በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ የካቲት 11, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,589
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 14,684
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,647
በቁጥር (ከየካቲት 5, 2014 እስከ የካቲት 11, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 14
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 51
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 45
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ዞን የአማራ ብሔር ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ላይ በተደጋጋሚ ጥቃቶች ማድረሳቸው ተዘግቧል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የካቲት 5 ላይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዶንጎሮ ወረዳ ቦቶሮ ቦራ የአማራ ብሔር ታጣቂዎች 20 ሰዎችን ገድለው በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ስዎች ቤቶችን አቃጥለዋል። በተጨማሪም ቡድኑ የተለያዩ ንብረቶችን ዘርፎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን ወስዷል። የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ከየካቲት 7 እስከ 9 ድረስ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ነዋሪዎችን ገድሏል። ከዚህ ቀደም በዚህ አካባቢ አብዛኞቹ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የሚደርሱት በአማራዎች ላይ ሆኖ ጥቃቶቹ የሚፈጸሙት ደግሞ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ነበር። የካቲት 9 ላይ የአማራ የብሄር ታጣቂዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ ሰዎች በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ነገሶ እና ሃሮ አያና ቀበሌዎች ጥቃት ፈጽመው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ገድለዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ የካቲት 14, 2014)። ባለፈው ሳምንት በኦነግ-ሸኔ ጥቃት ምክንያት ከሆሮ ጉዱሩ እና ከምስራቅ ወለጋ ዞኖች የተፈናቀሉ ከ400 በላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ አማራዎች አዲስ አበባ የደረሱ ሲሆን መንግስት እንዲረዳቸውና የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል (ኢሳት፣ የካቲት 11, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በመንግስት እና በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ቡድኖች በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡነ ግንደበረት ወረዳ፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ፣ እና በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሚኤሶ በረዳ ተዋግተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሃይሎች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ከህግ አግባብ ውጪ እርምጃዎችን መውሰድ ቀጥለዋል። የካቲት 5 ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች በአቡነ ግንደበረት ወረዳ አዋራ አካባቢ አንድ እስረኛን ተኩሰው ገድለዋል። ሟቹ ከአንድ ቀን በፊት ኦነግ-ሸኔን ይደግፋሉ ተብለው ተጠርጥረው ከታሰሩ 20 ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። በተመሳሳይ ቀን የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ ፌደራል ፖሊስ፣ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ሺኩቴ ከተማ የአካባቢው ነዋሪዎች የኦነግ-ሸኔ አባላትን እየመገቡ ነው በማለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጥይት ተኩሰዋል። በዚህ ጥቃት የሁለት ህፃናት ህይወት ሲያልፍ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው ቆስሏል። ከሁለት ቀናት በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እዚያው ከተማ ውስጥ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪን ተኩሰው ገድለዋል። ግድያው የተፈፀመበት ምክንያት ግን አይታወቅም።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔ ላይ ሁለት የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። የካቲት 9 ላይ በቅርቡ በወረ ጃርሶ ወረዳ ሸንኮራ ሸሸንግ ቀበሌ በአርሶ አደሮች ላይ የተፈጸመውን አፈና እና ግድያ በመቃወም በጎሃ ጽዮን ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። ሰልፈኞቹ ጎሃ ፅዮንን ከባህርዳር ከተማ የሚያገናኘውን የአባይ በረሃ ዋና መንገድ ለሰአታት ዘግተውታል። ከሳምንት በፊት የካቲት 2 ላይ የኦነግ-ሸኔ አባላት ቢያንስ 18 ገበሬዎችን በማፈን ለማስለቀቅ የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ያልቻሉትን ሰባት ገበሬዎች ገድለዋል። ሁለተኛው የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው አርብ የካቲት 11 ላይ ሲሆን የአቡነ ግንደበረት ከተማ ነዋሪዎች የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን ተቃውመው “ለኦሮሞ ህዝብ ትግል” በሚል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መግደል እና ንብረት ማውደም እንዲያቆም ጠይቀዋል (የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ የካቲት 11, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል የአክሌድ መረጃ በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በርሃሌ እና ኤረብቲ ሁለት የከፍተኛ መሳሪያ ድብደባዎችን መዝግቧል። የካቲት 9 ላይ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሀት) የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና አጋር ታጣቂዎችን በኤሬብቲ በከፍተኛ መሳሪያ ደብድቧል። በተመሳሳይ ቀን ከበርሀሌ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአዳ ከተማ አቅራቢያ አላ ወንዝ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባደረጉት የከፍተኛ መሳሪያ ድብደባ ከአንድ የአፋር ቤተሰብ የሆኑ 10 ሰዎች ሲሞቱ 13 ሰዎች ቆስለዋል። በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በተፈጠረው የትጥቅ ግጭት ሳቢያ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መፈናቀላቸውን ቀጥለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 10, 2014)።
