በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 12, 2014 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 2,942
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,091
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,270
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከግንቦት 6 እስከ 12, 2014 2 በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 17
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 93
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 26
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የክልሉ ሃይሎች በፋኖ ሚሊሻዎች እና የአማራ ብሄርተኛ የፖለቲካ ቡድኖች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ውጊያዎች እና የጅምላ እስራቶች እንደነበሩ ተዘግቧል። እነዚህ ክስተቶች እና ተፅዕኖዎቻቸው ከዚህ በታች ባለው የሳምንታዊ ትኩረት ክፍል ተዘርዝሯል። በተጨማሪም ግንቦት 9 ቀን በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ባቲ ከተማ በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እንደተተወ የሚገመት ፈንጂ ፈንድቶ ሦስት ህጻናትን ጨምሮ አምስት ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድል አምስት ተጨማሪ ሰዎችን አቁስሏል።
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ እና በመንግስት ሃይሎች መካከል ግጭቶች ቀጥለዋል። ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ኦዳ ቡልቱም፣ ገመቺስ እና ሚኤሶ ወረዳዎች፤ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን መልካ ባሎ ወረዳ፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደገም ወረዳ ያያ ሃሮ ቀበሌ እና ኩዩ ወረዳ ኡዩ ጨበረ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ዋልኪቴ ወረዳዎች ግጭቶች ተመዝግበዋል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ግንቦት 10 ቀን፤ የኦነግ–ሸኔ አባላት በፊንፊኔ ልዩ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ኬንቴሪ ቀበሌ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ካምፕ አጥቅተዋል። ኦነግ–ሸኔ 16 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትን መግደሉን እና ከ25 በላይ የሠራዊቱን አባላት ማቁስሉን ገልፇል (ኦኤምኤን፣ ግንቦት 11, 2014)። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ሸዋ ዞን አቦቴ እና ወረጃርሶ ወረዳዎች ከኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ጋር በጋራ ባደረጉት ዘመቻ 44 የኦነግ–ሸኔ አባላት መገደላቸውን እና አምስት የቡድኑ አባላት ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ግንቦት 13, 2014 )። ሌሎች 233 የኦነግ–ሸኔ አባላት ከሀገር ሽማግሌዎችና ከአባ ገዳዎች (ባህላዊ መሪዎች) ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰላም እጃቸውን እንደሰጡም ተዝግቧል።
ግንቦት 7 ቀን፤ የያያ ጉለሌ ወረዳ ነዋሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ዋቤ ከተማ በመሰባሰብ ኦነግ–ሸኔን እና የአማራ ፋኖ ታጣቂዎችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ በተለያዩ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል። ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ የካሬ ዶቢ ቀበሌ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸው የተገመተ የመንግስት ሃይሎች ቢያንስ አራት ሰዎችን በጥይት መተው ገድለዋል። ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያለው ምክንያት አልታወቀም። ግንቦት 11 ቀን፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ዋልቂቴ ወረዳ ምናሬ ከተማ አቅራቢያ ኦነግ–ሸኔ ተብሎ የተጠረጠረ ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን ተኩስ ከፍቶ ሦስት የኢትዮ–ቴሌኮም ሰራተኞችን ገድሏል። ሰራተኞቹ በአካባቢው የኔትወርክ ጥገና አድርገው ወደ ሆለታ እየተመለሱ ነበር።
