ኢትዮጵያ በቁጥር (ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 5, 2014) 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 2,921
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 15,984
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,233
ኢትዮጵያ በቁጥር (ከሚያዚያ 29, 2014 እስከ ግንቦት 5, 2014) 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 10
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 34
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ:12
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኮንሶ ዞን እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያለው ሁከትና ብጥብጥ ባለፈው ሳምንትም ቀጥሏል። ግንቦት 1 ላይ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ እና ከክልሉ ልዩ ሃይሎች የተወጣጡ ሃይሎች ከደራሼ የብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር በጊዶሌ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት ሃታያ እና ሰለሌ ገጠር መንደሮች ውስጥ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። በግጭቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል። በኋላም ግንቦት 3 እና 4 ላይ በኮንሶ ዞን ሰገን ወረዳ ጉማይዴ ከተማ በቾ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ አንድ ሰው ገድለዋል። ባለፈው ሳምንት በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተከሰተው ብጥብጥ ባለፈው ሚያዚያ የተደረገው ከባድ ውጊያ የቀጠለ ነው (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 15, 2014 እስከ ሚያዚያ 28, 2014 ይመልከቱ)።
የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሃት) በትግራይ ክልል ባድመ እና ራማ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በኤርተራ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ከባድ መሳሪያ ተኩሰዋል። በኋላም በኤርትራ ወታደሮች እና የትህነግ/ህወሃት ሃይሎች መካከል ውጊያዎች በራማ አካባቢ ተመዝግበዋል። ባድመ ከተማ ጦርነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ከጀመረበት ጥቅምት 2013 ጀምሮ በኤርትራ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትህነግ/ህወሃት ላይ ያለው ጥምረት የውጥረት ምክንያት ሲሆን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ማህበረሰብ የኤርትራ ወታደሮችን በትግራይ ክልል የትግራይ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ በደል በመፈጸም ይከሳል (ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ የካቲት 26, 2013)። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ2010 በጀመሩት የሰላም ስምምነት ሚያዚያ 1994 ላይ በተላለፈው የኤርትራ እና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ መሰረት ኢትዮጵያ የባድመ ከተማን ለኤርትራ መልሳለች (አልጀዚራ፣ ሃምሌ 2, 2011)።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔን የሚያወግዙ ሰልፎች መደረጋቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ዘግበዋል (የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ግንቦት 5, 2014፤ የኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ግንቦት 1, 2014)። በሌላ በኩል የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር በምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ ወረዳ፣ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሳግሊ ቀበሌ እና በጉጂ ዞን ጉሚ ኢዳሎ ወረዳ ተዋግተዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ከውጊያዎቹ ጎን ለጎን በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የተዘገቡባቸው ኩነቶች ተመዝግበዋል። ግንቦት 2 ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ዙሪያ ወረዳ ገላን ወዴሳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ኦነግ-ሸኔን ይደግፋሉ በሚል ስምንት ሰዎችን ገድለው አንድ ሌላ ሰው አቁስለዋል። ከአንድ ቀን በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሚዳግዱ ቀበሌ በተመሳሳይ ምክንያት ሶስት በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ገድለዋል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መከላከእያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይሎች ሰሜን ሸዋ ዞን ለማና ካሬ ቆራ መንደሮች ውስጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን መኖሪያ ቤቶች በከባድ መሳሪያ በመደብደብ አውድመዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ግንቦት 4 ባወጣው መግለጫ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ 297 በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መገደላቸውን ገልጿል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር፣ ግንቦት 4, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ወቅታዊ ሁኔታ ትንተና
