ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ የካቲት 25, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,643
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,063
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6,958
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከየካቲት 19, 2014 እስከ የካቲት 25, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 9
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 36
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 6
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያውያን በንጉስ ዳግማዊ ሚኒሊክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በጣሊያን ሃይሎች ላይ በ1888 የተጎናጸፈው ድል የሚከበርበትን 126ኛውን የአድዋ ድል አክብረዋል። በአዲስ አበባ የበአሉ ማክበሪያ ቦታ ላይ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በህዝቡ እና የመንግስት ባለስልጣናት መካከል ውጥረት ሰፍኖ ነበር። በዳግማዊ ሚኒሊክ አደባባይ በተከበረው በዓል ላይ አንዳንድ ሰዎች ፀረ-መንግስት መፈክሮችን አሰምተዋል። የካቲት 24 የአድዋ ድል በዓል በተከበረ ማግስት የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፖሊሶች በሀዲያ ዞን ሆሳዕና የሚገኘው ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በመግባት የሚኒሊክን ምስል የያዘ ቲሸርት የለበሱ ተማሪዎችን ደብድበው አቁስለዋል። የጸጥታ ሃይሎቹ ተማሪዎቹን የዳግማዊ ሚኒሊክን ምስል እና አርማ የሌለውን የድሮውን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ከሰዋቸዋል። የድሮውን ባለሶስት ቀለም የኢትዮጵያ ባንዲራ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ግጭት ለመጨረሻ ግዜ የተነሳው በጥር ወር መጀመሪያ በቡራዩ ነበር (ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥር 7, 2014 እስከ ጥር 13, 2014ን ይመልከቱ)።
የካቲት 25 ላይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሁለት በሰው አልባ አይሮፕላኖች የተደረጉ ድብደባዎችን በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ያልታወቀ ኢላማ ላይ በሽሬ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ እና በባህር ነጋሽ ሪዞርት አካባቢ አድርሰዋል። በእነዚህ ጥቃቶች ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። በደቡብ ትግራይ ዞን የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ሃይሎች 160 ወጣቶችን ከአላማጣ አፍነው ወስደዋል። እነዚህ ወጣቶች ከራያ ብሔር እንደሆኑ ይታመናል። እንደ እማኞች ገለጻ ከሆነ ወጣቶቹ በትህነግ ታፍነው የተወሰዱት ለቡድኑ እንዲዋጉ ለማስገደድ ነው (ኢሳት፣ የካቲት 24, 2014)።
የካቲት 23 ላይ ከሶማሊያ የመጡ የማረሃን ጎሳ ታጣቂዎች ከማቃቡል-ኢስማኤል ጉምአድሌ ንዑስ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር በሶማሌ ክልል በሌሄሎው ዩቁብ መንደር አቅራቢያ በመሬት ውዝግብ ምክንያት ተዋግተዋል። ግጭቱ ከሶማሊያ የመጣው ቡድን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተነሳ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱን መክተዋል። በእነዚህ ኩነቶች ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን በመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የካቲት 21 ላይ የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በአኝዋክ ዞን አቦቦ ወረዳ መንደር 11 እና 12 አካባቢዎች 220 ከብቶችን ከወሰዱ ከደቡብ ሱዳን ከመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በእነዚህ ግጭቶች ሁለት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ተገድለዋል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት፣ የካቲት 22, 2014)። በእለቱም በአኙዋክ ዞን ጎግ ወረዳ ኡቡዋ መንደር በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረገ ውጊያ አንድ ታጣቂ እና አንድ የክልሉ የጸጥታ ሃይል አባል መሞታቸው ታውቋል። ሌላ ታጣቂም ቆስሏል። የካቲት 22 ላይ የሙርሌ ታጣቂዎች በኑዌር ዞን ማኩዬ ወረዳ ላንግጆክ ቀበሌ እና በአኙዋክ ዞን ሌላ አንድ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ሰው መግደላቸው ተዘግቧል (ኢትዮጳያን ኢንሳይደር፣ የካቲት 23, 2014)። