በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 19, 2014 1እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 2,957
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,210
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,279
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 10
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 89
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 9
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል እና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። መንግስት በሀገሪቱ “የህግ ማስከበር” ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በአዲስ አበባ ከ349 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተዘግቧል ። በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ሁከትን በመቀስቀስ፣ ከአል ሸባብ እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና በከተማዋ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ረብሻ ለመፍጠር ማሴርን የመሳሰሉ የተለያዩ “የወንጀል ተግባራትን” በመፈጸም ተጠርጥረው ታስረዋል (የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ግንቦት 18, 2014)። ከአል ሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት 84 ሰዎች የታሰሩት ከሶማሌ ክልል ፖሊስ ጋር በመተባበር ነበር። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመጉ) እስከ ግንቦት 19 ድረስ በሀገሪቱ 18 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰራተኞች መታሰራቸውን ዘግቧል (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ግንቦት 20, 2014)።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የአማራ ክልል ዞን አስተዳደሮች በዞናቸው ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን ቁጥር አስታውቀዋል። የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር የኦነግ-ሸኔ አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ 33 ሰዎችን ጨምሮ 145 ሰዎች መታሰራቸውን አስታውቋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 18, 2014)። የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር የጸጥታ ሃይሎች በዞኑ 422 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 18, 2014)። የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ማዕከል በሆነችው በደሴ ከተማ ብቻ 100 የሚጠጉ ሰዎች የከተማዋን ሰላም በማደፍረስ፣ ሀይማኖታዊ ግጭት በማነሳሳት፣ በጦር መሳሪያ ዝውውር እና በዘረፋ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 18, 2014)። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 88 ሰዎች፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን 595 ሰዎች እና በምስራቅ ጎጃም ዞን 527 ሰዎች ከአንድ ሳምንት በላይ በተደረገው “የህግ ማስከበር” ዘመቻ ተይዘዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 18, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 19, 2014፤ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 19, 2014) በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ ሰው በማገት የተጠረጠሩ 36 ሰዎች፣ ከጸጥታ መዋቅር ከድተው የወጡ 26 ሰዎች እና ሌሎች 89 በስርቆት የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር እነዚህ እስራቶች በጎንደር የጀመሩት ሚያዝያ 18, 2014 ዓ.ም በከተማው ውስጥ በሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መሆኑን ገልጿል (ስለዚህ ኩነት የበለጠ ዝርዝር ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከሚያዚያ 15, 2014 እስከ ሚያዚያ 28, 2014ን ይመልከቱ)።