መጪው ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ለሚገኙ ብዙዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም እና አስቸጋሪ ጊዜን ለማቆም ተስፋ ሰጪ እድልን ይወክላል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩ ሁከት እና አለመረጋጋት አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ጎድቷል። የዋጋ ንረት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል። መፈናቀል፣ እርግጠኛ አለመሆን እና መንግስት ጦርነቱን ለመደገፍ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን መጨመር በመላ ሀገሪቱ በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ያለመው ሀገራዊ ምክክር ህዳር 2015 ላይ እንደሚጀመር አስታውቀዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 6, 2014)። ብዙ የፖለቲካ ተቋማት የመጀመርያው የኮሚቴ አመራረጥ ሂደት ኢ-ፍትሃዊ እና አግላይ ነው ሲሉ ያወገዙት ኮሚሽኑ አጀማመሩም ቀላል አልነበረም። ቢሆንም በመላ አገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን መከፋፈል ለማስተካከል የሚሞከርበት አጋጣሚ ነው።
ታህሳስ 20, 2014 ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ያቋቋመውን አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በአብላጫ ድምፅ፣ በአንድ ድምፅ ተአቅቦ እና በ13 ተቃውሞ አጽድቋል (የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ታህሳስ 20, 2014)። የተቃውሞ ድምጽ የሰጡት ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ እና በቀጠለው ግጭት ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ከጥቂት ወራት በኋላ 11 የተለያየ ትምህርት እና ልምድ ያላቸው ኮሚሽነሮች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተመረጡ በኋላ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን እንዲመሩ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ጥር 27, 2014 ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ከ632 ጥቆማዎች 42 እጩዎችን መርጠው ይፋ አድርገዋል (የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ጥር 27, 2014)።
በአዋጁ መሠረት ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የሚደረግ ምክክር ነው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያለው ሃላፊነት በአምስት ነጥቦች ሊጠቃለል ይችላል:- (1) ለብሔራዊ ምክክሩ አጀንዳ ማውጣት፤ (2) ተሳታፊዎችን መለየት፤ (3) ሀገራዊ ምክክሩን መምራት፣ (4) ከሀገራዊ ምክክሩ የተገኙት ውጤቶችን አፈፃፀም መከታተል እና፣ (5) “ወቅታዊ ችግሮችን” በውይይት ለመፍታት የሚረዳ ዘላቂ ሀገራዊ ምክክር ሥርዓት መዘርጋት (አዋጅ ቁጥር 1265/2014፣ አንቀጽ 2, 6 እና 9)።
በሚያዚያ ወር ማገባደጃ ላይ ኮሚሽኑ በ2010 የተመሰረቱትን የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና ሀገራዊ የዕርቀ-ሰላምኮሚሽንን ሃላፊነት ተረክቧል (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሚያዝያ 25, 2014)። የእነዚህ ሁለት ኮሚሽኖች ኮሚሽነሮች ታዋቂ ሰዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ነበሩ (ቦርከና፣ ጥር 28, 2011፤ ቦርከና፣ ጥር 28, 2011)። የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ዋና አላማ በውስጥ ወሰን ላይ የሚነሱ እና ከማንነት ጋር የተያያዙ አለመግባባቶች ለመፍታት ነበር (አዋጅ ቁጥር 1101/2011)። በሌላ በኩል የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኑ የተቋቋመው “በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ ብሄራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም እርቅ እንዲሰፍን” ለመስራት ነበር (አዋጅ ቁጥር 1102/2011፣ አንቀጽ 5)። እነዚህ ኮሚሽነሮች በአባላቶቻቸው መታሰር፣ የቀጠለው ጦርነት እና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለመቻልን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች አላማቸውን ማሳካት ባለመቻላቸው ሃላፊነታቸው ወደ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተዘዋውሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሃላፊነቶቹን ለመወጣት እንቅስቃሴዎቹን በአራት ምዕራፎች ከፍሏል። የመጀመሪያ በሆነው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ኮሚሽኑ ግቡን ለመምታት የሚያስችለውን ፍኖተ ካርታ እና ስልቶቹን ይነድፋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ወቅት አገራዊ ውይይቱን የሚመለከቱ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን እና ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ላይ ነው። በሁለተኛው ምዕራፍ – የዝግጅት ምዕራፍ – ኮሚሽኑ ስልጠና ይሰጣል እንዲሁም የሀገራዊ ምክክሩንቱ ተሳታፊዎች እና አጀንዳዎች ይለያል። ከዚያም በሦስተኛው ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ምክክሩን ይጀምራል እንዲሁም ያስተባብራል። ኮሚሽኑ በመጨረሻው ምዕራፍ የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት ተግባራዊ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሊቀመንበር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታ እና ስልቶቹን ለባለድርሻ አካላት ይፋ በማድረግ ለውይይት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 6, 2014)።
ኮሚሽኑ ገና በመጀመርያ ደረጃ ላይ ይገኛል። ስለዚህ ተግባራቶቹን በዝርዝር ለመገምገም አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተቃውሞቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት – ከ50 በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት – መግለጫ ያወጣ ሲሆን ሂደቱ ሁሉን አቀፍ ያልሆነ እና እምነት ያጣ በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽነሮችን ምርጫ ሂደት እንዲያቆም ጠይቋል። የጋራ ምክር ቤቱ እምነት እንዳይታጣ የ632ቱ እጩዎች ስም ለህዝብ ይፋ መሆን እንደነበረበት እና የ42ቱ እጩዎች ምርጫ በአዋጁ በተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች መሰረት የተደረገ ስለመሆኑ ግልጽ የሆነ ማሳያ ባለመኖሩ ስጋቱን ገልጿል (የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የካቲት 10, 2014)። ምክር ቤቱ በረቂቁ ላይ ሁለተኛ ምክክር ሳይደረግ አዋጁ መጽደቁንም ተቃወመ። ቢሆንም ከረዥም ውይይት በኋላ ሚያዚያ 28 ላይ 40 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በመጪው ሀገር አቀፍ ውይይት ለመሳተፍ ድምጽ ሰጥተዋል (ኢሳት፣ ሚያዚያ 28, 2014)።
ሌሎች ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ መግለጫዎችን አውጥተዋል። የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ኮሚሽኑን በኮሚሽነሮች ምርጫ ሂደት ምክንያት “ገና ሳይመሰረት የመከነ ” ሲል ጠርቶታል (ባልደራስ፤ የካቲት 14, 2014)። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አዋጁ የፀደቀበትን መንገድ እና የኮሚሽነሮችን የአሿሿም ሂደት በመቃወም እነዚህ ድክመቶች እንዲቀረፉ ጠይቋል (ኢዜማ፣ የካቲት 16, 2014)። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) መግለጫዎችን ያወጡ ሲሆን “ኮሚሽነሮች የተጠቆሙበት መንገድ ገለልተኛ ያልሆነ(ኦፌኮ)፣ ያልታወቀ (ኦነግ) እና ውክልና የሌለው (ኦብነግ)” ነው ብለዋል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ጥር 27, 2014)።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከባድ ፈተና ተጋርጦበታል። ብሄራዊ ውይይቱ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የሀገሪቱ ባለድርሻ አካላት በውይይቱ መሳተፍ አለባቸው። ሆኖም ግንቦት 2013 ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ‹አሸባሪነት› የተፈረጁት ትህነግ/ህወሃት እና ኦነግ-ሸኔ በብሔራዊ ውይይቱ መሳተፋቸው ግልፅ አይደለም። ነገር ግን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ምንም ገደብ የለም” ስለሆነም ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል (ገበያኑ፣ መጋቢት 3, 2014)። ለጊዜው በመንግስትና ትህነግ/ህወሃት መካከል ቢያንስ በድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረገ ይህ እንዴት እንደሚሳካ ግልጽ አይደለም። ምንም እንኳን መጋቢት 2014 ላይ ለሰብአዊ እርዳታ በሚል የተኩስ አቁም የታወጀ ቢሆንም በሰሜኑ ክፍል በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ሌላ ዙር ጦርነት ሊነሳ እንደሚችል የተለያዩ ምንጮች ያመለክታሉ (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 8, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 5, 2014)።
