ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 በጨረፍታ
ዋና ቁጥሮች
- አክሌድ ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 ድረስ 117 የተደራጁ የፖለቲካ የግጭት ኩነቶች እና 409 ሟቾችን መዝግቧል።
- ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ወቅት በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት በተከሰቱ ግጭቶች ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በኦሮሚያ ክልል ሲሆን በክልሉ 208 ሟቾች ነበሩ። አፋር ክልል በ60 የተዘገቡ ሟቾች ቁጥር ይከተላል።
- ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ጊዜ በተደጋጋሚ የተከሰተው የኩነት አይነት ውጊያ ሲሆን 73 የዚህ አይነት ኩነቶች እና 166 ሟቾች ተመዝግበዋል።
ዋና ሂደቶች
- በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እንዲሁም ታጣቂዎች መካከል በአፋር ክልል ቂልባቲ-ረሱ ዞን 2 ግጭት በድጋሚ ተቀስቅሷል።
- በትግራይ እና አማራ ክልሎች ወሰኖች አካባቢ በትህነግ/ህወሃት እና የመንግስት ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ቀጥሏል።
- በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት የተወሰደ የአየር ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድሏል።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና ኦሮሚያ ታጣቂዎች ጋር መዋጋቱን ቀጥሏል።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ
- ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 የነበሩ ሁኔታዎች አጭር መግለጫ
- ወርሃዊ ትኩረት:- የኦነግ-ሸኔ እድገት በኦሮሚያ ክልል
ከታህሳስ 23, 2014 እስከ ጥር 23, 2014 የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ወር በመላው ሰሜን ኢትዮጵያ በትህነግ/ህወሓት እና በፌደራል መንግስት እንዲሁም የአፋር እና አማራ ክልል መንግስታት ጋር ግንኙነት ባላቸው ሃይሎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። ጥር 5 ላይ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 የሚገኘውን የአባላ ከተማን በከባድ መሳሪያ ደብድበዋል። ከዚያም የከባድ መሳሪያው ድብደባው ወደ መጋሌ አካባቢ የተስፋፋ ሲሆን ከጥር 16 ጀምሮ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ወደ ክልሉ በመግባት ከአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአፋር ታጣቂዎች ጋር በቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በመጋሌ፣ አባላ፣ በርሃሌ፣ እና ኤሬብቲ ተዋግተዋል። የክልሉ አመራሮች ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ወቅት ከ300,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 30, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ ጥር 23, 2014)። የትህነግ/ህወሓት አመራር በአፋር እየተካሄደ ያለውን ውጊያ ትህነግ/ህወሃት በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና በኤርትራ መንግስት ተደራጅቷል የሚሉት “የቀይ ባህር አፋር ሃይል የፈጠረውን ስጋት ለማስወገድ የሚወሰድ እርምጃ ነው” ሲል ገልጿል (የትግራይ ውጭ ግንኙነት ቢሮ፣ ጥር 17, 2014)። የአፋር ክልል መንግስት የቀይ ባህር አፋር ሃይል የሚባል አለመኖሩን ገልጾ የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ መኖራቸውንም አስተባብሏል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 18, 2014)።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች በትህነግ/ህወሓት እና በመንግስት ሃይሎች መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። አብዛኛዎቹ እነዚህ ውጊያዎች የሚካሄዱት በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ነው። ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ወቅት በምዕራብ ትግራይ ዞን ሁመራ እና ፀገዴ፤ በደቡብ ምስራቅ ትግራይ ዞን ሚላዣት እና ዳንዲያ፤ በደቡብ ትግራይ ዞን ጥሙጋ፣ ቸርቸር፣ ኮረም፣ እና አላማጣ በትህነግ/ህወሓት እና የመንግስት ሃይሎች መካከል ውጊያዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሃይሎች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በማይ-አይኒ የስደተኞች ካምፕ፣ ደደቢት፣ እና ማይ ፀምሬ፤ በደቡብ ትግራይ ዞን ኮረም እና ማይጨው፤ በደቡብ ምስራቅ ትግራይ ዞን ሳምሪ፣ እና መቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ ፈጽሟል። እነዚህ የአየር ድብደባዎች ተፈናቃዮችን እና ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ በርካታ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ገድለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እና የታጠቁ ግጭቶች ወሩን ሙሉ ቀጥለዋል። ከታህሳስ እስከ ጥር 2014 ባለው ወቅት በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ታጣቂዎች ተዋግተዋል። በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የደረሱ ከ20 በላይ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ከነዚህ ጥቃቶች ውስጥ አስራ አንዱ በኦነግ-ሸኔ የተፈፀሙ ሲሆን ስድስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ደግሞ የተፈጸሙት በአማራ ታጣቂዎች ነው። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎችም በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በቡራዩ፣ በቄለም ወለጋ ዞን ገባ ከሚሳ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ኦሶሌ ቀበሌ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ተኩሰው ገድለዋል። በሌላ በኩል ጥር 5 ላይ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ጊንዶ ቀበሌ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የኦነግ ፓርቲ አባል የሆነን ግለሰብ ከወሊሶ ከተማ ወደ አማያ ሲሄድ ከነበረ የህዝብ ማመላለሻ ላይ በማውረድት ተኩሰው ገድለዋል።
ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23 ባለው ወር በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ሁለት ውጊያች እና አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆነ ግለሰብ ላይ የደረሰ ጥቃት ተመዝግበዋል። በወሩ መጀመሪያ ላይ በአሶሳ ዞን በገመድ አካባቢ ከትህነግ/ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። እነዚሁ ቡድኖች በካማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን አፍነው ሊወስዱ ከሞከሩ ከትህነግ/ህወሓት ጋር ግንኙነት ካላቸው ሃይሎች ጋር ተዋግተው ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ጥር 10 ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በማኦ-ኮሞ ልዩ ዞን ቶንጎ ውስጥ ከፌደራል ፖሊስ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። ይህ ቡድን በዚሁ ከተማ የሚገኘኝ የስደተኞች ካምፕን ዘርፎ አቃጥሏል። በተጨማሪም ጥር 3 ላይ በመተከል ዞን ድባቴ የአማራ ታጣቂዎች አራት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ተኩሰው አንድ ሰው ሲገድሉ ሶስት ሴቶችን አቁስለዋል። ከዚህ ጥቃት በስተጀርባ ያለው ምክንያት አልታወቀም።
ባለፈው ወር ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያደርሱ በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ ቢያንስ ስምንት ሰዎችን ገድለዋል፣ ህጻናትን አግተዋል፣ ከብቶችን ዘርፈዋል። በአኝዋክ ዞን ታጣቂዎች ሶስት ሰዎችን ገድለው አራት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን አቁስለዋል። እነዚህ ጥቃቶች የተመዘገቡት ቡድኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረጉ ካልተመዘገበ ከአንድ አመት ገደማ በኋላ ነው። የካቲት 17, 2013 ላይ በተፈጠረ ሌላ ኩነት ቡድኑ በአኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ባንዴራ ቀበሌ ከአካባቢው ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች በክልሉ ውስጥ በአብዛኛው ይንቀሳቀሱ የነበረው በ2009 የነበረ ሲሆን አክሌድ በአኝዋክ ዞን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የደረሱ ሰባት ጥቃቶችን መዝግቧል።
ወርሃዊ ትኩረት፡ የኦነግ-ሸኔ እድገት በኦሮሚያ ክልል
