በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 9, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,695
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,247
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,048
በቁጥር (ከየካቲት 26, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 9
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 46
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –10
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መዋጋታቸውን ቀጥለዋል። በእነዚህ ወገኖች መካከል መካሄዳቸው የተመዘገቡ ሁሉም ውጊያዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ነበሩ (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከመጋቢት 3 እስከ 6 በምዕራብ ሸዋ ዞን ከጊንጪ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙት ጊብሲ ሾኔ እና ዴቤቲ ሾኔ ቦኒ አካባቢዎች ኦነግ-ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል። በተመሳሳይ ከመጋቢት 1 እስከ 3 በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ ዙሪያ ወረዳ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች፣ እና ከአካባቢው ታጣቂዎች ጋር ተዋግቶ 20 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ አብዛኛዎቹ ውጊያዎች በምዕራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ እና ጉጂ ዞኖች ይከሰቱ ነበር። ሆኖም አክሌድ ከመስከረም 21 እስከ መጋቢት 9, 2014 ድረስ በምዕራብ ሸዋ ዞን በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተካሄዱ 30 ውጊያዎችን መዝግቧል። ከታህሳስ 23, 2010 እስከ መስከረም 20, 2014 ድረስ ግን አክሌድ በምዕራብ ሸዋ ዞን በኦነግ-ሼኔ እና የክልል ሃይሎች መካከል የመዘገበው ሁለት ውጊያዎች ብቻ ነበር።
በተጨማሪም መጋቢት 8 ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን መተሐራ ከተማ አልጌ ቀበሌ ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በትንሹ 10 ሰዎች ገድለው ከ20 በላይ አቁስለዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 9, 2014፤ ኢሳት፣ መጋቢት 9, 2014)። አንዳንድ እማኞች ይህ ጥቃት የተፈጸመው በኦነግ-ሸኔ ሆኖ ኦሮሞ ያልሆኑ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ ነው ብለው ያምናሉ (ኢሳት፣ መጋቢት 9, 2014)። የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች ጥቃቱ ብሄርን መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት አጥብቀው ተናግረዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 9, 2014)። መተሐራ ስኳር ፋብሪካ በዚህ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በፀረ-መንግሥት ኃይሎች ኢላማ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የካቲት 2014 ላይ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ኦነግ-ሸኔ በሚያደርሰው ጥቃት ምክንያት ማምረት እንዲያቆም ተደርጎ ነበር (ብሉምበርግ፣ የካቲት 7, 2014)። በተመሳሳይ መጋቢት 8 ላይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ እንዶዴ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ አባላት አንድ ቄስን ጨምሮ ስምንት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል (ኢሳት፣ መጋቢት 10, 2014)።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ የጉሙዝ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይሎች እና ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በውጊያው ሰላሳ የታጣቂው ቡድን አባላት ሲገደሉ ሌሎች 15 ቆስለዋል ተብሏል። ሃያ ሰባት የቡድኑ አባላትና በርካታ የጦር መሳሪያዎችም ተማርከዋል። በተጨማሪም መጋቢት 7 ላይ በመተከል ዞን ዲባቴ ወረዳ ቢሻን አዲ አካባቢ የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በማስቆም 18 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ የኦሮሞ ተወላጆችን አፍነው ወስደዋል። በማግስቱ የዲባቴ ወረዳ ነዋሪዎች በመተከል ዞን ባርባራ በመሰባሰብ “በአማራ ሃይሎች እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል” በመቃወም የአማራ ልዩ ፖሊስ እና የፋኖ ታጣቂዎች ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል እንዲወጡ በሰላማዊ መንገድ ጠይቀዋል (ኦኤምን፣ መጋቢት 8, 2014)።