የካቲት 8 ላይ በሶማሌ ክልል ፋፋን ዞን አው ባሬ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች አንድ የተሳፋሪዎች መኪና በፍተሻ ጣቢያ ላይ ባለመቆሙ ተሽከርካሪው ላይ ተኩስ ከፍቷል። ሁለት ተማሪዎች ተገድለዋል። ድርጊቱን ተከትሎ ሰልፈኞች በተቃጠለ ጎማ መንገዶችን በመዝጋት ለተጎጂዎች ፍትህ ጠይቀዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት: የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት
ባለፈው ሳምንት የካቲት 8 ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 23, 2014 ላይ ያሳለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል። 63 ተወካዮች ውሳኔውን የተቃወሙ ሲሆን 21 ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል (የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የካቲት 8, 2014)። ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ ምክር ቤቱ ለጸጥታ አካላት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ያልተጠናቀቁ ተግባራትን – ለምሳሌ የታሰሩ ሰዎችን መልቀቅ ወይም በመደበኛ የፍትህ ሂደት ማስተናገድ – በአንድ ወር ውስጥ እንዲያጠናቅቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት የተቃወሙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሁንም ከፍተኛ የጸጥታ ስጋቶች እንዳሉ አጥብቀው በመግለጽ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ትህነግ የሚሳተፍባቸው እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ኦነግ-ሸኔ የሚሳተፍባቸውን ግጭቶች ጠቁመዋል ( ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 8, 2014)።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳትን የተቃወሙ ተወካዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትህነግ ወይም ኦነግ-ሸኔ ጋር ድርድር ላይ የተመሰረተ ሰላም ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት የሚቃወሙ የኢትዮጵያ መንግስት ወሳኝ ክፍሎችን ይወክላሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጊዜ ማብቃት የተቃወሙት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የብልጽግና ተወካዮችም ከትህነግ ጋር መነጋገር እና የትህነግ እና ኦነግ-ሸኔን “አሸባሪ” የሚል ስያሜ መሰረዝንም ተቃውመዋል። የአብን ባለስልጣን የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ መንግስትን “የዜጎችን ደህንነት ሳያረጋግጥ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ለማስደሰት” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያለጊዜው በማንሳቱ ከሰውታል (ሮይተርስ፣ የካቲት 8, 2014)። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ለክሱ ከትህነግ ጋር መንግስት እንዳልተነጋገረ መልስ ሲሰጡ “እስካሁን [ማለትም እስከ የካቲት 15, 2014] ድረስ ምንም አይነት ድርድር የለም ። ይህ ግን ከትህነግ ጋር ውይይት የመኖር እድል መኖሩን አያስቀርም” ብለዋል (ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 15, 2014)።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ውሳኔ በደስታ ተቀብለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የታሰሩ ቀሪ ሰዎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የካቲት 8, 2014፤ ኢሰመኮ፣ የካቲት 8, 2014)። ተመድ ህዳር 2014 ላይ ከትህነግ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩበት 16 ሰራተኞቹ መካከል የመጨረሻዎቹ 3ቱ ባለፈው ሳምንት መለቀቃቸውን ገልጿል (ኢትዮጵያን ኢንሳይደር፣ የካቲት 12, 2014)። ሌሎቹ ባለፉት ጥቂት ወራት ተለቀዋል። የፍትህ ሚኒስቴር የፕሬስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ጉዳይ አሁን በ”መደበኛ” ህጋዊ አሰራር ይፋጠናል ብለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ የካቲት 11, 2014)።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመንግስት እና የጸጥታ ሃይሎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ግለሰቦችን የመፈተሽ እና የማሰር ስልጣን ሰጥቷል። በተጨማሪም የጸጥታ ስጋት ካለ ጎዳናዎች እንዲዘጉ፣ የአስተዳደር መዋቅሮች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲታገዱ ወይም አስተዳዳሪዎች እንዲተኩ፣ እና ሌሎችንም ይፈቅዳል (የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር፣ ጥቅምት 24, 2014)። ይህንን ተከትሎ ከጥቅምት እስከ የካቲት 2014 በአብዛኛው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከትህነግ ወይም ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ታስረዋል (ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 27, 2014 እስከ ህዳር 3, 2014)። በተጨማሪም በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የጸጥታ ምክንያቶችን በመስጠት መንገዶችን ዘግተው ከወሎ ዞኖች ተፈናቅለው ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚጓዙ ተፈናቃዮችን አስቁመዋል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ጥቅምት 26, 2014)።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በይፋ ቢነሳም ከህግ ውጪ የሚደረጉ እስራቶች ግን ቀጥለዋል። የካቲት 10, 2014 ላይ ኢሰመኮ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ እስራቶችንና ተከሳሾች በእስር ላይ ሆነው ምርመራ እንዲደረግባቸው የሚፈቅደው ሂደት ያለአግባብ ጥቅም ላይ መዋል ላይ” ያለውን ስጋት የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል (ኢሰመኮ፣ የካቲት 10, 2014)። መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ቀሪ እስረኞችን ለፍርድ ማቅረብ መቻሉ ለጊዜው ግልፅ አይደለም።