ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 2, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,673
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,150
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,001
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከየካቲት 26, 2014 እስከ መጋቢት 2, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 20
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 21
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –15
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ሃይሎች እና የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እንዲሁም ታጣቂዎች በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በኮነባ፣ አባላ፣ መጋሌ፣ ኢሬብቲ፣ እና ዳሎል አካባቢዎች መዋጋታቸውን ቀጥለዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ፣ ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ዛሪማ ወረዳ ትህነግ/ህወሃት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ አማራ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ ፋኖ ታጣቂዎች፣ እና የአማራ ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። የካቲት 28 ላይ በባድመ አካባቢ ባለ አወዛጋቢ ድንበር አካባቢ የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ከኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ጋር ተጋጭተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በ1994 የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ድንበር ኮሚሽን ባድመን ለኤርትራ ያደረገውን ውሳኔ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ሰኔ 2010 ላይ ወስኗል (ዘ ዋሺንግተን ፖስት፣ ግንቦት 28, 2010)። ካለፈው አመት ጀምሮ ትህነግ/ህወሀት ከትግራይ ያልሆኑ ሃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል። ግጭቱ ከተጀመረበት ጥቅምት 2013 ጀምሮ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ሃይሎች እና ተባባሪ ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ጋር በመሆን በትግራይ ክልል ይገኛሉ።
ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከማዕከላዊ ትግራይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ መድረስ መጀመራቸው ተነግሯል። የትህነግ/ህወሓት ተወካይ ይህንን አስተባብለው የትኛውም የትግራይ ተወላጆች በሌሎች ክልሎችና አጎራባች አገሮች አልተጠለለም ብለዋል። የቆቦ ከተማ ከንቲባ ከተማዋ ከደቡብ ትግራይ ዞን ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ እና አላማጣ አካባቢ የተፈናቀሉ ከ50,000 በላይ አማራዎችን በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ቀደም ሲል አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃችዮች እዚያው በትግራይ ክልል ተጠልለው ይኖሩ ነበር። በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሉ የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ መቀሌ በአየር የሚጓጓዘው ብቻ ነው። በአባላ ከተማ በሰመራ-አባላ መንገድ እና በደቡብ ትግራይ ላይ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው ግጭት ዕርዳታ በጭነት መኪናዎች ማድረስ የማይቻል ያደረገ ሲሆን የመጨረሻው የሰብአዊ እርዳታ በመኪና የገባው ታህሳስ 6, 2014 ላይ ነበር (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 26, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ ጥር 16, 2014)። የሰብዓዊ እርዳታ የሚያደርሱ መኪኖች በሰመራ-አባላ ዋና መንገድ ተጉዘው ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቁሳቁሶቻቸውን ያደርሱ ነበር።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት ለፋኖ አባላት ስልጠና መስጠት አላቆምም ያለ አንድ የፋኖ አመራር መታሰሩን ተከትሎ በፋኖ ታጣቂዎች እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች መካከል በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ፣ ጁቤ፣ ቢውኝ፣ እና ግንደ ወይን ውጊያ ተደርጓል (ዋዜማ ራዲዮ፣ የካቲት 28, 2014)። በሞጣ በተፈጠረው ግጭት አራት የክልሉ ፖሊስ አባላት ሲገደሉ ስድስት ደግሞ ቆስለዋል ። የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ የጸጥታ ሃይሎች የፋኖ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትተዋል እየተባለ የሚወራውን ወሬ አስተባብለው በሞጣ እና አካባቢው የተከሰተውን ውጊያ ለማጣራት ቃል ገብተዋል (የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 1, 2014)። በጥር ወር መጨረሻ መንግስት መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎችን ወደ እውቅና ያለው የጸጥታ አደረጃጀት ለማስገባት ፍላጎት እንዳለው አሳይቷል (ፋና ቴሌቪዥን፣ ጥር 20, 2014)። በአማራ ክልል የሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎችን ጨምሮ መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎች በክልሉ ትህነግን ለመታገል ታጥቀው ስልጠና ወስደዋል።