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከፈረ አዲስ አመት (ከታህሳስ 23) ጀምሮ አክሌድ በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያደረሷቸው ስድስት ጥቃቶችን፣ ሁለት አፈናዎችን እና አንድ ውጊያ መዝግቧል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ባለፈው አመት አክሌድ ቡድኑ የተካፈለበት በየካቲት ወር ውስጥ የተከሰተ አንድ ውጊያ ብቻ መዝግቧል።
በኦሮሚያ ክልል የካቲት 21 ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እንዲሁም ልዩ ፖሊስ ሃይሎች በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ መሊዩ ጨካ ቀበሌ የጋራ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽመዋል። ባለፈው ሳምንት የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች የተሳተፉበት አንድ ብቻ ውጊያ ተመዝግቧል። ይህም ካለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር ቡድኑ የተሳተፈባቸው ኩነቶች ብዛት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። ለምሳሌ ከየካቲት 12 እስከ 18 አክሌድ በኦነግ-ሸኔ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል ስምንት የውጊያ ኩነቶችን መዝግቧል።
በመጨረሻም የካቲት 23 ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በዳንጉር እና ጉባ ወረዳዎች መካከል ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝዎችን ሲያጓጓዝ የነበረ መኪና ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርሰው የደህንነት ሃይሎችን ጨምሮ ከ20 በላይ ሰዎችን ገድለዋል። ጥቃቱ ሲደርስ አውቶብሱ በጸጥታ ሃይሎች ታጅቦ ነበር።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የዩክሬን ግጭት በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ
ሩሲያ የካቲት 17 ላይ በዩክሬን ያደረገችው ወረራ እና ከዚያ በኋላ በሩሲያ ኃይሎች እና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት በዓለም ዙሪያ የዜና ማሰራጫዎችን ትኩረት ስቧል። አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን ይህም የሩብል የመግዛት አቅም እንዲቀንስ እና የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። ዩክሬን እና ሩሲያ ሁለቱም ዋና የጥራጥሬ አምራቾች በመሆናቸው ግጭቱ በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። ኢትዮጵያ ከግጭቱ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እሩቅ ብትሆንም እንደ ነዳጅ፣ ስንዴ፣ እና ማዳበሪያ ያሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባ በመሆኑ በዩክሬን እና ሩሲያ የሚፈጠሩ ክስተቶች በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ማለት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በትህነግ ላይ በሚደረገው ጦርነት አጋር የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል። እነዚህ አዝማሚያዎች በኢትዮጵያ ባሉ ግጭቶች ላይ ምን አይነት ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በዚህ ሳምንት ዘገባ ውስጥ ተዳሷል።
