በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከመጋቢት 24, 2010 እስከ ግንቦት 26, 2014 1 እነዚህ ቁጥሮች የሚያመለክቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት መጋቢት 24, 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ መከሰታቸው የተዘገበ የግጭት ኩነቶችን ነው።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 2,973
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 16,351
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 7,296
በቁጥር: ኢትዮጵያ, ከግንቦት 20 እስከ 26, 2014 2በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የተካተቱ አንድ አንድ ኩነቶች በዘገባ መዘግየት ምክንያት በቀጣይ ሳምንታት ቁጥሮች ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።
- የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች: 13
- በተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ህይወታቸው እንዳለፈ የተዘገቡ ሰዎች: 20
- በግጭት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ በተቃጡ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ: 16
ኢትዮጵያን በተመለከተ በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን እዚህ፣ ሁሉንም የአክሌድ ስራዎች ደግሞ እዚህ ጋር በመጫን ያገኛሉ።
የሁኔታዎች አጭር መግለጫ
ከመንግስት “ከህግ ማስከበር” ዘመቻ ጋር በተያያዘ እስራቶች እና ግጭቶች በአማራ ክልል ቀጥለዋል (ለበለጠ መረጃ ኢፒኦ ሳምንታዊ፡ ከግንቦት 13 እስከ 19, 2014ን ይመልከቱ)። ከደሴ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ግንቦት 18 ቀን በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ ባንቧ ወሃ ክፍለ ከተማ ኬላ በተባለ ቦታ በፋኖ ሚሊሻ ስም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች የእጅ ቦምብ ፖሊሶች ላይ ወርውረው ሶስት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸው ተነግሯል። የአይን እማኞች ግን ይህንን ክስ ውድቅ በማድረግ የአካባቢው የፋኖ ሚሊሻዎች በእስር ላይ የሚገኙ የፋኖ አባላት እንዲፈቱ ለመጠየቅ በተሰባሰቡበት ወቅት አንድ የፖሊስ አባል ጠመንጃው ባርቆበት ራሱን እና ሌላ አንድ ፖሊስ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት ሁለት የፋኖ አባላት በጸጥታ ሃይሎች ተደብድበው ታስረዋል የሚለው ወሬ ከተናፈሰ በኃላ በአካባቢው ውጥረት ሰፍኖ ነበር (ኢኤምኤስ፣ ግንቦት 21, 2014)። ግንቦት 25 ቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ጎርደም ተራራ ላይ የፖሊስ ሃይሎች፣ የቀበሌ ሚሊሻ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማንነቱ ካልታወቀ ታጣቂ ቡድን ጋር ተዋግተው ሁለት ቡድኑ አባላት ሲገደሉ ሌላ ሁለት የቡድኑ አባላትን ደግሞ በቁጥጥር ስር አውለዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በከተማው እየተካሄደ ባለው “የህግ ማስከበር” ዘመቻ 223 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንቦት 21 ቀን በምዕራብ ጎንደር ዞን ስር አዳኝ ጫኩ ወረዳ በነጋዴ ባህር ከተማ ሰዎችን በማገት እና በመግደል የተጠረጠሩ “ሽፍቶችን” ደብቀዋል ተብለው የተጠረጠሩ ቢያንስ 25 ሰዎች ታስረዋል (ኢኤምኤስ፣ ግንቦት, 21 2014)።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሃይል “ክልሉን የግጭት ማዕከል ለማድረግ” ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ያሏቸውን ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎችን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ይፋ አድርገዋል (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 24, 2014)። በአዲስ አበባ ግንቦት 25 ቀን ሁለት ፖሊሶች አንድ ጋዜጠኛን ከግንቦት 18 ጀምሮ በእስር ላይ በሚገኝበት ሶሰተኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ደብድበውታል። ይህ ጋዜጠኛ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በመገናኛ ብዙሃን ላይ በተወሰደ እርምጃ ከታሰሩ 18 ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰራተኞች መካከል አንዱ ነው።
