የአመፅ እንቅስቃሴዎች እና ተመሳሳይ ግጭቶች በመባባሳቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ታህሳስ 27, 2014)። የመንግስት ሃይሎች በኦነግ-ሸኔ ላይ ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዋል፤ በተመሳሳይ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች በፀረ-መንግስት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግስት ያወጣው ዘገባ (ምንም እንኳን ጊዜውን ባይጠቅስም) በቅርቡ በተወሰደ እርምጃ 1,643 ታጣቂዎች መሞታቸውን ጠቅሷል (ኢቢሲ፣ ታህሳስ 27, 2014)። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በተከሰቱት ግጭቶች ከ195,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የመንግስት ቃል አቀባይ አመልክተዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ታህሳስ 27, 2014)።
በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ስር የሚገኙ በርካታ የገጠር አካባቢዎች በቅርቡ በፀረ-መንግስት ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መውደቃቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች በዋና ዋና የትራንስፖርት መስመሮች አካባቢዎች ተጠናክረዋል (ዋልታ ኢንፎ፣ ጥር 3, 2014)። በተጨማሪም ኦነግ-ሸኔ በጉጂ እና ቦረና አካባቢዎች ጠንካራ ቢሆንም ከእነዚህ አካባቢዎች የሚወጡ ዘገባዎች በመሰረተ ልማት እጦት የተነሳ ብዙም አይደሉም። አክሌድ በምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ ፌደራል ሃይሎች፣ እና አማራ ብሄር ታጣቂዎች መካከል የተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶችን መዝግቧል።
ኦነግ-ሸኔ ከዚህ ቀደም እንቅስቃሴው ውስን በሆነባቸው አካባቢዎች ጭምር እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ቀጥሏል። ታህሳስ 2014 ላይ በኦነግ-ሸኔ እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል መካከል በመኤሶ (ምዕራብ ሀረርጌ) መዋጋታቸው ዘግቧል። ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ ግጭቶች ቢደረጉም ይህ በምስራቅ ኦሮሚያ ከቡድኑ ጋር የተራዘመ ግጭት ሲከሰት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው (የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዲስ መረጃ፣ ታህሳስ 29, 2014)። በሐረር ከተማ የሚገኙ የመንግስት ሃይሎች ኮማንደር ጨምሮ በርካታ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ተናግረዋል (ኢቢሲ፣ ታህሳስ 29, 2014)። በአካባቢው እንቅስቃሴ እየጨመረ ያለው ከትህነግ ጋር ጥምረት የፈጠሩት የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን እያፈገፈጉ ባለበት ወቅት ነው። በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የፌደራል ወታደሮች የኤ2 አውራ ጎዳናን መልሰው ሲቆጣጠሩ የእነዚህ ግዛቶች ቁጥጥር ተመልሶ ለአማራ ክልል ባለስልጣናት ተላልፏል።
በሚቀጥሉት ወራት የኦነግ-ሸኔ እርምጃዎች ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ ኦነግ-ሸኔ ከትህነግ ጋር የፈጠረው ጥምረት ቡድኑ መጀመሪያ ካሰበው በላይ ዋጋ ያስከፈለ መሆኑ ተረጋግጧል። ትህነግ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ባደረሰው መጠነ ሰፊ የመብት ረገጣ ምክንያት ጥምረቱ በኦነግ-ሸኔ ደጋፊዎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረ ከመሆኑም በተጨማሪ በቅርቡ ትህነግ ከአፋር እና አማራ ማፈግፈጉን ተከትሎ የኦነግ-ሸኔ አመራሮች መጀመሪያ ያሰቡትን ወታደራዊ ጥቅም አላስገኘላቸውም። ሁለተኛ መንግስት የጃዋር መሃመድ እና ሌሎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት በቅርቡ ከእስር መፈታትን በኦሮሚያ ክልል ግጭት በሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ፖለቲካዊ ዥዋዥዌ ላይ ቦታ ካላቸው ፖለቲከኞጭ ጋር ስምምነት በመፍጠር ኦነግ-ሸኔን ማንኛውንም ህዝባዊ ድጋፍ ሊያሳጣው እንደሚችል ያሳያል። በመጨረሻም የኦነግ-ሸኔ ወታደራዊ ግስጋሴው የፌደራል መንግስቱ ሁሉንም ሀብቱን በሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል ባለው ግጭት ላይ ሲያውል በነበረበት ወቅት ላይ የተደረገ ነው። በመሆኑም ከእነዚህ ሀብቶች ውስጥ የተወሰኑት ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲዞሩ ከተደረገ የቡድኑ ተዋጊዎች በመላው ክልል ከባድ ምላሽ ይገጥማቸዋል።