ግንቦት 15 ቀን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ክልሉ እና የፌዴራል መንግስት “የወንጀል እንቅስቃሴዎችን” ለመከላከል በጋራ ባደረጉት የህግ ማስከበር ዘመቻ ከ4,500 የሚበልጡ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልፀዋል (አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 15, 2014)። ከታሰሩት መካከል የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የፋኖ ሚሊሻ አባላት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል አዛዥ ይገኙበታል። እንዲዚህ ዓይነት የጅምላ እስራት በሃገሪቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተስተዋለው ባለፈው ጥቅምት 23, 2014 ዓ.ም በታወጀው እና በየካቲት 8, 2014 ዓ.ም በተነሳው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ነበር። በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ከትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) ወይም ኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው ታስረው ነበር (ስለዚህ እስራት የበለጠ ዝርዝር ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከጥቅምት 27, 2014 እስከ ህዳር 3, 2014 ይመልከቱ)።
ከባለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦነግ-ሸኔ እና በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች መካከል የተመዘገበው የውጊያ ኩነቶች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንምግጭቱ ግን ባለፈው ሳምንትም ቀጥሏል። ግንቦት 13 ቀን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በአመያ ወረዳ አጃሞ ኩራ ቀበሌ እና ቶሌ ወረዳ ባንቱ ከተማ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ተዋግቷል። ኦነግ-ሸኔ 30 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትን መግደሉን እና 25 ማቁሰሉን ተናግሯል (ኦኤምኤን፣ ግንቦት 14, 2014)። ግንቦት 18 ቀን በምዕራብ አርሲ ዞን ሄባን አርሲ ወረዳ ኦነግ-ሸኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ተዋግተው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል።
በክልሉ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቀጥሏል። ግንቦት 14 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ በደንጎሬ ጨሌ ቀበሌ አንድ ሰውን የኦነግ-ሸኔ አባል ነው በማለት ተኩሰው ገለውታል። ሟች ከጥቂት ቀናት በፊት በደልቦ መስቀሌ ታስሮ ነበር። በማግስቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል አባላት በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ በባኮ አኖ ቀበሌ ሁለት ዘመዳማቾችን እና ወላጆቻቸውን የኦነግ-ሸኔ አባላት ናችሁ በማለት ሁለት ዘመዳሞቾቹን ተኩሰው ገድለዋቸዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ በግንቦት 19 ቀን የጀልዱ ወረዳ ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ሽኩቴ ከተማ በመሰባሰብ ኦነግ-ሸኔን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
በጋምቤላ ክልል ግንቦት 13 ቀን ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በአኝዋክ ዞን ዲማ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ኡኩጎ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ተኩስ በመክፈት አራት ሰዎችን ገድሏል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። በተመሳሳይ እለት ማንነቱ ያልታወቀ ታጣቂ ቡድን በመርከስ ቀበሌ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ሁለት ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። እነዚህን ጥቃቶች የፈፀመው አንድ ታጣቂ ቡድን ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም።
በመጨረሻም አንዳንድ ዘገባዎች በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ከዚህ ቀደም አባላቱ እጃቸውን ለመስጠትና ጥያቄያውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ተስማምቶየነበረ ማንነቱ ያልተጠቀስ ታጣቂ ቡድን አንዳንድ አባላት ተመልሰው ወደ ጫካ መመለሳቸውን አሳታውቀዋል (ኢሳት፣ ግንቦት 19, 2014)። መጋቢት 10 ላይ የክልሉ መንግስት እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) የፖለቲካ እና የትጥቅ ክንፍ አመራሮች በዞኑ ባህላዊ የሰላም እና የዕርቅ ሥነ-ሥርዓት አድርገዋል (ስለካማሺ ባህላዊ የሰላም እና የእርቅ ሥነ ሥርዓት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)። ወደ ጫካ ለመመለስ የወሰኑት የጉሕዴን አባላት ይሁኑ አይሁኑ ከሆኑም ለምን ወደጫካ ለመመለስ እንደወሰኑ ግን ግልጽ አይደለም። ቀደም ሲል በክልሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎች አልተሳኩም። ባለፈው ሳምንት የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “በዚህ ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ” ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል (ኢሳት፣ ግንቦት 19, 2014)።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ ለብልጽግና ፓርቲ ሌላው ወሳኝ ወቅት?