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የፓርቲው ዘጠኝ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከሌሎች 300 ሰዎች ጋር ከግልገል በለስ እስር ቤት ተፈተዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 10, 2014፤ ቪኦኤ አማርኛ፣ መጋቢት 12, 2014)። የመፈታቱ ዜና የመጣው በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማለም የካማሺ ዞን አስተዳደር አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች ለውይይት ከተቀመጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነው። እየቀጠለ ላለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሆን በዞኑ ያሉ ታጣቂ ሃይሎች ሌሎች ጥያቄዎችን ጨምሮ ከቡድናቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እንዲፈቱ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበው ነበር። መጋቢት 10 ላይ የክልሉ መንግስት እና የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የፖለቲካ እና የትጥቅ ክንፍ አመራሮች በካማሺ ከተማ ባህላዊ የሰላም እና የዕርቅ ሥነ-ሥርዓት አድርገዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ መጋቢት 12, 2014)። ሁለቱ ወገኖች በመተከል ዞን ተመሳሳይ ሥነ-ሥርዓት ለማካሄድ አቅደዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ በርካታ ሰልፎች ተካሂደዋል። መጋቢት 4 ላይ በመዲናይቱ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በሰልፈኞች መካከል በተነሳ ሁከት በርካታ ተማሪዎች ቆስለዋል። “በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያለውን ጥላቻ” የሚያንፀባርቃሉ የተባሉ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውን ተከትሎ ከአንድ ሳምንት ውጥረት በኋላ ግጭት ተቀስቅሷል። በግጭቱ በርካታ ተማሪዎች ቆስለዋል ተብሏል። የፌደራል ፖሊስ ሃይሎች ጣልቃ በመግባት ሁከት ፈጣሪዎችን በመበተን በርካቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል። በራሪ ወረቀቱ ላይ ያለው ቅሬታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለፀው የካቲት 26 ላይ የኦሮሞ ተማሪዎች “ፀረ-ኦሮሞ በራሪ ወረቀቶች” መሰራጨቱን ለመቃወም በተሰበሰቡበት ወቅት ነው።
መጋቢት 8 ላይ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአውሲ ረሱ-ዞን 1 ሰመራ ከተማ የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) በአፋር ክልል ያደረገውን ወረራ እና የፌደራል መንግስት ምላሽ አለመስጠቱን አውግዘው ሰልፍ አድርገዋል። የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና የከተማው ፖሊስ ሰልፈኞቹን በሃይል የበተኑ ሲሆን በዚህም 20 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን አምስት ተማሪዎች ደግሞ ታስረዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 9, 2014)።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሳምንት 23 የሰብአዊ እርዳታ የያዙ መኪኖች ወደ ትግራይ ክልል በማቅናት ላይ መሆናቸውን አስታውቆ በቀን ለሰብአዊ እርዳታ የሚጏዙትን የጭነት መኪኖች ቁጥር ወደ 40 ለማሳደግ ቃል ገብቷል (የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መጋቢት 8, 2014)። መጋቢት 14 ላይ መንግስት የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች በተሽከርካሪዎቹ ላይ “በአባላ እና መቀሌ ኮሪደር” አካባቢ ተኩስ በመክፈቱ መኪኖቹ ሰብአዊ እርዳታውን ለማድረስ እንዳልቻሉ ገልጿል (ኢሳት፣ መጋቢት 14, 2014)። በአፋር ክልል በአባላ ከተማ በሰመራ-አባላ መንገድ ላይ ያገረሸው ግጭት እርዳታ በጭነት መኪና ለማድረስ አዳጋች ያደረገ በመሆኑ ከታህሳስ 6 ጀምሮ ምንም አይነት እርዳታ በመኪና ወደ ክልሉ አልገባም (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 26, 2014)። የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በሰመራ-አባላ ዋና መንገድ ተጉዘው ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን ያደርሱ ነበር። መንግስት “የምግብ እቃዎችን የጫኑ 43 መኪኖች በአፋር ክልል ርዕሰ መዲና ሰመራ 38 ኪሎ ሜትር እርቃ በምትገኘው ሰርዶ ማለፍ አቅቷቸው እንደቆሙ” ገልጿል (የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መጋቢት 8, 2014)። ከሁለት ሳምንታት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከማዕከላዊ ትግራይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ መድረስ መጀመራቸው ተነግሯል። ባለፈው ሳምንትም ይህ የቀጥለ ሲሆን ተጨማሪ የትግራይ ተወላጅች ተፈናቃዮች ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን ቀጥለዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ መጋቢት 9, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በጋምቤላ ስላለው ግጭት ወቅታዊ መረጃ
ለአንድ አመት ያህል ከተረጋጋ በኋላ የሙርሌ ጎሳዎች በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ድንበር በኩል ወደ ጋምቤላ ክልል ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግጭት ተበራክቷል፣ ይህም ሞት የሚያስከትሉ ውጊያዎችን እና መፈናቀል ፈጥሯል። እነዚህ ጥቃቶች አብዛኛውን ጊዜ ርቀው በሚገኙ ቦታዎች (የገጠር ቀበሌዎች) – ከብት ሊዘረፍባቸው የሚችሉ ‘ቀላል’ ኢላማዎች – ላይ ያነጣጠሩ ቢሆኑም እነዚህ ጥቃቶች ከባድ እየሆኑ በመምጣታቸው ምክንያት የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት ከታህሳስ 23 ጀምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ከደቡብ ሱዳን የመጡ የታጠቁ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሊሞክሩ ሲሉ ከጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግተዋል (የጋምቤላ ክልል መንግስት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ፣ መጋቢት 6, 2014)። ከታህሳስ 23 ወዲህ አክሌድ በአጠቃላይ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ የደረሱ ሰባት ጥቃቶችን እና ሁለት ጠለፋዎችን መዝግቧል።
