ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥር 20, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,512
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 14,363
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,495
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከጥር 14, 2014 እስከ ጥር 20, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 30
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 54
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 9
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባሳለፍነው ሳምንት በአፋር ክልል ቂልባቲ ራሱ-ዞን 2 በአባላ፣ በርሀሌ፣ ኢሬብቲ፣ እና መጋሌ አካባቢዎች በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እንዲሁም ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተካሂዷል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። እንደአፋር ክልል መንግስት ገለጻ በዚህ ግጭት ከ220,000 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 18, 2014)። በትህነግ የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት የውጭ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ሃይሎቹ በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና በኤርትራ መንግስት ተደራጅቷል ብሎ የሚያምነውን የቀይ ባህር የአፋር ሃይል “የጋረደውን ስጋት ለማስወገድ እርምጃ እየወሰዱ ነው” ብሏል። እና የኤርትራ መንግስት (የትግራይ ክልል መንግስት የውጭ ግንኙነት ፅህፈት ቤት፣ ጥር 17, 2014)። የአፋር ክልል መንግስት የቀይ ባህር የአፋር ሃይል እና የኤርትራ መንግስት በአፋር ክልል አሉ መባሉን አስተባብሏል፣ ትህነግን በቂልባቲ ራሱ-ዞን 2 ያሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ከሷል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 18, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በትህነግ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይል መካከል ውጊያዎች መከሰታቸው ታውቋል። እነዚህ ዞኖች ከትግራይ ክልል ጋር ይዋሰናሉ። በተጨማሪም በጥቅምት 2013 ከጀመረ ወዲሁ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር በሆኑት የትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን ወልቃይት፣ ፀገዴ፣ እና ሁመራ አካባቢዎች ጦርነት ተዘግቧል።
በተጨማሪም የትህነግ ሃይሎች ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ደቡብ ትግራይ ዞን ዋጃ፣ ጥሙጋ፣፣ እና አላማጣ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦችን አጥተዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 19, 2014)። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ሸሽተው በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ ተጠልለዋል። በቀደምት ጊዜያት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ራያዎች በአማራ ክልል መንግስት ለመተዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ለመንግስት በሰላማዊ ሰልፎች እና በፅሁፍ አሳይተዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥቅምት 12, 2011፤ ቦርከና፣ ጷጉሜ 4, 2010)።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት መድረሱም ተዘግቧል። ጥር 15 ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጎቡ ሰዮ ወረዳ ባፋኖ አካባቢ የኦነግ-ሸኔ አባላት ከአዲስ አበባ ወደ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ አሶሳ የሚጓዙ አምስት ተማሪዎችን እና አንድ ነጋዴን አግተው ወስደዋል። በማግስቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ታፍነው የተወሰዱትን ግለሰቦች ለመታደግ በኦነግ-ሸኔ ላይ በአጎ (ጎቡ ሰዮ ወረዳ) በጋራ ወታደራዊ ዘመቻ አድርገዋል (አዲስ ማለዳ፣ ጥር 16, 2014)። ግለሰቦቹ ይለቀቁ አይለቀቁ የታወቀ ነገር የለም።
እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች የቶሬ እና የሻሞሌ ከተሞችን ሲቆጣጠሩ በገላና ወረዳ ቀርሳ እና ጀቤ ሲሬ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ሲዋጉ ግጭቱ ተባብሷል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 20, 2014)።
ባለፈው ሳምንት ኦነግ-ሼንን ይደግፋሉ ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ በርካታ ከህግ ውጪ የሆኑ እርምጃዎች ተወስደዋል። ጥር 17 ላይ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ባቲ ከተማ ጉሬ ቀበሌ ውስጥ የፌደራል ፖሊስ ሃይሎች የኦነግ-ሸኔ አባላትን ደብቃችኋል በሚል ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል። ጥር 16 ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኦነግ-ሸኔን የተቀላቀሉ ወጣቶች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ጥር 16, 2014)። በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳዳሪ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው በዞኑ ውስጥ ከኦነግ-ሸኔ ጋር በመተባበር እና “ሁከትን በማነሳሳት” የተጠረጠሩ ከ1,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን አሳውቋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 19, 2014)። እስሩ በምን ያህል ጊዜ እንደተፈፀመ ግልፅ አይደለም ። ከህዳር 2014 ጀምሮ ኦነግ-ሸኔም እና ትህነግ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎችን እንደገና በተቆጣጠሩበት ወቅት ከ260 በላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መገደላቸውን የዞኑ አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 19, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ልታነሳ ስለመሆኑ
