ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ መጋቢት 23, 2014) 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 2,807
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 15,513
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ – 7,087
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 17, 2014 እስከ መጋቢት 23, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች – 13
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች – 53
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ –13
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች እና ኮንሶ ዞኖች በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። መጋቢት 17 ላይ በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ዲመያ በተባለ ቦታ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ከኮንሶ ብሄረሰብ ታጣቂዎች እና ከደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ውጊያ አድርገዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች በውጊያው ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል። ዲመያ በአሌ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁለቱን መስተዳድሮች በባለቤትነት ያወዛግባል። በተመሳሳይ ቀን በሰገን ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች የሰገን አካባቢ ወረዳ ገቢዎች ፅህፈት ቤት ኃላፊን ከጓደኞቻቸው ጋር በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ እራት እየበሉ ተኩሰው ገድለዋል። ከአንድ ቀን በኋላ ከአሌ ልዩ ወረዳ የመጡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በኮንሶ ዞን ዲመያ፣ ሰገን፣ እና ኮልሜ ክላስተር አካባቢዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ሲገድሉ 13 አቁስለዋል። በርካታ ቤቶችንም አቃጥለዋል። መጋቢት 22 ላይ ከደራሼ ልዩ ወረዳ የመጡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አንድ የቀበሌ አስተዳዳሪ፣ አንድ የአካባቢ ታጣቂ ቡድን አባል፣ እና ሁለት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። በዚህ አካባቢ ግጭት የተቀሰቀሰው በ2010 ኮንሶ ወረዳ ወደ ዞን እንዲሁም አሌ ወረዳ ደግሞ ልዩ ወረዳ ከሆኑ በኋላ ነው። ከዚህ ቀደም እነዚህ አካባቢዎች አማሮ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ኮንሶ፣ እና አሌ ወረዳዎችን ባቀፈው እና መጋቢት 19, 2003 ላይ በተመሰረተው የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ስር ይተዳደሩ ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ አብዛኞቹ ግጭቶች ከድንበር ውዝግቦች ጋር የተገናኙ ናቸው (ስለ ግጭቱ ተለዋዋጭነት የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦን የሰገን አካባቢ ህዝቦች የግጭት ገጸን ይመልከቱ)።
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የጉራጌ ዞን በኩሴ ውጥረት ነግሷል። ኩሴ ከሀዲያ ዞን ጋር የሚዋሰን ሲሆን በጉራጌ እና ሀዲያ ዞኖች ውዝግብ ይደረግበታል (ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 19, 2014)። አካባቢው በጉራጌ ዞን እንዲካተት የተደረገው በህዝበ ውሳኔ ነበር። በቅርቡ ኩሴ በዚሁ ዞን ውስጥ እንደ ከተማ ለመታወቅ ሂደቱን ጀምሯል። ነገር ግን ከ2010 ጀምሮ አንዳንድ የሀዲያ ወጣቶች ኩሴን የሀዲያ ዞን አካል ለማድረግ አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የሀገሪቱ አዲስ ክልል በሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ በምትገኘው ጉራፈርዳ ከተማ እና በደቡብ ቤንች ወረዳ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ሶስት ሰዎችን ገድለው ከ20 ያላነሱ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል።
ባለፈው ሳምንት የአፋር ክልል ልዩ ሃይሎች እና ተባባሪ ታጣቂዎች ከትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) ታጣቂዎች ጋር በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 ኤረብቲ ወረዳ፣ በአባላ ወረዳ ጉቢ ቀበሌ፣ እና በኮነባ ወረዳ ሶካርዶራ ቀበሌ መዋጋት ቀጥለዋል። ጦርነቱ እየተካሄደ ቢሆንም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በሰመራ-አባላ-መቀሌ መስመር ወደ ትግራይ ክልል ደርሰዋል (አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ መጋቢት 24, 2014፤ ትዊተር @ረዳ_ጌታቸው፣ መጋቢት 23, 2014)። ይህ ከታህሳስ 6 ወዲህ የሰብአዊ እርዳታ በተሽከርካሪ ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። መጋቢት 15 ላይ ሁለቱም ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል ውጊያ ለማቆም ተስማምተዋል። በተጨማሪም ወደ 39 ሜትሪክ ቶን የሚጠጋ የስነ-ምግብ አቅርቦቶች ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በሚበሩ አውሮፕላኖች ደርሰዋል (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 22, 2014)። ከዋና ከተማው ወደ መቀሌ በሳምንት ሁለት የሰብአዊ በረራዎች አሉ። ሆኖም በትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ ነው (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 22, 2014፤ ቢቢሲ አማርኛ፣ መጋቢት 23, 2014)።