በተጨማሪም ግንቦት 25 እና 26 የአፋር ብሄረሰብ ሚሊሻ አባላት በአማራ ክልል በአርጎባ ልዩ ወረዳ ወርቁ አዲስ በተባለው አካባቢ ንፁሀን ዜጎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ የአፋር ብሄረሰብ ሚሊሻ አባላት እና የአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች ለሁለት ቀናት ያህል ተዋግተው ቢያንስ አንድ ሰው መሞቱ እና ሁለት ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል። ይህ ግጭት የተነሳው ግንቦት 23 ቀን የአፋር ተወላጅ የሆነ ሰላማዊ ሰው ከአርጎባ ልዩ ወረዳ መዲና ገበያ ሲመለስ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ከተገደለ በኋላ ነው (ቪኦኤ አማርኛ፣ ግንቦት 27, 2014)።
በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ቀጥሏል (ከዚህ በታች ያለውን ካርታ ይመልከቱ)። ግንቦት 23 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ የመንግስት ፀጥታ ሃይል አባላት በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ ኢርጎ ዋሻቦ ቀበሌ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)-ሸኔን ይደግፋሉ ያሏቸውን አምስት ሰዎችን ተኩሰው ሲገድሉ ሌሎች ሁለት ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል።በተመሳሳይ ግንቦት 25 ቀን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ የመንግስት ፀጥታ ሃይል አባላት በምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦ ዙሪያ ወረዳ በጎሞሳ ሳቶ ቀበሌ የኦነግ-ሸኔ አባላትን ይደግፋል እና ይደብቃል በሚል አንድ ሰው ተኩስው በመግደል ቤቱን አቃጥለዋል። ግንቦት 23 ቀን የአማራ ፋኖ ሚሊሻዎች በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ጃርደጋ ወረዳ ዳርጌ ቆቲቻ መንደር የሰላማዊ ሰዎችን መኖሪያ ቤት አቃጥለው ባልና ሚስትን ገድለዋል። የአማራ ፋኖ ሚሊሻዎች በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ጉዲና ጅሬኛ ቀበሌ ከእርሻቸዉ ሲመለሱ የነበሩ አርሶ አደሮች ላይም ተኩስ በመክፈታቸው የሶስት ሴቶች ህይወት ማለፉን ተዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል አንድ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተፈፀመ ከመጠን ያለፈ ሃይል ኩነት ተመዝግቧል። ግንቦት 24 ቀን በምስራቅ ሀረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ በመንግስት የተካሄደውን “ወጣቶችን በግዳጅ ወደ መከላከያ ሠራዊት ምልመላ” በመቃወም ሰልፍ በወጡ ወጣቶች ላይ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ጥይት ተኩሷል (ኦኤምኤን፣ ግንቦት 26, 2014)። የክልሉ ልዩ ሃይል በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ በወሰደው ከመጠን ያለፈ ሃይል አንድ ሞት እና 17 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት አድርሷል።
ባለፈው ሳምንት የአክሌድ የመረጃ መረብ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶችን በጋምቤላ ክልል መዝግቧል። ግንቦት 24 ቀን የጋምቤላ ነፃ አውጪ ግንባር እና ኦነግ-ሸኔ አባላት በአኝዋክ ዞን በጋምቤላ ወረዳ በጎሊ ቀበሌ በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል። ታጣቂዎቹ በጥቃቱ ወቅትም ሶስት ሰዎችን አፍነው ወስደው የነበረ ቢሆንም ከአንድ ቀን በኋላ ለቀዋቸዋል። በማግስቱ የሱርማ ብሄረሰብ ታጣቂዎች በአኘዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ዲማ ከተማ አካባቢ አንድን አርሶ አደር አድፍጠው ገድለዋል።
ከሳምንታት አንጻራዊ መረጋጋት በኋላ ባለፈው ሳምንት በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል አለመረጋጋት ታይቷል። ግንቦት 24 ቀን የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) አባላት ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር በካማሺ ዞን ሚዥጋ ወረዳ ሶጌ ከተማ ውስጥ ባደረጉት ውጊያ 16 የጉህዴን አባላትን፣ የሚዥጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን እንዲሁም አንድ የአካባቢውንባለሀብት እና ልጁን ጨምሮ 19 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። በማግስቱም የጉህዴን ታጣቂዎች በክልሉ ልዩ ሃይል ላይ በካማሺ ከተማ ከበባ አድርገው ነበር። እነዚህን ክስተቶች ተከትሎ የካማሺ ዞን አስተዳደር የሰአት እላፊ ያወጀ ሲሆን በዞኑ ውስጥ ሞተር ሳይክሎችን መገልገልም ከልክሏል (ሪፖርተር፣ ግንቦት 28, 2014; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 28, 2014)። መጋቢት 10 ላይ የክልሉ መንግስት እና የጉሕዴን የፖለቲካ እና የትጥቅ ክንፍ አመራሮች ባህላዊ የሰላም እና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት በዞኑ አድርገው ነበር (ስለካማሺ ባህላዊ የሰላም እና የእርቅ ሥነ ሥርዓት የበለጠ መረጃ ለማግኘት ኢፒኦ ሳምንታዊ: ከመጋቢት 3, 2014 እስከ መጋቢት 9, 2014 ይመልከቱ)። ነገር ግን ከሳምንት በፊት በካማሺ ዞን ከዚህ ቀደም አባላቱ እጃቸውን ለመስጠትና ጥያቄያውን በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ተስማምቶ የነበረ ማንነቱ ያልተጠቀስ ታጣቂ ቡድን አንዳንድ አባላት ተመልሰው ወደ ጫካ መመለሳቸውን የሚያመላክቱ ዘገባዎች ወጥተው ነበር። ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት “በዚህ ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ” ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር (ኢሳት፣ ግንቦት 19, 2014)። አንዳንድ የጉህዴን አባላት ከባህላዊው የሰላም እና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት በኋላ ትጥቅ ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተነግሯል (ሪፖርተር፣ ግንቦት 28, 2014; ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 28, 2014)።
ሆኖም ግን የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መንግስት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ1,200 በላይ የጉህዴን አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጥተው የተሃድሶ ስልጠና በመተከል ዞን መውሰዳቸውን ገልጿል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 26, 2014)። በተጨማሪም በመተከል ዞን ከዳንጉር እና ማንዱራ ወረዳዎች በሰላም እጃቸውን የሰጡት 493 ወጣቶች የተሃድሶ ስልጠና መውሰድ ጀምረዋል (ኢኤምኤስ፣ ግንቦት 23, 2014)። በመተከል ዞን ዲባጤ ወረዳ ከ12,000 በላይ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን የዲባጤ ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል። የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአማራና የሲዳማ ክልል ልዩ ሃይሎች እና የአካባቢ ሚሊሻዎች በኦነግ-ሸኔ እና ማንነቱ ባልታወቀ ታጣቂ ቡድን ላይ በጋራ በወሰዱት እርምጃ የመንግስት ሃይሎች በዲባጤ ወረዳ የሚገኙ 17 ቀበሌዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቋል (የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ ግንቦት 23, 2014)። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሚያዚያ 17 ጀምሮ በዲባጤ ወረዳ ቦንፎ ቀበሌ የሚገኘውን የኦነግ-ሸኔ ማሰልጠኛ ጣቢያ በማውደም፣ 43 የኦነግ-ሸኔ አባላትን ገድሎ 60 የሚሆኑ የቡድኑን አባላት እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን መያዙን ገልጿል (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ግንቦት 30, 2014)። ይህ ቀበሌ ላለፉት ሶስት አመታት በኦነግ-ሸኔ ቁጥጥር ስር ነበረ።
በመጨረሻም ግንቦት 26 ቀን በአማራ እና በቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ በቢዝራካኒ ካር በር ባህላዊ የሰላም እና ዕርቅ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል (አዊ ኮሙኒኬሽን፣ ግንቦት 25, 2014; አዊ ኮሙኒኬሽን፣ ግንቦት 26, 2014)። ይህ ሥነ-ሥርዓት ከአማራ ክልል ከአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ እና ቻግኒ ከተማ እንዲሁም ከቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ዲባጤ እና ማንዱራ ወረዳዎች የተውጣጡ የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ህዝባዊ ውይይትን ተከትሎ ነበር (አዊ ኮሙዩኒኬሽን፣ ግንቦት 26, 2014)። ከዚህ ቀደም በእነዚህ አካባቢዎች የብሔር ሚሊሻዎች አልፎ አልፎ ይጋጩ ነበር።
ሳምንታዊ ትኩረት፡ የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች ከኤርትራ ወታደሮች ጋር ያደረጉት ውግያ
በትግራይ ክልል ከመጋቢት ወር መጨረሻ አንስቶ እስክ ግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንታት ድረስ አንጻራዊ መረጋጋት የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ላይ ውግያዎች እና በርካታ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች መዘገባቸውን ተከትሎ በክልሉ አለመረጋት ተከስቷል። እነዚህ ኩነቶች ቢኖሩም በትግራይ ክልል ሰፊ ውግያ አልተከሰተም፤ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ/ህወሓት) እና የኢትዮጵያ ጦር በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊያገረሽ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 8, 2014; የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት – ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 29, 2014)። በተመሳሳይ የኤርትራ መንግስት ትህነግ/ህወሓት ለአዲስ ዙር ግጭት መዘጋጀቱን በመግለጽ የኤርትራ ወታደሮች ሀገሪቱን ለመከላከል “አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው” ሲል ተናግሯል (ቢቢሲ አማርኛ ፣ ግንቦት 9, 2014)።