ጥር 18 ላይ የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23, 2014 የታወጀው የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የሚጠይቅ ውሳኔ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በቅርቡ በፌዴራል መንግሥት የተገኘውን የግዛት ይዞታ በማጣቀስ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ አስፈላጊ የሆነው ሁኔታ…. ተቀይሯል” ብሏል (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት-ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 28, 2014)። ምንም እንኳን የውሳኔ ሃሳቡ በኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት ገና መጽደቅ የሚቀረው ቢሆንም መግለጫው በኢኮኖሚው ላይ ፈጣን ተጽእኖ አሳድሯል። የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የቦንድ ገበያ በዚህ ምክንያት “በዚህ አመት በታዳጊ ገበያዎች ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም ያለው ሉዓላዊ ዕዳ” ሊሆን ችሏል (ብሉምበርግ፣ ጥር 23, 2014)።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን አጽድቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም እንኳን ኢትዮጵያ አሁንም በጦርነት ላይ ነች። ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው በአፋርም ሆነ በአማራ ክልሎች ከትህነግ ጋር ውጊያዎች በየቀኑ እየተካሄዱ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ደግሞ መንግስት ያለውን አመፅ በመታገል ላይ ነው። ትህነግ ከምዕራብ ትግራይ ዞን ውጪ መላውን ትግራይ እንዲሆም በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች እና በአፋር ክልል ቂልባቲ ራሱ-ዞን 2ን ይዟል። ኦነግ-ሸኔ ትልልቅ ከተሞችን ባይዝም በምዕራባዊ እና ደቡባዊ የኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን በማጥቃት፣ መንገዶችን በመዝጋት፣ የግል ንብረቶችን እና የመንግስት ተቋማትን በመዝረፍ ለማስተዳደር የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ አድርጎታል። በመላ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ተፈናቅለዋል።
መንግሥትም ሌሎች ፈተናዎችምም እየገጠሙት ነው። በጦርነቱ ወቅት ትህነግን ለመመከት በክልሉ የተደራጁት የአማራ ታጣቂዎች (ፋኖ) የወደፊት እጣ ፈንታን በሚመለከት ከፍተኛ ክርክር እየተካሄደ ነው (ፋና ቴሌቪዥን፣ ጥር 20, 2014፤ ሮይተርስ፣ ጥር 13, 2014)። በበአማራ ክልል ባለስልጣናት የተደራጁ ታጣቂዎችን ምንም እንኳን ትነህግን ለመዋጋት የሰለጠኑ እና የታጠቁ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ጥልቅ ምኞት አላቸው። እነዚህን ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት ወይም ወደ ፌዴራል ታጣቂ ሃይሎች ወይም የክልል ልዩ ሃይሎች መቀላቀል በጣም አከራካሪ ነው – ይህ ከህዳር 22, 2014 እስከ ታህሳስ 22, 2014ን በሚሸፍነው ኢፒኦ ወርሃዊ የተካተተው ሁኔታ ነው።
በጦርነቱና ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የጦር መሳሪያ ፍላጎት ለማሟላት ህጋዊ ያልሆኑ መንገዶች የተስፋፉ ሲሆን የጦር መሳሪያ ዝውውር በመላ አገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ይህንን ችግር የሚያባብሰው ይሆናል (ኢቢሲ፣ ጥር 24, 2014)። እንዲሁም ባለው አለመረጋጋት እና በዶላር ምንዛሬ በተዳከመው ብር ምክንያት የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል (እስከ 40%) ይህም ለኑሮ ውድነት አስተዋጾ አድርጓል (ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ፣ ጥር 17, 2014)።
ከእነዚህ ተግዳሮቶች አንፃር በተለይም በጦርነቱ ምክንያት አሁንም ችግር ውስጥ ባሉ ወገኖች ዘንድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትት በተወሰነ መልኩ ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል። እንደተገለፀው በሳምንቱ ውስጥ የትህነግ ሃይሎች በአፋር ክልል አካባቢዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ከ220,000 በላይ ሰዎችን አፋናቅለዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 18, 2014)። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት የቀረበውን ሀሳብ በተመለከተ የአፋር ህዝብ ፓርቲ የፌደራል መንግስት የአፋር ክልልን ሁኔታ ችላ በማለት ከሶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለበት እንዲቀጥል ጠይቋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ጥር 18, 2014)።።
ለአንዳንዶች ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ሀገሪቱ ወደ መደበኛ ሁኔታ እንደምትመለስ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ በተለይ በተሻሻለ የደህንነት ፕሮቶኮሎች ምክንያት ለታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እውነት ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሚሽን ባወጣው መግለጫ የውሳኔ ሃሳቡን “አበረታች” በማለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በፌዴራል መንግስት የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ አሳስቧል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጥር 18, 2014)። የፌደራል መንግስት በዚህ አመት ሊደረግ ለታቀደው ብሄራዊ ውይይት በርካታ ታዋቂ እስረኞችን ለቋል (ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ታህሳስ 29, 2014)።
የኢትዮጵያ የመጨረሻው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የትህነግ ሃይሎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በፍጥነት እየገሰገሱ በነበረበት ወቅት ነበር። በታህሳስ 2014 ላይ ትህነግ ወደ ትግራይ ክልል ሲያፈገፍግ በፌዴራል መንግስቱ ላይ የጣለው ስጋት ቢወገድም አሁንም ከትግራይ አዋሳኝ በሆኑት የአፋር እና አማራ ክልሎች የቀጠሉት ጦርነቶች ኢትዮጵያ ካለችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ ገና እንዳልራቀች የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። ሆኖም የአደጋ ጊዜ ሃይሎች መቃለል እና እስረኞች መፈታት ጥሩ ምልክት ነው።