ከትግራይ የተፈናቀሉ ግለሰቦች ሰብአዊ እርዳታ ለማግኘት ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን ቀጥለዋል። በአፋር ክልል ቂልባቲ ረሱ-ዞን 2 በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ሰዎች በየቀኑ እንደሚፈናቀሉ የሚያሳዩ ዘገባዎች አሉ (የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ መጋቢት 22, 2014)። በተጨማሪም በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች በተለይም ሴቶችና ህጻናት አስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 20, 2014፤ ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 21, 2014)። ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በግጭቱ ምክንያት የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች እንደተፈናቀሉ እና የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል (የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ፣ መጋቢት 23, 2014)። ምንም እንኳን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው ቢመለሱም፣ መተዳደሪያቸው ስለወደመ አልያም የእርሻ ወቅት ስላመለጣቸው አሁንም እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ቀሪዎቹ አሁንም በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር ይኖራሉ።
በተጨማሪም መጋቢት 18 ላይ በጋምቤላ ክልል የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች ባልታወቀ ምክንያት የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። አንድ ሰው ሲሞት አንድ ሰው ቆስሏል።
በኦሮሚያ ክልል መጋቢት 23 ላይ በምዕራብ ጉጂ ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ መልካ ሩቃ በተባለ ቦታ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ጋር ተዋግቶ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። መጋቢት 22 ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ከተማ አቅራቢያ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ማረሚያ ቤት አባል የሆኑ ሶስት ፖሊሶችን አግቷል። የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ነዋሪዎች ለጠለፋው ተጠያቂው ኦነግ-ሸኔ ነው ብለው ያምናሉ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ መጋቢት 26, 2014)። ቀደም ሲል በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ባለሰልጣናት የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ተጠያቂ ያደርጉ ነበር። መጋቢት 10 የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መንግስት እና የጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮች – የፖለቲካ እና ታጣቂ ክንፎች – በካማሺ ከተማ ባህላዊ የሰላም እና የእርቅ ስነ-ስርዓት አድርገዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)።
ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን ወልቃይት ውስጥ ገሃነብ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በርካታ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተገደሉት ትህነግ/ህወሃትን የሚቃወሙ አማራዎች እንደሆኑ ይታመናል። ጥቅምት 2013 ላይ የትግራይ ግጭት ሲጀምር የአማራ ክልል ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ ዞን ወልቃይት፣ ሁመራ፣ እና ጸገዴ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ አማሮች ለበርካታ አስርት ዓመታት የአማራ ክልል አካል ለመሆን ሲጠይቁ ቆይተዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ መጋቢት 25, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ በኦሮሞ እና አማራ ክልሎች መካከል ያለው ውጥረት