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመባል የሚታወቀው ኦነግ-ሸኔ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለፉት ጥቂት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የነበረ ሲሆን ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23 በነበረው ወቅት የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በደቡብ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ክልል በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል። ቡድኑ በዚህ ወር አዳዲስ ግዛቶችን መያዙ ቡድኑ እየተጠናከረ መምጣቱን እና በኦሮሚያ ክልል ገጠር እና ከተማ አካባቢዎች ድጋፍ እያገኘ እንደሆነ ሊያመለክት ይችላል። ምንም እንኳን ኦነግ-ሸኔ ዋና ዋና ከተሞችንና አውራ ጎዳናዎች ባይቆጣጠርም ቡድኑ ግዛቶችን መያዙ እና መቆጣጠሩ በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት አዲስ ምዕራፍ የሚያመላክት ከመሆኑም በላይ በመንግስት ታጣቂዎች እና በኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ሊኖር ለሚችል የበለጠ ጦርነት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የኦነግ-ሸኔ ተዋጊዎች በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ፌዴራሊስት እና የኮንፌደራሊስት ሃይሎች ህብረት ውስጥ የሚገኙት ትህነግ/ህወሃት እና ሎሎች ስምንት ቡድኖችን ጨምሮ ከሌሎች ፀረ-መንግስት ሃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥረዋል። ምንም እንኳን በግንባሩ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ያላቸውን እንቅስቃሴ ቢቀንሱም የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በክልሉ መስፋፋታቸውን ቀጥለዋል። ኦነግ-ሸኔ ከሌሎች የህብረቱ ቡድኖች ጋር ያለው ግንኙነት በኢፒኦ ወርሀዊ:- ከጥቅምት 22, 2014 እስከ ህዳር 21, 2014 ላይ ተዳሷል።
በጥር ወር አጋማሽም የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በፍጥነት በትጥቅ ተበልጠው የበላይነት ከተወሰደባቸው የአካባቢ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተው በምዕራብ ጉጂ ዞን በርካታ ወረዳዎችን ተቆጣጥረዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 28, 2014፤ ሪፖርተር፣ የካቲት 16, 2014)። በተጨማሪም ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ወቅት በምስራቅ ወለጋ ዞን የተካሄዱ ውጊያዎች እንደ ኑኑ ኩምባ ባሉ አካባቢዎች 22 ቀበሌዎች መንግስት ከማጥቃቱ በፊት በኦነግ-ሸኔ ቁጥጥር ስር እንደነበሩ የሚያሳዩ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል ያልተረጋገጠውን የቡድኑን ቦታዎችን ዘልቆ መቆጣጠር ያሳያል (ኢቢሲ፣ የካቲት 1, 2014)። በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ሃይሎች በቅርቡ በአዲስ ጥቃት እንደገና ከመቆጣጠራቸው ከሁለት ወራት በፊት ከተማውን ማጣታቸውን አምነዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ የካቲት 7, 2014)። የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በምዕራብ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችንም እየተቆጣጠሩ ነው።
ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23, 2014 ባለው ወቅት የትህነግ/ሕወሃት ሃይሎች ከአካባቢው ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንን ሲቆጣጠሩ በኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ላይ የሚወሰደው ከባድ እርምጃ ቀጥሏል። የመንግስት ባለስልጣናት በዞኑ በተደረገ እንቅስቃሴ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ1,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጸዋል። በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይም በደል እንደደረሰ አንዳንድ ዘገባዎች የሚያሳዩ ሲሆን ኦነግ-ሸኔን ደግፈዋል በሚል የተከሰሱ ብዙ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች በጸጥታ ሃይሎች በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ያመለክታሉ (አዲስ ስታንዳርድ፣ የካቲት 8, 2014)።