ሃምሌ 2013 ላይ ኢትዮጵያ “[የኢትዮጵያ] መከላከያ ሰራዊትን በእውቀት፣ በክህሎት፣ እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ አቅምን ለመለወጥ” በሚል ዓላማ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች (አናዶሉ ኤጀንሲ፣ ሃምሌ 5, 2013)። ስምምነቱ የተደረሰው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በትግራይ ክልል ከነበራቸው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር ከተነሱ ክሶች ጋር ተያይዞ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት እና ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት በከፋበት ወቅት ነበር። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሩስያ ቪቶ በኤርትራ ወይም በኢትዮጵያ ላይ ሊወሰድ የታሰበውን እርምጃ ያለማቋረጥ አጨናግፏል (ዘ ኢኮኖሚስት፣ የካቲት 29, 2014)። ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ ጥቃቷን እንድታቆም እና ሁሉንም ወታደሮቿን በአስቸኳይ እንድታስወጣ የውሳኔ ሃሳብ በቀረበበት ወቅት ኢትዮጵያ በስብሰባው ያልተሳተፈች ሲሆን ኤርትራ ደግሞ ውሳኔውን ከተቃወሙ አምስት ሀገራት አንዷ ነበረች (አልጀዚራ፣ የካቲት 24, 2014)።
በአገር አቀፍ ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጠንካራ ደጋፊዎች ሩሲያ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት ላይ ካላት ኢ-ጣልቃ ገብነት አንፃር ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አድንቀዋል (አፍሪካኒውስ፣ ግንቦት 23, 2014)። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከሩሲያ ጋር ቢቀራረቡም የሩስያ ጦር በዩክሬን እየወሰደ ያለው እርምጃ ለሁለቱም ሀገራት በርካታ አስከፊ ጉዳቶች አሉት። ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አጀንዳዎችን በተሳካ ሁኔታ ብታከናውን እንኳን በምግብ እና በግብርና ምርቶች ገበያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤ ይህም የኢትዮጵያ መንግስት የግብርና ግብዓቶችን እና የምግብ ድጎማዎችን ማስቀጠል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።
ዩክሬን በዓለም ላይ አምስተኛው የስንዴ ላኪ ነው። ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የሚመረተውን የስንዴና ሌሎች የእህል ዓይነቶችን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም አሁንም በአብዛኛው በመንግስት በኩል እንዲገቡ ተደርገው በከተማ አካባቢ በተደጎመ ሂሳብ በሚሸጥ ወደሃገር የሚገቡ እህሎች አስመጪ ነች። ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ የሚገባው ከዩክሬን እና ሩሲያ ነው (ተመድ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ የካቲት 8, 2011)።
ማዳበሪያ ለእህል ምርት ወሳኝ ግብአት ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ የአቅርቦት መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ ሊወደድ ይችላል። ሩሲያ የማዳበሪያ ዋነኛ አምራች ስትሆን የአሜሪካን ማዕቀብ መጣል ተከትሎ ሀገሪቱ ወደ ውጭ መላክ ልታቆም ትችላለች። የኢትዮጵያ መንግስት በየአመቱ በሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚቆጠር ማዳበሪያ አስመጥቶ ለገበሬዎች ያከፋፍላል (ኒውስ ቢዝነስ ኢትዮጵያ፣ ሚያዚያ 22, 2014)። በአገር ውስጥ ማዳበሪያ የሚያከፋፍሉት የግብርና ኤክስቴንሽን ጽሕፈት ቤቶች በገጠር አካባቢዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ ተወካዮች ናቸው። ለሰብል ግብአት የሚሆን ማዳበሪያ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የአካባቢውን የግብርና ኤክስቴንሽን መሥሪያ ቤቶች የአከባቢን ፍላጎት ለማሟላት ያላቸውን አቅም ሊገድብ ይችላል በዚህም ምክንያት ለመንግሥት ፖለቲካዊ ድጋፍ ማመቻቸትን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል (ፊዩቸር አግሪካልቸርስ፣ ግንቦት 2004)።
በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በደረቅ እና ለም የግብርና የአየር ንብረት ውስጥ የሚከሰት ሲሆን የእህል ዋጋ ንረት በተለያየ መንገድ የግጭት አዝማሚያዎች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ስንዴ በሚመረትባቸው የኦሮሚያ ገጠራማ አካባቢዎች የእህል ዋጋ መናር እንደ ኦነግ-ሸኔ ያሉ ታጣቂዎች ከአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ገቢ እንዲሰበስቡ ምቹ እድል ይፈጥራል። በተጨማሪም የተገደበ የማዳበሪያ አቅርቦት የመንግስትን የህዝብ አስተያየት ላይ ተጽእኖ የማሳረፍ አቅም ሊቀንስ ይችላል። በደቡብ ኦሮሚያ በድርቅ ሳቢያ ዘላኖች ባልተሰበሰበ ምርት እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ የእህል ዋጋ መናር መንግሥት በገጠር ውስጥ ላሉት ቡድኖች ውድ የሆነውን ሸቀጥ (ስንዴ) በማቅረብ ታጣቂዎችን ከሕዝብ የሚለይበት