በ2008 ላይ በነበረው የፀረ-ትህነግ/ህወሃት ሰልፎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት ተቃውሞው ላይ ከታዩት ጥምረቶች አንዱ በኦሮሞ እና በአማራ ተቃዋሚዎች መካከል የነበረው የተቀናጀ ጥምረት ነበር ( አፍሪካን አርጊዩመንትስ፣ መስከረም 17, 2009)። የትህነግ አመራሮች በሁለቱም ክልሎች የወሰዱት የሃይል እርምጃ በሰላማዊ ሰልፈኞች ዘንድ የጋራ የጭቆና ስሜትን በማጎልበት የተቃውሞ ሰልፎቹ እንዲቀናጁ እና በመጨረሻም በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን እንዲለቁ በማድረግ በኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በ2010 ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሁለቱ ክልሎች ያሉ የውስጥ የፖለቲካ ክፍፍሎችን አልፈው በኦሮሞ እና በአማራ መካከል ያሉ ግንኙነቶች እየሻከሩ ሄደዋል ። በሁለቱም ክልሎች ያሉ የመሪው የብልጽግና ፓርቲ ክንፎች መካከል ውጥረት የነገሰ ሲሆን በሁለቱም ወገን ባሉ ብሔርተኛ አካላት መካከል ደግሞ ውጊያ እየተካሄደ ነው። በሁለቱ ክልሎች ባሉ ኃይሎች መካከል ባለፈው ሳምንት የነበረው ውጊያ ውጥረቱ እና ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸውን ያሳያል። በመሰረቱ በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ሃይሎች መካከል ያለው ግጭት ከወሰን ውዝግብ ጋር ከመያያዝ ያለፈ ነው። እነዚህ በኢትዮጵያ የተለመዱ እና በአካባቢ የተወሰኑ ሆነው የሚቀጥሉ ቢሆንም በክልል ደረጃ ካለው የፖለቲካ ልዩነት የተነሳ ግጭቱ ሊባባስ የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነው።
በአማራ ክልል በገዢው መንግስት ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ላይ ያለው ቁጣ እየጨመረ ነው። መጋቢት 2014 ላይ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን አጣዬ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ በመላ ክልሉ ትልልቅ ሰልፎች ተካሂደዋል። በእነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እንደ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ያሉ የአማራ ብሄርተኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፈው የነበረ ሲሆን አሁን በኢትዮጵያ የገዥው መንግስት አካል ናቸው (ለተጨማሪ መረጃ ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከመጋቢት 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 22, 2013ን ይመልከቱ)። ባለፉት ሶስት አመታት የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ አንቂ ባለሙያዎች የኦሮሚያ ክልል መንግስት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ አማራዎችን ለመጠበቅ በቂ እርምጃ አልወሰደም ብለው ሲያወግዙ ቆይተዋል። አክሌድ በኦሮሚያ ክልል ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ ቢያንስ 420 የሚሆኑ ጥቃቶችን መዝግቧል።
በኦሮሚያ ክልል ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል ስር ይተዳደሩ የነበሩ ቦታዎችን የአማራ ታጣቂዎች በኃይል እየወሰዱ ነው በሚል ክስ ተመሳሳይ ውዝግቦች እየተፈጠሩ ነው። ከመጋቢት 23, 2013 ጀምሮ በኦሮሚያ ውስጥ ከአማራ ብሔር ታጣቂዎች ጋር በተያያዙ ውጊያዎች እና ጥቃቶች ቢያንስ 330 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት በሁለቱ ክልሎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ድንበር ላይ ሁለት ውጊያዎች እንደነበሩ ተዘግቧል። በአማራ ክልል የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳደር ሃላፊዎች መጋቢት 20 ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አሞራቤት ቀበሌ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ቆስለዋል ሲሉ ገልጸዋል (የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኮሙኒኬሽን፣ኮሙኒኬሽን፣ መጋቢት 21, 2014)። በተመሳሳይ ቀን ማንነቱ ያልታወቀ እና በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት “አክራሪ የአማራ ታጣቂ ቡድን” በሚል የተገለጸ ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንን በሚያወዛግበው ቆርኬ/አውራ ጎዳና አካባቢ በሚያልፉ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ታጣቂዎች እና ፖሊስ ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርሷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 22, 2014)። በዚሁ ጥቃት 28 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 15 መቁሰላቸው የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት አስታውቀዋል (ሮይተርስ፣ መጋቢት 22, 2014)። በዚህ ጥቃት ዋና ከተማዋን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው ዋና መንገድ ለተወሰኑ ሰአታት ተዘግቷል። አውራ ጎዳና ወይም ቆርኬ አካባቢ ላለፉት ጥቂት ወራት በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ነበር (ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 22, 2014)።.