የግዛት ቁጥጥርን የተመለከቱ መረጃዎች በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥቅምት 23, 2014 ላይ በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከታወጀ ወዲህ በመንግስት ባለስልጣናት በጥብቅ የተገደቡ ናቸው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት “ስለ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ፣ የጦር ግንባር ዘገባዎች፣ እና ውጤቶች በማንኛውም ሚዲያ ማሰራጨት የተከለከለ ነው” (ሮይተርስ፣ ህዳር 17, 2014)። መንግስት ስለ ኦነግ-ሸኔ ሪፖርት ባለማድረጉ ቡድኑን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል በተጨማሪም ግጭት በሚፈጠርባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ያለው የመሰረተ ልማት ደካማነት በአካባቢው ጋዜጠኞች ለሚገጥማቸው ችግር አስተዋጽኦ ያደርጋል። ህዳር 22, 2014 ላይ 14 የከረዩ አባ ገዳዎች – የከረዩ ባህላዊ ሽማግሌዎች – ባልታወቀ ታጣቂ ቡድን ተገድለዋል። የመጀመርያው የመንግስት ዘገባ ለግድያው የኦነግ-ሸኔን ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ይህ ግን አዲስ ስታንዳርድ በለቀቀው ቀደምት ዘገባ ተስተባብላል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ህዳር 24, 2014፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ ህዳር 24, 2014)። በኃላም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባደረገው ምርመራ ሽማግሌዎቹ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ከህግ አግባብ ውጪ መገደላቸውን ለማመን ምክንያታዊ የሆኑ ምልክቶች አግኝቷል (ኢሰመኮ፣ ጥር 25, 2014)።
ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 23, 2014 ድረስ ባለው ወቅት የመንግስት ሃይሎች በኦነግ-ሸኔ ቁጥጥር ስር የሆኑ ቦታዎችን ለማስመለስ ባደረጉት ሂደት ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል። ጥር 3 ላይ የሆሮ ጉዱሩ ዞን አስተዳዳሪ በስራቸው ያሉ ሃይሎች 433 የኦነግ-ሸኔ አባላትን ገድለዋል፣ 115 ማርከዋል፣ እንዲሁም ቡድኑን በሎጅስቲክስ ይደግፋሉ የተባሉ 623 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲሉ ገልጸዋል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 3, 2014)።
የትርክት ጦርነት
በግጭቱ ዙሪያ ያለውን ትርክት መቆጣጠር ለኦነግ-ሸኔ ቀጣይነት እንደወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ያህል አስፈላጊ ነው። እንደሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶች ሁሉ የኦነግ-ሸኔ አመራሮችም የኢትዮጵያን በርካታ ግጭቶችና ፈተናዎችን በመጠቀም የመጀመሪያው የኦነግ ፓርቲ ሃሳብ የሆነውን የኦሮሞ ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ ማስተዳደር ለአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሔዎች ናቸው የሚሉትን አላማዎች ማሳካት ይፈልጋሉ። ከዚህ አንፃር የኦነግ-ሸኔ አመራሮች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በተለይም በሃገሪቱ ምዕራብ ክፍል ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ በማግኘት የኦነግን ካባ በተሳካ ሁኔታ ወርሰዋል። የኦነግ እሴቶች በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ በጣም ስር የሰደዱ በመሆናቸው በክልሉ ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም የፖለቲካ ተጽእኖ የኦሮሞን ቋንቋ፣ ባህል፣ እና የመሬት መብት ጥያቄዎችን መመለስ አለበት። የዚህ ትርክት ቁልፍ የኦነግ-ሸኔ ቡድን በኢትዮጵያ ባለፉት መንግስታት ስር የተደረጉ የኦሮሞ ባህል ጭቆና ቅጥያ አድርጎ የሚያስቀምጠው አሁን በኦሮሚያ ውስጥ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚፈጸሙ የመንግስት ጥቃቶች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በየካቲት ወር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ወታደራዊ ስትራቴጂው በራሱ ብቻውን አይሰራም” በማለት ባደረጉት ንግግር ይህንን ሁኔታ ያመኑ ሲሆን በመላ ኦሮሚያ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ከታጣቂ ቡድኑ ጎን በመሰለፍ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችን በቤታቸው እና በእርሻቸው ውስጥ እንዲጠለሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል (ኢቢሲ፣ የካቲት 15, 2014)።
የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች እንቅስቃሴ እየሰፋ ሲድሄድፉ በኦነግ-ሸኔ እና የመንግስት ሃይሎች መካከል ባለው ግጭት እየጨመረ የመጣው ባህሪ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ነው። በልዩ ሃይሎች ከተገደሉት የከራዩ አባ ገዳ የሀገር ሽማግሌዎች በተጨማሪ የመንግስት ታጣቂዎች ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈጽሙት ግድያ ህዝብ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችን ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ አድርጓል። አክሌድ በኦሮሚያ እ.ኤ.አ በ2021 የፀጥታ ሃይሎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የፈጸሙባቸው ከ40 በላይ አጋጣሚዎችን መዝግቧል። እነዚህ ጥቃቶች ከመሰወር እና ያለ ክስ ረጅም ጊዜ በእስራት ላይ ከመቆየት ጋር በመሆን ኦነግ-ሸኔ በሚያቀርበው ትረካ ውስጥ ተካተዋል። የጸጥታ ሃይሎች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መንግስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ በማስረጃነት ለሚያቀርበው ኦነግ-ሸኔ ዋና የመመልመያ ነጥብ ነው (ትዊተር @OdaaTarbiiWBO፣ ታህሳስ 30, 2014)።
ብጥብጥ የመንግስትም ፕሮፓጋንዳ መገለጫ ባህሪ ሲሆን መረጋጋት የጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ባህሪ እና የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በቁጥጥራቸው ስር ላሉ ህዝቦች ካቀረቡት ተቃራኒ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራል። በመንግስት ሚዲያዎች በተለይም የአማርኛ ቋንቋ ዜናዎች የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች ላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ በደል ፈጽመዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል (ኢሳት፣ ጥር 19, 2014)። በግጭቱ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በቡድኑ በደረሰባቸው ጥቃቶች ተገድለዋል እንዲሁም ተፈናቅለዋል። አለመረጋጋት እየጨመረ በመምጣቱ በኦሮሚያ ክልል የተቋቋሙ የአማራ ታጣቂዎች ሊደርስባቸው የነበረውን የማፈናቀል ሙከራ ኦሮሞ ነዋሪዎችን በማጥቃት እና መኖሪያ ቤት በማውደም ተዋግተዋል (ኦቢኤን፣ ታህሳስ 25, 2014)። ኦነግ-ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የወንጀል ድርጊቶች በስፋት ሲስተዋሉ ለመለቀቅ ገንዘብ እንዲሰጡ የሚጠየቁባቸው አፈናዎች፣ ዘረፋዎች፣ እና የበቀል ግድያዎችም ተዘግበዋል። የመንግስት ሚዲያዎች ኦነግ-ሸኔን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች በቡድኑ አባላት እንዲሁም ምንም አይነት የፖለቲካ አጀንዳ በሌላቸው ወንጀለኞች ለወንጀል የሚያጋልጥ የደህንነት ክፍተት በመፍጠር ይከሳሉ።
የፖለቲካ ተለዋዋጭነት፡- የውስጥ ቡድኖች መከፋፈል
ጃዋር መሃመድ፣ በቀለ ገርባ፣ እና ሌሎች የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላት በታህሳስ ወር ማገባደጃ ከእስር መፈታታቸው የግጭቱን ተለዋዋጭነት የመቀየር አቅም አለው (ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ታህሳስ 29, 2014)። በኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ላይ ልዩ ተፅዕኖ ያላቸው በጣም የተከበሩ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን አባላት እንደመሆናቸው መለቀቃቸው በስልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ከእነዚህ ፖለቲከኞች ጋር ስምምነት በመፍጠር የኦነግ-ሸኔን ህዝባዊ ድጋፍ ለመንፈግ እንደፈለጉ ሊያመለክት ይችላል። እነዚህ ስምምነቶች ከትህነግ እና ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚደረገው ብሄራዊ ውይይት ወይም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ልዩ ሁኔታዎችን ሊያካትቱ ይችላሉ። ኦነግ-ሸኔ በ2011 የተገነጠለው የኦነግ ፓርቲ ባለስልጣናት በፌዴራል እስር ቤት ያሉ ሲሆን በእስር ቤት ውስጥ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመቃወም የረሃብ አድማ በማድረግ ላይ ይገኛሉ (አዲስ ስታንዳርድ፣ የካቲት 4, 2014)።
ይህ ምን ያህል እንደሚሳካ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። በ2010 ጃዋር መሃመድ እና ሌሎች አሁን በኦፌኮ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦነግ-ሸኔ አዛዦች በአቢይ አህመድ ስር ላለው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እጃቸውን እንዲሰጡ ማሳመን አልቻሉም ነበር። አሁን ይህን ማድረግ ይችሉ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የበርካታ የኦሮሞ ብሔርተኛ ፓርቲዎች የፖለቲካ አላማ ከኦነግ-ሸኔ ጋር የተቆራኘ ቢሆንም በድርጅቶቹ መካከል ያለው ትስስር ግን የተዳከመ ይመስላል። አዳዲስ ግንኙነቶች ቢፈጠሩ እንኳን ኦነግ-ሸኔ ከትህነግ/ህወሀት ጋር ያለው አጋርነት እንዲሁም ከመንግስት ጋር የፖለቲካ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለው ፍላጎት አስቸጋሪ ነጥቦች ሊሆኑ ይችላሉ።