ኦነግ–ሸኔ ከኦሮሚያ ክልል ውጭ በተከሰቱ ሁለት ጥቃቶችም ተሳትፏል። በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አማሮ ወረዳ ትፋተ ቀበሌ የኦነግ–ሸኔ አባላት ከብቶች ሲጠብቁ የነበሩ ሁለት ሕፃናትን በጥይት ተኩሰው ገድለው ከ40 በላይ ከብቶችን ዘረፈዋል። ግንቦት 6 ቀን፤ በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ባቲ ወረዳ ጨቆርሲ ቀበሌ ከአማራ ክልል ባቲ ወረዳ እና ክአፋር ክልል አዳር ወረዳ የመጡ የአካባቢው ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ መሪዎች የሽምግልና ስብሰባ እያደረጉ ባለበት ወቅት ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን ተኩስ ከፍቷል። የባቲ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ የባቲ ወረዳ ሚሊሻ ጽ/ቤት ሃላፊን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች ቆስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፤ ግንቦት 8, 2014)። አንድ የጥቃቱ ተጎጂ ለጥቃቱ ተጠያቂው ኦነግ–ሸኔ ነው ሲሉ አመላክተዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 8, 2014)። የሽምግልና ስብሰባው በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በአፋር ክልል ዞን 1 ባሉ አርብቶ አደሮች መካከል አልፎ አልፎ የሚፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ያለመ ነበር።
ባለፈው ሳምንት በቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ሁለት ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ሁለቱም ጥቃቶች የተፈጸሙት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ነው። ግንቦት 7 ቀን፣ በመተከል ዞን ዲባጢ ወረዳ ጊፎ ቀበሌ ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት አንድን ሰው የኦነግ–ሸኔ አባል ነው በማለት ተኩሰው ገድለዋል። በማግስቱ በዚሁ ቀበሌ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በአካባቢው ወደ ሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ለሚገኙ ዘመዶቹ እህል እያደረሰ የነበረ አንድ ሰው ተኩሰው ገደለዋል። የዚህ ጥቃት ምክንያት አልታወቀም።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል በደራሼ ልዩ ወረዳ በተፈጠረው አለመረጋጋት እና በትጥቅ በታገዘ ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ 330 የሚጠጉ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቀዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 11, 2014)። በዚህ ዘመቻ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችም ተይዘዋል። ከሚያዚያ 19, 2014 ዓ.ም ጀምሮ በደራሼ ልዩ ወረዳ ስድስት ግጭቶች ተመዝግበዋል። በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት በወረዳው ባንኮች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት እና መንገዶች ለተከታታይ ሳምንታት ተዘግተው ነበር (በእነዚህ ኩነቶች ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 15, 2014 እስከ ሚያዚያ 28, 2014 እና ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከሚያዚያ 29, 2014 እስከ ግንቦት 5, 2014 ይመልከቱ)።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሶስት አመት ፍኖተ ካርታውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አጋርቷል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13, 2014)። ኮሚሽኑ የመጪውን ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማዘጋጀት፣ ተሳታፊዎችን የመለየት፣ ሀገራዊ ምክክሩን የማመቻቸት፣ ከሀገራዊ ምክክሩ የተገኙ ውጤቶችን አፈፃፀም የመከታተል፣ እንዲሁም “ወቅታዊ ችግሮችን” በውይይት ለመፍታት የሚረዳ ዘላቂ የሀገራዊ ምክክር ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት ተጥሎበታል (አዋጅ ቁጥር 1265/2014፣ አንቀጽ 2, 6 እና 9) (ኮሚሽኑ በቅርቡ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከሚያዚያ 29, 2014 እስከ ግንቦት 5, 2014 ይመልከቱ)።
በተጨማሪም የሶማሌ እና የአፋር ክልል መንግስታት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውይይት አድርገዋል። በዚህም ውይይት ክልሎቹ ሠራዊቶቻቸውን አለመግባባት ካለባቸው አካባቢዎች ለማስወጣት፣ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን ለማካሄድ፣ የተፈናቀሉ ግለሰቦችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ፣ የግጭቱን መንስኤ ለማጥናት እና ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ተስማምተዋል (የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ ግንቦት 5, 2014)። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ውዝግብ ምክንያት በተደጋጋሚ ግጭት ያጋጥማል። ግጭቱ ከኢሳ ጎሳ የሆኑ የሶማሌ ተወላጆች በሚኖሩባቸው ሶስት ቀበሌዎች ላይ የሚከሰት ነው። እነዚህ ሶስት ቀበሌዎች በአፋር ክልል ዞን 1 እና 3 እንዲሁም በሶማሌ ሰቲ ዞን ይገኛሉ። እነዚህም በሚሌ ወረዳ አዳይቱ ቀበሌ፣ በገዋኔ ወረዳ ኡንዱፎ ቀበሌ እና በአሚባራ ወረዳ ገዳማይቱ ቀበሌን ያካትታሉ (ስለዚህ ግጭት የበለጠ ማብራሪያ ለማግኘት የኢፒኦ የግጭት ማብራሪያ ገፅ ላይ የአፋር–ሶማሌ ድንበር ግጭት ገፅን ይመልከቱ)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የአማራ ክልል ውጥረት ግጭት ቀስቅሷል
ባለፉት ጥቂት ወራት በአማራ ክልል በፋኖ ሚሊሻዎች እና በፌዴራል መንግስት መካከል ውጥረት ነግሷል። ባለፈው ሳምንት ውጥረቱ ተባብሶ የክልሉ ልዩ ሃይል የፋኖ ሚሊሻ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ወይም ትጥቅ ለማስፈታት ሲሞክር በርካታ ግጭቶች መከሰታቸው ተዘግቧል። የተወሰኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ወንበር የያዘው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባላትን፣ ጋዜጠኞችን እና ግለሰቦችን ጨምሮ የአማራ ብሄርተኛ አካላት ላይ የተወሰደው እርምጃ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ እና በአማራ ብሄርተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የወረደ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል።
የፋኖ ታጣቂዎች እና የአብን የፖለቲካ ድርጅትን ጨምሮ የአማራ ክልል ብሄርተኛ ድርጅቶች፣የፌዴራል መንግስትን የአማራ ተወላጆችን ጥቅም ወደ ጎን በመተው እና ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚደርሱ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ የአማራ ተወላጆችን መከላከል ባለመቻሉ ሲነቅፉት ቆይተዋል። ከፌዴራል መንግሥት አንፃር ደግሞ የፋኖ ሚሊሻዎች ከፌዴራል መንግሥት ዕዝ መዋቅር ውጪ ስለሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን ደኅንነትና ፀጥታን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው። የፋኖ ሚሊሻዎች በምዕራብ ትግራይ ዞን የትግራይ ተወላጆችን በመግደል፣ በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ግጭት በመፍጠር እና በኢትዮጵያ/ሱዳን ድንበር ላይ ያለውን የሳሳ የፖለቲካ ግንኙነት አደጋ ላይ በመጣል ይከሰሳሉ (በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥቱ እና ብሄርተኛ ድርጅቶች መካከል ከዚህ በፊት ሰለነበረው ውጥረት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከመጋቢት 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 22, 2013ን ይመልከቱ)።
በአማራ ክልል የፋኖ ሚሊሻዎች እና የአብን ፖለቲከኞች ተወዳጅ ሲሆኑ አብን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት መቀመጫዎችን ይዟል። ይህ ተወዳጅነት እንዳለ ሆኖ አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪዎች የፋኖ ታጣቂዎች በክልሉ ከተሞች ሲዘዋወሩ የሚከተለው የጸጥታ ችግር እያሳሰባቸው ይገኛል (ዲደብሊው አማርኛ፤ግንቦት 13, 2014)። የተወዳጅነታቸው ምንጭ በምዕራብ ትግራይ ዞን የአማራን ጥቅም ለማስከበር ከሚያደርጉት ሙከራ፣ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የሰላማዊ አማራዎች ደህንነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መንግስትን ከመቃወም እና ትህነግ/ህወሃት በአማራ ክልል ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ለመመከት ተዋጊዎችን በማሰባሰባቸው ነው። በዚህ ምክንያት የፋኖ አመራሮችን ለመበተን ወይም ለማሰር የሚደረጉ ሙከራዎች ብዙ ጊዜ ብጥብጥ እና ሰልፎችን ያስከትላሉ።
የባለፈው ሳምንት ሁከት የጀመረው የአማራ ክልል ባለስልጣናት በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የጦር መሳሪያዎች በሳምንቱ መጨረሻ እንዲመዘገቡ የሚጠይቅ አዋጅ ካወጡ በኋላ ነበር (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 8, 2014)። የክልሉ መንግስት በአማራ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ ያሉ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን፣ ተኩሶች እና በፍርድ ቤት ውሳኔዎች ጣልቃ መግባቶች በመኖራቸው“የህግ ማስከበር” እርምጃው አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 11, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 13, 2014)። በዚህ ኦፕሬሽን ከ4,500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 15, 2014)። የክልሉ መንግስት ይህ እርምጃ በፋኖ ሚሊሻዎች ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ “ወንጀለኞች” ላይ መሆኑን ግልጿል። ይሁን እንጂ በክልሉ የሚገኙ ብዙዎች የአዋጁ ቅርፅ እና አዋጁን ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ የአማራ ብሄርተኞችን እና ጥቅም ለመጨፍለቅ እንደሆነ አድርገው ተረድተውታል።
ይህ የቅርብ ጊዜው ግጭት በሰሜን ወሎ ዞን በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የክልሉ ልዩ ሃይል የፋኖን ስልጠና ልምምድ ለማስቆም በሞከረበት ወቅት ከፋኖ ሚሊሻዎች ጋር የተፈጠረው ግጭት መቀጠሉን ያሳያል። በተጨማሪም ይህ የቅርብ ጊዜው ግጭት በጎንደር ከተማ በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ሁከትና ብጥብጥን እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ሃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ መታሰራቸውን ተከትሎ የተከሰተ ነው። ተፈራ ማሞ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልን እስከ የካቲት ወር ድረስ ሲያዙ የነበረ ሲሆን ያለምንም ማብራሪያ ከስልጣናቸው ተነስተዋል (ሮይተርስ፤ ግንቦት 12, 2014)። ብርጋዴር ጀነራሉ በፌዴራል መንግስቱ ላይ ከፍተኛ ትችት ይሰነዝሩ የነበረ ሲሆን የፌዴራል መንግስቱ በአንድ ወቅት ያዙት የነበረውን የአማራ ክልል ልዩ ሃይል ለማፍረስ ተንቀሳቅሷል በማለት ከሰው ነበር (ዘጋቢ፣ የካቲት 19, 2022)።
ባለፈው ሳምንት ግንቦት 11 ቀን በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ የመንግስት ሃይሎች ወደ አካባቢው በመግባት የፋኖ ቡድንን አባላት ትጥቅ ለማስፈታት መሞከራቸውን ተከትሎ የፋኖ አባላትና የመንግስት ታጣቂዎች ተጋጭተዋል። በጥቃቱ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በዚህ ግጭት የህዝብ ተቋማት፣ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ንግዶች እንዲሁም ከተማዋን ከባህርዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ተዘግተዋል። በዚሁ እለትም ነዋሪዎችና ወጣቶች በሞጣ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በመሰባሰብ በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶች እንዲፈቱ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮሳቸው ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቀ ግለሰቦች ተገድለዋል። ግንቦት 12 ቀን፤ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ አንድ የታሰረ ግለሰብ እንዲፈታ በጠየቁ ወጣቶች እና የጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሲገደሉ በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ቆስለዋል (ዲደብሊው አማርኛ፤ግንቦት 13, 2014)። በተጨማሪም የአማራ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአማራ ክልል ፖሊስ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ማንነቱ ባልታወቀ ታጣቂ ቡድን ላይ በወሰዱት የጋራ ወታደራዊ እርምጃ ለገንዘብ ብለው ሰዎችን ያፍናሉ ያሏቸውን ሶስት የቡድኑ አባላትን ገድለዋል።
እንደ ዘገባዎች ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቅርብ ጊዜው እርምጃ ጋር በተያያዘ ታስረዋል (ሮይተርስ፣ ግንቦት 15, 2014)። ብዙ የአብን ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች ከታሰሩት መካከል ይገኙበታል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 13, 2014)። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ እነዚህን እስሮች የተቃወመ ሲሆን የመንግስት ሃይሎች ህግን እንዲያከብሩም ጠይቋል። ኮሚሽኑ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ብዙዎቹ ታሳሪዎችያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩ እና ባልታወቀ ቦታ ታስረው እንደሚገኙም ተጠቁሟል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግንቦት 24, 2014)።
የተለያዩ ምንጮች በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በሰሜኑ ክፍል ሌላ ዙር ውጊያ ሊነሳ እንደሚችል ያመለክታሉ (ዲደብሊው አማርኛ፤ግንቦት 8, 2014; አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 5, 2014)። ከትህነግ/ህወሃት ጋር በነበረው በባለፈው ዙር ግጭት የፋኖ ሚሊሻዎች የፌዴራል መንግስቱ አጋር በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ነገር ግን በሌሎች ግጭቶች ውስጥ እጃቸው በመኖሩ የፌዴራል መንግስቱ ከቀጥተኛ የፖለቲካ ቁጥጥር ውጪ ቡድኑን እየታገሰ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። የፌዴራል እና የክልል ባለስልጣናት ቡድኑን ትጥቅ እንዲፈታ ማድረግ ወይም አሁን ባለው የጸጥታ ዕዝ መዋቅር ውስጥ እንዲዋሃድ ማስገደድ መቻል አለመቻላቸው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን የፋኖዎች ትጥቅ መፍታት ግጭት እንደገና ቢነሳ የፌዴራል መንግስቱን አጋሮች ዝርዝር ይቀንሳል።