የሙርሌ ታጣቂዎች የሚሳተፉበት ድንበር ዘለል ጥቃት ባለፉት ዓመታት አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን የከብት ዘረፋ እና በኢትዮጵያ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫዎች ያሉ ቡድኖች በሚያደርጉት ግዛት ዘልቆ ለመግባት የሚደረግ ጥረት ምክንያት ተባብሷል። ከሁሉም ከባዱ ኩነት በ2008 በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የሙርሌ ታጣቂዎች 208 ሰዎችን ገድለው 145 ህጻናትን ያገቱበት ክስተት ነው። ይህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል (አልጀዚራ፣ ሚያዚያ 10, 2008፤ ሱዳን ትሪቡን፣ ሚያዚያ 10, 2008)። ምንም እንኳን ወታደራዊ ምላሹ የተወሰነ ውጤት ያለው ቢመስልም ከ2008ቱ ክስተት በኋላ ቢያንስ 14 ሌሎች ሞት የተከሰተባቸው ጥቃቶች ተከስተዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ የተመዘገቡ ናቸው። በቅርቡ በተፈጠረ አንድ ክስተት ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ታጣቂዎች በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ አምቡላንስ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ስምንት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። የካቲት 29 ላይ ከኢትዮጵያ የመጡ የአኙዋክ/ኑዌር ተወላጆች በደቡብ ሱዳን ቦማ ፓያም በሚገኘው የሙርሌ የከብት ካምፖች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቤቶችን አቃጥለው በርካታ ሰዎችን ገድለዋል። የድንበሩ አካባቢ አጠቃላይ ሩቅ በመሆኑ በአገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ምንጮች ያልተዘገቡ ሌሎች በርካታ ወረራዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
በጋምቤላ ድንበር ያለው ግጭት በደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ያለውን ጥልቅ የጸጥታ ጉዳዮችን ያሳያል። በደቡብ ሱዳን የሙርሌ እና ሌሎች ተቀናቃኝ ቡድኖች ተሳታፊ የሆኑበት መደበኛ ያልሆነ የግጭት ሁኔታዎች ከኢትዮጵያው ጋምቤላ ክልል ጋር የሚዋሰነው የጆንግሌ ግዛት ከደቡብ ሱዳን 10 ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ያለበት ክልል እንዲሆን አድርጎታል። ግጭቱ ተለዋዋጭ የሆነውን አገራዊ ፖለቲካ እና የጆንግሌ ግዛት ከፀረ-መንግስት አመጽ ጋር ያለውን ግንኙነት ያንፀባርቃል (በጆንግሌይ ግዛት ውስጥ ስላለው የግጭት ተለዋዋጭነት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የአክሌድን ከሃምሌ 25 እስከ ነሃሴ 25, 2013 ዘገባ ይመልከቱ)። በአንፃሩ ለረጅም አመታት ሁከት ሰፍኖበት የነበረው በኢትዮጵያ የሚገኘው የጋምቤላ ክልል ባለፈው አመት በሀገሪቱ ከፍተኛ ሰላም ከነበረባቸው አካባቢዎች አንዱ ሆኖ ቆይቷል (ከዚህ በታች ያለውን ምስል ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ያለው የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት የፌደራል መንግስትን የጸጥታ ሃብት እና ለድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ምላሽ የመስጠት አቅም ቀንሶታል። ልክ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች በፌዴራል መንግስት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚደረገው ጥረት በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ አባላትን በመመልመል ላይ ይገኛሉ (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ጥር 12, 2014)። የካቲት 8 ላይ የጋምቤላ ክልል ተወካይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረጉት ውይይት የሙርሌ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ያደረሱት ጥቃት “ከክልሉ ቁጥጥር በላይ ነው” ሲሉ የፌደራል መንግስት የድንበር አካባቢ ቁጥጥር ላይ እንዲያግዝ ጠይቀዋል። ሁለተኛ ተወካይ በእነዚህ ቡድኖች የተፈጠረው አለመረጋጋት በአካባቢው ያለውን የኢኮኖሚ እድገት ማደናቀፉን ጠቁመዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ የካቲት 23, 2014)።
በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ውይይት እየተካሄደ ቢሆንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ጉዳዩን ለመፍታት ብዙም ለውጥ ባለማምጣታቸው ግጭቱ ቀጥሏል። በጥር ወር መጨረሻ ላይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስለ ጋራ የድንበር ፀጥታ ጉዳዮች ተወያይተዋል (ቪኦኤ፣ ጥር 25, 2014፤ አይ ሬዲዮ፣ ጥር 26, 2014)። በሁለቱም ድንበሮች በኩል ካለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮች አንጻር በመጪዎቹ ወራትም ድንበር ዘለል ጥቃቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ።