በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ጥር 27, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,540
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 14,389
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,530
በቁጥር (ከጥር 21, 2014 እስከ ጥር 27, 2014) 2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 14
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 29
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 26
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባሳለፍነው ሳምንት ግጭት የቀጠለ ሲሆን በትግራይ/አፋር ክልሎች አዋሳኝ የሆነው አባላ ከተማ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ሃይል ከአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአካባቢ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። የትህነግ ታጣቂዎች ወደ ምስራቅ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ውጊያዎች በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ወደ በርሀሌ፣ መጋላ፣ ኩነባ፣ እና ኤረብቲ አካባቢዎች ተስፋፍተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ተፋላሚ ወገኖች በከባድ መሳሪያዎች እና ትንንሽ መሳሪያዎች ከባድ ውጊያ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 23, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ኤሊያዳር ወረዳ የሃዩ ከተማ እና የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች ትህነግ በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 የፈጸመውን ጥቃቶች በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 22, 2014፤ ኢሳት፣ ጥር 23, 2014)። በተጨማሪም የአፋር ዲያስፖራ ቡድን በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ትህነግ በቂልባቲ ራሱ-ዞን 2 የፈጸማቸውን ጥቃቶች አውግዘው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 25, 2014)። ሰልፈኞቹ የፌደራል መንግስት በዞኑ የተቀሰቀሰው ግጭት ላይ ያሳየውን ዝምታም አውግዘዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን በኦሮሚያ ልዩ ሃይሎች እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ያለው ውጊያ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በገላና ወረዳ የቶሬ፣ ሻሞሌ፣ እና ቀርሳ አካባቢዎችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረውታል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 28, 2014)።
በምስራቅ ወለጋ ዞን የፌደራል ሃይሎች በኦነግ-ሸኔ እና በዞኑ በሚንቀሳቀሱ “ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች” ላይ በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል። የአካባቢው ባለስልጣናት በምስራቅ ወለጋ ዞን በኑኑ ኩምባ ወረዳ 22 ቀበሌዎች በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደነበሩ ገልፀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ፣ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ዘመቻ 14ቱን ቀበሌዎች በድጋሚ በቁጥጥራቸው ስር ማስገስገባታቸውን አሳውቀዋል (ኢቢሲ፣ የካቲት 1, 2014)። የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ በተካሄደ ሌላ ዘመቻ ከኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ጋር ከተዋጉ በኋላ ቦታውን መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል (ኢቢሲ፣ ጥር 30, 2014)። ባለፈው ሳምንትም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ጋር በቄለም ወለጋ ዞን አንፊሎ ወረዳ ውጊያ አድርገው 17 ተዋጊዎችን መያዛቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በአማራ ታጣቂዎች እና በአካባቢው ኦሮሞ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ግለሰቦች ተፈናቅለዋል ንብረትም ወድሟል። በዳኖ ወረዳ የአማራ ታጣቂዎች በአጂሎ ዳሌ ቀበሌ በኦሮሞ ገበሬዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ስምንት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን መግደላቸው ተነግሯል። በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ እና አሙሩ አካባቢዎች ተጨማሪ ግጭቶች እና የአማራ ታጣቂዎች የተሳተፉበትና በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
በጋምቤላ ክልል የሙርሌ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ያደረሷቸውን ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች በተመለከተ ለመወያየት የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ የክልሉ ባለስልጣናት ጥር 25, 2014 ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ ተጉዘዋል። በወሩ መጀመሪያ ላይ የደረሱ ጥቃቶች ቢያንስ የስምንት ሰዎችን ህይወት መጥፋት እንዲሁም አፈና እና የቀንድ ከብቶችን ዘረፋ አስከትለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 13, 2014)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የሰብአዊ እርዳታ የሚያደርሱ አጋር ድርጅቶች አዲስ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ለመደገፍ እየጣሩ ነው። ጥር 10, 2014 በቶጎ ከተማ አቅራቢያ ማንነቱ ባልታወቀ ታጣቂ ቡድን እና በፌደራል ሃይሎች መካከል የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ 20,000 ሰዎች መፈናቀላቸው ይገመታል (የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን፣ ጥር 27, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት: ሰብአዊ ቀውስ በኢትዮጵያ