በተጨማሪም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኮሚሽኑን ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር በአዋጁ ውስጥ እንዴት እንደተገለፀ አያውቅም። በሰሜን የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይኖር ሀገራዊ ምክክሩ እንዴት እንደሚካሄድ ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት ውስጥ ባሉ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ድርድር በማድረግ እንዲጀመር ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ሊቀመንበሩ “የእኛ ስራ በድንገት ዕርቅ መፍጠር ወይም በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ድርድር እንዲደረግ ማዘዝ አልያም ማስገደድ ሳይሆን በአለመግባባቶች ላይ መግባባት ላይ እንዲደርስ ለውይይት ክፍት እንዲሆን ማድረግ ነው” ብለዋል (ገበያኑ፣ መጋቢት 3, 2014)። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ምክክሩ የነደፈውን ፍኖተ ካርታ እስካሁን ስላላወጣ የሀገራዊ ምክክሩን አጀንዳ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ ግጭቶች አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ። እነዚህ አዝማሚያዎች (1) በፌዴራል መንግሥትና በትህነግ/ህወሃት መካከል ያለው የሰሜኑን ግጭት፤ (2) በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ወታደሮች መካከል ያሉ ውጊያዎች፤ (3) በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች የሚደርሱ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፤ እና (4) ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር በተያያዙ የሚነሱ ግጭቶች ናቸው (በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን አዝማሚያዎች በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 15, 2014 እስከ ሚያዚያ 28, 2014 ይመልከቱ)። ኮሚሽኑ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ካሳተፈ እና እነዚህ አካላት የተስማሙበትን የሀገራዊ ምክክሩን ውጤቶች አፋፃፀም ያለምንም መጓተት የሚከታተል ከሆነ በማንነትን መሰረተ ያደረጉ እና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያይዙ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የበለጠ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። ከማንነት እና ራስን በራስ ማስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግጭቶች መንስኤዎች አንዱ የመንግስት ለጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት ነው። ለሰሜኑ ግጭት በሀገራዊ ምክክሩ በኩል ዘላቂ ሰላም ማምጣት ብዙዎቹ ጉዳዮች ውስብስብ እንደመሆናቸውና ከፖለቲካዊ ውሳኔዎች ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ከኦነግ-ሸኔ ጋር ያለው ግጭትም እንደዚሁ ነው። የኮሚሽነሮቹ የስራ ዘመን ሶስት አመት ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመናቸው ሊራዘም ይችላል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት የሚፈታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ማዳበር እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ምቹ መደላደልን” መፍጠር ይጠበቅበታል (አዋጅ ቁጥር፣ 1265/2014፣ አንቀጽ 6(5))።
በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ምክክሩ ይሳካል ወይም አይሳካል የሚለውን ለመደምደም በጣም ገና ነው፤ ምክንያቱም ከላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የውይይቱን አጀንዳ እንዴት እንደሚይዝ፣ ባለድርሻ አካላትን እንዴት እንደሚመርጥ እና ሀገራዊ ምክክሩን እንዴት እንደሚያካሂድ ገና ስልቶቹን አላሳወቀም። ሀገራዊ ምክክሩብሄራዊ ውይይቱ እና ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ያለውን ስኬት ወይም ውድቀት የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ አካታችነት፣ ህጋዊነት፣ ግልጽነት እና ታማኝነት ይወስናል። ቀደም ሲል እንደተገለፀው የኮሚሽነሮች ሹመትና ምርጫ ሂደት ግልጽነት የጎደለው ነበር። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱትን የተለያዩ ግጭቶች መንስኤዎችን የሚፈታ ሁሉን አቀፍ፣ ህጋዊ፣ ግልጽ እና እምነት የሚጣልበት ሀገራዊ ምክክር ለመመስረት አሁንም እድል አለው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እነዚህን ሁኔታዎች ያላካተተ ሀገራዊ ምክክር ካደረገ ልክ እንደአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እና የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን አይነት ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው ይችላል።