ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥር 13, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,475
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 14,280
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,457
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከጥር 7, 2014 እስከ ጥር 13, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 12
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 51
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 41
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል መዋጋታቸውን ቀጥለዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከጥር 6 እስከ 9 በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ፣ እና የኦሮሞ የአካባቢ ታጣቂዎች ከኦነግ-ሸሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተዋግቷል። ብዙም ሳይቆይ የመንግስት ሃይሎች ቦታውን መልሰው ተቆጣጥረዋል (ኦቢኤን፣ ጥር 10, 2014)። ጥር 11 ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት በነገሌ ቦረና ከተማ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ሰንዝረው አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ሲገድሉ ሶስት ሰዎችን አቁስለዋል። በማግስቱ የኦነግ-ሸኔ አባላት በጉጂ ዞን አዶላ ሬዴ ወረዳ ሲጓዙ የነበሩ የብልፅግና ፓርቲ ባለስልጣንን በጥይት ተኩሰው ገድለዋል።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ ጃርደጋ ውስጥ የአማራ የአካባቢ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ሲገድሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኽዕቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። እንዲሁም በሆሮ ጉድሩ ዞን አሙሩ ወረዳ ጭዳቲ መንደር 15 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል (ኦኤምኤን፣ ጥር 14, 2014)።
በአፋር ክልል በአፋር/ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ውጊያዎች ቀጥለዋል። የአፋር ክልል መንግስት ጥር 7 እና 8 ላይ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) በአፋር ክልል ከልቤቲ ራሱ ዞን አባላ እና መጋሌ አካባቢዎችን በከባድ መሳሪያ ደብድቦ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን መግደሉን አስታውቋል (የአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ጥር 8, 2014)። በአባላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚጓዙ የሰብአዊ እርዳታ የያዙ መኪኖች በግጭቶቹ ምክንያት ከታህሳስ 5 ጀምሮ መንቀሳቀስ አልቻሉም (የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 12, 2014)።
ይህ በእንዲህ ባለፈው ሳምንት የትህነግ ሃይሎች በትግራይ ክልል ሚላዛት እና ዳንዴ አከባቢዎች የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች ያደረሱትን ጥቃቶች መመከት ችለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥር 9, 2014)። በተጨማሪም በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃይሎች በደቡብ ትግራይ ዞን በማይጨው፣ ኮረም፣ እና ሳምሬ አካባቢዎች የአየር ድብደባ ፈፅመው በደርዘን የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መሞታቸው ተነግሯል (የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 12, 2014)።
በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ የሰሜን ጎንደር እና ዋግ ኽምራ ዞን አካባቢዎች ግጭቶች የነበሩ ሲሆን ለብዙ ሺህ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል (የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 12, 2014)። ምንም እንኳን በአማራ ክልል ከሚገኙ 32 የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፖች ውስጥ 31ዱ የተዘጉ እና አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ቢሆንም አሁንም ወደቤታቸው የተመለሱ እና የምግብና የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጦት እያጋጠማቸው ያሉ ነዋሪዎች ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 9, 2014)። የአማራ ክልል መንግስት በአማራ ክልል በግጭቱ ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት እንዳልተኮተኮተ ገልጿል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 11, 2014)።
ጥር 12 ላይ በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂ ቡድኖች አባላት በኑዌር ዞን በአካቦ ወረዳ ስምንት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለው ማንነታቸው ያልታወቁ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ አምስት አቁስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 13, 2014)። በተጨማሪም ቡድኑ በጋምቤላ ክልል ኑዌር እና አኝዋክ ዞኖች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናትን አፍኗል።
ሳምንታዊ ትኩረት: በኦሮሚያ ክልል በሃይማኖታዊ በአል አከባበር ወቅት የተፈጠረ ግጭት