ባለፈው ሳምንት የመድፍ ድብደባ በትግራይ ክልል እንደተፋፀመ ተዘግቧል። ምንም እንኳን ውስን ቢሆንም ይህ ድብደባ ጦርነቱ እንዲያገረሽ እና ከመጋቢት ወር መጨረሻ ወዲህ የተፈጠረው መረጋጋት ተከትሎ በሰብአዊ አገልግሎት ላይ የታየው ውስን መሻሻል እንዳይቀለብስ ስጋት አለ። በግንቦት 20 እና 21 የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን በሸራሮ ከተማ በትህነግ/ህወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታዎች ላይ በርካታ መድፎችን በመተኮስ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያረፉበትን ትምህርት ቤት ሲመታ ቤቶችንም አወድሟል። በጥቃቱ የ14 ዓመት ሴት ልጅ ስትገደል 18 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። ባለፈው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ግንቦት 16 ቀን የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና የትህነግ/ህወሓት ሃይሎች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን አዲ ሃገራይ ወረዳ በምዕራብ አዲ አዋላ ተዋግተዋል። ትህነግ/ህወሓት የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት የጀመረውን ጥቃት መመከቱን እና አራት ወታደራዊ አዛዦችን ጨምሮ ቢያንስ 120 የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮችን መግደሉን፣ 195 ወታደሮችን ማቁሰሉን እና ሌሎች አራት ወታደሮችን መማረኩን አስታውቋል (ዲደብሊው አማርኛ፣ ግንቦት 23, 2014)። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የትህነግ/ህወሓት መግለጫ ውድቅ በማድረግ ትህነግ/ህወሓትን ውጊያውን በመቀስቀስ ከሷል (ቢቢሲ አማርኛ፣ ግንቦት 22, 2014)። የኤርትራ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።
ምንም እንኳን ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ – አሁን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ – የሰላም ድርድር እየተካሄደ መሆኑን በቅርብ በተካሄደ ቃለ ምልልስ ያመላከቱ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከትህነግ/ህወሓት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ላለመቀበል ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ ነው። ኦባሳንጆ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰላም ጥረቶች “በጣም በዝግታ ግን በተረጋጋ ሁኔታ” እየሄዱ ነው ብለዋል። በመቀጠልም “የዛሬው ሁኔታ ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው የተሻለ ነው” በማለት አብራርተዋል (ቢቢሲ፣ ግንቦት 24, 2014)። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ናይጄሪያን የጎበኙ ሲሆን ኦባሳንጆ በቅርቡ በኢትዮጵያ በመገኘት “የወደፊት የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል” (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት – ኢትዮጵያ፣ ግንቦት 29, 2014)። ግንቦት 23 ቀን ኦባሳንጆ ከትህነግ/ህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ጋርም ተገናኝተዋል (ቲዊተር @ ረዳ_ጌታቸው፣ ግንቦት 23, 2014)።
ምንም እንኳን እነዚህ መሻሻሎች ቢኖሩም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ አሁንም እጅግ አሳሳቢ ነው። መቀሌ የሚገኘው ከ300,000 በላይ ህሙማንን የሚያስተናግደው ትልቁ ሪፈራል ሆስፒታል የአይደር ሆስፒታል ጄነሬተሩን ለማስኬድ የሚያስችል ነዳጅ በማጣቱ ከግንቦት 21 ጀምሮ ለህጻናት እና ፅኑ ህሙማን ክፍል አገልግሎት መስጠት ማቆሙን አስታውቋል (ኦሲኤችኤ፣ ግንቦት 26, 2014) ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ 320 የሚጠጉ የሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ የጭነት መኪኖች ወደ ትግራይ ቢገቡም በትግራይ ክልል ያለው የነዳጅ እጥረት ከከተሞች ዉጭ ባሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ተግዳሮት ሆኗል።
አሁን ለኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግጭት ወሳኝ ወቅት ነው። መደበኛ የሰላም መፍትሄን ለማመቻቸት የተከፈቱ ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብአዊ መንገዶችን ይበልጥ ለማስፋት አስፈላጊው ጥረቶች ሁሉ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው።
ማስተካከያ፡- ቀደም ሲል የወጣው የዚህ ዘገባ ቅጂ የአርጎባ ልዩ ወረዳ በአፋር ክልል እንደሚገኝ ገልፆ የነበረ ሲሆን በአማራ ክልል እንደሚገኝ ተገልፆ ተስተካክሏል።