ዕድል ሊፈጥር ይችላል። የስንዴ ሽያጭ ድጎማን በሀገሪቱ የከተማ አካባቢዎች ማድረግ ለመንግስት ካለፉት አመታት የበለጠ ዋጋ ያስከፍለዋል። በትግራይ ለተፈናቀሉ ግለሰቦች የምግብ እህል ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትም እንዲሁ ውድ ሊሆን ይችላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የእህል ምርት ብዙ ጊዜ ከፍተኛ የፖለቲካ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የውጭ ወይም የሀገር ውስጥ የኢንቨስትመንት እርሻዎችን (ከተናጥል ኦፕሬሽን ጋር ሲነጻጸር) የሚካሄድ ነው። የእህል ዋጋ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል ባለው ጦርነት ምክንያት መጨመሩ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ምርታማነት ያለው መሬት ዋጋን ከፍ ሊያደርግ ይችላል። በትግራይ ክልል ደቡብ ትግራይ እና ምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ በአንፃራዊነት ምርታማ መሬት ያላቸው እና በእህል ዋጋ መናር ምክንያት ግጭት ሊፈጠርባቸው እንደሚችል በምሳሌነት የሚቀርቡ ናቸው። የኢፒኦ ግጭት ገጽ በእነዚህ የግጭት አካባቢዎች ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ይሰጣል።
በኢትዮጵያ መንግስት የነዳጅ ድጎማ ያደርጋል። ነገር ግን ታህሳስ አጋማሽ ላይ መንግሥት የነዳጅ ዋጋን ለማስተካከል ፍላጎት እንዳለው ገልጾ ነበር (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ታህሳስ 20, 2014)። የነዳጁ ዋጋ ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ ለማመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅርቡ “ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ነዳጅ አቅራቢ ነች” ሲሉ ገልጸው በኢትዮጵያ ያለው ዋጋ ከጎረቤት አገሮች ያነሰ በመሆኑ የኢትዮጵያ ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገሮች በድብቅ ይገባል ብለዋል (ኢትዮጵያን ኢንሳይደር፣ የካቲት 15, 2014፤፤ ኤፍቢሲ፣ ጥር 6, 2014)። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ወራት መንግሥት የነዳጅ ዋጋ አልጨመረም (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የካቲት 18, 2014፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 26, 2014፤ ኤፍቢሲ፣ ታህሳስ 28, 2014)። አሁን የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ብዙ ነዋሪዎች መንግስት የነዳጅ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ሊያደርግበት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ከተከሰተ መሰረታዊ ምግብን ጨምሮ የሌሎች ምርቶች ዋጋ ይጨምራል። ላለፉት ወራት በዋና ከተማዋ ነዳጅ ለመሙላት ረጃጅም ሰልፎች የነበሩ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከአቅርቦት መቀነስ ጋር ተያይዞ ነዳጅ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር (ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 4, 2014፤ ኤፍቢሲ፣ ጥር 23, 2014)። ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ካሉ 123 ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ በ58 ከመቶው ብቻ ነበር ነዳጅ ለማከፋፋል የነበረው (ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 9, 2014)። መንግሥት አንዳንድ የነዳጅ ኩባንያዎችን “ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት” በመፍጠር ተጠያቂ አድርጓል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 25, 2014፤ ፋና ቴሌቪዥን፣ የካቲት 9, 2014)።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በወሰደችው እርምጃ ምክንያት የሚከተለው ኢኮኖሚያዊ መዘዝ በኢትዮጵያ ያለው የማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ እና ጥራጥሬ ዋጋ ላይ መንጸባረቅ ሲጀምር በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመንግስት ሰዎች ከፍተኛ የግጭት ጫና እና አነስተኛ የመቋቋሚያ ዘዴዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ።