በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 16, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,786
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,149
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,049
በቁጥር (ከመጋቢት 10, 2014 እስከ መጋቢት 16, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 14
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 24
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –10
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጊያ ባለፈው ሳምንትም ቀጥሏል። በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና በአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና ተባባሪ ታጣቂዎች መካከል የተደረጉ ውጊያዎች በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በሚገኙት በርሃሌ፣ ዳሎል፣ ኤረብቲ፣ እና ኮነባ ወረዳዎች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። መጋቢት 15 ላይ የፌዴራል መንግስት በትግራይ ለሰብአዊነት ሲባል የተኩስ አቁም አውጇል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ መጋቢት 15, 2014)። በትህነግ/ህወሃት አባላት የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግስትም የሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት “ጦርነቱ እንዲቆም” ስምምነቱን ገልጿል (የትግራይ የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 15, 2014)። የዚህ ሳምንት ሳምንታዊ ትኩረት የዚህ የተኩስ አቁም ትግበራ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር ያብራራል።
ባለፈው ሳምንት የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከ16 እስከ 18 አመት የሆናቸውን ልጃገረዶች ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሴቶችን እና አንድ ወንድን መግደላቸው ታውቋል። ሟቾቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትን በመመገብ እና ገዢውን ብልፅግና ፓርቲን ይደግፋሉ በሚል በቡድኑ ታስረው ነበር።
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ መካከል ውጊያዎች ቀጥለዋል። በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ገመቺስ ወረዳ ጉዩቦ ቀበሌ እና በጭሮ ከተማ ሸነን ዱንጎ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስና የቀበሌ ታጣቂዎች ከኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ጋር ተዋግተዋል። በግጭቱ ሶስት የኦነግ-ሸኔ አባላት ሲገደሉ ሌሎች ሶስት ደግሞ ቆስለዋል። ተጨማሪ ሶስት የታጣቂ ቡድኑ አባላትም በሸነን ዱንጎ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘዋል።
በተጨማሪም መጋቢት 15 ላይ በተጎጂው ኦነግ-ሸኔ ነው ብሎ የታመነ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ በሚገኘው የኦሮሞ አባ ገዳዎች (ባህላዊ የሀገር ሽማግሌዎች) ማህበር ሊቀመንበር እና የጉጂ አባ ገዳ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ንብረቶችን ዘርፏል። ኦነግ-ሸኔ ይህን ክስ አስተባብሏል (ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 16, 2014)። መጋቢት 10 ላይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ቡልቡላ ከተማ ስታዲየም ውስጥ የአካባቢው ታጣቂዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ሶስት የአካባቢ ታጣቂዎች እና አንድ የ12 አመት ህጻን ሞተዋል። በፍንዳታው 35 ሰዎች ቆስለዋል። ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።
በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት መጋቢት 10 ላይ በድባጤ ወረዳ የአማራ እና የፋኖ ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ተኩሰው ገድለው አንድ ሰው አቁስለዋል ተብሏል። ተጎጂዎቹ በድባጤ ወረዳ ቢሻን አዲ አካባቢ በአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ከህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ታፍነው ከተወሰዱት 18 የኦሮሞ ተወላጅ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች መካከል ናቸው። መጋቢት 13 ላይ የፋኖ ታጣቂዎች በድባጤ ወረዳ ቱስኪ ጋምቤላ ቀበሌ አንድ ወጣት ተኩሰው ገድለው ከህብረተሰቡ በርካታ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል። በማግስቱ በድባጤ ወረዳ በዳማዳስ ገጠር ቀበሌ ታጣቂዎቹ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎችን ገድለው ከ50 በላይ ቤቶችን አቃጥለዋል። ቁጥራቸው ያልታወቀ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ጥቃት ምክንያት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 8 ላይ የድባጤ ነዋሪዎች በመተከል ዞን በባርባራ በመሰባሰብ “በአማራ ሃይሎች እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል” ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን የአማራ ልዩ ፖሊስ እና የፋኖ ታጣቂዎች ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል እንዲወጡ ጠይቀዋል (ኦኤምኤን፣ መጋቢት 8, 2014)።
ባለፈው ሳምንት በፋፋን ዞን ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ በአካባቢው የጎሳ መሪ ሹመት ሥነ ሥርዓት ወቅት በሱማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የሶማሌ ብሄረሰብ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል የሹመት ሥነ ሥርዓት ሂደቱን ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ነው። በዚህ ግጭት ሰባት ሰዎች ሲሞቱ ከ20 በላይ ቆስለዋል።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የተኩስ አቁሙ ትግበራ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች
የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ እንዲቻል የተኩስ አቁም አውጇል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ መጋቢት 15, 2014)። ብዙም ሳይቆይ በትህነግ/ህወሃት አባላት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት “ጦርነቱ እንዲቆም” ተስማምቷል (የትግራይ ውጭ ጉዳይ ፅ/ቤት፣ መጋቢት 15, 2014)። መንግስት እና የትግራይ ክልላዊ መንግስት የተኩስ አቁሙን ለማስፈጸም ማቀዳቸውን ያመለከቱ ሲሆን የትግራይ ክልላዊ መንግስት “ይህ ጦርነት ማቆም የተሳካ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ” ቃል ገብቷል (የትግራይ ውጭ ጉዳይ ፅ/ቤት፣ መጋቢት 15, 2014)።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ስምምነት ቢያደርጉም በሰሜን ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ ፈተናዎች አሉ። የተኩስ አቁም ከመታወጁ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ መንግስት የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ወደ መቀሌ በሚወስደው “የአባላና መቀሌ ኮሪደር” አቋርጠው ለማለፍ የሞክሩ እርዳታ የጫኑ 23 መኪኖች ላይ ተኩስ ከፍተዋል ሲል ከሷል (ኢሳት፣ መጋቢት 14, 2014)። መጋቢት 19 ላይ የትግራይ ክልላዊ መንግስት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት የተኩስ አቁም ቢያወጅም የእርዳታ አቅርቦትን ከልክሏል በማለት ከሷል (ጌታቸው ረዳ፣ መጋቢት 19, 2014)። የፌዴራል መንግስት መንገዶችን የዘጋው ራሱ ትህነግ/ህወሃት ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ መጋቢት 20, 2014)። የግብረሰናይ ሃላፊዎች በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ውስጥ በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ሳምንቱን ሙሉ በትህነግ/ህወሃት እና የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና ተባባሪ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች መደረግ መቀጠላቸውን ገልጸዋል (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 16, 2014)።
ላለፉት ጥቂት ወራት በአፋር ክልል በአባላ ከተማ በሰመራ-አባላ መንገድ ላይ በድጋሚ የጀመረው ግጭት እርዳታ በጭነት መኪናዎች ማድረስን ከሞላ ጎደል የማይቻል ያደረገ ሲሆን ከታህሳስ 6 ጀምሮ ምንም አይነት እርዳታ በመኪና ወደ ትግራይ ክልል አልገባም (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ጥር 26, 2014)። ይህም በክልሉ የሚኖሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦችን ለከፍተኛ ችግር የዳረገ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምግብና መጠለያ ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እንዲሁም ሱዳን ተሰደዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ማድረስ ይቻል ዘንድ የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ከአፋር እና አማራ ክልሎች ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል (የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ መጋቢት 20, 2014)።
የተኩስ አቁሙ ትግበራ ላይ የሚያጋጥሙ ሌሎች ችግሮችም አሉ። ከአገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትህነግ/ሕወሃት ጦር ወደ ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ከተንቀሳቀሰበት የታህሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአፋር ክልል ጦርነት አላደረገም። ከታህሳስ መጨረሻ ወዲህ የመንግስት ሃይሎች ውጊያውን በጫንቃቸው ላይ ለተሸከሙት ለአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች፣ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች እና ለአፋር ክልል መንግስት ታማኝ የሆኑ ሃይሎችን የሚደግፉ የመድፍ እና የአየር ጥቃቶች በማካሄድ ላይ ብቻ የተገደበ ተሳትፎ አድርገዋል። ይህ በአፋር ክልል ባሉ ብዙዎች ዘንድ የክህደት እና የቁጣ ስሜት የፈጠረ ሲሆን የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች “በአፋር ክልል” ላይ ባሉበት ሁኔታ የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ እነዚህን ችግሮች ጠቅሰው የአፋር ሃይሎች የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች በክልሉ የሚገኙ በርካታ ወረዳዎችን ተቆጣጥረው ባሉበት ሁኔታ እርዳታ በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 15, 2014)። በመሆኑም የፌዴራል መንግስት በ”ተኩስ አቁም” ወቅት ከትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ጋር በቀጥታ ባይዋጋ እንኳን የፌዴራል መንግስት በጦር ግንባር የሚገኙትን መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ዘዴ ስለሌለው ጦርነቱ የመቆም እድሉ አናሳ ነው።
የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች ባሉባቸው የአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር እና ዋግ ኽምራ ዞኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ አለ። የፌዴራል ወይም የአማራ ክልል መንግስታት በአማራ ክልል ያሉ ኢ-መደበኛ የፋኖ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ውጊያ የፌደራል መንግስት በጦር ሜዳ ላይ ያለውን ድክመት የሚያሳይ ነው። በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ አንድ የፋኖ አመራር ለፋኖ አባላት የሚሰጡትን ስልጠና አላቆምም በማለታቸው በመንግስት ሃይሎች መታሰራቸውን ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ፣የጁቤ ፣ቢወግን፣ እና ግንደወይን ከተሞች ተዋግተዋል (ዋዜማ ሬዲዮ፣ የካቲት 28, 2014)። በአፋር እና አማራ ክልሎች ያሉ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ከፌዴራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውጭ ያሉ መሆናቸውን እና በአካባቢ ቁጥጥር ላይ ያላቸውን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሰብአዊ እርዳታ በተደረገው የተኩስ አቁም አዋጅ ላይ ትልቅ ስጋት ይፈጥራሉ።
ምንም እንኳን ጦርነቱ ለዘለቄታው እንዲቆም ከፍተኛ ፍላጎት ያለ ቢሆንም ከቦታ ጋር የተያያዙ ውስብስብ ችግሮች እና በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልሆኑ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህን ምክንያቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ እርምጃዎች ካልተወሰዱ በስተቀር ጦርነቱ እንደገና ሊቀጥል ይችላል። ተጨማሪ እርምጃዎቹ ሁለቱም ወገኖች አከራካሪ የሆኑ አካባቢዎችን በተመለከተ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶችን፣ የታጣቂ ሃይሎች ከአወዛጋቢ አካባቢዎች መውጣትን፣ እንዲሁም በሁሉም ግጭት ያለባቸው አካባባኢዎች እርዳታ መድረስን ይጨምራሉ።