ባለፈው ሳምንት የክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ተከብሯል። በኦሮሚያ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን በቡራዩ ከተማ በተከበረው በዓል ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ያለአርማው የለበሱ በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ የኦሮሚያ ፖሊስ ከልክሏል። ምእመናን ታቦት ከአዲስ አበባ ወደ ቡራዩ ከተማ እየሸኙ ነበር። ይህንን ተከትሎ ግጭት የተቀሰቀሰ ሲሆን የኦሮሚያ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት ተኩሶ በትንሹ 3 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን አቁስሏል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 13, 2014)። ኩነቱ ከግጭት ቀጠና ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ሳይቀር በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ውስብስብ መከፋፈል አጉልቶ ያሳያል።
በ1985 በትህነግ መሪነት የተቋቋመው የሽግግር መንግስት የወጣው የኢትዮጵያ ህጋዊ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሃል ላይ ብሔራዊ አርማ አለው። ብሄራዊ አርማ የሌላቸው ባንዲራዎች ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከፓን ኢትዮጵያዊነት ጋር ይያያዛሉ። አርማው የሌለው ባንዲራ ብዙ ጊዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭቶች ውስጥ በተሰማሩ የየአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች ተይዞ ይታያል (ቢቢሲ ዜና፣ ታህሳስ 25, 2014)። ለአንዳንዶች ዓርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ መለያየትን የሚሻገር የሀገር ኩራትና የአንድነት ምንጭ ነው። ለኦሮሞ ብሔርተኛ ፖለቲከኛ ደጋፊዎች የኢትዮጵያ አንድነት እና ተጓዳኝ ባንዲራው የኦሮሞን ራስን በራስ የማስተዳደር እንዳይችል ያደረገ የፖለቲካ ጭቆና እና አለመቻቻል ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።
ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። ባለፈው ዓመት ብዙ አገራዊ ምልክቶች የጦፈ ክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆነዋል። ግንቦት 2013 ላይ ኢፍጣርን የሚያከብሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች በአዲስ አበባ መሀል ከሚገኘው መስቀል አደባባይ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ያልታወቁ አካላት የዝግጅቱን ቦታ እንዲቀይሩ ጠይቀዋል” በሚል በፀጥታ ሃይሎች በኃይል ተበትነዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ግንቦት 2, 2014)። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ መስቀል አደባባይ ያሉ የሕዝብ ቦታዎችን በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞች ላይ በብቸኝነት ለመቆጣጠር ትፈልጋለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተቺዎች የመንግስት አካላትን “በኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች” ተሞልተው የክልል የጸጥታ አካላትን በመጠቀም የግል የፖለቲካ አላማን ያስፈጽማሉ እንዲሆም እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ኢላማ ያደርጋሉ ሲሉ ይወቅሳሉ (ቦርከና፣ ጥር 13, 2014)። በ2008 በርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከቄሮ ተቃዋሚዎች ጋር በመቆም ከኦሮሚያ ክልል መሬት በመውሰድ የአዲስ አበባ ከተማ ወሰንን ለማስፋት የወጣውን የመንግስትን “ማስተር ፕላን” አስቁመዋል። በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪዎች የአማራ ክልል ታጣቂዎችን በኦሮሚያ ክልል የመሬት ወረራ እና አለመረጋጋት ፈጥረዋል በማለት በግልፅ ከሰዋል (ኦቢኤን፣ ጥር 5, 2014)።
የፌደራል መንግስቱ በቡራዩ የከሰተውን ኩነት በተመለከተ ብዙም ያላለ ሲሆን ከመንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች ስለ ድርጊቱ የሰጡት አስተያየት የለም። የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈት ቤት “የጥምቀት በዓልን ለማወክ የሚፈልጉ አካላት” እንደነበሩ ጠቅሰው የግጭቱ መንስኤ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል (በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ጥር 13, 2014፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ጥር 14, 2014)።
ቡራዩ እና ሌሎች በመዲናዋ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች በተለይ በሚቀጥሉት ወራቶች ለከፋ ብሔር ተኮር ግጭቶች ተጋላጭ የሚሆኑ ቦታዎች ናቸው። በኦሮሚያ ክልል የምትተዳደረው ነገር ግን ከመላው ሀገሪቱ የመጡ ግለሰቦች የሚኖሩባት ከተማዋ በ2010 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከኤርትራ ከተመለሰ በኋላ ግጭት ሲቀሰቀስ ከፍተኛ ብሔር ተኮር ጥቃት የተፈጸመባት ከተማ ነበረች (አልጀዚራ፣ መስከረም 7, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በቡራዩ እንደነበረውረው አይነት ሁከትና ብጥብጥ መከላከል ከባድ ሲሆን ስለሀገሪቷ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጥልቅ እና ሁሉን አቀፍ ውይይትን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዲዛይንና አጠቃቀም ምክንያት በቡራዩ የተከሰተው ግጭት በሀገሪቷ ውስጥ አሁን ያለውን ሥር የሰደደ የፖለቲካ ልዩነት ያሳያል።