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በኩነቱ ላይ ወዲያው እርስ በእርስ የተቃረኑ ሲሆን ውጥረቱ አሁንም ድረስ አለ (ዲደብሊው አማርኛ፣ መጋቢት 22, 2014፤ ኢሳት፣ መጋቢት 22, 2014)። መጋቢት 26 ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግስት “‘ስሙ ያልተጠቀሰ በአማራ ስም የሚንቀሳቀስ ጽንፈኛ ሃይሎች’ ቡድን’” አስጠንቅቆ መግለጫ አውጥቷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ መጋቢት 26, 2014)። ይህ መግለጫ የኦሮሚያ ክልል መንግስት አውራ ጎዳና ከተማን ለመውረር “የመንግስት መኪናዎችን ተጠቅሟል” ሲል በከሰሰው የዐማራ ማህበር በሰሜን አሜሪካ የተባለ ተደማጭነት ያለው የዲያስፖራ ቡድን ተነቅፏል (የዐማራ ማህበር በሰሜን አሜሪካ፣ መጋቢት 26, 2014)። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ድርጊቱ የተፈፀመው የኦሮሞ ታጣቂዎች አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ነው ብሏል (አማራ ኮሚኒኬሽን፣ መጋቢት 22, 2014)።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን የሳበ ቢሆንም በገዥው ፓርቲ የኦሮሚያ እና አማራ ክንፎች እንዲሁም በሁለቱም ወገን ያሉ ንቁ ብሔርተኛ ኃይሎች መካከል ያለው መከፋፈል ዛሬ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት አደገኛ አዝማሚያዎች አንዱ ነው። የአማራም ሆነ የኦሮሚያ ክልሎች የልዩ ሃይል ፕሮግራሞቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ያስፋፉ ሲሆን በሁለቱ ክልል ሃይሎች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ቀጥተኛ ውጊያ ከፌዴራል መንግስት አቅም በላይ ይሆናል።
ከእነዚህ ልዩ ሃይሎች በተጨማሪ በሁለቱም ክልሎች ያሉ አክራሪ ብሔርተኛ ድርጅቶች መኖራቸው የሰላሙን ጥረት የበለጠ ያወሳስበዋል። በኦሮሚያ ክልል የኦነግ-ሸኔ ሃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ የአማራ ተወላጆችን ገድለዋል እንዲሁም ከአማራ ታጣቂዎች ጋር በየጊዜው ይጋጫሉ። በአማራ ክልል ፋኖ እና ሌሎች ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል መንግስት ጋር በትህነግ/ህወሃት ላይ ጦርነት በመክፈት መሳሪያ እና ስልጠና አግኝተዋል። ይህ ጥምረት እንዳለ ሆኖ መንግስት ፋኖዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ያደረገው ሙከራ ከፍተኛ ግጭት አስከትሏል። ከአማራ ክልል የተውጣጡ ኢ-መደበኛ ታጣቂዎች በበርካታ አወዛጋቢ አካባቢዎች- በምዕራብ ትግራይ ዞን፣ በቤንሻንጉል/ጉሙዝ መተከል ዞን፣ እና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ግጭት ውስጥ ተሳትፈዋል።
እስካሁን ድረስ ያሉት ግጭቶች አጭር እና አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ቢሆንም ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተበጀለት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ኃይሎች መካከል ጦርነት የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ነው። ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እንደመሆናቸው ኢ-መደበኛ የሆኑ ሃይሎች መኖራቸው ማንኛውንም የፖለቲካ መፍትሄ ያወሳስበዋል። ከእነዚህ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች አንፃር በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በክልሎች መካከል ውዝግብ ባለባቸው ቦታዎች ውጊያዎች በየጊዜው መከሰታቸው አይቀርም።