በሰሜን ኢትዮጵያ እና በኦሮሚያ ክልል ያያሉ ግጭቶች እንዲሁም በሀገሪቱ ደቡብ/ምስራቅ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እና የመንግስት ሃብት እንዲጣበብ እያደረገ ነው። በትግራይ ክልል የትህነግ ባለስልጣናት ለወራት መሰረታዊ አገልግሎቶችን መስጠት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ ለአደጋ ተጋልጧል።
በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ትህነግ እና የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች መካከል በቅርቡ በአዲስ መልክ በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት ከ300,000 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ክልል ባለስልጣናት አሳውቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 30, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 23, 2014)። በአባላ ከተማ ሰመራ-አባላ መንገድ እና በደቡብ ትግራይ በድጋሚ የጀመረው ግጭት እርዳታ የሚያደርሱ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ እንዳይችሉ ያደረገ ሲሆን ከታህሣሥ 6 ጀምሮ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መግባት አልቻለም (የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 26, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 16, 2014)። የሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱ መኪኖች በሰመራ -አባላ ዋና መንገድ ተጉዘው ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን ያደርሱ ነበር። እንደተጠቀሰው ከጥር 16, 2014 ጀምሮ በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ያለው ግጭት እየተባባሰ በመምጣቱ የሰብአዊ እርዳታ የሚያደርሱ መኪኖች በሰመራ -አባላ መንገድ መጓዝ አልቻሉም። ቢሆንም ከጥር 18 እስከ ጥር 27 ባለው ጊዜ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በርካታ የሰብአዊ በረራዎችን በማዘጋጀት እንደ “ኢንሱሊን፣ ሄሞዳያሊስስ፣ ኦክሲቶሲን፣ ቴታነስ ቶክሳይድ፣ ጓንት እና የቀዶ ጥገና ቁሳቁስ” ያሉ “ዋና የህክምና ቁሳቁሶችን” ለትግራይ ክልል አቅርቧል (የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ጥር 27, 2014፤ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ ጥር 18, 2014)።
በአፋር ክልል ከተፈጠረው ግጭት በተጨማሪ በደቡብ ትግራይ ዞን ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ እና አላማጣ አካባቢዎች የሚኖሩ የራያ ብሄረሰብ አባላት በቅርቡ በእነዚህ አካባቢዎች ትህነግ ባደረሰው ጥቃት ተፈናቅለዋል። እነዚህ ተፈናቃዮች የሰብአዊ እርዳታ እየጠየቁ ነው (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 16, 2014)። ከእነዚህ ተፈናቃዮች አብዛኞቹ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ውስጥ ይገኛሉ። የዋጃ እና ጥሙጋ ቀበሌ አስተዳዳሪ እንዳሉት በቅርቡ በቆቦ ከተማ ከ12,000 በላይ ሰዎች ተጠልለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 19, 2014)።። ምንም እንኳን በአማራ ክልል ቀደም ሲል በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ቢመለሱም በኑሮ፣ መሰረተ ልማቶች፣ እና የእርሻ መሬቶች ላይ በደረሰ ውድመት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 24, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በኦነግ-ሸኔ ጥቃቶች እና በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂዎች መካከል ባሉ ውጊያዎች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ እና ጉጂ ዞኖች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ግለሰቦች በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ እና አማራ ክልሎች ተበታትነው ይገኛሉ (ቪኦኤ አማርኛ፣ ታህሳስ 26, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 16, 2014)። በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና ግጭቶች እየቀጠለ በሄደ መጠን የተፈናቃዮች ቁጥርም እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ (ስምንት ዞኖች)፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (ሰባት ዞኖች)፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (አንድ ዞን)፣ እና በሶማሌ (አሥር ዞኖች) ክልሎች የሚኖሩ 6.8 ሚሊዮን ሰዎች በተከታታይ ሦስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ ለድርቅ ተጎጂ ሆነዋል (የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 30, 2014)። ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል (አብይ አህመድ አሊ፣ ጥር 26, 2014)። ከአንድ ሳምንት በፊትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል (አብይ አህመድ አሊ፤ ጥር 26, 2014)። በእነዚህ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል እንደ የግል ባንኮች፣ ድርጅቶች፣ እና የክልል መንግስታ ያሉ የተለያዩ ሀገር አቀፍ ተቋማት የገንዘብ እና የተለያዩ አቅርቦቶች ለኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል መንግስታት እየለገሱ ነው።
እነዚህ ቀውሶች የመንግስትን ሃብት እና በግጭት እና በድርቅ የተጎዱትን ህዝቦች ለመርዳት ያለውን አቅም እየተፈታተኑት ነው። ለእነዚህ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት የሀገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ የሃብት ክፍተቶች በርካቶችን ለችግር ዳርጓቸዋል። በመላ ሀገሪቱ ያሉ ውጊያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት እንዲታወክ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እርዳታ እንዲያስፈልጋቸው ምክንያት ሆኗል፤ ይህ አዝማሚያ ግጭቶች እየቀጠሉ በሄዱ መጠን እንደሚቀጥል ይጠበቃል።