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቡድኖች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚያደርሷቸው ጥቃቶች ቀጥለዋል። አክሌድ ባለፈው ሳምንት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የደረሱ ስምንት ጥቃቶችን መዝግቧል። ከእነዚህ ጥቃቶች መካከል ሁለቱ የተፈጸሙት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ነው። ሌሎች ሶስት ጥቃቶች በአማራ ታጣቂዎች ተፈጽመዋል። የካቲት 29 ላይ ኦነግ-ሸኔ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ ኦበራ ክራሮ ቀበሌ ላይ ጥቃት በማድረስ ሰባት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድሏል ተብሏል። ጥቃቱ በማግስቱ በኢጃጂ ከተማና አካባቢው ቀጥሎ ውሏል። በሌላ የኦሮሚያ አካባቢ ከየካቲት 26 እስከ 28 ድረስ የአማራ እና ፋኖ ታጣቂዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ኮራን ጎጎ እና ቆርኮራ ሙሊ መንደር ውስጥ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የከረዩ አርብቶ አደሮችን ተኩሰው ገድለዋል። በተጨማሪም መጋቢት 1 ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያለውን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆነ ግለሰብ በቀኚ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜቲ አንድ ፖሊስ እና ሹፌሩን ገድሏል። ከዚህ ቀደም ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት ያለው አባ ቶርቤ በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ባለስልጣናትን ገድሏል። ባለፈው ሳምንት የተፈፀመው ግድያ በዚህ ቡድን ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም።
በጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸሙ ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ቀጥለዋል። የካቲት 30 ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡነ ግንደበረት ወረዳ ቃላቴ በተባለ ቦታ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ አባትና ልጅን ተኩሶ ገድሏል። ሟቾቹ የኦነግ-ሸኔ ቡድን አባል የሆነ አንድ የቤተሰባቸውን አባል ደብቀዋል በሚል ክስ ታስረው ነበር። በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ሰራዊት-በተቃዋሚ ታጣቂ ቡድን በኑዌር ዞን ላሬ እና ጂካዎ ወረዳዎች በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በጥቃቱ አንድ ሰው ሲሞት፣ ስድስት ቆስለዋል፣ እንዲሁም ደቡብ ሱዳናዊያንን ጨምሮ ከ9,500 በላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ተፈናቅለዋል። በተጨማሪም ቡድኑ ከእነዚህ አካባቢዎች ንብረቶችን እና የኢትዮጵያ እና የክልል ባንዲራዎችን ዘርፏል። የክልሉ መንግስት እንደገለጸው ይህ ጥቃት የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ሰራዊት-በተቃዋሚ ሃይሎች ከደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ሃይሎች ጋር በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢዎች ከተዋጉ በኋላ መፈጸሙን ገልጿል (የጋምቤላ ክልል መንግስት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ፣ መጋቢት 4, 2014)።
በመጨረሻም የካቲት 26 ላይ በአዲስ አበባ የካራማራን የድል በዓል ለማክበር ሲያቀኑ የነበሩ 35 የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላትን ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል በሚል ክስ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል። በእለቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የኦሮሞ ተማሪዎች በስድስት ኪሎ ካምፓስ በመሰባሰብ በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የጥላቻ እና የማንቋሸሽ ቃላትን የያዙ በግቢው ውስጥ የተበተኑ በራሪ ወረቀቶችን በመቃወም ሰልፍ አድርገዋል (ኦኤምኤን፣ የካቲት 26, 2014)። በሳምንቱ መገባደጃ መጋቢት 2 ላይ የዩንቨርስቲ ዲግሪ ያላቸው ማየት የተሳናቸው የኦሮሞ ተወላጅ ወጣቶች በአዲስ አበባ ስታዲየም ፊት ለፊት ተሰባስበው የኦሮሚያ ክልል መንግስት አለው የተባለውን አድሎአዊ የቅጥር ፖሊሲ እያወገዙ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አቅንተዋል ። የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ሰልፈኞቹን በትኗል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በመተከል ዞን የተፈጠረው ግጭት የኢትዮጵያ አዲስ የውክልና ጦርነት ሆኗል ወይ?
በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል በትህነግ/ህወሃት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል ያለው ግጭት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተቀዛቅዟል። ትህነግ/ ህወሃት አሁንም ለአፋርና አማራ ክልል መንግስታት ታማኝ ከሆኑ ሃይሎች ጋር ከፍተኛ ውጊያ እያካሄደ ቢሆንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚሳተፍባቸው ኩነቶች ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሰዋል።
ይህ የውጊያው መቀዛቀዝ የተከሰተው በድርድር ወሬዎች፣ በሁለቱም ወገኖች በግጭቱ በተዳከሙ ተዋጊዎች፣ እንዲሁም የግዛት ገደቦች በተፈጠረበት ወቅት ነው። በሰሜናዊው የውጊያ መስመሮች አንጻራዊ ጸጥታ የሰፈነ ቢሆንም በሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለው ሁከት ግን ቀጥሏል። ይህም ጥልቅ የሆኑ የጸጥታ ችግሮችን ያሳያል።
በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተው ግጭት መቀነሱን ተከትሎ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል። የካቲት 23 ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በመተከል ዞን በዳንጉር እና ጉባ ወረዳ መካከል በሚገኘው የአፍሪካ ግብርና ልማት አካባቢ ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝዎችን ሲያጓጉዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ባደረሰው ጥቃት አንድ ከፍተኛ አዛዥን ጨምሮ 20 የኢትዮጵያ ወታደሮችን እና ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። የፌደራል ወታደሮች ከአማራ እና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተወጣጡ ሃይሎች ጋር በመሆን በነጋታው በሰጡት ምላሽ 30 የደፈጣ ጥቃቱን ፈጻሚዎች ገድለዋል። ድርጊቱ በተፈጸመበት አቅራቢያ የጉሙዝ እና ትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ሌሎች አስራ አንድ ሰዎች ስለፀጥታ እንቅስቃሴ መረጃ ሰጥተዋል በሚል ክስ ተይዘው በጸጥታ ሃይሎች ተገድለዋል። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በህይወት እያለ ሲቃጠል ተመዝግቧል ይህም በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተግባር ላይ ቅሬታ አስነስቷል (ኢሰመኮ፣ መገቢት 4, 2014)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መፍትሄዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሃብት ቢውልም አሁንም ቢሆን ፌደራል መንግስቱ ሰላም ማስፈን አልቻለም። በብዙ መልኩ በዚህ አካባቢ ያለው ግጭት በመላ ኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የፖለቲካ ግጭት ያሳያል። በታሪካዊ የመሬት ጉዳዮች እና በአስተዳደር ድንበሮች ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት እየተባባሱ የመጡ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ዘመን ወደፊት በወጡ ሰፊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክንያትየአካባቢ ግጭቶች ተባብሰዋል።
እነዚህ አዝማሚያዎች በመተከል ዞን እርስ በእርስ የተጣመሩ ሲሆን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ውስብስብ እና ከባድ ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች አንዱን የፈጠሩ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ1,300 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። የግጭቱ መነሻ በመተከል ዞን ለም መሬት ላይ የሚደረጉ የይገባኛል ጥያቄዎች ናቸው። የአገሬው ተወላጆች ‘ሰፋሪዎች’ – ኦሮሞ እና አማራ – መሬታችንን በግዳጅ ወስደዋል ሲሉ የሚወነጅሉ ሲሆን ገበሬዎችን በማጥቃት እና ቤቶችን በማውደም ምላሽ ሰጥተዋል። ከነሃሴ 26, 2012 እስከ መስከረም 20, 2013 ባለው ወቅት የተቋቋመው በመከላከያ የሚመራው የፌደራል ኮማንድ ፖስት ደህንነት በፌደራል መንግስቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በይፋ አሳይቷል (አዋሽ ፖስት፣ ነሃሴ 18, 2013)። ይህም ሆኖ ግን ግጭት ቀጥሏል።
ጉዳዩ ከመሬት ውዝግብ የዘለለ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው ያሉ ግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ቡድኖች ከሰፊው ማህበረሰብ ጋር ባላቸው የዘር ትስስር ምክንያት ክልሉ ውስጥ የውክልና ግጭት እንዲካሄድበት አድርጓል። ልክ በትግራይ ክልል እንደሚገኙት ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ዞኖች ሁሉ መተከል ውስጥ በታሪክ የአማራ ነው የሚባል ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት ያለ ሲሆን መተከል በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ውስጥ እንደ ዞን መያዙ ትህነግ/ህወሓት የአማራ ክልል ያለው ሃብት ውስን እንዲሆን ላለው ፍላጎት እንደ ማስረጃ አድርገው ይቆጥሩታል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መስከረም 23, 2013)። ይህም የመተከል ዞንን እንደ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ባሉ የአማራ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ድርጅቶች ፖለቲካዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ያደርገዋል። በመተከል ዞን የሚገኙ የአማራ ታጣቂዎች ብዙ ጊዜ ከአካባቢው የአማራ ብሄር ተወላጆች ጋር አንዳንዴ ደግሞ ከፋኖ ወጣት ታጣቂዎች ጋር በጥምረት ይሰራሉ። በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት በርካታ ፀረ-መንግስት ታጣቂዎች መካከል ቢያንስ አንዱ የሆነው የጉሙዝ ነፃነት ግንባር ከኦነግ-ሸኔ እና ከትህነግ/ህወሀት ጋር በግልፅ ተሰልፏል።
ከእነዚህ አዝማሚያዎች በተጨማሪ ክልሉ በ4.2 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ውድ ከሚባሉት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው እና ባለፈው ወር ኤሌክትሪክ ማምረት የጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ ነው (ፍራንስ24፣ የካቲት 12, 2014)። የካቲት 23 ላይ በአውቶብስ ላይ በደረሰው ጥቃት የተገደሉት ወታደሮች ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚሄዱ ጎብኝዎችን የሚያጓጉዝ መኪና ሲያጅቡ እንደነበር ተዘግቧል። መተከል ዞን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ካላት ረጅም ድንበር የተወሰነውን ያካትታል።
ከነሃሴ 26, 2012 እስከ መስከረም 20, 2013 ጀምሮ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ከአማራ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ እና ሲዳማ ክልሎች የተወጣጡ ልዩ ሃይሎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሚመራው ኮማንድ ፖስት ጋር በክልሉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እያከናወኑ መሆኑን አምነዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መስከረም 5, 2013)። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዘገባ እንደሚያሳየው የቡድኖቹ በቦታው አሁንም መገኘት ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በመተከል ዞን ባለው ግጭት ውጤት ላይ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል (ኢሰመኮ፣ መጋቢት 4, 2014)።
በመተከል ያለው ግጭት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰፊ ብሄራዊ ግጭት አካል ሲሆን አካባቢያዊ እና ክልላዊ እንዲሁም አለማቀፋዊ ውዝግቦችን የሚያንፀባርቅ ነው። እነዚህ ሰፊ ጉዳዮች እልባት እስኪያገኙ ድረስ መተከል የውክልና ግጭቶች መገኛ ሆና ትቀጥላለች፤ ብጥብጡም ይቀጥላል።