በ2013/14 በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ክልሎች በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል። እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለሕዝብ ምክር ቤት አምስት መቀመጫዎችን በማሸነፍ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አራት መቀመጫዎችን በማሸነፍ በሁለትኝነት ደረጃ ይከተለዋል (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሐምሌ 5, 2013)። በምርጫው ወቅት ገዥው ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በወላይታ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል በመሳሰሉት ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን በማስር እና የፖለቲካ ፅህፈት ቤቶቻቸውን በመዝጋት የወሰደው የመከላከል እርምጃዎች ገዥው ፓርቲ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ለሚነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ለመታገስ ፈቃደኛ አለመሆኑን በግልፅ አሳይቷል (አዲስ ስታንዳርድ፣ ነሐሴ 4, 2013፤ አፍሪካኒውስ፣ መጋቢት 9, 2014፤ ኦብነግ፣ ጥቅምት 19, 2012)።
በዚያን ጊዜ አብን ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ግምት ውስጥ በማስገባት በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ከብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ የበላይነት የተለየ ይመስል ነበር። አብን ምዕራብ ትግራይ ወደ አማራ ቁጥጥር ስር እንዲመለስ እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ እንግልት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ሙግት አድርጓል።
በይበልጥ አብን እንዲሁም በአጠቃላይ የአማራ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በ2013/14 ትህነግ/ህወሓት ከትግራይ ክልል ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየገፋ በመጣበት ወቅት ተዋጊዎችን በመቀስቀስ የአማራ ክልልን እና ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ከትህነግ/ህወሓት በመከላከል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይህ መደጋገፍ ቢኖርም በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ እና አካባቢዋ በኦሮሞ ልዩ ዞን አቅራቢያ በተፈጠረው ሁከት የፌዴራል መንግስትን በብቃት ማጣት ከሰዋል። በ2013 በሚያዝያ ወር መጨረሻ በባህር ዳር በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የአብን ደጋፊዎች የብልፅግና ፓርቲ ባነርን በማቃጠላቸው እና ፀረ-አብይ መፈክሮችን በማሰማታቸው ተቃውሞ ሰልፉ ወደ ብጥብጥ ተቀይሯል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ወርሀዊ:- ከመጋቢት 23, 2013 እስከ ሚያዚያ 22, 2013ን ይመልከቱ)። ይህ የሁለቱ ግንኙነት በአማራ ክልል ከትህነግ/ህወሓት ጋር የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት የመንግስት ታጣቂዎች በትህነግ/ህወሓት በሚደርስባቸው ጥቃት ደጋግመው ከተለያዩ ቦታዎች ሲያፈገፍጉ በምትኩ የአማራ ሃይሎች ቁልፍ ከተሞችን እና መንገዶችን ለመከላከል በቦታው በነበሩት ወቅት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።
ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው ባለፈው ሳምንት የተፈጸሙ እስራቶች በአብን እና በአማራ ብሔርተኞች እና የፌዴራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ በጣም ያሽቆለቆለ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ሲሆን ለገዥው ፓርቲ ደግሞ ትልቅ ቁልፍ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞበወደፊት አስተዳደር፣ ከትህነግ/ህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር እና የሀገራዊ አቅጣጫው ላይ አንድምታ ሊኖረው ይችላል።
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የፖለቲካ አጋሮች ሀገሪቱ አሳሳቢ የሆነ የፖለቲካ ውጥቅጥ ውስጥ በነበረችበት ጊዜያት በተደጋጋሚ ተቀያይረዋል። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ያደረጏቸው አጋሮች ላይ የፈጸሙት “ክህደት” በ2011 ዓ.ም ክረምት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰፊ አመጽ እንዲነሳ እና ወጣቶችን በኃይል እንዲጨፈለቁ ምክንያት ሆኗል (ፎሪን ፖሊሲ፣ ጥር 17, 2014)። በአማራ ክልል እስካሁን ድረስ በአንፃራዊነት ያለው ግጭት የተገደበ ቢሆንም በ2011/12 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል እንደነበረው ሁሉ ሰፊ እስራት እና ውሱን ግጭቶች በቀላሉ ሊዛመቱ እና ክልሉን ሊያጥለቀልቁ ይችላል።
በፌዴራል መንግስት እና በአብን እና የአማራ ብሔርተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ በሚቀጥሉት ሳምንታት ሊጤኑ የሚገባቸው በርካታ ቁልፍ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ነጥብ የሰሜኑ ግጭት ሲጀመር እና በትግራይ ክልል በቀጠለው ግጭት በትህነግ/ህወሓት ክፉኛ የተጎዳውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያለበትን ሁኔታ ይመለከታል። መከላከያ ሰራዊቱ በበቂ ሁኔታ ወደ ሙሉ ጥንካሬው ከተመለሰ እና ትህነግ/ህወሀት ለዋና ከተማዋ አዲስ አበባ አስጊ ካልሆነ የአማራ ክልል በዋና ከተማዋ እና በትግራይ ክልል መካከል እንዳለ የመሃል ቦታ ያለው ጥቅም ብዙም አይሆንም። ነገር ግን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሊያውም ትልቅ ጦርነት እየተዋጉ የሃገሪቱን ጦር መገንባት በጣም ከባድ ስራ እንደሚሆን መታሰብ አለበት። በመሆኑም ትንሽም ቢሆን በአማራ ክልል እንዲሁም በአማራ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ላይ መደገፍ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። የአማራ ብሔርተኛ ፖለቲከኞችን እና ንቅናቄዎችን ሙሉ ለሙሉ መጨፍለቅ ለፌዴራል መንግስቱ የተሳሳተ ስሌት ሊሆን እና ዋና ከተማዋን ለከፋ የትህነግ/ህወሓት ጥቃት ሊያጋልጥ ይችላል።
በሁለተኛ ደረጃ የአማራ ብሔርተኝነትን የወደፊት እጣ ፈንታ እና የፖለቲካ አጀንዳን ማጤን አስፈላጊ ነው። “የአማራ ጥያቄ” እና የሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም የአማራ ክልል መንግስት ባለስልጣናት ግድያ የአማራ ብሔርተኝነት ትርክቶችን ተፅእኖ፣ ተወዳጅነት እና ያላቸውን ሃይል አጉልቶ አሳይቷል (አፍሪካን አፌርስ፤ ጥር 12, 2013)። የአማራ ብሔርተኞች ባለፉት ጥቂት አመታት ብዙ የፖለቲካ አላማዎቻቸውን አሳክተዋል:- በአሁኑ ሰአት የአማራ ባለስልጣናት ምዕራብ ትግራይን እያስተዳደሩ ነው፣ የትህነግ/ህወሀት ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ተቀልብሷል፣ እንዲሁም የወደፊቷ ኢትዮጵያም የበለጠ ወደ ኢትዮጵያዊነት የሚያዘነብል አቅጣጫ እንደምትይዝ የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ። ነገር ግን ምንም እንኳን አብን የአማራ ብሔርተኝነትን ሥልጣን በተወሰነ ደረጃ መያዝ ቢችልም በመንግሥት ውስጥ ያለው ተሳትፎ ለአንዳንድ አባላቶቹ አንድ እርምጃ ያፈነገጠ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን በፓርቲው ውስጥም አለመስማማቶች መታየት ጀምረዋል (አብን፤ ግንቦት 1, 2014)። የአማራ ብሔርተኛ ፖለቲካ ጽንፈኛ አካላት እንደ ፋኖ ወጣት ሚሊሻዎች የመሳሰሉት ከወዲሁ ከክልልና ከፌዴራል ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። ከከፍተኛ የፖለቲካ ጭቆና ጋር ታያይዞ በነዚህ ቡድኖች መካከል የሚፈጠረው የተስፋፋ ግጭት አስከፊ ሊሆን ይችላል።
በመጨረሻም እስር እና ጭቆና እየተካሄደ ያለበትን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ምንም እንኳን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተከሰቱት የእስር ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆኑም ወቅቱ የፌዴራል መንግስት ከትህነግ/ሕወሃት ጋር ያለውን ግጭት ለማስቆም አዲስ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ሊጠቁም ይችላል። በትህነግ/ሕወሃት ባለስልጣናት ለድርድር የማይቀርቡ ነጥቦች መካከል አንዱ የአማራ ሃይሎች ከምዕራብ ትግራይ መውጣት ነው፤ ይህ ለአማራ ብሄርተኞች ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው። እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ማስረጃ ባይኖርም ድርድሩ እየተካሄደ ከሆነ ምዕራብ ትግራይ እና አሁን ያለው የአማራ ክልል አስተዳደር ሁኔታ ለድርድር ሊቀርብ ይችላል።